Tuesday, February 5, 2013


ታግዷል የተባለው ፊልም እንዳይታገድ የእጅ አዙር ድራማ ተሰራበት

ፍትህ ሆይ የት ነው ያለሽው?

ዛሬ ምሽት ኢቴቪ ያስተላልፈዋል ተብሎ የነበረውና ዛሬ በፍርድ ቤት እንዳይታይ እግድ የተጣለበት ፊልም በአስተዳደራዊ እርምጃ በሚመስል መልኩ በከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኛ ደብዳቤው ኢቴቪ መዝገብ ቤት ተፈርሞ ከገባ በኋላ ተስቦ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ጠበቆች ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ቢሮ ቢሄዱም፤ ውሳኔውን ልናነበው እንፈልጋለን የሚል ምክንያት በመስጠት ጥቂት መስመሮች ያሉትን ደብዳቤ ለሰአታት ቢሮዋቸው ውስጥ ካስቀሩ በኋላ የስራ መውጫ ሰአት ሲደርስ ነገ ተመለሱ ዛሬ አላለቀም የሚል ምክንያት ሰጥተው ነገ ተመለሱ የሚል ምላሽ ለጠበቆቹ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ ጠበቆች ፕሬዚዳንቱን ለማናገር ጥረት ቢያደርጉም ፕሬዝዳንቱ ማናገር አልችልም የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡ የፍ/ቤትን ውሳኔ በቀጭን የስልክ መስመር መሻር የሚቻልበት አሰራር በአገሪቱ ውስጥ ባይኖርም የፕሬዚዳንቱ ድርጊት ይኸው ነበር፡፡ ውሳኔው ዛሬ ተፈጻሚ መሆን ያለበት ዛሬ መሆኑ እየታወቀ በእጅ ጥምዘዛ የተፈጸመው ውሳኔውን ተፈጻሚ ያለማድረግ ድርጊት ስለ አገሪቱ የፍትህ ስርአት ፍትሃዊነት እና ታማኝነት ደጋግመን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ በዚህ ጉዳይም የህግ ባለሞያ አስተያየት ይዘን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን፡፡

‹‹ፊልሙ›› እንደሚገመተው ዛሬ የመታየት እድሉ ሰፊ ነው - ፍ/ቤቱ እንዳይታይ ውሳኔ ቢያሳልፍበትም፡፡ ሆኖም የፍ/ቤቱም ቀዳሚው ውሳኔ መሪዎቻችን እየተካሄደባቸው ካለው አሳዛኝ የምስክርነት የችሎት ድራማ ጋር ተያይዞ ሙሉ እምነት የሚጣልበት አልነበረም፡፡ አንድ ሊታወቅ የሚገባው ቁም ነገር የ‹‹ፊልሙ›› መታየት ወይም አለመታየት በሙስሊሙ ህብረተሰብ ትግል ላይም ሆነ በመሪዎቻችን ላይ የሚፈጥረው አንዳችም እክል እንደሌለ ነው፡፡ በተቃራኒው የ‹‹ፊልሙ›› መታየት ከሚጥሰው ሕግ በተለይም ዛሬ የተሰጠውን የፍ/ቤት ውሳኔና የተጠርጣሪዎችን ከፍርድ ውሳኔ በፊት ነጻ ሆኖ የመገመት (Presumption of innocence) መሰረታዊ የህግ መርህ የሚጥስ ከመሆኑም በላይ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ትግል የበለጠ የሚያፋፍም መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከፊልሙ መታየት ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ስሜታዊነት ሳይንጸባረቅበት የተለመደ ስክነቱን በማሳየት ቀጣይ ሂደቶችን እንዲጠብቅ እንጠይቃለን፡፡

አላሁ አክበር

No comments:

Post a Comment