በሌላ በኩል ደግሞ ይኸው ጣቢያ አንዲት አይነት ሰላማዊ ተቃውሞ ብናሳይ ሊፈጁን የተዘጋጁ ፖሊሶች እንዳሉ ይገልፅበት በነበረው የETV2 የፖሊስ ፕሮግራም ላይ ፕሮግራሙን የዘጋበት ዓርፍተ ነገር ፍፁም አስደምሞኝ ነበር። በፕሮጋራሙ መቋጫ ላይ አንዲት አይነት ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞን የኢድ ሰላት ላይ ማሳየት “የሀገር ገፅታን ማበላሸት” እንደሆነ ደምድሞ አልፏል። በጣም እኮ ነው ሚደንቀው እናንተየ…!!! ፖሊስ መስጅድ እየገባ ምእመናን መጨፍጨፉ፣ ሰላማዊ የመብት ጥያቄን የጠየቁ ሰዎች ሽብርተኛ ተብለው መታሰራቸው፣ ጋዜጠኞች የመብት ጥያቄን በመደገፋቸው የተነሳ የሚደርስባቸውን ስቃይ እና መከራ በመፍራት ከሀገር መሰደዳቸው፣ የግል ጋዜጦች መታገድ ወዘተ… የሀገር ገፅታን ሳያበላሽ፤ ህገ መንግስቱ ይከበር፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ፣ የሀይማኖት ነፃነት በተግባር ይረጋገጥ ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ “የሀገር ገፅታን የሚያበላሽ” ተብሎ መገለፁ ለመሆኑ ሀገሪቷ ምን አይነት ገፅታ እንዲኖራት ነው የሚፈለገው? የሚል ጥያቄን ያጭራል። ለነገሩ ጋዜጠኞቹ ከላይ የወረደላቸውን ፅሁፍ እንደ ገደል ማሚቱ ከማስተጋባት በዘለለ የማገናዘብ መብት የላቸው ሆዳቸው አምላካቸው ከሆኑ ጋዜጠኞች ይህንን መስማት የሚደንቅ አይደለም!!!።
መንግስት ከህዝብ ልብ ለመፋቅ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ከሰው እስከ በሬ አስሯል፣ ገድሏል፣ አቁስሏል… የተከበሩ የፀሎት ቦታዎችን ደፍሯል፣ ጋዜጣና ጋዜጠኞችን አሳዷል፣ አግዷል… ብቻ ምኑ ቅጡ ላለፉት ዘጠኝ ወራት እንደ ኢህአዴግ ከህዝብ ልብ ለመፋቅ ጥረት ያደረገ መንግስት በዓለም ዙሪያም ማግኘት ይከብዳል። አሁን ላይ ይህንን በደንብ ይገነዘበዋል የሚል ግምት አለኝ። እንደሚቆጭበትም ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ነገር ግን ባዶ ቁጭት ብቻውን ዋጋ አይኖረውም። ማንም ሊክደው የማይችለው ሙስሊሞች በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ካለፉት መንግስታት በተሻለ አንፃራዊ ለውጦችን አስመዝግበዋል። ይህም ኢህአዴግን ወደ ህዝቡ ልብ ለመመለስ ቆርጦ ወደ ተግባር ከገባ ነገሮችን ገር ያደርግለታል። ግን ሊታወቅ የሚገባው ነገር ባለፉት ዘጠኝ ወራት የጠፉት ጥፋቶች በአብዛኛው ላለፉት ሀያ አመታት የተገነባውን በኢህአዴግ ላይ ያለንን ጥሩ እይታ በአንዴ ገደል የሚከት ነው። እንደውም አብዛኞቻችን ኢህአዴግ ለሙስሊሞች ያረገዘልን ሴራ ከአፄ ዩሐንስ የከፋ ነው ብለን እንድናምን አድርጎናል። ታዲያ ይህንን በአንድ ጊዜ ከዜሮ በታች የወረደውን እምነታችንን ለመጠገን ምናልባትም ለማውረዱ ዘጠኝ ወራትን ከመፍጀቱ አንፃር ለመጠገኑ ደግሞ፤ “መገንባት ከማፍረስ የበለጠ ጊዜን ይወስዳልና” እስከ ምርጫ 2007 ድረስ የወሬ ሳይሆን የተግባር ተጨባጭ ለውጦች ማሳየት ግድ ይለዋል። ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ አንድ እርምጃ ወደኛ ከተራመደ እኛ ደግሞ ሁለት እርምጃ ወደርሱ ተራምደን የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ካለንበት ተጨባጭ እየተነሳን በማሳየት ከገባበት መቀመቅ ልናወጣው እንችላለን። ከዚህ ውጭ ግን አሁን ባለበት የግትርነት ስሜት እገፋበታለሁ ካለ ምንም ችግር የለም!!! “መንግስት የህዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል እንጂ ህዝብ እደሆን የመንግስት ጨቋኝነት ከመኖር አያግደውም” የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በተላያዩ ጨቋኝ ስርዓቶች ውስጥ አልፈናል መጨቆን ለኛ አዲስ አይደለም “ዛሬም ቢሆን ተጨቋኝ መሆናችንን አውቀን ልንኖር እንችላለን!!!” ነገር ግን፣ መንግስት እንደ መንግስት ህዝባቸውን ይጨቁኑ ከነበሩ መንግስታት ትምህርት ሊወስድ ይገባዋል። እሩቅ መሄድም አያስፈልገውም እራሱ ጥሎት የገባውን ደርግን መመልከት በቂ መማርያ ነው። ደርግ በጦር መሳርያ ከአፍሪካ እንደርሱ የታጠቀ አልነበረም፤ ግን ምን ዋጋ አለው!!! መሳርያው ቢኖርም መሳርያውን ተሸክሞ ለደርግ ስርዓት ለመሰዋት ዝግጁ የሚሆን የህዝብ ድጋፍ ግን አልነበረውም። በዚህም የተነሳ ወያኔ ይህ ነው የሚባል የጦር መሳርያ ሳይዝ በራሱ በደርግ መሳርያ ደርግን ለመጣል ችሏል። የህዝብን ድጋፍ ማጣት መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ከዚህ የበለጠ ማሳያ የለም።
ኢህአዴግ ከዚህ አንፃር የህዝበ ክርስቲያኑን ድጋፍ ለማግኘት ብሎ በሙስሊሙ ላይ የሚያከናውነውን ረገጣ ለህዝበ ክርስቲያኑ በማሰብ እና አለኝታ በመሆን የሚደረግ እንደሆነ ለማሳየት የሚያደርገው ጥረት የተበላ እቁብ ከሆነ ውሎ አድሯል ህዝበ ክርስቲያኑም አሁን ያለውን የሙስሊሙ ተጨባጭ በሚገባ ከመረዳቱም በላይ በዚህ የመብት ጥያቄ ላይ የህዝበ ክርስቲያኑን ኢንተረስት የሚጋፋ ምንም ነገር እንደሌለ በተጨባጭ መረዳት ችሏል። በመሆኑም ከህዝበ ክርስቲያኑ በኩል ምናልባት የፓርቲ ፖለቲካ ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር ይህ ነው የሚባል ኢህአዴግን ከጭንቅ ጊዜ ሊያድን የሚያስችል ድጋፍ ማግኘት ፍፁም አዳጋች ነው።
በስተመጨረሻም “ኢህአዴግ ሆይ ጊዜው አልመሸም እና የጭንቅ ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ተመከር!!!” የሚለው መልእክቴ ነው አበቃሁ…!!!
No comments:
Post a Comment