እንግዲህ ከላይ ካየናቸው የሕገ-መንግስት አንቀፆች በመንተራስ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም በመንግስት ላይ (በመረጧቸው ተወካዮች ላይ) እምነት በሚያጡበት ጊዜ ውክልናቸውን ማንሳት (ቀይ ካርድ ማሳየት) እና እምነት ለሚጥሉበት ሌላ አካል ውክልናቸውን መስጥት ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው ነው። የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ደግሞ አንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል እንደመሆኑ መጠን የዚህ ሉዓላዊ ስልጣን ተጋሪ ይሆናል ማለት ነው። በመሆኑም ሙስሊሙ ማህበረሰብ በመንግስት ላይ እምነቱን ካጣ ቀይ ካርድ የመምዘዝ ሕገ-መንግስታዊ መብት አለው ማለት ነው። ነገር ግን ይህ ሲባል የካርድ አመዛዘዙ ስነስረዓትም በሕገ መንግስቱ ላይ በተደነገገው መልኩ መሆን ይኖርበታል።
ቀይ ካርድ መዘዛ በሕገ መንግስታችን
ለመሆኑ ቀይ ካርድ መምዘዝ ሕገ መንግስታዊ መብታችን ከሆነ ይህንን መብት በምን አይነት መልኩ መጠቀም ይቻላል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሀገሪቱን የፖለቲካ ስልጣን አያያዝ መንገድ ማጤን ያስፈልጋል። በሕገ-መንግስታችን ምእራፍ፥6 አንቀፅ፥56 “የፖለቲካ ስልጣን” “በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግስት የሕግ አስፈፃሚ አካል ያደራጃል/ያደራጃሉ ይመራል/ይመራሉ” ይላል። ከዚህ አንቀፅ ደግሞ እንደምንረዳው የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚገኝ የአብላጫ ወንበር መሰረት መሆኑን እንረዳለን። በመሆኑም ሕዝቦች ሉዓላዊ ስልጣናቸውን (ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን) በመጠቀም መንግስትን ቀይ ካርድ መስጠት ከፈለጉ የሚኖራቸው አማራጭ በምክር ቤቱ ውስጥ ያለውን ወንበር በመንጠቅ እምነት ለሚጥሉበት አካል መስጠትና በምክር ቤቱ ያለውንም አብላጫ ወንበር በማሳጣት ሀላፊነቱን እምነት ለሚጥሉበት አካል ያስረክባሉ ማለት ነው። ይህንንም ሕገ መንግስቱ እንዲህ ሲል ያብራራዋል “ማንኛውም የምክር ቤት አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በሕግ መሰረት ከምክር ቤት አባልነቱ ይወገዳል።” ምእራፍ፥6 አንቀፅ፥54 ንዑስ አንቀፅ፥7
እንግዲህ ከሀገሪቱ የበላይ ህግ ሕገ-መንግስቱ መረዳት እንደሚቻለው ሉዓላዊ ስልጣን የህዝቦች ነው እንጂ ማንም የመንግስት ባለስልጣን ስልጣኑን እንደ ርስት በመያዝ ያልተመቸውን ሁሉ “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ አለው!!!” እያለ የሚወነጅልበትና ስልጣንን ለርሱ ብቻ እንደተፈጠረ ንብረቱ የሚገለገልበት መሳርያ አይደለም። የፖለቲካ ስልጣን በህዝብ በጎ ፍቃድ ይሰጣል እንዲሁም ህዝብ አመኔታውን ሲያጣ ደግሞ ይነጠቃል፤ ታዲያ እውነታው ይህ ከሆነ አሁን ካለንበት ተጨባጭ አንፃር ሙስሊሙ ህብረተሰብ ቀይ ካርድ መምዘዝ ቢያስፈልገው በምን መልኩ ሊተገብረው ይችላል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።
የቀይ ካርድ አመዛዘዝ አሁን ባለንበት ተጨባጭ
የኢህአዴግ መንግስት ከቀደምት መንግስታት አንፃር ካሳየን አንፃራዊ ለውጥ አኳያ ለረዥም ዘመናት ስንደግፈው ኖረናል። ግና ካሳለፍነው አመት ጀምሮ እየሰራው ያለው የህግ ጥሰት እና ወንጀል በመካከላችን ልዩነት እንዲፈጠር በር ከፍቷል ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እኛ ሙስሊሞች የእስከዛሬውን መልካም ጅምር በማየት ቁጣችንን ዋጥ በማድረግ እንደውም የመንግስትን ጥፋት በመሸፋፈን ጭምር ችግሮች በጊዜ እንዲፈቱና ልዩነቱ ሳይሰፋ በቶሎ ቀዳዳው እንዲደፈን ከፍተኛ ትግል ስናደርግ ቆይተናል። የጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ አዲሱ መንግስት ተረጋግቶ ስልጣን እስኪጨብጥና ጥያቄያችንን ድጋሚ እስከሚያጤን ድረስ የሰጠነው ፋታም ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን ይህንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ አዲሱ መንግስት ችግሮችን ይፈታል ብለን ስንጠብቅ ነገሮች ሁሉ “ከድጡ ወደ ማጡ” እያመሩ አዲሱ መንግስትም “ታጥቦ ጭቃ” እንደሚባለው አይነት ሲሆንብን ለአመታት ስንደግፈው ለኖርነው መንግስት የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ለመምዘዝ ተገደናል። ሁኔታዎች የማይለወጡ ከሆነም ሕገ-መንግስታዊ መብታችንን (ሉዓላዊ ስልጣናችንን) በመጠቀም ቀይ ካርድ የማንመዝበት ምንም ምክንያት የለም። ነገር ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት መንግስት በቶሎ ልብ ገዝቶ ህብረተሰቡን ይፋዊ ይቅርታ በመጠየቅ ሀገራዊ መግባባትን ለማስፈን እንደሚጥርና ለዚህ ጥፋት የዳረጉት ሀላፊዎች ላይም ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ ተስፋችን ነው።
አሁን ካለንበት ተጨባጭ አንፃር ቀይ ካርድ ለመምዘዝ ካስፈለገን ልንከተለው የሚገባን አካሄድ መጀመሪያ ጥያቄዎቻችን በደንብ የገባቸው እና የተረዱን በምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አወዳድረን ስናበቃ ዓንዱን ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን፤ በመቀጠልም በየምንኖርበት ክልል ላይ የመረጥናቸው የኢህአዲግ የምክር ቤት አባላት ላይ እምነት ማጣታችንን እና እነርሱ ሊወክሉን እንደማይችሉ የሚገልፅ ፔቲሽን አሰባስበን ስናበቃ ለዚህ ፓርቲ በመስጠት ተወካዮቹ የኢህአዲግ አባላት የምክርቤቱን ወንበር እንዲለቁ እና በምትካቸው እምነት የምንጥልበት ሰው እንዲተካ በሕገ መንግስቱ ላይ በምእራፍ፥6 አንቀፅ፥54 ንዑስ አንቀፅ፥7 ላይ በሰፈረው መልኩ ጥያቄያችንን ለምንስማማበት ተቃዋሚ ፓርቲ ውክልናን በመስጠት እናቀርባለን። በህጉም መሰረት እነዚያ የምክር ቤት አባላት ተወግደው የምንፈልገው የተቃዋሚ ፓርቲ ቦታው ላይ እንዲሰፍር በማድረግ እንደ ሱማሌ፣ አፋር፣ ሀረር፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ፣ አዳማ ወዘተ ባሉት ክልሎች ላይ ኢህአዴግ መቀመጫውን እንዲያጣ ማድረግ። የኛን እንቅስቃሴም አይተው ሌሎች በስርዓቱ የተጨቆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም የኛን አርዓያ እንዲከተሉ በማድረግ በህጋዊ መንገድ ኢህአዲግ በህዝብ የተሰጠውን ውክልና በዓግባቡ ባለመጠቀሙና ሉዓላዊ ስልጣን ደግሞ የህዝቦች በመሆኑ ሕዝቦች እምነት ለሚጥሉበት አካል ስልጣኑን(ሀላፊነቱን) እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል።
ከላይ ለማየት የሞከርነው ምናልባት ወደፊት ትግስታችን ተሟጦ ሕገ መንግስታዊ መብታችንን ተጠቅመን ቀይ ካርድ ማሳየት ካስፈለገን ልንከተለው የሚገባንን ስነስረዓት ነው። እዚህ ቦታ ላይ ሳልጠቅስ ማለፍ የሌለብኝ ነጥብ ቢኖር ምናልባት ጥያቄያችን ሳይመለስ ቀርቶ ከላይ ወደተጠቀሰው እርከን እንኳ የምንሻገር ቢሆን ሰላማዊነታችን እስከፍፃሜው ድረስ አብሮን ሊዘልቅ የሚገባው ባህሪያችን እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል። በተጨማሪም የስርዓቱ መበላሸት የዜግነት ግዴታችንን ከመወጣት ሊገታን አይገባም፤ በልማት እና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለን ተሳትፎ እንደወትሮው ሁሉ እስከ ትግላችን ፍፃሜ ድረስም አብረውን ሊቀጥሉ ይገባል።
በስተመጨረሻም ቀይ ካርድ ማሳየቱ ከላይ የተጠቀሱት:- ጊዜ የሚፈልጉ አካሄዶች እና ስርዓቶች የሚኖሩት ከሆነ ዛሬ ላይ ቢጫውን ካርድ እንዳውለበለብን ሁሉ ነገም በቀዩ ካርድ እርከን ላይ ቀይ ካርድ ማውለብለብ እንችላለን ወይ የሚሉ ጥያቄዎች ቢነሱ ምላሹ አዎን ይቻላል የሚል ነው የሚሆነው፤ ያም የምናውለበልበው ቀይ ካርድ ኢህአዴግ ከልባችን መፋቁንና በመረጥናቸው የኢህአዲግ አባላት ተወካዮቻችን ላይ እምነት ማጣታችንን የሚገልፅልን ይሆናል።
No comments:
Post a Comment