Wednesday, September 26, 2012

ውጤታማ የሆነ የትግል ስልት ለመቀየስ የሙስሊሙ ህብረተሰብ አዕምሮ በሙሉ ተጨምቆ፣ አሉ የሚባሉ ሃሳቦች ሁሉ አንድ ቦታ ፈሰው ውይይት ሊደረግባቸው ግድ ይላል፡፡

"ካድሬዎቹ በሙሉ ክተት አውጀው ቤት ለቤት እየዞሩ፣ በቀን ከሶስቴ በላይ እየተመላለሱና ስልክ እየደወሉም ጭምር ሙስሊሙ በግድ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ የማሸበር ስራእየሰሩ ይገኛል፡፡ አልወስድም ያለውን ሰው አሸባሪ ነህ፣ ከቀበሌ ቤት ትባረራለህ፣ ድርጅትህ ይዘጋል…እያሉ መጠነ ሰፊ የማሸማቀቅና የሽብር ስራ ይፈጽማሉ፡፡"

ውድ የተከበራችሁ ኢትዮጲያውን ሙስሊሞች
ሙስሊሙ ህብረተሰብ የተከፈተበትን መጠነ ሰፊ ዘመቻ ለመመከት በየጊዜው አዳዲስ ስልቶችን እየቀየሰ ሲንቀሳቀስና በአላህ ፈቃድም አብዛኛዎቹ ሴራዎች እንዲከሽፉ አንዳንዴም ከታሰቡለት ዐላማ በተቃራኒ ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ሲጠቀምባቸው ቆይቷል፡፡ እነዚህ ስኬቶች ሊገኙ የቻሉት እንቅስቃሴያችን ህዝባዊ እንደመሆኑ ከህዝቡ የሚመጡ የተለያዩ አስተያየቶችን ሹራ በማድረግ የተሻሉና አዋጭ የሆኑ ሃሳቦችን በመለየት ስራ ላይ እንዲውሉ በመደረጉ ነው፡፡ በሂደታችን እጅግ ወሳኝ የሚባል ሚና የነበራቸው የሰደቃና አንድነት ፕሮግራም፣ ዓለምን ያስደመመው የዝምታ ተቃውሞ፣ የሰኞና ሐሙስ ጾምና የጋራ ኢፍጣሮች፣ የቁኑት ፕሮግራም፣ የአንድነት ነሺዳችን፣ በአንድ ብር ታሪክ እንስራ ዘመቻ …እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴያችን እንዴት ይቀጥል የሚለው ጉዳይ ካስጨነቃቸው ግለሰቦች አዕምሮ የፈለቁ ሃሳቦች ናቸው፡፡ ኮሚቴዎቻችንም ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥማቸውና የአቅጣጫ ለውጥ ሲያስፈልግ በፌስቡክ ላይ ተከፍተው ከነበሩ የተለያዩ የመወያያና ሃሳብ መስጫ መድረኮች ጠቃሚ ግብዓቶች ሲያገኙ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
ሙስሊሙ ህብረሰብ በአሁኑ ሰዓት ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ትልቅ መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ መንግስት የመጅሊስ ምርጫን በቀበሌና እሱ በሚፈልገው መንገድ ለማድረግ ሲል በሃይማኖታዊ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ምርጫዎችም ጭምር ታይቶ የማይታወቅ የህግ ጥሰት እያከናወነና ህገ መንግስቱን ከስር መሰረቱ እየናደው ይገኛል፡፡ ካድሬዎቹ በሙሉ ክተት አውጀው ቤት ለቤት እየዞሩ፣ በቀን ከሶስቴ በላይ እየተመላለሱና ስልክ እየደወሉም ጭምር ሙስሊሙ በግድ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ የማሸበር ስራ እየሰሩ ይገኛል፡፡ አልወስድም ያለውን ሰው አሸባሪ ነህ፣ ከቀበሌ ቤት ትባረራለህ፣ ድርጅትህ ይዘጋል…እያሉ መጠነ ሰፊ የማሸማቀቅና የሽብር ስራ ይፈጽማሉ፡፡ የምንታገሳችሁ ምርጫ እስኪደረግ ብቻ ሲሆን ከዛ በኋላ ልክ እናስገባቹሃለን እያሉም ይፎክራሉ፡፡ በጥቅሉ መስከረም 27 ሊደርጉት ያሰቡትን ምርጫ እንደ ትልቅ አገርአቀፍ ፕሮጀክት ይዘው ለማሳካት አለ የሚሉትን አቅም በሙሉ አሟጠው በመጠቀም ላይ በመሆናቸው ሙስሊሙ ህብረተሰብም ሴራቸው እንዲከሽፍ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ውጤታማ የሆነ የትግል ስልት ለመቀየስ የሙስሊሙ ህብረተሰብ አዕምሮ በሙሉ ተጨምቆ፣ አሉ የሚባሉ ሃሳቦች ሁሉ አንድ ቦታ ፈሰው ውይይት ሊደረግባቸው ግድ ይላል፡፡
ከዚህ በመነሳት ድምጻችን ይሰማ ገጽ በተከታዮቹ ሁለት ጉዳዮች ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በሙሉ በመሳተፍ ሃሳቡን እንዲያካፍል ጥሪ ታቀርባለች
1. መስከረም 27 የታሰበውን ምርጫ በምን መንገድ ማክሸፍ ይቻላል? እንዲሰረዝ ማድረግ ካልተቻለስ ተቀባይነቱን በምን መልክ ማሳጣት ይቻላል? መንግስት "ምርጫ ጠየቁ ተደረገላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለ ተቃውሞ ዐላማው ሌላ ነው" በሚል ሙስሊም ላልሆኑ ወገኖች ሊነዛ የሚችለውን ፕሮፖጋንዳ በምን ማክሸፍ ይቻላል?
2. ምርጫው ተደረገም አልተደረገም ተቃውሟችንን ምን ምን ዐይነት አዳዲስ ስልቶችን በመጠቀም ልናሳድገው እንችላለን? የጁሙዓውን ተቃውሙ ተላምደውት እንደ ሰላቱ አንድ አካል እየቆጠሩት ይመስላልና ጫና መፍጠር የሚያስችሉ ሌሎች ተጨማሪ የተቃውሞ መንገዶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ጥያቄዎቻችን መልስ ካጡ ከአገር ጫፍ እስከ ጫፍ የተነቃነቀው ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከኢሕአዴግ ጋር ሊኖረው የሚችለው የወደፊት አቅጣጫ ምን ሊሆን ይችላል?
በነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ በቡድን በቡድን በመሆን በመወያየትና ዓሊሞችና ሙሁራኖችን በማወያየት አዳዲስ ሃሳቦች እናፍልቅ፡፡ የተቃውሞ ሂደቱን ለማገዝ በየመስጂዱ የተቋቋሙ ጀመዓዎች ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው ይወያዩበት፡፡ ከዚህ በፊት ስብስብ ያልተፈጠረባቸው መስጂዶች እራሳቸውን አደራጅተው በጉዳዩ ላይ ይወያዩበት፤ እራሳቸውንም በሹራ የሚወሰነውን ውሳኔ ለማስፈጸም ያዘጋጁ፡፡
ያላቹህን ሃሳቦች እስከ መጪው እሁድ ደረስ ድምጻችን ይሰማ ገጽን https://www.facebook.com/DimtsachinYisema በመክፈት ፖሰት በማድረግ ሳይሆን የግል ሜሴጅ በመላክ እንድታደርሱን እንጠይቃለን፡፡ የአንድ ግለሰብ ሃሳብ የኡማውን ታሪክ ለመቀየር ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላልና የመጡልንን ሃሳቦች ሳንንቅ እንላካቸው፡፡ አላህ ይወፍቀን!

 

No comments:

Post a Comment