Thursday, January 17, 2013

መንግስት በምስክር እጦት ጭንቅ ውስጥ ገብቷል


ሰበር ዜና


መንግስት በምስክር እጦት ጭንቅ ውስጥ ገብቷል፡፡


የብዙዎች ምላሽ ‹‹በሐሰት አንመሰክርም›› የሚል ሆኗል፡፡


በእስር ላይ የሚገኙ መሪዎቻችን እና ሌሎች ወንድሞቻችንን በአሸባሪነት ከስሶ ሲያንገላታ የቆየው መንግስት በምስክር እጦት ችግር ውስጥ መግባቱ ታወቀ፡፡ መንግስት ኮሚቴዎቻችን ላይ በመሰረተው ክስ በሐሰት ሊያስመሰክራቸው ያዘጋጃቸው 197 (አንድ መቶ ዘጠና ሰባት) ሰዎች መኖራቸውን ለፍርድ ቤት ቢያሳውቅም የተገለጸውን ቁጥር ያህል ምስክሮች ማግኘት አልቻለም፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ለምስክርነት የታሰቡት ብዙዎቹ ግለሰቦች ምስክር ለመሆን ፈጽሞ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ነው፡፡ መሪዎቻችን ባልዋሉበት እና በማያውቁት ወንጀል የከሰሳቸው መንግስት በየአካባቢው ‹‹ድጋፍ ይሰጡኛል፤ እተማመንባቸዋለሁ›› የሚላቸውን ግለሰቦች ለምስክርነት ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግላቸውም በሐሰት አንመሰክርም የሚል ቆራጥ አቋም ማሳየታቸው ተሰምቷል፡፡


ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሳቸውን የመብት ጥያቄዎች ለመንግስት እንዲያደርሱለት በአስር ጣቱ አምኖባቸው የመረጣቸው ኮሚቴዎቻችን እና ሌሎች ዳኢዎች መንግስት እውቅና ሰጥቷቸውና ስለ ሰላማዊነታቸውም በመንግስት ብዙሀን መገናኛዎች መስክሮላቸው፤ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ድርድር ሲያደርጉ እንደቆዩ ይታወሳል፡፡ ሆኖም መንግስት የቀረቡትን የመብት ጥያቄዎች ለመመለስ አለመፈለጉና እነሱም ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረባቸው ‹‹አሸባሪ›› የሚል ታፔላ ተለጥፎባቸው ከሐምሌ 2004 ጀምሮ በእስር እና ስቃይ ላይ የሚገኙት መሪዎቻችን ንጹህ መሆናቸውን የተረዱ ብዙዎች በሀሰት እነሱ ላይ ለመመስከር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በቀጥታ መግለጽ ችለዋል፡፡


መንግስት ይህን የመስካሪዎች እምቢታ ተከትሎ አዳዲስ ምስክሮችን ለመመልመል ቀን ከሌት እየሰራ እንደሚገኝ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ የመንግስት ደህንነቶች ቁጣና ንዴት በተሞላበት መልኩ ሰዎችን ምስክር እንዲሆኑ በአካልም ጨምር እየሄዱ በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ደህንነቶቹ በአዲስ አበባ አንድ አንድ መስጊዶች በመገኘት ግለሰቦችን በግድ በመያዝ ምስክር እንዲሆኑ እየጠየቁ ሲሆን፤ ፈቃደኛ አልሆንም ያሉ ሰዎችንም ‹‹የማትመሰክር ከሆነ አንተን ነው የምንከስህ›› በማለት በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የሀሰት ምስክርነትን (ሸሀደተ ዙር) አስከፊ ወንጀልነት የተረዱ በርካታ ሙስሊሞች አሁንም በእምቢታቸው የዘለቁ ሲሆን፤ አሁንም ግን ጥቂት የማይባሉ ‹‹ተገደን ነው የምንመሰክረው›› የሚል ምላሽ እየሰጡ ያሉ ግለሰቦች በመኖራቸው ከዚህ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ከአስከፊው የሀሰት ምስክርነት መዘዝ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲጠብቁ አደራ እንላለን፡፡


አቡበከር ሲዲቅ (ረ.ዓ) የአላህ መልዕክተኛ (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸውን ዘግበዋል፡- ‹‹የከባዶች ከባድ የሆነውን ሀጢአት አልነግራችሁንም›› እኛም ‹‹አዎ! የአላህ መልዕክተኛ እንዴታ!›› አልን፡፡ እሳቸውም ‹‹በአላህ ማጋራት (ሽርክ) እና ወላጅን ያለመታተዝ ናቸው›› አሉና ተደላድለው ከተቀመጡበት ድንገት ተነስተው እንዲህ አሉ ‹‹አዋጅ! ውሸት መናገር እና በሐሰት መመስከ›› እያሉ የሚያቆሙት አልመስልህ እስኪለኝ ድረስ ደጋገሙት ፡፡ ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል፡፡


አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment