Saturday, July 28, 2012

ዱላን ያሰለለ መንፈስ Brutality Of Ethiopina Gov.

ዱላን ያሰለለ መንፈስ


‹‹ወንድ ካለቀሰ ከባድ ነገር አለ ማለት ነው›› ይባላል፡፡ ወንድ ለዚያውም ጎረምሳ ያለፈን ክስተት አስቦ ሲያለቅስ ማየትም ልብን የሚነካ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ አላህ በሱረቱ ቲን ላይ የሰው ልጅን ባማረ አቋም ፈጠርነው ብሎ የዝቃጮች ዝቃጭ መሆንን የመረጡትን ደግሞ እንዳሰቡት ማድረጉን ይነግረናል፡፡ የሠው ልጅ ‹‹ሰብዐዊነት›› የተባለ ተፈጥሮ ‹‹ማሰብ፤ ማሰላሰል›› የተሰኘ ነገር ቢፈጥርበትም ‹‹ጭካኔ›› የተባለ እርኩሰነትም አለበት፡፡ የሠው ልጅ ሰብዐዊነቱን ሲያጣ ከአውሬ የባሰ አውሬ እንደሚሆን ብዙ ምሳሌዎች ማሳየት ይቻላል፡፡ ለአሁኑ ግን ባለፈው ሳምንት በሠላማዊያን ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሠውን አሰቃቂ ድርጊት በጨረፍታ ማሳየት እንሞክር፡፡ ታሪኩን የሚያጫውተን ወንድም ታላቁ አንዋር መስጂድ ዙርያ በንግድ የሚተዳደር ወንድማችን ነው፡፡




አንድ ሠው፣ ጾመኛና የቤተሠብ ኃላፊነት ያለበት ሰው አስቡ፡፡ ይህ ሠው በጠዋት የእለት ጉርሱን ለማግኘት ሲወጣ በሐገሪቱ ለወራት የዘለቀው የሙስሊሙን የመብት ጥያቄንም ያስባል፡፡ መች ይሆን መብታችን የሚከበረው? ጥያቄያችንስ ተገቢውን ምላሽ የሚያገኘው መቼ ነው? ማለቱ አልቀረም፡፡ መንግስትስ መች ይሆን ልብ ገዝቶ ጥያቄውን በቅንነት የሚያየው? ይጠይቃል፤ መልስ ግን የለውም፡፡

የሚሠራበት ሱቅ ሆኖ ሥራውን ሲያከናውን ካረፈደ በኋላ የዙሁር አዛን ሠማ፡፡ ለአዛኑም ትክክለኛውን ምላሽ በመስጠት በጀመዐ ሰግዶ ህዝበ-ሙስሊሙ በግፍ የታሰሩት ህጋዊ ኮሚቴዎቹ እንዲፈቱና 3ቱ መሰረታዊ ጥያቄዎችም እንዲመለሱ በሚጠይቅበት የተክቢራ ተቃውሞ ለደቂቃዎች ከተሳተፈ በኋላ እዛው አንዋር መስጂድ አካባቢ ወደሚገኘው ሱቁ አምርቶ ሥራውን ማከናወን ቀጠለ፡፡ ሠላማዊ ተቃውሞው ለደቂቃዎች ከቀጠለ በኋላ ግን አስፋልቱ ጭር ይል ያዘ ፖሊሶችም ሱቆችን በጉልበት ማስዘጋት ተያያዙት፤ ግራ ገባው፤ ምን እየተካሄደ ነው ሲል ራሱን ጠየቀ ቆየት አለና መስጂዱ በነዚሁ ታጣቂ ፖሊሶች ተዘጋ፡፡ መስጂዱ ውስጥ ያሉ ሠዎች ግን እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልሠጡም፡፡ መንገዱ ጭር አለ፡፡ በታክሲዎችና በሌሎች መኪኖች ፋንታ በፖሊስ መኪናዎች ተሞላ፡፡ ድንገት የድንጋይ እሩምታ ሰማ፡፡ ወደ እሩምታው አቅጣጫ ሲዞር ጥቂት ጎረምሶች ናቸው፡፡ ፖሊሶችም ድንጋዩ ሲወረወር ዞር ብለው እንኳ ሳያዩት በራሳቸው ጉዳይ ተጠምደዋል፡፡

ድንጋይ ወርዋሪ ጎረምሶቹ በአለቆቻቸው በታዘዙት መሠረት ድንጋዩን ወርውረው ሄዱ፡፡ ፖሊሶቹ ግን ዝም አሏቸው፤ ጭጭ፡፡ ከነሱ መሄድ በኋላ የተሠበረ አውቶቡስ መጥቶ ቆመ፡፡ ፖሊሶችም የጭስ መዓት ወደ መስጂዱ ቅጥር ግቢ መተኮስ ተያያዙት መርካቶ ተኩስ በተኩስ ሆነ፡፡ ፖሊስ በቦታው ከበቂ በላይ ኃይል ቢኖረውም ብዙ ኃይል ጣልያን ሠፈር ወዳለው ጅንአድ ግቢ መከማቸቱን ተያያዘው፡፡ የፖሊስ አዛዦቹም ባዶ እጁን ባዶ ሆዱን በሆነ ጾመኛና ሠላማዊ ህዝብ ላይ ጭስና ጥይት እያከታተሉ በመተኮስ አካባቢውን በማመሳቸው የአሸናፊነት፣ የማን አህሎኝነት ኩራት ይነበብባቸዋል፡፡ ከፒያሳ እስከ መሳለሚያ መንገዱን ዘግተው አላፊ አግዳሚውን በያዙት ቆመጥ ያራውጡት ጀመር፡፡

ተራኪያችን ይህንን ሁሉ ትዕይንት አንዱ ጥግ ላይ ሆኖ ሲከታተል ለቤተሰብ ሠላም መሆኑን ደውሎ ለማረጋገጥ ስልኩን ከኪሱ ያወጣል፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን ከርቀት ስልኩን ሲያወጣ ያየው አንድ ሲቪል መጥቶ ‹‹ለምን ትቀርጻለህ›› ብሎ ጮኸበት፡፡ እሱ ግን እየቀረጸ አለመሆኑን ሊያስረዳው ቢሞክርም ሰውየው ሊሰማው አልፈቅደም፡፡ ይባስ ብሎም ወስዶ ለፖሊሶቹ አስረከበው፡፡ ለፖሊሱ ሲያስረክበው ግን ከዱላም ጋር ነው የተረከበው፡፡
አንዋር መስጂድ ውስጥ ከታገቱት 50ሺህ በላይ ከሚሁኑ ሙስሊሞች ውስጥ 1ሺህ ያህሉ ወደ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ፡፡ ከአስር ሰላት በኋላ ጀምሮ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ የገባው ወደ 1ሺህ የሚሆነው ህዝበ-ሙስሊም እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ከ10 ደቂቃ ድረስ የቅጣት አይነት ሲያስተናግድ ቆየ፡፡ በዝናብ መሬቱ ላይ መደፋት ጠጠሩ ቆርቁሮት የተንቀሳቀሰ ሠው ድብደባ ማስተናገድ ሆነ፡፡ ያ ሁሉ ሠላማዊ ሠው ወንጀሉ ተቃውሞውን በሰላም ማሰማቱ ነበር፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት እኛ በቤቶቻችን የወንድምና እህት እስረኞችን ስቃይ እያሰብን ሐዘን ተቀምጠናል፡፡ ማዘን ይገባናል ንጹሃን ዜጎች ያለ ኃጢያታቸው እንኳን ለሠው ለእንስሳ የማይገባ ቅጣት ሲያስተናግዱ እንዴት አንዘን?

የዚህ ግፍ ገፈት ቀማሽ ወንድማችን እንደሚለን እስረኞቹ የሚቀጠቀጡበት ዱላ በአንድ እጅ የሚያዝ አይደለም፡፡ ታዲያ ይህን በሚያህል ዱላ የሰውነት ክፍል ሳይለይ የተመታ ሰው ምን ይሆን እጣው? ሞት? አካል ማጣት? ወይስ ምን? በድብደባው እጃቸው የተገነጠለ፣ እግራቸው የተሰበረ፣ ጭንቅላታቸው የተሰነጠቀ፣ ኧረ ምኑ ቅጡ ይወራል? ሁሉም አይነት ድብደባ አስተናገዱ ግን፤ ግን አሁንም እረፍት አላገኙም ጠጠር ላይ ከነቁስላቸው በዛ ዝናብ በደረታቸው እንዲተኙ ታዘዙ፡፡ ያ ቅዝቃቄ ብቻውን ቆፈን የማስያዝ አቅም ያለው ቢሆንም ለቁስለኛ ደግሞ ልብ ማራድና ደረት የሚሠነጥቅ ህመም አለው፡፡ አስቡት…..

ሥቃዩ በዚህ አላበቃም፡፡ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከአስር ላይ ያን ሁሉ ስቃይ ከተቀበሉበት አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተነስተው ከ20 በሚበልጡ መኪናዎች ታጉረው ወደ ሰንዳፋ ተጋዙ፡፡ ሰንዳፋ እንደገቡ በባዶ እግራቸው ቅዝቃዜው በሚያርድ ምሽት የተቀዳደደ ልብሳቸውን ሳይቀይሩና የሚለበስ ሳይሰጧቸው እብነ በረድ ላይ አስተኟቸው፡፡ ይህን ሁሉ ስቃይ ያስተናገደ ሰው እንዴት እንቅልፍ ይመጣዋል? የባጥ የቆጡን እያሰቡ አርፍደው ሸለብ ሊያደርጋቸው ሲል ግን የተኙበት ክፍል ድንገት በኃይል ተከፍቶ ‹‹ሁላችሁም ዉጡ›› የሚል ድምጽ አስተጋባ፡፡ ዳግም ስቃይ ዳግም ህመም…

ከጠዋቱ 12 ሰዐት ሰንዳፋ ላይ ቅዝቃዜና ብርዱ ኃይለኛ ነው፡፡ ‹‹ኑ ስፖርት ስሩ›› ተብለው በጠጠር ላይ በደረታቸው ተሳቡ፣ አሸዋ ላይ ተንከባለሉ፣ መግረፊያ እስኪሰበር ተደበደቡ፡፡ በምሽቱ ድብደባ የተሠበሩና የቆሰሉት ሰዎችም ‹‹የግዳጅ ስፖርቱ›› ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ሃኪም ህክምና ያስፈልጋቸዋል ይረፉ ያላቸው እንኳ ነበሩበት፡፡ መጮህም ሆነ ማልቀስ አይፈቀድም፡፡ ቢጮሁ ደግሞ ዱላው አይጣል ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ተርፎም በጠጠር ላይ በባዶ እጃቸው እንዲንፏቀቁ የተደረገው በጾመኛ አንጀታቸው መሆኑን ስታስቡ አልቅሱ አልቅሱ ይላችዃል፡፡

በዚህ አላበቃም፤ ጠጠር ላይ ተንፏቀው ከጨረሱ በኋላ በአሸዋ ላይ እንዲንከባለሉ ተደረጉ፡፡ የዚህ ምስጢር የገባቸው ግን ቆይቶ ነው፡፡ በዛ ሹል ጠጠር ሲሳቡ የተጋጋጡ የተላላጡ ነበሩ በዚህም ምክንያት መሬቱ በደም ጨቅይቷል፡፡ ሰውነቱ ያልተጋጋጠው ደግሞ ልብሱ በደም ርሷል፡፡ በአሸዋ ያንከባለሏቸው ደሙ በሰውነታቸው (በልብሳቸው) ላይ እንዳይታይ አስበው ነበር፡፡ ያ ጠጠር ግን በደም ርሶ ነበር፡፡ ቅዳሜ የታፈሱ ሰዎች እሁድን እንዲህ በስቃይ ካሳለፉ በኋላ ለፉጡር እንዳንድ ደረቅ ዳቦ ተወረወረላቸው፡፡ ከነጋ በኋላም በግምት ወደ መቶ የሚጠጉ ሙስሊሞች ከተለያየ ቦታ ታፍሰው በመምጣት እነሱም የስቃዩ ተካፋይ ሆነዋል፡፡
እንደማንም እሁድ አለፈ፡፡ ለሱሁር ዳቦ ተሰጥቷቸው ሰኞ ቀኑን እሁድ ያስተናገዱትን ስቃይ ሰኞም ደገሙት፡፡ በዚ ሁሉ ስቃይ መሃል ግን የሚታየው የመንፈስ ጥንካሬ አስገራሚ ነበር፡፡ መተዛዘኑ ‹‹አንተ ትብስ፣ አንተ ትብስ›› መባባሉ ልብ የሚነካ እንደነበር የተፈቱት ያጫውቱናል፡፡ አንዱን ዳቦ ለሌላው ለማካፈል የነበረው መተዛዘን ልብን ያበረታል፡፡ ሁሉም ሶላቶች ተሰግደዋል፡፡ በዱላው ብዛት ብዙ ደም የፈሰሳቸው፣ ሽንታቸው ያመለጣቸውም እንደ ደንቡ ራሳቸውንና ልብሳቸውን አጽድተው ሲሰግዱ ነበር፡፡ ዱላው ሰውነታቸው ላይ ባረፈ ቁጥር የአላህን ስም ብቻ በመጥራት ይጽናናሉ፡፡

ስቃዩ በዱላ ብቻ አይበቃም፡፡ ሌላም አለ፡፡ ‹‹በሽንት ሰዐት›› ለሽንት የሚኬደው መንገድ ከ 1 ኪሎ ሜትር ያላነሰ በመሆኑ ከመንገዱ ርዝመት የተነሳ ሽንት ይጠፋል፡፡ ከተመለሱ በኋላ ግን ተመልሶ ይመጣል፡፡ ሆኖም፤ ሰዐቱ ስላለፈ መውጣት አይቻልም፡፡ ያለው እድል በልብስ መልቀቅ ወይም ስቃዩን ችሎ መቀመጥ ብቻ ነበር፡፡

ሰኞ ሲመሽ ሁለት ደረቅ ዳቦዎች ሆድ ከሚቆርጥ ሽሮ ጋር እንደተሰጣቸውም ያስታውሳሉ፡፡ ምን ያደርጋል ሰውነታቸው በቅጣት በመድከሙ ሁለት ዳቦ መጨረስ አቃታቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መጡና ሰብስበው የስድብና የማስፈራሪያ ናዳ አወረዱባቸው፡፡ እስረኛ ምንስ ቢባል ምን ያመጣና ነው? ለዚያውም ሠውነቱ በዱላ የዛለ እስረኛ፡፡ መቼም ከመስማት ውጪ አማራጭ የለም ሰሟቸው፡፡ ሰውየው ‹‹አጀንዳችሁ ፖለቲካዊ እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ ከአክራሪዎችና አሸባሪዎች ጋር ተባብራችኋል›› አሏቸው፡፡ ህገ-መንግስቱ የኃይማኖት ነጻነት በማወጁ ከዚህ በኋላ ምንም አይነት የኃይማኖት ጥያቄ ማንሳት እንደማይቻልም አስጠነቀቋቸው፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩን የምንነግራቸው ግን ጥያቄያችን በጽሁፍ የሠፈረው የመንግስትና ኃይማኖት መለያየት እንዲከበር ነው፡፡ እንዲሁም እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ህግ አስከባሪ አካላት ሥራቸው በጽሁፍ የሠፈረ ህግ በተግባር እንዲተገበርና እንዳይጣስ መቆጣጠር መሆኑን ነው፡፡ እኛ ያልነውም ‹ህጉ ተጥሷል፡፡ መንግስት ሳያገባው በሀይማኖታችን ጣልቃ ብቻ ሳይሆን ከፊት ለፊት ገብቷል›› ነው፡፡

ያው ግን ታሳሪ፤ ታሳሪ ነው፡፡ እስረኞችን ማስፈራራትና መወንጀል ቀጥሎ እንዲህ አሏቸው፡፡ ‹‹ጥፋታቹ ከባድ ቢሆንም እናንተን ለመጀመሪያ ግዜ እንደተሳሳታቹሁ በማሰብ በምህረት እንለቃችኋለን፡፡ የምትለቀቁትም በምሽት ነው፤ ይህም የራሱ ምክንያት አለው!››
ከዚያም አሻራ ተነሱ፣ ፊልም ተቀረጹ፣ ፎቶ ተነሱ፣ ቃለ-መሃላም ፈጸሙ፡፡ በግዳጅ የፈረሙበት የእስር ወረቀት ግን ‹‹ከአክራሪዎቹ ጋር ህገ-መንግስቱን ለመናድ በተደረገው ነገር ላይ ተሳታፊ ሆኜ በመገኘቴ›› የሚል ነበር፡፡ ሁሉም የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጥ ሳይደረግ እንዲህ ባለ ወረቀት ላይ እንዲፈርም ሲጠየቅ ‹‹ስህተት ነው፤ ኮሚቴው ህገ-ወጥ አይደለም፡፡ ህገ-መንግስት ለመናድም አልተባበርኩም›› ቢልም ሰሚ አላገኙም፡፡ የሆነ ሆኖ ፈረሙና ተጭነው በምሽት አዲስ አበባ ገቡ፡፡ አዲስ አበባ ሲደርሱ ከምሽቱ 5 ሰዓት ሆኗል፡፡ ከተማዋ አንቀላፍታለች፡፡ የክረምቱ ብርድ አይጣል ነው፡፡ ለቤተሰብ እንዳይደውሉ ስልክ የላቸውም፡፡ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው በየአካባቢያው ተጭነው የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ አራገፏቸው፡፡ ድብደባ የተፈጸመባቸው ሠዎችም ድንግዝግዝ ባለ ምሽት ወደየቤታቸው ተበታተኑ፡፡ ተራኪያችንም በኪሱ ገንዘብ ስላልነበረው በባዶ እግሩ ወደ ቤቱ ሲሄድ ያገኘው የሚያውቀው ክርስቲያን ጓደኛው ‹‹ወንድሜ አንድ ችግር ቢያጋጥመው እንጂ በዚህ ድቅድቅ ጨለማ በእግሩ አይጓዝም›› በሚል እያዘነ በኮንትራት ታክሲ ወደ ቤቱ ሸኘው፡፡ ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡

እነዚህ የተፈቱት ናቸው፡፡ ከነሱ ጋር ታስረው ጺም ስላላቸውና የትምህርት ደረጃቸው ከፍ ስላለ ብቻ በግምት 200 የሚሆኑ ሙስሊሞች ከክፍለ ከተማ፣ ከአ.አ እና ከፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች መጥተው ‹‹ለተጨማሪ ምርመራ›› በሚል ተጨማሪ የስቃይ ቀናት ወይም ወራት እንዲያስተናግዱ ወስነውባቸዋል፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ስለመፈታታቸው ምንም መረጃ አልደረሰንም፡፡ አላህ ይርዳቸው፤ ይርዳንም፡፡

እስሩም ሆነ ድብደባው የሞራል ጥንካሬን ቢፈጥር እንጂ እንደማያደክመን ታስረው የተፈቱት ወንዶሞቻችን፣ እህቶቻችን ምስክሮች ናቸው፡፡

አላሁ አክበር!!!

No comments:

Post a Comment