Monday, November 19, 2012

የመራኑ ሃቢብቲ የቃሊቲ የዚያራ ትረካ



የመራኑ ሃቢብቲ የቃሊቲ የዚያራ ትረካ

"ስለፌዴራል ፖሊሶች ግን ባላወራ ይቀለኛል፡፡ ቅንነት የሚባል ነገር
አልፈጠረባቸውም፡፡ ህዝቡ የሚደናበር መስሏቸው እስከ አፍንጫቸው ታጥቀው በህዝቡ መሃል በመኪና አስሬ ይመላለሳሉ፡፡ ግብር ከፍሎ በሚያስተዳድራቸው ወንድሞቻቸው መሃል ሳይሆን በሃገሪቱ ላይ የሆነ የጠላት ጦር ወረራ ፈፅሞ ለግዳጅ የተሰማሩ ነበር የሚመስሉት፡፡ የአሜሪካን ጦር አባላት እጅግ በሚያስፈራው የአፍጋኒስታን የቶራ ቦራ ተራራ አካባቢ ሲሰማሩ እንኳ እንደዚህም የታጠቁ አይመስለኝም፡፡ ፌዴራል ፖሊሶቹ ክላሻቸውን ወደ ሰላማዊው ህዝብ ደግነው በፓትሮል ወዲህ ወዲያ ይላሉ፡፡ እብዛኛው የፌዴራል ፖሊሶቹ አባላት ከታጠቁት ትጥቅ በተጨማሪ ደረታቸውን ያሳበጠ የደረት መከላከያም አድርገዋል፡፡"

ቃሊቲ አቅሏን ሳተች
ወደዳችሁም ጠላችሁ ግርማ ሞገሱ ከሩቅ ይስባችኋል፡፡ በነጭ ጀለቢያ ተውቦ ፍፁም ርጋታ በተላበሰ ሁኔታ ሊዘይሩት የመጡትን ጠያቂዎች በአይኑም፣በፈገግታውም፣ ጭንቅላቱንም ጭምር በመነቅነቅ ምስጋናውን ይገልፃል፡፡ ይህ ሁኔታ ለረጅም ሰዐት የዘለቀ ቢሆንም እሱና ጓደኞቹ ያለምንም ድካም ጠያቂዎቻቸውን(ዘያሪዎቻቸውን) ተቀብለው እያስተናገዱ ነው፡፡ ጠያቂዎችም ያለምንም ፋታ መፍሰሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ልክ የአባይ ዉሃ አገር አቆራርጦ እየፈሰሰ ከግብፁ አስዋን ግድብ እንደሚጨመረው አይነት ጠያቂዎችም በረጅሙ እየፈሰሱ ከዚህ ቆፍጣናና ልበ ሙሉ ወጣት አጠገብ ሲደርሱ ከንግግግር ይልቅ እንባ ይተናነቃቸዋል፡፡ ይህ ወጣት በቅርቡ ወደዚህች አለም ከመጣች ሳምንት ያልሆናት የሱመያ አባት የሆነው አህመዲን ጀበል ነበር፡፡
ውድ አንባቢያን ከሰላምታዬ አስቀድሜ በቀጥታ ወደቃሊቲ እስር ቤት ያስገባሁህ ወድጄ እንዳይመስልህ ናፍቆት ነበረብኝና ነው፡፡ የቃሊቲ ትርክቴን ያቋረጥኩት የአንተን ልብ ለማንጠልጠልም አይደለም፡፡እመለሳለሁ፡፡ ናፍቆቴን ላጣጥም ብዬ እንጂ፡፡
መቼም አትፈርድብኝም አይደል?፡፡ ከዘጠኝ ወር በፊት ከሞቀው ቤታቸው አስነስቼ ለመንግስት ችግሬን አስረዱልኝ፣ፍላጎቴን በትህትና ይህ ነው በሉልኝብዬ በፊርማዬ ጭምር አረጋግጬ የላኳቸው ፣መንግስትም ይህን አምኖ በክብር ቢሮው ድረስ ጠርቶ አናግሯቸው እንነበረ ሁላችንም አንረሳውም፡፡አሸባሪእንዳልሆኑ እኔና አንተን ጨምሮ አለም ቢመሰክርም ዛሬ ግን በአክራሪ ብሄርተኞች የሚመራው ሽብር ፈጣሪው መንግስታችን ኮሚቴዎቻችንንአሸባሪ ናችሁበማለት ወደ ወህኒ ከወረወራቸው 3 ወራት እንዳለፋቸው ይታወቃል፡፡ ከዛ ወዲህ ኮሚቴዎቻችንን በቅርበት ብዙም የማየት እድል አልነበረኝም ፡፡ መንግስት ፍርድ ቤት እንኳ ሲያቀርባቸው በዝግ ችሎት ደብቆ ነበር፡፡ ሲገቡም ሲወጡም አናያቸውም ነበር፡፡ እናም አሁን አንተም እኔም እነኝህን የሰላም አምባሳደር ብንናፍቃቸው ይፈረድብናል ትላለህ? ለዚህም ነው እንግዲህ ከጠዋቱ 12 30 ሲሆን 4 ጓደኞቼ ጋር በመሆን ወደ ቃሊቲ ያመራነው፡፡ለአንድ አምስት ጉዳይ እዛ ስንደርስ ግን በሰዉ ብዛት ደንግጬ ነበር፡፡(የተጓዝነው በጓደኛችን መኪና በመሆኑ ቶሎ እንደምንደርስና የተሻለ ቦታ ጠብቀን ነበር ወደቃሊቲ ያመራነው)፡፡ በዛ ሰዐት የነበረውን የሰዉ ብዛት ላየ መቼም ህዝቡ እዛው አድሮ እንጂ ከነጋ ነው የመጣው ብዬ ለማመን ተቸግሬ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን አድናቆቴ ወዲያው በኖ ጠፋ፡፡ ለጀግኖቻችን ይህችን ማድረግ ማለት ምንም ማለት እንዳልሆነም ተረዳሁ፡፡ሲያንሳቸው እንጂ፡፡ እስረኞችን የመጠየቂያ ሰዐት በጣም ገና በመሆኑ ሰልፌን ትቼ አካባቢውን መቃኘት ዞር ዞር ማለት ጀመርኩ፡፡ ሰዎች ከአዲስ አበባ የተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ቃሊቲ እየጎረፉ ነው፡፡ ከጠዋቱ 3ሰዐት አካባቢ የሰዉ ብዛት ከምነግራቸሁ በላይ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ የደህንነት ሃላፊዎችና የቃሊቲ ባለስልጣናት በተስማሙት መሰረት ሰልፉ እንደ ከዚህ ቀደሙ በነበረበት በኩል ሳይሆን ረጅም ሰልፉን ውጦ ያስቀርልናል ብለው ባሰቡት መንገድ ነበር ሰዉን በውስጥ ለውስጥ መንደር ውስጥ እንዲሰለፍ ያደረጉት፡፡ ሴት እህቶቻችንንም ከወንዱ በመለየት ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በስተደቡብ በኩል ወደታች ያለውን ውስጥ ለውስጥ መንደር እንዲሰለፉ አደረጉ፡፡ ይህን ያደረጉት ህዝቡ የፈለገ ቢበዛ ወደ አስፋልት እንደማይወጣ እርግጠኞች ሆነው ነበር፡፡ ቅዳሜ ከምንጮቼ ባገኘሁት መረጃ የየክፍለከተማ የደህንነት ሃላፊዎችና ከሌሎች ቦታዎች የተወከሉ የፀጥታ ሰዎች በአዲስ አበባ ደረጃ ያደረጉትን ስብሰባ አካፍዬህ ነበር፡፡ ታዲያ በዚሁ ስብሰባቸው አበል የለመዱ የየክፍለ ከተሞቹ ደህንነቶች ነገሩን ሆን ብለው ለጥጠው ውጥረት ለመፍጠር እንደሞከሩ ታዝበናል፡፡ በተለይ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደህንነት ሃላፊው ሙስሊሙ ዚያራ ሳይሆን ለጦርነት እንደሚንቀሳቀስ በማሰብ ከፍተኛ ሃይል እንዲመደብ ሲወተውቱ እንደነበር ከስብስባው ለመረዳት ችለን ነበር፡፡ እንግዲህ የዛሬውን የቃሊቲ ፀጥታ ሁኔታ ሳየው ያሸነፈው የፌዴራሉ የመረጃና ደህንነት ሃላፊው የአቶ ጌታቸው ይመሰላል፡፡ በወቅቱ ምንጮቼ ባደረሱኝ መረጃ መሰረት የአቶ ጌታቸው ፍላጎት የተወሰኑ ልዩ ሃይሎችን መድበን ስራው በአብዛኛው በመደበኛ ፖሊሶች እንዲሆን እንደነበር ገልጬ ነበር፡፡የግንቦት ሰባትንና የኤርትራን የሽብር መረብ ብጥስጥሱን እንዳወጡትና እንዳሽመደመዱት ሁሌም እታች ላሉት የደህንነት አባላት እንደ ጀብዱ ማውራት የሚቀናቸው በፌዴራሉ ድህንነት ውስጥ የፀረ ሽብርና ሃላፊው አቶ ነብዩ ባስቸኳይ ተጠርተው ስብሰባውን ቢካፈሉም የየክፍለ ከተማ የደህንነት ሃላፊዎን ሃሳብ ከሰሙ በኋላ ምንም ሳይወስኑ ለድጋሚ ስብሰባ ቀጥረዋቸው እንደተለያዩ ነበር መረጃው እንደረሰን ማሳወቃችን ይታወቃል፡፡ በዚህ ስሌት ስንሄድ ሃላፊዎቹ በቃሊቲ የሚኖረው የፀጥታ አጠባበቅ በአቶ ጌታቸው ሃሳብ እንደሄዱ እንረዳለን፡፡ ህዝቡ ላይ ውጥረት በሚፈጥር መልኩ ወደ ቃሊቲ እንዳይሄድ ማድረግና ቃሊቲ መዳረሻዎች ላይ ሲደርሱ አፍኖ መጠየቅ እንደማይቻል ነግሮ ህዝቡን ተመለሱ ማለት ሌላ አደገኛ ውጥረት እንደሚፈጥር በማሰባቸው ይመስላል ፣ከዚያ ይልቅ የመረጡት የመጣውን ህዝብ ማለቂያ ወደሌለው የቃሊቲ አካባቢ የውስጥ ለውስጥ መንደር ህዝቡ እንዲሰለፍ የወሰኑት፡፡ በምንም ተአምር ግን ህዝቡ ወደ አስፋልት እንዲወጣ አልፈለጉም፡፡ እዛው መንደር ለመንደር ይራወጥ ብለው የወሰኑ ይመስላል፡፡ ግና እንደ ጅረት የሚፈሰውን ህዝብ ማለቂያ የሌላቸው የቃሊቲ ውስጥ ለውስጥ መንደሮችም ሊቋቋሙት እንዳልቻሉ ከደቂቃዎች በኋላ ታዩታላችሁ፡፡ እናም ሁኔታው የአዲስ አበባ የደህንነት ሰዎች ህዝቡን ወደ ቃሊቲ እንዳይመጣ ከመከላከል ይልቅ ተውጦ የሚቀርበትን ዘዴ ዘይደው እንደተዘጋጁበት መረዳት ይቻላል፡፡ ዘዴያቸው ውጤታማ ሆኖ እንደሆነ እስኪ ወደ ኋላ እናያለን፡፡ ለማንኛውም እኔ አሁን ሌሎች የማውቃቸው ሰዎች አግኝቼ ቀድሞ ከተሰለፍኩበት እጅግ የተሻለ ቦታ አገኘሁ፡፡ ሰዉ ከአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ጋር በመሆን በሚደንቅ ሁኔታ እራሱን ያስተናግድ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረቦች ከህዝበ ሙስሊሙ ጋር በፍፁም መግባባትና ወንድማማችነት መንፈስ ሰልፉ ስርአት እንዲይዝ ሲጥሩ ነበር፡፡ ከህዝበ ሙስሊሙም ምስጋና ሲቸራቸው ነበር፡፡ እኔም ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ የሙስሊሙ ሰላማዊነትን በመረዳታቸው በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ ነበር ስራቸውን ሲረሩ የነበረው፡፡ ስለፌዴራል ፖሊሶች ግን ባላወራ ይቀለኛል፡፡ ቅንነት የሚባል ነገር
አልፈጠረባቸውም፡፡ ህዝቡ የሚደናበር መስሏቸው እስከ አፍንጫቸው ታጥቀው በህዝቡ መሃል በመኪና አስሬ ይመላለሳሉ፡፡ ግብር ከፍሎ በሚያስተዳድራቸው ወንድሞቻቸው መሃል ሳይሆን በሃገሪቱ ላይ የሆነ የጠላት ጦር ወረራ ፈፅሞ ለግዳጅ የተሰማሩ ነበር የሚመስሉት፡፡ የአሜሪካን ጦር አባላት እጅግ በሚያስፈራው የአፍጋኒስታን የቶራ ቦራ ተራራ አካባቢ ሲሰማሩ እንኳ እንደዚህም የታጠቁ አይመስለኝም፡፡ ፌዴራል ፖሊሶቹ ክላሻቸውን ወደ ሰላማዊው ህዝብ ደግነው በፓትሮል ወዲህ ወዲያ ይላሉ፡፡ እብዛኛው የፌዴራል ፖሊሶቹ አባላት ከታጠቁት ትጥቅ በተጨማሪ ደረታቸውን ያሳበጠ የደረት መከላከያም አድርገዋል፡፡ ከነሱ ውስጥ ጥቂቶቹ ደግሞ ከጥቁር ማይካ ስባሪ የተሰራ የሚመስል ጥቁር መነፅር አድርገዋል፡፡ ህዝቡ እንኳን ሊፈራቸው ሙድ ነበር ሲይዝባቸው የነበረው፡፡ እነሱ ግን ሽብር ለመልቀቅ ይመስላል በተደጋጋሚ ይሽከረከራሉ፡፡ በፖሊስ ታርጋ 0193, 0108,009300860154 ፕሊስ ታርጋ የለጠፉ ፓትሮሎች ተጭነው ለማሸበር የሚችሉትን አድርገዋል፡፡ ታርጋ የሌላቸውም ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ህዝቡ መሃል በፓትሮል ከሚንቀሳቀሱት ዉጪ እግረኞችም ነበሩ፡፡ ይህ ሁሉ ሽር ጉድ ምንም ላልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ነው ፡፡ ኮሚቴዎቹን ለመዘየር በተሰለፈ ህዝብ ላይ፡፡
ከጠዋቱ 3 ሰዓት የተጀመረው ኮሚቴዎቻችንን የመጎብኘት ሂደት 4 ሰዐት ሆኖም እንኳ ሰልፉ ንቅንቅም አላለም ነበር፡፡ ጭራሽ ከሰዐት ወደ ሰዐት ሰዉ ከልክ በላይ እየጨመረ ነበር የመጣው፡፡ቅድም የነገርኩህ የአዲስ አበባ የደህንነት ሃላፊዎችና የቃሊቲ ባለስልጣናት ህዝቡ የፈለገ ቢሞላ ወደ አስፋልት እንዳይወጣ በጉራንጉር መንደር ማሰለፋቸው ስትራቴጂ አሁን ውጤቱ እየተበላሸባቸው የመጣ መሰለ፡፡ ህዝቡ ከልክ በማለፉ ሰልፉ ወደ አስፋልት መውጣት ጀመረ፡፡ አሁን የፀትታ ሰዎች መደናገጥ ጀመሩ፡፡ ድንገትም መረበሽ ይታይባቸው ጀመረ፡፡ በየሰልፉ አቅጣጫ በመሄድም ሁኔታውን ማረጋገጥ ጀመሩ፡፡ አዎ አይናቸው አልዋሸም፡፡ ህዝቡ ሞልቶ ወደ አስፋልት እየወጣባቸወ ነው፡፡ እዚህ ጋር እኛ ከተሰለፍንበት በኩል ባጋጣሚ ወደ አስፋልቱ አቅጣጫ በአጀብ የሚሄድ የፌዴራል ፖሊስ አዛዝ በሬድዮው ከሃላፊዎቹኮድ 07 ጠይቀው የወጡ ሰዎች እንደገና እየተሰለፉ ነው እንዴ ይህን ተከታተሉ፣ሰልፉ ወደ አስፋልት እንዳይወጣየሚል ቃል ከመገናኛ ሬዲዮው የሰማነው፡፡ ሁላችንም ሳቅን፡፡ መቼም ይህን ፅሁፍ የምታነቡና በወቅቱ የፌዴራል ፖሊሱን ሁኔታ ያያችሁ በዚህ ፅሁፍ በትክክል ሁኔታውን እንዳልገለፅኩት ትረዳላችሁ፡፡ ፌዴራሎቹ በሰዉ መብዛት የሚያደርጉትን እንዳሳጣቸው ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከመንግስት ጋር ከልክ በላይ ተነቃቅተናል፡፡ ዚያራው ከልክ በላይ ረብሿቸዋል፡፡
በሴቶቹ በኩልም በተመሳሳይ እንዲሁ ነው፡፡ የነሱም ሰልፍ ወደ አስፋልት እንዳይወጣ የፀጥታ ሃላፊዎቹ የሚችሉትን አድርገዋል፡፡ እንዲሰለፉ የተሰጣቸው ቦታ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በስተደቡብ ያለው ቦታ በመሆኑ የፈለገ ቢበዙ ወደአስፋልቱ ሳይሆን ቁልቁል ወደ ጉስቋም ማሪያም ቤተክርስቲያን ነበር የሚሄዱት ፡፡ ምንጮም ሴቶቹ ወደዛ እንደሄዱና የሚያስተባብሩ ፖሊሶች ደክሞዋቸው እንደደተመለሱ ነግረውኛል፡፡
የክርስቲያን ወንድሞች ትብብር
ህዝቡን በተመለከተ እርስ በርሱ ሲተባበርና አንዱ ላንዱ ሲተዛዘን ይታይ ነበር፡፡ አንድ ሰው ለራሱ ውሃ ሲገዛ አጠገቡ ላሉት በርካታ ጠያቂዎችም ይገዛ ነበር፡፡ብስኩቶች፣ኩኪሶች በብዛት እየተገዙ ይታደሉ ነበር፡፡ ከጎንህ ያለው ክርስተያን ይሁን ሙስሊም ማንም ግድ አይሰጠውም ፡፡ ብቻውን የሚበላና የሚጠጣ ማንንም አታገኝም ነበር፡፡ ክርስቲያን ወንደሞችንም በዚህ ፅሁፍ ሳላመሰግናቸው አላልፍም ፡፡ ከየቤታቸው ለተጠማው ውሃ በጀሪካን ሲያቀብሉ ታይተዋል፡፡ መቼም ለመንግስት እንደ መከባበርና መቻቻል የሚባል ጠላት የለውም፡፡ ምስሊሙ ከክርስቲያኑ አንድ ሆነው ሲያይ ተባሉልኝ፣ ተናከሱልኝ እያለ ማታ ማታ ETV የሚለቀው ፊልምና መግለጫ ገደል እንደገቡበት ሲያይ ሁለት እጁን ጭንቅላቱ ላይ አድርጎ እዬዬውን እንደሚያሰነካው አልጠራጠርም፡፡
የሰላም አምባሳደሮቹ ከፍርግርጉ ሽቦ ጀርባ መቼም እልህ አስጨራሽ በሚያስብል ሁኔታ የተሰለፍኩት ሰልፍ ኮሚቴዎቻችንን በግፍ ወዳሰረው ወህኒ ቤት ደጃፍ አደረሰኝ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላም ግቢ ውስጥ ገባሁ፡፡ ጉድ ነው፡፡ ግቢው ውስጥ ስለገባሁ ኮሚቴዎቻችንን ያገኘሁ እንዳይመስላችሁ፡፡ እዛም ራሱን የቻለ ሌላ ሰልፍ አለ፡፡ ቢሆንም 20 ደቂቃዎች በኋላ የኪስ ቦርሳዬን፣ ፓስፖርቴንና ስልኬን አስረክቤና ከእግር እስከራሴ ተፈትሼ ገባሁ፡፡ ፈታሹ ይፈትሸኝ እንጂ አይኔ ግን ከፍተሻው ቦታ 500 ሜትር ርቅት ላይ ሰው ወደ ከበባቸውና ከፍርግርግ ሽቦ ጀርባ ወዳሉት ድንቆቹና ውዶቹ የሰላም አምባሳደሮች ወዳሉበት ቦታ ነበር አይኔ የተወረወረው፡፡ አሁንም 2 ረድፍ ሰልፍ ሁነን ወደነሱ አቀናን፡፡ ሰልፉ 2 የሆነበት ምክንያት ሴቶችና ወንዶች ለየብቻ በመሰለፋችን ነው፡፡ አሁን በጣም እየተቃረብን ነው፡፡ እኔ ካለሁበት 20 ሜትር ርቀት ላይ ኡስታዝ ባህሩና ሸህ መከተ ሙሄ በመጀመሪያው ረድፍ ሆነው ህዝቡን ሰላም ሲሉ ይታየኛል፡፡ ከፊት ለፊቴ ያሉትን ሰዎች ደረማምሼ እነሱ ጋር መድረስ አማረኝ፡፡ አደብ አይደለምና ስሜቴን ተቆጣጠርኩት፡፡ 5 ደቂቃ ውስጥ ግን እራሴን ከኡስታዝ ባህሩ ፊት አገሁት፡፡
እውነት ለመናገር በዚህ ወቅት እራሴን ተቆጣጥሬው ነበር ለማለት አልችልም ፡፡ የሆነ አሁን የማላስታውሳቸውን ቃላቶች እያወጣሁ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ኡስታዝ ባህሩ እየሳቀአሚንሲለኝ አስታውሳለሁ፡፡ ሸህ መከተ ሙሄ፣ኡስታዝ ሰዒድ፣ሙኒር…. እያነጋገሩካቸው እያለፍኩ ነው….ኣኣኣ እዚህ ጋር ግን ቆምኩኝ፡፡ የሆነ ሰው አጠገብ ደርሼ ነበር፡፡ ደማቅ ፈገግታ ተለዋወጥን፡፡ ወደዳችሁም ጠላችሁ ግርማ ሞገሱ ከሩቅ ይስባችኋል፡፡ በነጭ ጀለቢያ ተውቦ ፍፁብ ርጋታ በተላበሰ ሁኔታ ሊዘይሩት የመጡትን ጠያቂዎች በአይኑም፣በፈገግታውም፣ ጭንቅላቱንም በመነቅነቅ ጭምር ምስጋናውን ይገልፃል፡፡ ይህ ሁኔታ ለረጅም ሰዐት የዘለቀ ቢሆንም እሱና ጓደኞቹ ያለምንም ድካም ጠያቂዎቻቸውን ተቀብለው እያስተናገዱ ነው፡፡ ጠያቂዎችም ያለምንም ፋታ መፍሰሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ልክ የአባይ ዉሃ አገር አቆራርጦ እየፈሰሰ ከግብፁ አስዋን ግድብ እንደሚጨመረው አይነት ጠያቂዎችም በረጅሙ እየፈሰሱ ከዚህ ቆፍጣናና ልበ ሙሉ ወጣት አጠገብ ሲደርሱ ከንግግግር ይልቅ እንባ ይተናነቃቸዋል፡፡ ይህ ወጣት በቅርቡ ወደዚህች አለም ከመጣች ሳምንት ያልሆናት የሱመያ አባት የሆነው አህመዲን ጀበል ነው፡፡ አናም እሱጋር ስደርስ ቆም ብዬ አየሁት፡፡ በአይናችን ተነጋገርን፡፡ቢሆንም ከኋላዬ ሌሎች አሉና ቦታውን መልቀቅ ነበረብኝ፡፡ ግን አላደረኩትም ፡፡ ከመልቀቄ በፊት የሆነች ቃል ተነፈስኩኝ፡፡ አህመዲንን ጨምሮ አጠገቡ ያሉ ሁሉ ሳቁ፡፡ የተናገርኳት ቃልአቡ ሱመያ ማብሩክ ብያለሁነበር ያልኩት፡፡ በቅርቡ አህመዲን ጀበል ሱመያ የተባለች ሴት ልጅ እንደተወለደለት ሁላችንም እናውቃለን፡፡ እቤቱ ሂጄ መብሩክ ማለት ሲገባኝ ቃሊቲ ውስጥ አልኩት፡፡ አላህ የዚህን መንግስት መጨረሻው ቃሊቲ ያድርገው ፡፡ ሌላ ምን ልበል ብላችሁ ነው? በዚህ ሁኔታ ሰላም እያልን ወደፊት አቀናን፡፡ ኮሚቴዎቻችንና የተከበሩት ዱአቶቻችንን እየተሰናበትን ነው፡፡ ሁላችንም ጠያቂዎች መቆየት ብንፈልግም የማይቻል ነው፡፡ ለሌሎች ወንድሞችና እህቶችም ደግሞ ተራውን መልቀቅ አለብን፡፡ በዚህ ሁኔታ ኡስታዝ አቡበከር ጋር ደረስኩኝ፡፡ በጣም በንቃት ሆኖ ሰላምታ ይሰጣል፡፡ ትዝ ይለኛል እሱንና (ኡስታዝ አቡበከርንና አህመዲንን )ለመጨረሻ ግዜ የጨበጥኳቸው አንዋር መስጂድ በተደረገው የሰደቃና የአንድነት ፕሮግራም ላይ መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ ዛሬ እሱ ከሽቦ አጥር ጀርባ ሁኖ ሳየው ክፉኛ አዝኜ ነበር፡፡ አጠገቡ እንደደረስኩ ሰላም ስለው ምላሽ ከሰጠኝ በኋላ የሆነ ነገር ልለው ፈለኩኝ፡፡ ግን ምን? እነዚህ ጆሮ ጠቢዎች ምን ያስወራሉና፡፡ ቢሆንምኡስታዝ አብሽሩ ኢንሻአላህ በአላህ ፍቃድ ነስሩ ቅርብ ነውአልኩት ፡፡ኢንሻ አላህ አለኝ፡፡ ቀጥዬ ደግሞ እነሱን ለመዘየር ውጪ ያለው ህዝብ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ነገርኩት፡፡ ሁሉም ሰው ለነሱ እንደሚያስብና ዱአ እንደሚያደርግም ነገርኩት፡፡ ደስ አለው፡፡ ደስ እንዳለው የተረዳሁት ደማቅ ፈገግታ ጋር የተናገራት ነች፡፡ይሄን ብዬው ቦታ ለቀቅኩ፡፡ኡስታዝ አቡበከር የነበረው መጨረሻ አካባቢ ስለነበረ በሱ በኩል 3 ያህል የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ነበሩ፡፡ ሳያቸው ገላመጡኝ፡፡ ! እንዳልወደዱኝ ገባኝ፡፡ ቢሆንም ደስ ብሎኛል ፡፡ እጅግ በቅርበት አናግሬያቸዋለሁ፡፡ እነሱን በደንብ ላይበት የምችልበት ቦታ ሁኜ ቆምኩ፡፡ ሴቶች ስሜታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ነበርና በብዛት ሲያለቅሱ ይታይ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ እጅግ የሚየሳዝን ቢሆም አንዳንድ ጨካኝና ከሰው ልጅ ያልተፈጠሩ የሚመስሉ የማረሚያ ቤት ጥበቃ አባላት የተናገሩት አሳዝኖኛል፡፡ኮሚቴዎቻችንን ሲያዩ አንጀታቸው አልችል ያለ ሴት እህቶቻችን ሲያለቅሱ ያየ አንድ ወታደርምን እዚህ ያለቅሳሉ ይሄ ማልቀሻ መሰላቸው እንዴ?” ሲል ሰማሁት፡፡ መቼም ይህ ንግግሩ ከመሃይምነት ብቻ የመነጨ ነው ብዬ አላስብም ፡፡ ከአውሬነት ባህሪ እንጂ፡፡ ይህን ስል ሌሎች ደግ የማረሚያ ቤቱ ጥበቃ ባልደረቦችንም ዘንግቼ አይደለም፡፡ ከልባቸው በደግነት መንፈስ ህዝቡን ሲተባበሩ አይቻለሁ፡፡ አንዳንዶቹምቶሎ ቶሎ በሉ ሌሎች ወንድሞቻችሁም ሊያዩዋቸው ይፈልጋሉበማለት ሲያስተባብሩ ነበር፡፡
ከእንግዲህ በኋላ የህዝብም እንጂ የቤተሰቦቻቸው ብቻ ያልሆኑት ጀግኖች
ዚያራዬን አጠናቅቄ ወጥቼ ወደላይ ጥቂት እንደተጓዝኩ የሆኑ ሴቶች እየተጋፉ አንዲት ህፃን የታቀፈችን ሴት ከበው ይዘይራሉ፡፡ ቀረብ ብዬ ሳይ የጀግናውና ውዱ ወንደማችን የኡስታዝ ያሲን ኑሩ ባለቤት ከአንድ ጥላ ስር ተቀምጣለች፡፡ ህፃኗን የያሲንን ልጅ ታቅፋ ስለደከማት አረፍ ብላ ነበር፡፡ ወዲያው ግን በርካታ ለዚያራ የመጡ እህቶች በዚያራ አጣደፈፏት፡፡ ዱአም ሲያደርጉላት ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በአቅራቢያቸው ለነበሩ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረቦች አልጣማቸውም፡፡ ሴቶቹን አባረሩ፡፡ የጀግናው የያሲን ኑሩ ባለቤትንም ተነስታ እንድትሄድ ነገሯት፡፡ ተራዎች፡፡ ድሮስ ለተራ መንግስት አሽከር ሆነው ግብረ ገብነት ከነሱ አንጠብቅም፡፡ ወደ አንዷ እህት ጠጋ ብዬ (ልጅቷ ከያሲን ኑሩ ሚስት ጋር አብራ ነች)ቅድሚያ ሰጥተዋት መግባት እንደምትችል ነገርኳት፡፡ ልጅቱምአላህ ይስጥልን ገብተን ዘይረን ነው የወጣነው፡፡ ልጇን ለማጥባት ፈልጋ ነው ያረፈችውአለችኝ፡፡ ሱብሃነላህ፡፡ አጂብ ነው፡፡ የያሲ ኑሩ ባለቤት ባለቤቷን ለማየት ከህዝብ ጋር ተሰለፈች፡፡ በልቤ ጀግኖቹ ኮሚቴዎቻችን ከእንግዲህ የቤተሰቦቻቸው ብቻም ሳይሆኑ የህዝብ እንደሆኑ ተሰማኝ፡፡
መደምደሚያ
ይህን ፅሁፍ የምታነቡ ወንድሞችና እህቶች ሆይ ፅሁፉን ስላበዛሁ አውፉ በሉኝ፡፡ በተቻለኝ አሳጥሬ ነው እየነገርኳችሁ ያለሁት፡፡ የቱን ጠቅሼ የቱን እንደማልፍም ጭምር እየተቸገርኩ ነው የፃፍኩት፡፡ እኔ ያየሁትን ሁሉ ልንገራችሁ ብልማ ግማሽ ቀንም አይበቃን፡፡ በተቻለኝ ግን ዋና ዋና ነገሮችን እንድትጨብጡ ነው የሞከረኩት፡፡ በተለይ ከሃገር ዉጪ ያሉ ወገኖች ብዙ እንደምትጠብቁ ነግራችሁኛል፡፡ እጅግ አሳጥሬ ነው ያቀረብኩት፡፡በአጠቃላይ ግን ኮሚቴዎቻችንን ደብቃ የያዘችው ቃሊቲ አቅሏን እስክትስት ተጨናንቃ ነበር፡፡ ከነበረው ከፍተኛ ሙቀት ጋር ተደማምሮ አካባቢው ብው ብሎ ሊፈነዳ የተቃረበ ይመስል ነበር፡፡ እኔም ኮሚቴዎቻችንን አላህ እንዲያስፈታልን እለምነዋለሁ፡፡ ፅሁፌን የምቋጨው ግን ለኡስታዝ አቡበከር የተናገርኩትን ብዬ ነው፡፡ኡስታዝ አብሽሩ ኢንሻአላህ በአላህ ፍቃድ ነስሩ ቅርብ ነው፡፡ ኢንሻ አላህ በሉኝ እናንተም እንደ ኡስታዝ አቡበከር፡፡ አበቃሁ፡፡

No comments:

Post a Comment