Tuesday, January 29, 2013

የሐሰት ምስክርነቱ አሁንም ቀጥሏል!


የሐሰት ምስክርነቱ አሁንም ቀጥሏል!

በአቃቤ ህግ እና በዳኛ መካከል ለውጥ ጨርሶ ጠፍቷል!

ድምጻችንን ያሰሙልን ዘንድ መርጠን የላክናቸው መሪዎቻችን እና አጋሮቻቸው ከረጅም ጊዜ የእስር ቤት ቆይታና ድብደባ በኋላ የተመሰረተባቸው ኢ-ፍትሀዊ ክስ በእርግጥም ፍትህ የተጓደለበት መሆኑን ካሁኑ እያረጋገጥን ነው፡፡ ገና የፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩ አንስቶ ብዙ መድልዎ ሲካሄድ እንደቆየ ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡ ክሱ ኢ-ህገመንግስታዊ ይዘት የነበረውና የህግ አተረጓጎም ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መተላለፍ ሲገባው ተከሳሾች እንዲከላከሉ የተደረገ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ይህም ሳያንስ መሪዎቻችንን በሞራል ከሚደግፋቸው ህዝብ አይን ለማራቅ የክሱ ቦታ ከልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወደ ቃሊቲ እስር ቤት አቅራቢያ ተዛውሯል፡፡ ይህም ግን አልበቃቸውም፡፡ መሪዎቻችንን ለመክሰስ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው ብቸኛው ነገር የሐሰት ምስክርነት ብቻ መሆኑን በመገመት በማእከላዊ የምርመራ ጣቢያ የሀሰት ምስክሮች በፕሮጀክተር የታገዘ ስልጠና ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች የተሰባሰቡት እኒህ የሀሰት ምስክሮች ይህንን ከባድ ወንጀል ለመስራት የተስማሙት ያላዩትንና ያልሰሙትን፣ በጭራሽ ያልተፈጸሙ ክስተቶችን ሁሉ እንዳዩና እንደሰሙ አድርገው ለመመስከር ነው፡፡ እያደረጉትም ይገኛሉ፡፡

በምስክር መስሚያው የመጀመሪያ ቀን አቃቤ ህጎች ‹‹ለምስክሮቻችን ደህንነት ሲባል የምስክርነት ሂደቱ በዝግ ችሎት ይከናወን›› የሚል እጅግ ፍትሐዊነት የጎደለው ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ይህንኑ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በዝግ ችሎት እያስኬደው ነው፡፡ ይህ የተደረገበት ምክንያት ደግሞ ከሀሰት ምስክሮች ስልጠናው ጀምሮ ግልጽ ነው፡፡ የሀሰት ምስክሮቹ እስካሁን አይተዋቸውም ሰምተዋቸውም በማያውቋቸው ሰዎች ላይ ነው የሚመሰክሩት፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ኮሚቴዎቹ ሲናገሩ ሰምተናል ብለው የሚመሰክሩት ነገር ፈጠራ በመሆኑ እርስ በእርሱ የሚገጫጭ እና የሚቃረን፣ አልያም የማይገጥም ነገር ተናግረው በፍድ ቤት ፊት ማፈራቸው አይቀርም፡፡ እንግዲህ ፍርድ ቤቱ ይህ ሲሆን ህዝብ እንዳያይና እንዳይታዘብ ሲል ነው ሂደቱ በዝግ ችሎት እንዲካሄድ ያደረገው፡፡

በምስክር መስማት ሂደቶቹ እስካሁን የታዩት ነገሮች እላይ ከተገለጸው የተለዩ አይደሉም፡፡ በሁለተኛው፣ በሶስተኛውም ሆነ በአራተኛው ቀን በመሪዎቻችን ላይ የሀሰት ምስክርነት ሲሰጡ የነበሩት ግለሰቦች መሪዎቻችንን በመልክ አንዱን ከአንዱ መለየት እንኳን አልቻሉም፡፡ የሚመሰክሩበትን ሰው ማንነት እንዲያሳዩ ሲጠየቁ ሁሉም አስገራሚ ስህተቶችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ አቃቤ ህጎች ይህንን ችግር ለመፍታት መሪዎቻችን በአንድ ቋሚ ቦታ ብቻ እንዲቀመጡ በማድረግና ለምስክሮቹ አቀማመጣቸውን ከውጭ አስጠንተዋቸው በመግባት ለማገዝ ሞክረውም እንኳን ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ በአጭሩ ምስክሮቹ ‹‹መንግስት ገልብጡ! ጂሀድ ተዋጉ! ሱፍያዎችን ግደሉ! ክርስትያኖችን ግደሉ!›› ብለውናል እያሉ በፍፁም ያልተባሉ ንግግሮችን በመሪዎቻችን ላይ ከማላከክ ውጭ ማን ምን እንደተናገረ እንኳን መለየት አልቻሉም፡፡

የሚገርመው ግን ይህ አይደለም…! ዳኞች የሀሰት ምስክርነት ሲሰጥ በአይናቸው እያዩ እንኳን ግድ እየሰጣቸው አይደለም፡፡ ምስክሮች የሚመሰክሩበትን ሰው በአካል ማወቅ ሲያቅታቸው ‹‹ምስክሩ ረጅም ጊዜ ሊሆነዉ ይችላል ተከሳሾቹን ካያቸዉ፡፡ ስለዚህ አለመለየታቸዉ የሚያሳስበን አይሆንም፤ ፍርድ ቤቱ የራሱን ግምት ይወስዳል›› ማለታቸው ነው የሚገርመው! ፍትህን ለማስከበር ቆሜያለሁ የሚል ዳኛ ምስክሮች ሲቀጥፉ ‹‹ግድየለም!›› ማለቱ ለብዙዎች የፍትህ ውድቀት ነው! ዜጎች በአገሪቷ ፍትህ ስርአት ላይ ሙሉ በሙሉ ተስፋ እንዲያጡ ያደርጋል፡፡

በዚህ ሁሉ ፍርደ ገምድልነት መካከል እንደረፋድ ጸሐይ የጠራው የህዝበ ሙስሊሙ አቋም አሁንም ግልጽ ነው! መሪዎቻችን ሽብርተኞች አለመሆናቸውን እናውቃለን! የሐሰት ክስ አይገዛንም! በጭራሽ አይገዛንም! እናም አጓጉል አትድከሙ! ዛሬ እናንተ የሀሰት ምስክሮችን ብትሰበስቡም እኛ ደግሞ አላህን ፈርተን ለሀቅ እንመሰክራለን! በመሪዎቻችን ላይ የተደፈደፈውን የሀሰት ክምር እንንዳለን! የኢትዮጵያ ህዝብ እውነታውን ያውቅ ዘንድም አላህ ይረዳናል!

ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለም!

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment