Tuesday, January 22, 2013

አዲስ አበባ ሬድዮ ቢላል ጥር 14/2005 Jan 22, 2013



በሐረር በአረፋ በዓል ወቅት የተያዙ ሙስሊሞች እስካሁን ፍትህ አለማግኘታቸው ጠቆሙ
አዲስ አበባ ሬድዮ ቢላል ጥር 14/2005

በሐረር ከታሰሩ አራት ወራትን ያስቆጠሩት ሙስሊም ወጣቶች እስካሁን ፍትህ ሳያገኙ እየተስተጓጎሉ እንደሚገኙ  ተጠቆመ፡፡ ጥቆማውን ያደረሱን የሐረር ነዋሪዎች እንደገለፁት ለወራት ጉዳያቸውን በሐረር ፍርድ ቤት ቢከታተሉም ያለምንም ፍትህ በእስራት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል  ፡፡
ታስረው የሚገኙት ሰባት ሙስሊሞች በትላንትናው እለትም ፍርድ ቤት ቀርበው ለፊታችን ጥር 20 2005 ቀጠሮ ተይዞላቸዋል ፡፡
ለቀጠሮ ዋነኛ ምክንያት የመንግስት አቃቢ ህግ መረጃ አላጠናከርኩም በማለቱ እንደሆነ ፍርድ ቤት የተገኙት ነዋሪዎች ለሬድዮ ቢላል አስረድተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በሐረር ከሁለት ሳምንት በፊት የአካባቢው ህዝበ ሙስሊም አንደኛ ዓመት የህዝበ ሙሰሊም ተቃውሞ በተካሄደበት ወቅት ተቃውሞውን መርታችኋል ተብለው በፀጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት 21 ሙስሊም ወጣቶች በዛሬው ዕለት ፈርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይቀርቡ መቅረታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
-----------------------------------------------
መፍትሄ ያጡት የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እየወጡ መሆናቸውን ገለፁ
አዲስ አበባ ሬድዮ ቢላል ጥር 14/2005
ለረጅም ጊዜ መፍትሔ ሲጠይቁ የነበሩት የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለትምህርት ቤት አስተዳደር የመስገጃ ቦታ ይዘጋጅልን ፣የጀምዐ ሰላት ይፈቀድልን ፣ የሂጃብ እና የኒቃም ጉዳይ ላይ የወጣው የመተዳደሪያ ደንብ ይስተካከል ብለው ቢጠይቁም ምላሽ ሰጪ አካል አጥተው ዩኚቨርስቲውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል፡፡
እንደ ተማሪዎቹ ገለፃ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል በመሰብሰብ እና በተወካዮቻቸው አማካኝነት ቢያቀርቡም ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡
ተማሪዎች እንደገለፁት በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ  በተካያሄደው ስብሰባ ወቅት የቀረበው ህግ እና ደንብ ሙስሊም ተማሪዎች ክፉኛ እንደሚበድል  መጥቀሳቸውን አስታውሰዋል ፡፡
በዛሬው ዕለት ቁጥራቸው ከ300 የሚበልጡ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንደወጡ ጠቅሰዋል ፡፡
በባህር ዳር አራቱም ካምፓሶች የሚገኙ ሙስሊሞች መልቀቃቸውን መንግስት እና የሚመለከተው አካል ዝምታን መምረጣቸው ከበስተጀርባው ምን ዓይነት መልዕክት እንዳለው ለመረዳት እንደቻሉ ጠቅሰዋል፡፡
በመጨረሻም እንደተማሪዎቹ ገለፃ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ እየደረሰው ያለው በደል በመላው ሃገሪቱ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ሳይዘምት መቆም እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
------------------------------------------
በጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ማውገዛቸው ተገለፀ
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሙስሊም ተማሪዎች የመስገጃ ቦታና የጀመዐ ሰላት መከልከል እንዲሁም ኒቃምና ጅልባብ መልበስ  መከልከል ተከትሎ በጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ሙስሊም ተማሪዎች በትላንትናው ዕለት ጉዳዩን በመቃወም ዱዐ በማድረግና ፆም በመፆም ማሳለፋቸውን ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በባህርዳር ዩኚቨርስቲ የሙስሊም ተማሪዎች ሰሚ ማጣት እንዳሳሰባቸውና ይህንንም  ጉዳይ ፒቲሽን በማሰማሰባሰብ ለዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን ማስገባታቸውን ምላሹንም በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ለሬዲዮ ቢላል ተናግረዋል ፡፡
በመጨረሻም የጂጂጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ምግብ አንመገብም በማለት ፆማቸውን ያፈጠሩት በአካባቢው ከሚገኝ አንድ መስጂድ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡  

No comments:

Post a Comment