Tuesday, August 21, 2012

ኮሚቴው ሳይፈታ በምርጫው አንሳተፍም!!

ኮሚቴው ሳይፈታ በምርጫው አንሳተፍም!!
የህዝብ ውክልና የሌለውና በማን አለብኝነት ያሻውን ሲገነባና ሲንድ የኖረው ህገወጡ መጅሊስ ያስቀመጠው የምርጫ የግዜ ሰሌዳ እነሆ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ይቀሩታል፡፡ መላው የሃገራችን ህዝብም በድምፁ መታፈንና በጥያቄው ምላሽ ማጣት ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ ገብቷል፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት ምርጫውን አስመልክቶ የመወሰን ስልጣን የህዝቡና የህዝቡ ብቻ ነው ብለው ቢያሳውቁም የመጅሊስ አመራሮች ግን ማንስ ምን አገባው በሚል አምባገነንነት ምርጫውን በቀበሌና እኔ ባሰብኩት ሂደት ከማድረግ ወደኋላ የሚለኝ አንዳችም ሃይል የለም እያለ ይገኛል፡፡ ድምፁን ከማሰማትና ወደፈጣሪው ስሞታውን ከማቅረብ ውጭ አማራጭ የሌለው ህዝበ ሙስሊምም እጃችሁን ጠምዝዘን ከሂደቱ ማስወጣት ባንችልም በሂደቱ ላይ የራሳችንን አቋም ከማንፀባረቅ የሚያግደን የለም ሲል ሚሊዮኖች ሆኖ በዒድ አደባባዩ ድምፁን አሰምቷል፡፡ ከፊታችን ያለውን ምርጫ መሳተፍና አለመሳተፍ ከበርካታ ነጥቦች አንፃር የሚታይ ቢሆንም የኮሚቴዎቻችን ጉዳይ ግን ልዩ ትኩረት የሚሻው መሆኑ ሁላችንንም ያስማማናል፡፡ ምርጫውን እንደ አንድ አጀንዳ ብቻውን ነጥለን ከተመለከትነው በቀጣዩ የመጅሊስ መዋቅር ውስጥ በህዝብ ድምፅ የተመረጡ ወኪሎች ማግኘት ከመቻልና ምርጫን አንሳተፍም ማለት ያለውን ኪሳራ እንደ ትልቅ ጉዳት አድርገን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ይህ ሁላችንንም የሚያግባባን ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫውም ሆነ ሂደቱ በሚያሳዝን መልኩ የህዝብን ፍላጎት በረገጠና ለማወያየት እድል እንኳን ባልሰጠ አካሄድ እየተተገበረ ሊያሳስበን የሚገባው ወሳኙ ጉዳይ የአጠቃላይ መብታችን ጉዳይና የህዝባችን ስሜት መሆኑ አሳማኝ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት በሌሎች ነጥቦች ዙሪያ በርካታ ትንተናዎች ሊሰጡ ቢችሉም ምርጫው በቀበሌም ይሁን በመስጂድ፡-


• የመብት ጥያቄዎቻችንን ገና ስናነሳ ትልቁ ጭንቀታችን ማን ሂደቱን ከጫፍ ያድርስልን የሚለው ጉዳይ ላይ መክረን ያመጣነው የመፍትሄ ሃሳብ ኮሚቴ መምረጥ ነበር፡፡ ይህንን ስናደርግም ፍቃደኛ ሆኑም አልሆኑም ጥያቄዎቻችንን ለመንግስት ሊያደርሱ ይገባል በሚል ብዙዎቹን በሌሎበት ጠቁመን አሁን ላሉበት እንግልት ዳርገናቸዋል፡፡ ኮሚቴዎቻችን የዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች ናቸው፡፡ ያለፉትን ግዜያት በመሪነታቸው ያየነው አንዳችም ማፈግፈግና የህዝብን ጥቅም አሳልፎ የመስጠት ዝንባሌ አላየንም፡፡ ዛሬ ላይ እነሱ በታሰሩበት የህዝብን ጥቅምና የነሱን በሳል አካሄድ ከንቱ ማስቀረት የሚፈቅድ ህሊና የለንም፡፡ ኮሚቴዎቻችን ከጎናችን ቢሆኑና በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በእስር እየማቀቁ ባይሆን ምርጫውን መሳተፍ ከባድ አጀንዳ አይሆንም ነበር፡፡ ኮሚቴዎቻችን ባይታሰሩ ኖሮ ይህን መሰሉን ምርጫ መሳተፍና አለመሳተፍ እነሱው ይወስኑልንና በውሳኔያቸው እንደምንፀና አንጠራጠርም፡፡ ዛሬ እነሱ በታሰሩበት ሁኔታ ምንም እንኳን ምርጫውን ፍትሃዊ ለማድረግ እየተለፈፈ ቢሆንም አቋማቸውን እስካላወቅን ድረስና ከእስር ነፃ ሁነው ሳይወሰን በምርጫው አንሳተፍም፡፡
• ጉዳዩ ጉልቻ የመቀያየር ብቻ ቢሆን ኖሮ ውድ ኮሚቴዎቻችንን ይህን ያህል መሰዋእትነት መክፈል ባላስፈለጋቸው ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ በመላ ሃገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድምና እህቶች የነሱን ፈለግ ተከትለው እራሳቸውን ለእስርና ድብደባ ባላጋለጡ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ በዚህ መልኩ በምርጫው መሳተፍ ከፀፀትም ከታሪክ ተወቃሽነትም የሚያድን አይደለም፡፡
• ኮሚቴዎቻችን ሳይታሰሩ አብዛሃኛው ድካማቸው የመብትን ምንነትና መብትን ለማስከበር ማለፍ ስለሚጠበቅብን ሂደት በማስገንዘብ ላይ ነበር፡፡ ከታሰሩም በኋላ ያለፉትን ሳምንታት ጥያቄዎቻችንን ለማስመለስና ይህንን ተከትሎ በተፈጠረብን መንገላታትና መዋከብ ሙሉ ግዜና የሰው ሃይል ያንን ለመከላከል እንጂ በምርጫ ጉዳይ ላይ የተሰራ ስራ አለመኖሩ ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ ካለው አጭር ጊዜ አንጻር ህ/ሰቡን ንቁ ተሳታፊ ማድረግ ያስቸግራል፡፡ በመሆኑም የታሰሩት ሳይፈቱ በምርጫው አንሳተፍም፡፡

• ስለ ምርጫ ስናወራ ምርጫ የሚመስል ነገር ለማድረግ እየታሰበ ያለው አዲስ አበባ ብቻ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ አንድ ወይም ሁለት ወንበር ብቻ ነው ያለው፡፡ ሌሎች ክፍላተ ሀገራት ግን ምርጫ ይኖራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ከተሞች (ባቲ፤ መካነሰላም፤...) የተወሰኑ ሰዎች ለምርጫ የቀረቡ ሲሆን ከነዚህ ሁለት ሰዎች ውጪ የሚመርጥ ካለ ይታሰራል ተብሏል፡፡ በአዲስ አበባ እና በፌዴደራል ደረጃም ቢሆን በተጨባጭ እንደምናውቀው ምርጫው አልቋል፤ ማን ምን እንደሆነ ስለተመዳደቡ መሳተፉ መፈናፈኛ የሚያሳጣ አደገኛ መጅሊስ የሚያመጣ ነገር ይሆናል- ህገወጡንም ምርጫ ህጋዊነትን ያላብሰዋል፡፡ ለዚህ የደከሙና የታሰሩትንም የመታሰራቸውን አግባብነት ማፅደቅ በመሆኑ ሳይፈቱ ምርጫ አንሳተፍም፡፡
• የታሰሩትን ችላ ብለን፤ የማንቀበለውን የምርጫ ሂደት አፅድቀን ብንሳተፍ ጥያቄዎቻችንም ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተዳፍነው እንዲቀሩና ከምርጫ በኋላና ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ ሰበብ አስባብ እየተፈለገ ሊወሰድ የሚችለውን እርምጃ በጣም ያብሰዋል፡፡ በምርጫው ሂደት ላይም የሚከሰቱትን ተገቢ ያልሆኑ አካሄዶችን በሚቃወሙ ላይ እስራት ይከተላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከምርጫ በኋላ ሊፈጠር የሚችል ማንኛውንም አይነት ቅራኔ በህገወጥነት የሚያስፈርጅና ህዝቡም በተባበረ ክንድ እንዳይነሳ ጋሬጣ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ሰዓት ምርጫን መሳተፍ ማለት በህ/ሰቡ ውስጥ ክፍፍልን ከመፍጠሩ በተጨማሪ አለመተማመንን ያሰርጻል፤ መጅሊስ ከተመረጠ በኋላ የኮሚቴዎቹን ጉዳይ አንስቶ ተቃዉሞ ማስነሳት በቀጥታ ለጥቃት ያጋልጣል፡፡ መጅሊስ በራሱ ጥያቄዎቹ ተመልሰው ምርጫ ተደርጓል የኮሚቴዎቹ ጉዳይ ህግ የያዘው ስለሆነ በህግ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይቻልም በማለት ዝግ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም በምርጫው መሳተፍ ለጋራ መብታችን ሲታገሉ ለታሰሩት ሰዎች ህልውና አደጋ ስለሚሆን አንሳተፍም፡፡
ከምርጫው ጋር በተገናኘ ሁሉም ሙስሊም እያንፀባረቀ ያለውና ሊይዝ የሚገባውም አቋም ይህ ነው፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ ያሉ ሙስሊሞች በቂ መረጃ ላይደርሳቸው ስለሚችል ሁላችንም በየክልሉ ላሉ ዘመዶቻችን ስልክ በመደወልና ሌሎችም መንገዶችን በመጠቀም መያዝ ያለባቸው አቋም ይህንኑ መሆኑን እናሳውቅ፡፡

No comments:

Post a Comment