Friday, December 7, 2012

ደማቁ የ 27 ተቃውሞ


ደማቁ የ 27 ተቃውሞ

ገና በማለዳው ነበር የአዲስ አበባ ሙስሊም ወደ አንዋር መስጊድ ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው፡፡ ብዙም ሳይቆይ መስጊዱ እንደተለመደው ሞልቶ ወደውጭ ሰው ማፍሰስ ጀመረ፡፡ የፈሰሰው ሰው አንዋርን እና ዙሪያውን ሞልቶ እስከ ሲኒማ ራስ እና ተክለሃይማኖት መድረሻ፣ በመርካቶ በኩልም እስከጣና አጥለቅልቆት ቦታውን ረመዳን ወር የገባ አስመሰለው፡፡ እንደ ሁልጊዜው ለሽያጭ የመጡ የመስገጃ ካኪዎች በቂ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ እናም ሁሉም በያለበት ልብሱን እያወለቀ ለሰላት ያነጥፍ ነበር፡፡ ሁሉም ጁምአን ለመስገድ፣ ከፈጣሪው ጋር ለመገናኘት ጓጉቷል፡፡ ለሰላት ቆሞ መንግስት ሙስሊሞች ላይ የሚያደርሰውን በደል አላህ ሃይ እንዲልለት፣ ለስቃዩ መቆሚያ እንዲያበጅለት፣ መሪዎቹን በሰላም ከእስር እንዲያወጣለት ጌታውን አጥብቆ ይለምናል፡፡ ገሚሱ እምባውን ያወርዳል፤ የአላህን ራህመት ይከጅላል፡፡
ይሄ ድንቅ ለመብቱ ቋሚ ትውልድ እንዲሁ ዱዓ አድርጎ ብቻ ዝም የሚል አይደለም፡፡ ሌላም ሀላፊነት እንዳለበት ይረዳል፤ በደልን በአቅም ልክ መታገል… ድምጹን ማሰማት… ለመብቱ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ… መስዋእትነት መክፈል… ሌላም ሌላም! ዛሬም መቶ ሺዎችን በአንዋር የሰበሰበው ይኸው የ‹‹መብታችን ይከበር!›› ሐጃ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ‹‹ህዝቡ ይፈራናል›› በሚል ከንቱ ስሜት አካባቢውን ጦርነት በሌለበት ‹‹የጦርነት ቀጣና›› ማስመሰል የሚወዱትና ከመከበር ይልቅ መፈራትን የሚፈልጉት ፌደራል ፖሊሶች አንዋርና ዙርያውን ቢከቡም መመኪያውን አላህ ባደረገው ህዝበ ሙስሊም ልብ ውስጥ አንዳችም ተጽእኖ ማሳደር አልቻሉም፡፡ ‹‹ግዴታዬን አደርሳለሁ! መብቴንም አውቃለሁ! እጠይቃለሁም!›› ሲል የቆየውን ጠንካራ ሙስሊም ትውልድ ልብ
ማንበርከክ አልተቻላቸውም፡፡ እናም ሰላት እንደተሰገደ አፍታ እንኳን ሳይቆይ ነበር የተክቢራ ድምጽ መስተጋባት የጀመረው፡፡ ‹‹አላሁ አክበር!›› … የአላህ ታላቅነት ተመሰከረ፡፡ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ተማሪዎች፣ ሰራተኞች አንድ አካል እስኪመስሉ ድረስ በጉያቸው የሸጎጡትን ወረቀት ላጥ አድርገው አወጡ… በትላልቁ 27 ቁጥር የተጻፈባቸው ወረቀቶች ተውለበለቡ፡፡ አንዋርና አካባቢው ነጭ ወረቀትና ጥቁር ቀለም በፈጠሩት ህብር ተብረቀረቀ፡፡ ሁሉም በባለስልጣናት የግል ፍላጎት በተደጋጋሚ እየተጣሰ ያለው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 27 እንዲከበርለት ያለማወላወል ጠየቀ፤ የሰለጠነ ህዝብ!

የህዝቡን ስሜት የአካባቢውን መልክ ሙሉ በሙሉ የቀየረው የወረቀት መአት ብቻውን የሚገልጸው አልነበረምና ድምጾች መፈክሮች ሆነው ተስተጋቡ፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በአንድነት ሀሳቡን ያለከልካይ ገለጸ፡፡ ‹‹የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 27 ይተግበር! ሰላም አጣን ባገራችን! መንግስት የለም ወይ! ሀስቡነላህ ወኒእመል ወኪል! ሕገ መንግስቱ ይከበር! አላሁ አክበር! የታሰሩት ይፈቱ! ጭቆና ይብቃን! ለዲናችን እንሞታለን! ኢስላም ሰላም ነው! በዲናችን ድርድር የለም! እኛ ጥቂቶች አይደለንም! መብታችን ይከበር! ኢቲቪ ሌባ! ኢቲቪ ውሸታም! አሸባሪ አይደለንም! ጥያቄያችን በአፋጣኝ ይመለስ!›› የሚሉ ድምጾች አስገመገሙ - ነጻ ድምጾች! መልእክታቸውን አደረሱ፡፡ መሪዎችን በማሰር እንቅስቃሴውን ማስቆም እንደማይቻል ገለጹ፡፡ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› ሲሉም አከሉ፡፡

እንደተለመደው ሁሉ የዛሬው ተቃውሞ ያለምንም ችግር በሰላም ነበር የተጠናቀቀው፡፡ ጨዋው ሕዝበ ሙስሊም ተቃውሞውን በሰላም አሰምቶ ወደየቦታው ተበታትኗል፡፡ ሰላም የሚያቅራቸው የመንግስት ካድሬዎችና ደህንነቶች ግን ከሚመለሰው ህዝብ መሃል የሚፈልጉትን እየመረጡ ለመያዝ እና ግርግር ለመፍጠር ሲሞክሩ ነበር፡፡ መርካቶ አካባቢም እንዲሁ አንድን ወጣት ለማሰር ግርግር ፈጥረው የነበረ ቢሆንም በህዝቡ ጥረት በሰላም ችግሩ ተፈትቷል፡፡ ህዝብ ሰላም አስከባሪ፣ ፖሊስ ሰላም አደፍራሽ ሆኖ የሚቀጥለው እስከመቼ ይሆን?

በዛሬው ታላቅ የአንቀጽ 27 ተቃውሞ ደምቆ የዋለው አንዋርና አካባቢው ብቻ አልነበረም፡፡ በሌሎች በርካታ ቦታዎችም ቢሆን የህዝበ ሙስሊሙ አንድነት ቦታ የማይገድበው መሆኑ በተጨባጭ ታይቷል፡፡ በተለይ በጂማ እና በበደሌ ከተሞች የተደረጉት ተቃውሞዎች ልዩ ነበሩ፡፡ የአባ ጂፋሯ ጂማ በጀግና የመብት ታጋይ ልጆቿ የተዋሀደ ድምጽ ደምቃ ውላለች፡፡ የበደሌ ፋኖዎችም መሪዎቻችን እንዲፈቱ፣ ድምጻችን እንዲሰማ፣ ጥያቄያችን እንዲመለስ ቆርጠው የቆሙ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ አዎ! በእርግጥም ደስ ይል ነበር… በተለያዩ ቦታዎች ለአንድ አላማ የተዋሀዱ ድምጾችን መስማት ምንኛ ያስደስት!

ድምጽ ሁሉ አንድ አይደለም፡፡ ውስጥን ተከትሎ ቃናውን ይለውጣል፤ ውስጡ ያዘለውን ምሬት በቃናው ይተፋል፡፡ የዛሬውም ተቃውሞ እንዲሁ ነበር፡፡ ሙስሊሙ ላይ እንደህዝብ እየተፈጸመ ያለው ዘርፈ ብዙ በደል ያጎረነነው ድምጽ በእልህ ታጅቦ የሺዎችን ጎሮሮ እየኮረኮረ ወጥቷል፡፡ የብዙዎች ፊት ‹‹አሁንም እስከመጨረሻው እንገፋለን! እስክትሰሙን እንጮሃለን!›› እያለ ሰላማዊ ቁጣውን ይገልጽ ነበር፡፡ እኛስ አላህ ይሰማናል! የህዝብን ድምጽ የማይሰማ መንግስት ግን ራሱን ‹‹መንግስት›› ብሎ የሚጠራበትን ሞራል የሚያገኘው ከወዴት ይሆን?

አላሁ አከበር!

No comments:

Post a Comment