Wednesday, October 24, 2012

የቢጫው ተቃውሞና አገራዊ መልእክቱ

የቢጫው ተቃውሞና አገራዊ መልእክቱ

እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሃይማኖታዊና ህገ-መንግስታዊ መብታችን መጣሱን በመቃወም የ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ትግልን የህይወታችን አንዱና ዋነኛው ክፍል አድርገን መጓዝ ከጀመርን እነሆ አንድ አመት ሊሞላን ነው፡፡ በዚህም የትግል ሂደት መንግስትና አጋሮቹ ለአመታት የተዘጋጁበትን በሚስጥር ዶልተው በተናጠል ሊወስዱብን ያሰቡትን የእምነትና የመብት ነጠቃ ዘመቻ ቀድመን በመረዳት ትግሉን ለነሱ ፈታኝ በሆነው የሰላማዊ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ሜዳ ዉስጥ በማከናወን ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህም ጠያቂው ጥያቄዉን በሰላም የመጠየቅ፣ መላሹም ለጥያቄው ተገቢ ምላሽ መስጠት መቻል አለመቻሉ በብዙሃን ዳኝነት የሚታይበት ብቻ ሳይሆን ማን ‹‹አሸባሪ›› ማንስ ‹‹ተሸባሪ›› መሆኑ በግልጽ የሚታወቅበት ሁኔታ ጭምር ተከስቷል፡፡ ሂደቱም እነሱ እንዲፈጠር ከተመኙት ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ በመልካም አስተሳሰብ የበላይነትንና እውነተኛ ሀገር ወዳድነታችንን በተግባር ማሳየት ያስቻለ እድል ሆኗል፡፡ ዳሩ ግን የፈለጉት አልሰምር፤ ያሰቡት አልሳካ ሲላቸው በግልፅ በጠራራ ፀሃይ በመላው ዓለም እና በሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ህግንና ህገ-መንግስትን በጣሰ መልኩ ፤ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ፍጹም የሌሉ በሚመስሉበት ሁኔታ ንፁሃን አማኞችን እምነታቸንን በማዋረድ መስጂዶቻችንን (የእምነት ቦታዎቻችንን) በመድፈር፤ ሽማግሌዎቻችንን (ኮሚቴዎቻችንን)ና ሺዎችን በማሰር ፤ ደማችንን በማፍሰስ ሽንፈታቸውን እያሳዩን ይገኛሉ ፡፡ ይህ በሚስጥር የተዶለተው ፖለቲካዊ ሴራ መክሸፍና በጠራራ ፀሃይ የሚፈፀም መንግስታዊ እብሪት ማሳያ በመሆኑም ሳይወዱ በግዳቸው ፍላጎታቸውና ማንነታቸው እርቃኑን ቀርቷል፡፡ ሙስሊሙን ለሀገር ስጋት አስመስለው በመሳል በፖለቲካው ሜዳ አሸንፈው ለእርድ እያዘጋጁት የነበረ ቢሆንም ከነሱ በተሻለ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሀገሪቱ ሰላም ዘብ የቆመ መሆኑን በታሪክ ላይረሳ በደሙ እያስከተበ ይገኛል፡፡ ትናንት ሰላማዊ የነበርን ህዝቦች በመሆናችን ዛሬ ላይ ሰላማዊ መሆን ሳይቸግረን በሰላማዊነታችን የሚደርስብንን መከራ ሁሉ በትእግስት በመቀበል ላይ ጸንተን እንገኛለን ፡፡ ለዚህም ነው ህዝበ ሙስሊሙ ‹‹የመንግስት›› ቅርጫ በ27/01/2005 ከመደረጉ ከሁለት ቀን በፊት ያደረገውን ተቃውሞ የ”ቢጫ ተቃውሞ” ለማድረግ ያስፈለገው ፡፡እንደምናውቀው ቢጫ ምልክት ለመሄድም፤ ለመቆምም፤ ለመቀጠልም፤ ለመፅናትም የመዘጋጃ ደወል፣የተዘጋጅተሃል ? ማሳሰቢያ እና የተዘጋጅ ትእዛዝ! ምልክት ነው፡፡ መልእክቱም ተቃውሞው ለቀረበበት ለመንግስት (ምክንያቱም ሙስሊሙን ከተኛበት እንዲባንን ያደረገው የመነግስት ስህተት በመሆኑ ) የሚተው ቢሆንም ጉዳዩ ከዚህ የዘለለ የወደፊት የሃገራችንን እጣ ፈንታ የሚያመላክት ቆምታ ይሻልና መልእክቱ ሃገራዊ እንድምታ እንዳለው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ቢደርስ ወደድን፡፡

ቢጫው ለመንግስት የሚሠጠው መልእክት፡-

ብዙሃንን ህዝብ ጥቂቶች በሚል በመፈረጅና በማግለል (Discrimination) የአሸባሪነት ታፔላ ለመለጠፍ የተደረገው ሙከራ በበቂ እውቀታዊ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ ፤ መነሻውን በጠቅላላ እውነታ ላይ ሳይሆን በጊዜያዊና ሚዛን በሳቱ ክስተቶች ላይ የገነባ ፤ መድረሻው በትክክል ያልተተነበየለት ፤ ሂደቱ መሬት ላይ ላለው ተጨባጭ ያልተገራ ፤ ለክስተቶች ክፍተት ሰጥቶ ከመንግስታዊ መዋቅራዊ አመራር ይልቅ ግለሰባዊ ፍላጎቶችና ስሜቶች እየተስተናገዱበት የሚገኝ ሆኗል፡፡ በከሰረ ፖለቲካዊ አካሄድ የኢትዮጵያን ሙስሊም አክራሪ ብሎ መፈረጅ ፤ በማን አለብኝነት ሃማኖታዊ ምርጫን የአማኙ ይሁንታ ሳይኖር በካድሬዎች ድራማ ለመመስረት መጣር፤ ስህተትን በሌላ አወሳሳቢ ስህተት ለማረም መሞከር ታላቅ ሀገራዊ ስህተት በመሆኑ መንግስት እንደህዝብ መሪ ቆም ብሎ እንዲያስብበት የቢጫ ምልክት አሳየን ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዚህ ስህተት የመግፋት ትርፉ በመንግስት ላይ ሌላ ውል አልባ የቤት ስራ መጨመር ብቻ በመሆኑ፡፡ ይህ እንዲህ ከገፋ ደግሞ ቀጣዩ የትግል ምእራፍ ይጀመራል ማለት ነው፡፡ የዚህኛው ምእራፍ መገለጫው ሰላማዊ ትግሉ አድጎ የህግ አስፈጻሚ አካሉ ያላከበረውን ህግ ህዝብ ይከበርልኝ ሲል የመንግስት የፍትህ አካላትን ከፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ የመሆንና ያለመሆን የይረጋገጥልኝ ከባድ ጥያቄ ያነሳል፡፡

ይህ ደግሞ መንግስትን የበለጠ የሚፈትንና የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ውሳኔ ከተጨማሪ የፍትህ አካላት ውሳኔ ጋር የሚያፋጥጥ አዲስ ምእራፍ ከፋች ይሆናል፡፡ ለአብነትም ህዝብ በህገወጥ አስፈፃሚዎች የተቀነባበረ ቅርጫ፤ በጉልበት የተሰየመ ሹመኛ በህዝብ እውቅና ያልተሰጠው ህገወጥ የመጅሊስ አወቃቀር መምራት የሚያስችለው ምንም የህግ ድጋፍ የለውም የሚል ነፃ የፍርድ ጥያቄ ያነሳል፡፡ በሌላ ቀላል ምሳሌም ኮሚቴዎቻችን ሚሊዮኖች የወከልናቸው መሪዎቻችን ሆነው ሳለ ለህግ ምርመራ በሚል መንግስት ሲይዛቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታታቸውን እየጠየቀ ለሰላም ባለው ቁርጠኝነት ዝም ማለትን መርጧል፡፡መንግስት የሚመዘነው ህዝቡ ለጠየቀው ጥያቄ በቀናነት መልስ መመለስ መቻል ያለመቻሉ ሆኖ ሳለ እነሱን ለመፈረጅ የሚደርገው ጥረት ከፍትህ ጋር መላተምን ፤ ከህዝብ ጋር ፀብን ፤ ለእንቅስቃሴው ሌላ አዲስ ጉዳይን መፍጠር ነው የሚሆነው ፡፡ በዚህ አግባብ ምናልባትም የፍርድ ውሳኔ ተፈትኖ በፖለቲካ ውሳኔ መሸነፍ ይከሰታል ፡፡በስተመጨረሻም መንግስት ህገ መንግስታዊ መብቴ ይከበርልኝ ባለ ትውልድ ፊት ምንም አይኖረውም፡፡ ምንም የሌለው ደግሞ…….

ቢጫው ለሁሉም የመንግስት ደጋፊና አባላት ያለው መልእክት

ከለታት በአንዱ ቀን ታላቁ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ “ አንዳችሁ ወንድሙን በዳይም ተበዳይም ሲሆን ይረዳው ” አሉ ስለፍትህ ብዙ የተማሩት ሶሃቦች (የነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች ) ግን በፍጥነት አንቱ የአላህ መልእክተኛ ሆይ ሲበደልስ እሺ በዳይ ሲሆን ግን እንዴት ልንረዳው ይቻለናል ሲሉ ጠየቁ ፡፡ ታለቁ ነብይም ሲመልሱ በደል በሚፈፅምበት ጊዜ “እጁን ትይዘዋለህ ” ይሄ ነው ወንድምን መርዳት አሉ ፡፡ የተሳሳተ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ አጥፊ ውሳኔዎች ሲወሰኑ ማጫፈር ታማኝነት ሊሆን አይችልም ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ግን ግላዊ ጥቅምና ሥልጣንን ለማደላደል ብቻ መሮጥ ሀገራዊ ጉዳት ሊያደርስ ይቻለዋልና ቆም ብላችሁ እንድታስቡ ለናንትም ነውና ቢጫ ምልክት አሳይተናችሁዋል ፡፡

ቢጫው ለኛ ለሙስሊሞች ያለው መልእክት፡-

ለጌታችንና ዲናችን ያለን ታማኝነት ፤ ለሀገራችን ያለን ቀናኢነት ፤ ሰላምን መንገድ አድርገን ለመምረጥ ያለን ቁርጠኝነትና ፅናት የበለጠ የሚፈለጉበት ሰዓት ላይ እንገኛለን፡፡ ከጠየቅናቸው ቀላል የመብት ጥያቄዎች አንፃር በመንግስታችን እየደረሰ ያለው ግፍ አንድ ዜጋ ሊታገሰው ከሚችለው ድንበር እየተሻገረ የመጣበት ወቅት መሆኑም እሙን ነው፡፡ በምንም መልኩ ቢሰላ አግባብ ነው ሊባሉ የማይችሉት የመብት ጥሰቶች ‹‹ታዲያ በዚህ ሁኔታ የሰላማዊ ትግል ውጤታማነት የቱ ጋር ነው›› ተብሎ የሚጠየቅበት ወቅትም መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ግን ደግሞ ቢጫ ይህንንም ሰክኖ ለማስተንተንና ቀጣዩን ለማቀድ ማስጠንቀቂያ ነውና ለኛም ለራሳችን ቢጫ አውለብልበናል ፡፡ ይህ የኳስ ጨዋታ ሜዳ ፍልሚያ ሳይሆን የሃገርና የዜጎች የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምሳሌያችንም ለዚያው ቀድር የሚመጥን ይሆናል፡፡ ለሚያስተውሉ ሁሉ ልቦናቸውን ሰብሰብ አድርገው ሂደታቸውን እንዲፈትሹ ቢጫችንን ደግመን ደጋግመን እናሳያለን፡፡

አብሽሩ በዚህ የሰላማዊነት ትግል መንገድ ድል ያላገኘ ተበዳይና ያልተሸነፈ በዳይ የለምና በጌታችን እርዳታ ለድል እንበቃለን ፡፡ በዳዮች ደግሞ ፍትህን ለጠየቀ ህዝብ ጉዳዩን በጥሞና ለማጥናት ከመሞከር ይልቅ ባላችሁ የዛሬሃይል ከሆነ የምትመኩት ተፈጻሚ በሆነው የጌታችን ቃል ተመከሩበት ስንል እንዘክራችኋለን፡፡ ለኛ ደገሞ መጪ ግዚያችንና የትግስታችንን ውጤት ምን እንደሆነ የምናይበትን ቃል እናነብላችኋለን ፡፡ እንድህም ይነበባል ““ ከሙሳና ከፈርዖን ዜና እውነተኞች ስንሆን ለሚያምኑ ሕዝቦች በአንተ ላይ እናነባለን፡፡ ፈርዖን በምድር ላይ ተንበጣረረ፡፡ ነዋሪዎቿንም የተከፋፈሉ ጓዶች አደረጋቸው፡፡ ከእነርሱ ጭፍሮችን ያዳክማል፡፡ ወንዶች ልጆቻቸውን በብዛት ያርዳል፡፡ ሴቶቻቸውንም ይተዋል፤ እርሱ ከሚያበላሹት ሰዎች ነበርና፡፡በእነዚያ በምድር ውስጥ በተጨቆኑት ላይ ልንለግስ መሪዎችም ልናደርጋቸው ወራሾችም ልናደርጋቸው እንሻለን፡፡ ለእነርሱም በምድር ላይ ልናስመች ፈርዖንንና ሃማንንም ሰራዊቶቻቸውንም ከእነሱ ይፈሩት የነበሩትን ነገር ልናሳያቸው (እንሻለን)፡፡”” (ሱረቱ-አልቀሶስ 3-6) እናም ቆም ብሎ ማሰብ ተስኗችሁ ባላችሁ ስልጣንና ሀይል መመካት ፤ መከፋፈል ፤ ማዳከም ፤ መግደል ፤ አበላሽ (የህዝብን ሰላም መንሳት) ከሆነ ተግባራችሁ አርግጠኛሁኑ በናንተም በሰራዊታችሁም ላይ የፈራችሁት ይከሰታል ፡፡ ተበዳይም ከጭቆና ቀንበርም ባለው ሃይል ሳይሆን በልግስና ነጻ ሊወጣ የፈጣሪ መሻት የፍጥረታት የሁልጊዜ እውነት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

አላህ ሆይ የስኬት ባለቤት አንት ነህና እርዳታህን ካነተ እንሻለን ወደኛ ወዳወርድከው መልካም ነገር ሁሉ ከጃይ ነን!

ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment