Friday, August 17, 2012

እንኳን ለ1433ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሰን

እንኳን ለ1433ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሰን
እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በእድሜያችን ከፆምናቸው ረመዳኖች የዘንድሮው በብዙ መልኩ እንደሚለይ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ እርስ በእረስ እንድንባላ ከተደገሰልን ድግስ አምልጠን ለወሩ ክብርና ሞገስ በሚገጥም የአንድነት እና እረስ በእርስ የመሰማማት ስሜት አሳልፈናል፤ አንገታችንን ሊያሰደፋ ከተሸረበብን የእምነት ነጠቃ ሴራ በማምለጥ ከምን ግዜውም በተለየ ቀጣዩ የትግል ተሰላፊ እኔን አድርገኝ በሚል ተማፅኖ አሳልፈናል፤ ዳግም ላናንሰራራ አከርካሪያችንን እንደመቱ በፎከሩብን ጠላቶቻችን ላይ ወሩ ባጎናፀፈን ትዕግስትና ፅናት ፉከራቸውን በማስታገስ አሳልፈናል፤ ‹‹እንግዲህ

ምን ይደረጋል›› ከሚሉት አጉል ብሂል በመውጣት የወሩ መገለጫ በሆነው የበላይነትና የአሸናፊነት ስሜት አሳልፈናል፡፡ አንዳንዶች በተሳሳተ መልኩ እንደተረዱት በእምነት ነፃነት እጦት አንገታችንን ደፍተን እያነባን ሳይሆን ለእምነት ነፃነት ያለንን ሁሉ ልንሰጥ እንደምንችል ለራሳችንም ለሌችም ማረጋገጫ በመስጠት አሳልፈናል፤ በውሃ ጥም የደረቀ ጉሮሮአችን ብሶት ባመነጨው ጨዋማ እምባችንን እያራስን ብቻ ሳይሆን አላህን በመማፀንና ለዲናችን ያለንን ፍቅር በማረጋገጥ ለወትሮው የደረቀው አይናችን እያነባ አሳልፈናል፤ በሌላም በሌላም ከወሩ ክብርና ሞገስ ጋር ከሚሄዱ መልካም መገለጫዎች ጋር በተሳሰረ መልኩ ወሩን አሳልፈናል፡፡ አሁን ደግሞ ዒድን ልናከብር እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡ አልሃምዱሊለላህ!!!

ሁላችንም እንደምናውቀው የዒድ በአላችን አንዱና ትልቁ መገለጫው ከዚህም ባለፈ የብዙሃነታችንና የአንድነታችን መገለጫ የሆነው የዒድ ሰላት ነው፡፡ የዒድ ሰላት እንደዛሬው እስታዲየም አይወጣ እንጂ በደርግም አገዛዝም በታላቁ አንዋር መስጂድ በመሰባሰብ ልዩ በሆነው የአንድነት ውበታችን ነበር የምናሳልፈው፡፡ ኢህአዴግ መብትን እንደ መብት ሳይሆን እንደ ልዩ ስጦታ እንደሰጠ የሚመፃደቅባትን ይህችኑ የአደባባይ የዒድ ሰላት ለመከልከል ምን ያህል ላይ ታች ሲል እንደከረመ ከዚህ በፊት ማስታወቃችን ይታወሳል፡፡ እነሱ ከማሴር አይቦዝኑምና ይህ አይገርመንም፡፡ እኛም ከነርሱ ብዙ ርቀት ቀድመናልና በሴራቸው ተተብትበን አንወድቅም፡፡ ዛሬ ላይ ዒድን ለመከልከል ያስቀመጧቸው ስልቶች በሙሉ መክሸፋቸውን ሲረዱ እያቃራቸውም ቢሆን አንድነታችንን የሚያዩበትን መድረክ የፈቀዱ ይመስላል፡፡ ሆኖም ስልታዊ በሆነ መንገድ አብሮነታችንን ሊነጥቁን ስለሚችሉ የሚከተሉትን ልናጤን ይገባል፡፡
1. በሚዲያ የዒድ ሰላት እስታዲየም እንደሚሰገድ ካወጁ በኋላ ህዝቡን በአካባቢ በመክፈል የዒድ ሰላት ወደሚሰገድባቸው የተለያዩ አካባቢዎች (ለምሳሌም አቃቂ፤ ሰበታ----) ለመከፋፈል እየሰሩ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡ ይህንን ግን በፍፁም የማንቀበለው ሲሆን ከፊል ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ታግተው የእስቴዲየሙ ሰላት እንደማይጀመር ሊያውቁት ይገባል፡፡
2. ከብዙ እርቀት፤ በትራንስፖርት እጦትና ቤተሰብ በማሰናዳት ምክንያት የሚዘገዩና መስገድ መብታቸው በመሆኑ የግድ ሊጠበቁ የሚገባቸውን ወገኖቻችንን ችላ በማለት በሚዲያ ከሚያውጁት የሰላት ሰአት ወይንም ከወትሮው በፈጠነ ሰአት በማሰገድ ህዝቡን ከየአቅጣጫው ለመበተን መሞከራቸው አይቀርም፡፡ ይህንን መከላከል የኛ ሃላፊነት ሲሆን ሴራቸውን ሊያከሽፍ በሚያስችል ፍጥነት ከስፍራው በመድረስና ከወትሮው ሰአት በተለየ የሚጀመርን ሰላት በመቃወም የተከበረውን የዒድ ሰላታችንን በአንድነት እንሰግዳለን፡፡ ይህንን ጥረታችንን አስተጓጉለው ከፊሉን ህዝብ ሳይሰግድ ለመመለስ ቢጥሩም ማናችንም ሰላት ሳንሰግድ እንደማንመለስ ሊያውቁት ይገባል፡፡
3. የአንድነታችንን ውበት ለመጪው ግዜ በታሪክነት ለማስቀረት ሁላችንም እያንዳንዱን ትዕይንት በካሜራ እና በሞባይላችን መቅረፅ አንዘንጋ
4. በመብታችን ላይ ተረማምደው ለሌሎቸ አሳልፈው የሰጡንን የመጅሊስ አመራሮችንም ሆነ ተቀፅላውን የኡለማ ምክር ቤት አመራሮች በየትኛውም መመዘኛ በተከበረው በአላችን ላይ ከፊታችን እንዲቆሙ እንደማንፈቅድ አውቀው በነሱ የሚሸፈን ምነም አይነት የንግግር ፕሮግራም እንዲኖር እንደማንፈቅድ ሊረዱት ይገባል፡፡
ለአሁኑ ይህን ያህል ካልን የዒድ በአላችንን አስመልክቶ ወሳኝ ነጥቦችን ይዘን ዳግም ተመልሰን እንደምንገናኝ እየገለፅን እንሰናበት፡፡

No comments:

Post a Comment