Friday, November 30, 2012

በመሪዎቻችን ላይ የተመሰረተው ህገ ወጥ ክስ ህዝብን የማሸበር አይነተኛ መገለጫ ነው!!

በመሪዎቻችን ላይ የተመሰረተው ህገ ወጥ ክስ ህዝብን የማሸበር አይነተኛ መገለጫ ነው!!

እነሆ በሀይማኖታችን ላይ የተፈፀሙብንን የመብት ጥሰቶች በግላጭ ወጥተን ‹‹የፍትህ ያለህ›› ስንል 11 የተቃውሞ ወራት አለፉ፡፡ በእዚህ ሁሉ ግዚያት የሙስሊሙ ህብረተሰብ እጅግ አስደማሚ የሰላማዊ ትግልን ባህል በአንድ በኩል በሁሉም ህብረተሰብ ዘንድ ሰርፆ እንዲገባ ያስቻለ ሲሆን በሌላ በኩል መንግስት በተከተለው እጅግ የተወላገደ አረዳድ የወሰዳቸው ሀላፊነት የጎደለው እርምጃዎች ከህዝብ ልብ ከነ አካቴው እንዲወጣ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በህገ መንግስቱ የተደነገገው ‹‹የሀይማኖት ነፃነት መብታችን ይከበር›› ብለን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቻችንን በማቅረባችን እስከ ህይወተ ህልፈት የደረሰ ብዙ ግፍ ተፈፅሞብናል፡፡ አሁንም ድረስ ይህ ግፍ ኮሚቴዎቻችንን ያለ ጥፋታቸው በግፍ በማሰርና ከሀቅ የራቀ ክስ በመመስረት እየተፈፀመብን ይገኛል፡፡ ይሁንና መሪዎቻችን የደረሰባቸውን ይህ ነው የማይባል የስቃይ ማዕበል የአላህን ውዴታ በመሻትና በአወሊያና በአንዋር ምድር የተጋባነውን ቃል ኪዳን በተግባር በማረጋገጥ ከፍተኛ ፅናት የሚጠይቀውን መስዋትነት ሁሉ ከፈለው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ ከጎናቸው ያሉ ዳዒዎችና ወንድሞችም እንደዚሁ፡፡ አላሁ አክበር!!

እኒያ ውድ የኢስላም ልጆች የደረሰባቸው መከራ ለጆሮ ሰቅጣጭ ነው፡፡ ዝርዝሩን በይደር በሌላ ግዜ የምንመለስበት ቢሆንም በጥቅሉ በማዕላዊ ወህኒ ቤት ዱላ እንጂ ህግን በማያውቁ የደህንነት አባል ተብዬዎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል፣ በኤሌክትሪክ ሾክ ቶርች ተደርገዋል፣ በጨለማና ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ለ10፣ ለ15 እና ለ20 ቀናት እንዲቆዩ ተገደዋል፣ ተገርፈዋል በዚህ ግርፋት የእግራቸው ጥፍሮች የመጠመጡም አሉ፤ በስቃይ ጤንነታቸው ታውኮ ሆስፒታል የተኙም ነበሩ፡፡

የመሪዎቻችን ሰብሳቢ እና ቀልብን በሚገዙ መሳጭ ዳእዋዎቹ የምናውቀው ኡስታዝ አቡበከር፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ታሪክ ከተቀበረበት ፈልቅቆ ያወጣው የታሪክ ምሁሩ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፣ ትግላችን ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ከፍተኛ ግንዛቤ በመፍጠር ለህግ መከበር ትልቅ ሚና የነበረው የህግ ባለሙያ ዳዒና የመስጂድ ኢማም ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፣ በማራኪ አንደበቱ ስንቶችን ወደ ዲን የጠራና በዳዕዋዎቹ የጥያቄያችንን ሰላማዊነት በማያወላውሉ አገላለፆች ያስቀመጠው ዳዒ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ፣ በምግባረ ሰናይ ስራዎች ላይ በቅንነት በማገልገልና በአንዋር መስጂድ የቁርዓን ተፍሲር በማስተማር የሚታወቀው ዳዒ ኡስታዝ ጀማል ያሲን እንዲሁም በሩህሩህነቱና በምሁራዊ አስተያየቱ የምናውቀው ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋን ጨምሮ ብንጠቅሳቸው የማንጠግባቸው የኮሚቴ አባላት፣ ዳዒዎችና የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት የሆኑ ወንድሞቻችን ላይ ይህ ዓይነቱ፤ ህገ መንግስቱ ላይ በማን አለብኝነት የተረማመደ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንደተፈፀመባቸው መስማት ምንኛ ልብን ያደማል!! እንዲያ የምንሳሳላቸው ኮሚቴዎቻችን እና ዱዓቶቻችን ላይ እንዲህ ዓይነቱ ሊሸከሙት ከባድ የሆነ ዘግናኝ የመብት ጥሰት መፈፀሙ አጠቃላይ ህዝበ ሙሊሙን በቁጭት የናጠና ውስጡ ላይ የማይሽር ቁስል ያስቀመጠ ክስተት ነው፡፡

በሥርዓት አልበኛ የመንግስት የደህንነት አባላት በግድ ‹‹አሸባሪዎች ነን›› በሉ ‹‹ህዝብን በማነሳሳት ሀገሪቱን በሽብር ልናውክ ድብቅ አጀንዳ በመያዝ ተንቀሳቅሰናል በሉ›› ‹‹ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ሁሉ ውሸት ናቸው በሉ›› ‹‹መንግስት የወሰደው እርምጃ ሁሉ ትክክል ነው በሉ›› በማለት በኢ-ሰብዓዊ ለእስር ከተዳረጉበት ሶስት ወር ውስጥ ሁለቱን ወር ነፍሳቸው እስኪወጣ ቢሰቃዩም፤ የጥያቄዎቻችንን አግባብነት ዳግም በማረጋገጥ የገቡትን ቃልና የህዝባዊነት አደራ በሚገባ ተወጥተዋል፡፡ ይህ አልሳካ ብሏቸው ልፋታቸው ሁሉ መና የቀረባቸው የመንግስት ደህንነቶች ምንም መረጃ ማግኘት ሳይችሉ ሲቀር ኮሚቴዎቻችንን በከፍተኛ ስቃይ በማስገደድ ለማንበብ እንኳ ፋታ ሳይሰጧቸው በውል በማያቁት ወረቀት ላይ አስፈርመዋቸዋል፡፡ ኮሚቴዎችም ወረቀቱ ምንም ይበል ምን በግዴታ የተደረገና እነርሱን ፈፅሞ የማይወክል መሆኑን ህዝባቸው በቀላሉ እንደሚረዳ ሙሉ መተማመን ስላላቸው ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ እኛም ጠንቅቀን እናውቃለን፤ በእስር ቤት ውስጥ በስቃይ እንዲናገሩም ሆነ እንዲፈርሙ የተደረጉትን በቪድዮም ይሁን በፅሁፍ ሰብስበው ከተለያዩ ከተቀነጫጨቡና ተቆርጠው ከተሰፉ ፊልሞች ጋር በማቀናበር የተለመደውን ዓይነት በቅጥፈት የተሞላ ውሸት በኢቴቪ ‹‹ዶክመንታሪ›› ሰርተው ‹‹አኬልዳማ›› ቢያሳዩን ፈፅሞ እንደማንሰማቸው አስረግጠን እንነግራቸዋለን፡፡

ከዚህ በፊት አወሊያ ውስጥ ቆፍረው መሳሪያ አስገብተው መልሰው ቆፍረው ሲያወጡ በቨዲዮ መቅረፃቸውን ማጋለጣችን አይዘነጋም፡፡ የአወሊያዉን ዘግናኝ ድብደባ ባካሄዱበት ሌሊት ለሰደቃው የታረዱ በሬዎችን ስጋ አሸክመው ወጥ ለመስሪያነት የሚያገለግሉ ቢላዋዎችንም አስይዘው እንደቀረፁም ተናግረናል፡፡ እኒህንና የአወሊያ ፕሮግራሞችን ቆራርጦ የማይገናኘውን አገናኝቶ በመስፋት ከኮሚቴዎቻችን እስር ጋር በማዛመድ የሚሰራ ‹‹አኬልዳማ ዶክመንታሪ›› ፊልም ቢኖር ይበልጥ ቁጣችንን ከመቀሰቀስ ውጪ ሌላ ሚና አይኖረውም፡፡ በዚህ ዓይነቱ ውሸት እንኳንስ ሙስሊሙን ይቅርና የትኛውንም ማህበረሰብ ማታለል አይቻልም፡፡ የሰሩትን ግፍ ሁሉ ሰርተው ሲያበቁ ለዚህ ዓይን ያወጣ ከባድ ወንጀላቸው መሸፈኛ የቅጥፈት ‹‹ዶክመንተሪ›› በመስራት ሸፍጥን መሸፈንና ህዝብን በተውኔት ማታለል ከእንግዲህ አብቅቶለታል፡፡

ኮሚቴዎቻችን ቁጣ አገንፍሎ ባወጣው የህዝባዊ ትግል መንፈስ ውስጥ ሰላምን ዘምረው ሰላማዊነትን የዘሩ የሰላም አምባሰደሮች ቢሆኑም ዛሬ ቀኑ ተቀይሮ በአደባባይ ክህደት በአሸባሪነት መከሰሳቸው የሀገርን ክብር የሚነካ እጅጉኑ ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡ የክሱ ዝርዝር በአወሊያና በአንዋር በብዙ መቶ ሺዎች ሆነን በዓይናችን ብሌን ያየነውንና ልባችን ተንጠልጥሎ በጉጉት ያዳመጥነውን የሰላማዊነትን እውነታዎች ሙሉ በሙሉ የሚክድ ነው፡፡ መቼ ነው ‹‹ህዝብ ሆይ! መንግስት ሀይማኖትህን ሊያጠፋ ቆርጦዋልና ተነስ ምን ትጠብቃለህ!?›› ያሉት? መቼ ነው ‹‹መንግስትን እንገልብጥ›› ብለው ያነሳሱት፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስ እንደ ረፋድ ፀሀይ ፍንትው ያለውን ሀቅ በጉልበት ለማጠልሸት የሚደረግ ከንቱ ሙከራ ነው፡፡ በህዝባዊነቱ የብዙ መቶ ሺዎች ተሳትፎና ምስክርነት ያለውን የሰላማዊ ትግል ሐቅ በፀረ ዴሞክራሲያዊና ኢሰብዓዊ ትርዒቶች ወደ ሽብር ማስጠጋት የሀገርን እሴት የሚያደበዝዝ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ አሁንም ደግመን ለሀገርም ለህዝብም የማይበጅ መሆኑን እያስታወስን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና በአፋጣኝ መሪዎቻችን፣ ዱዓቶቻችንና ወንድሞቻችንን እንዲፈታልን እንላለን፡፡

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment