Monday, August 6, 2012

መንግስት በእስልምና ሀይማኖት ጣልቃ መግባቱን እንደቀጠለ የሚያሳዩ 11 ማስረጃዎች


o መንግስት በእስልምና ሀይማኖት ጣልቃ መግባቱን እንደቀጠለ የሚያሳዩ 11 ማስረጃዎች መንግሥት በእስልምና ሃይማኖት ጣልቃ ስለመግባቱ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ እጅግ አስገራሚና አሳዛኝ በሆነ መልኩ ጣልቃ ገብነቱ ግልጽ ሆኖ እየተስተዋለ ነው፡፡ እስቲ በጥቂቱ ብቻ ለማስታወስ ልሞክር፡፡

1. መጅሊስ በደህንነቶች ተጽእኖ የሚመራ መሆኑ
መጅሊስ ግቢ ውስጥ የስራ ድርሻቸው የማይታወቅና አመራሮቹን እንኳ አንቀጥቅጠው የሚገዙ ‹‹ደህንነቶች›› በርካታ መሆናቸውና ለጉዳይ የሚመጡ ሰዎችን በተደጋጋሚ ቢሮ ውስጥ እያፈኑ ማስፈራራታቸው የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ያሳያል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት 1 በማዘጋጃ ቤት ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ጠርቶ ውይይት ባደረገበት ወቅት አቶ ሰይድ ሐሚድ የሚባሉ ሰው አዲስ አበባ መጅሊስ መስጂዶቻቸውን በተመረጡ ኮሚቴዎች እንዳያተዳድሩ በደህንነት አባላት ጭምር እንደሚያስፈራሯቸው ተናግረዋል። በቢሯቸው ለ20 ደቂቃ ያህል እንዳፈኗቸውም አስረድተዋል። ‹‹ደህንነት›› የተባለው አካል በርካታ ማስፈራራቶችን በመፈጸም የእስልምና ጉዳዮችን ሲሾፍር ቆይቷል። እንደውም ጉዳዩ በጣም የተለመደና ግልጽ የወጣ ከመሆኑ የተነሳ በየመጅሊሱ ላይ ‹‹የተሾሙት›› ደህንነቶች በስም እስከሚታወቁ ድረስ የሚደርስበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ደህንነት ‹‹ታምሩ›› ፌደራል መጅሊስ አካባቢ በጣም የሚፈራ ደህንነት ነው። ደብዳቤ የሚያስፅፈውም ሆነ ውሳኔዎችን የሚወስነው ለሰባት አመታት ያክል እሱ ነበር። ስልክ እየደወለ አንዳንዴም መጅሊስ እየመጣ ይህን አግዱ፣ ተቃውማችሁ ደብዳቤ ጻፉወዘተ ሲል ያዛል፡፡በኋላ ግን ስሙ በጣም እየገነነ እና ግልፅ እየወጣ ሲመጣ በግምገማ ወደ ሱማሌ ክልል አዛውረውት አሁን በሰሞኑ ጉዳይ ውጥረት ሲበዛባቸው መልሰው አምጥተውታል። እኒህ ደህንነቶች ደግሞ በተቋሙ ውስጥ የመሠረቱት የጥቅም ትስስር እንዲበጠስ ስለማይሹ መጅሊሱ በሙስናው እንዲቀጥል ያመቻቹለታል። ‹‹ጠላቶቹን›› ያስፈራሩለታል። ያስሩለታል። ይደበድቡለታል። በ2002 የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሊግ የሚባል ህጋዊ ማህበር ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም መስራቾቹ በደህንነቶች በደረሰባቸው ማስፈራሪያና ዛቻ እንዲሁም በኃላ አይን ያወጣ ግልጽ የማሸማቀቂያ ደብዳቤ ሲጻፍባቸው ማህበሩን ትተው ተቀመጡ፡፡እንደዚሁም የተለያዩ ኢስላማዊ የአስተሳሰብ መስመር (መዝሀብ) ተከታይ ሊቃውንትም ለ 9 ወራት ያህል ጉባኤ መስርተው ጥሩ የስምምነት ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ ለአንዳንዶቹ በግል በደህንነት በደረሰባቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ምክንያት ተንጠባጥበው ወጥተዋል። ጉባኤው እንዳይፈርስ አጥብቀው ሲታገሉ የቆዩት የአገሪቱ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስም ደህንነቶች ሲያስፈራሯቸው ‹‹እኛም ላገራችን ደህንነቶች ነን። ላገራችን እናስባለን!›› ሲሉ ቁጣቸውን መግለፃቸው ይታወሳል። መጨረሻም ይህ ወንጀል ሆኖባቸው ከሙፍቲነት ተባረዋል፡፡

2. ከአመታት በፊት ከንቲባው አሊ አብዶ የመጅሊስ ባለስልጣን መሾማቸው
1988 በደብረዘይት ከተማ በተደረገ ስብሰባ ከንቲባው አሊ አብዶ መድረክ ላይ በግልጽ ‹‹መሪ የሚሆናችሁ ጎበዝ ሰው አምጥቼላችኋለሁ›› በማለት አቶ አብዱረዛቅ የተባለን ግለሰብ መጅሊስ ላይ መሾማቸው ይታወሳል። በተጨማሪም በ2002 ምርጫ ወቅት ስለመጅሊሱ በፓልቶክ ሩም ውስጥ ተገኝተው ሲወያዩ የነበሩት የአሁኑ የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሪድዋን ሁሴን በአቶ ኤልያስ ሬድማን እና በነሃጂ ኡመር መካከል የነበረውን ፀብ ለማብረድ እንደሙስሊምነታቸው እሳቸው (እና አቶ ኤልያስ ሰኢድ የአዲስ አበባ መስተዳደር ምክትል አፈጉባኤ የነበሩት) አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን የመጅሊስ አመራር አባላት ከመጅሊሱ መዋቅር ውስጥ አሸጋሽገው መመልመላቸውን አምነዋል። እነርሱ መልምለው ያመጧቸው ግለሰቦች ይኸው ሕዝበ ሙስሊሙን በማወክና እምነት በማስለወጥ ዘመቻ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ግልጽ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው። መራጩ ህዝብ እንጂ የመንግስት ባለስልጣናት አይደሉም

3. የመንግስት ባለስልጣናት አህባሾችን ጋብዘው ማምጣታቸው
የአህባሽን አስተሳሰብ እንዲያስተምሩ ከውጭ አገር ድረስ እንዲመጡ የተደረጉት ዶክተር ሰሚር ቃዲ ሐምሌ 20/2003 በግዮን ሆቴል ጋዜጠኞች በተገኙበት ፌደራል ጉዳዮችና እሳቸው በጋራ በመሆን ካደረጉት በድምጽ የተቀዳ ንግግር የተወሰዱ ንግግሮች የመንግስትን ጣልቃ ገብነት የሚያሳዩ ናቸው፡- /ር ሰሚር፡- ‹‹በዶክተር ሽፈራው በተጋበዝኩ ጊዜ፣ እናንተን ከመገናኘቴ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ አስተውያለሁ። የኢትዮጵያ መንግስት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ሽፈራውና ሌሎችም ሚኒስትሮች ጉዳዩን በሚገባ ተረድተውታል። ትክክለኛ እና ጥበበኛ እርምጃም እየወሰዱ ነው። ለመስተንግዷቸው ሁሉንም ላመሰግን እወዳለሁ።›› • ዶክተር ሰሚር (ዋነኛና በየአገሩ የሚዞር የአህባሽ አንጃ አመራር አባል) ተጋብዞ የመጣው በፌደራል ጉዳዮች ነው። ፌደራል ጉዳዮችም ያለምንም ሐፍረት ጋዜጠኞችን ጠርቶ ሰፊ ንግግር አድርገዋል። ፌደራል ጉዳዮች የሀይማኖት መሪዎችን እያስመጣ አህባሽን ለማስፋፋት እና ከከተማዋ ሃብታሞች ብር እየለመነ ፈንድ ለማድረግ ማን መብት ሰጠው? ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ሚኒስትሮችስ የትኛው የእስልምና አንጃ ለኢትዮጵያ እንደሚስማማ ከዶክተሩ ጋር ውይይት ለማድረግ ማን መብቱን ሰጣቸው? ሀይማኖታችንን የሚመርጥልን መለስ ነውን?

4. የዶክተር ሽፈራው ንግግር
በዚሁ የግዮን ሆቴል ስብሰባ ዶክተር ሽፈራው ያደረጉት ንግግር የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ፍንትው አድጎ ያሳያል፡፡ በጥቂቱ እንመልከት፡- /ር ሽፈራው፡- ‹‹… ይህንንም የአገራችን ልጅ (የአህባሽ መሥራች ሸኽ ዐብደላ ሐረሪ) ኢትዮጵያዊ መሆናቸው አንድ ነገር ሆኖ ይህንኑ አስተምህሮ ባገራችንም ጭምር በምን ዐይነት መንገድ ልናራምድ እንችላለን በሚል የተለያዩ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይህንን ሥራ በበላይነት ሲመራ ነው የቆየው። ስለዚህም ዛሬ እዚህ ተገኝተው ለኛም የራሳቸውን መልእክትና ትምህርት እያስተላለፉ ያሉት (/ር ሰሚር) በራሳችን በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል ትልቅ ትኩረትና ቦታ የሰጠነው ጉዳይና እጅግ አድርገን ለማመስገን እንወዳለን።በዚህ ሂደት ላይ ትልቁን ድርሻም ሚናም እየተጫወቱ ያሉትን ሐጂ ዐብዱልከሪም በድሪን እና የእነሱን ተቋም (ፔትራም ካምፓኒ) በዚህ አጋጣሚ ለማመስገን እፈልጋለሁ። ይሄ (ከአሕባሾች ጋር) ግንኙነቶችን በመፍጠር የእነሱንም ጉዞ ደርሶ መልስ ምን ሁሉ በማቀነባበር በጣም መሠረታዊ በሆነ መንገድ እያገዙን ነው ያሉት። እነሱንም ለማመስገን እፈልጋለሁ። …… ይሄ ጀመርን እንጂ እንደተባለው የመጨረሻው አይደለም። ስለዚህ በቀጣይነት በሌሎች አጋጣሚዎች ተመሳሳይ መድረኮች ይኖራሉ ብለን ነው የምናስበው። በየክልሎችም ብዙ ይኖረናል እንዲህ ዓይነት መድረኮች።›› • ፌደራል ጉዳዮችን የሚያክል መንግስታዊ ተቋም ምን አግብቶት ነው በዚህ መልኩ ጣልቃ የሚገባው? • እየተናገሩ እንዳሉት እገዛው ሁሉ እየተደረገ ያለው ለመንግስት ነው። ውይይቶቹንም የሚያደርገው መንግስት ነው። መንግስት ምን አገባው? የፈለገውን ሀይማኖት የማስፋፋት ሥልጣን ማን ነው የሰጠው? በሐምሌ 2003 በሐረር ሐሮማያ ካምፓስ በፌደራል ጉዳዮችና በመጅሊሱ ትብብር የተዘጋጀውና ለ1300 ሰዎች የተሰጠው የአህባሽ ስልጠና ላይ ዶክተር ሽፈራው ይህንን ተናግረዋል፡- ‹‹ሌለኛው ከመጅሊሱ እውቅና ውጪ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ይቁሙ ብላችሁ ያቀረባችሁት አለ። ሼህ አህመዲን (የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት) የሚያነሱት እንደተጠበቀ ሆኖ በኛ በኩል ከፈቃድ ወጪ የሚደረግ ትምህርት፣ ዳዕዋ፣ ስብከት፣ ከፈቃድ ውጪ የሚሠሩ መድረሳዎች፣ ከፈቃድ ውጪ የሚሠሩ መስጊዶች፣ ከፈቃድ ውጪ የሚሠሩ ኹጥባዎች (የጁሙኣ ስብከቶች) ሁሉ መቆም አለባቸው ነው የምንለው! ይህንንም የመቆጣጠር ሙሉ ሥልጣኑ፣ ማንም የማይሻማው ሙሉ ሥልጣኑ የፌደራል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና በሥሩ ያሉ መዋቅሮች ብቻ ነው።›› • መጅሊሱ በአዋጅ ያልተቋቋመ፣ ከተራ ኤን..ኦነት ያልዘለለና የመንግስት አጀንዳ አስፈጻሚ፣ መሪዎቹም በካድሬዎች ጥቆማ ያለምርጫ ሹመት የሚሰጣቸው ሆነው ሳለ ማንኛውም ኢስላማዊ ስብከት ሁሉ በሱ ሥር እንዲገባ መደረጉ ከህገ-መንግስቱ የመናገርና ሀይማኖትን የማስፋፋት መብት ጋር ክፉኛ የሚጋጭ ነው። ጣልቃ ገብነትም ነው። ፌደራል ጉዳዮች ምን አግብቶት ነው በመጅሊስ ፍቃድ ካልሆነ ሰበካ ሊካሄድ አይችልም ሲል የሚወስነው? በየሦስት ዓመቱ የፍቃድ እድሳት የሚደረግለትና በመንግስት ሙሉ ቁጥጥር ሥር ያለው መጅሊስ በየትኛው ሕጋዊ ስልጣኑ ነው የእስልምና ስብከቶችን የሚቆጣጠረው? በዚህ መልኩ መጅሊሱን ከሕግ ውጭ በሆነ አካሄድ መደገፉ መንግስትን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብ ያደርገዋል

5. የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ሃላፊ አቶ ጸጋዬ ሀ/ማርያም ንግግር
በመስከረም 2004 በኮተቤ ኢትዮ ቻይና ቴክኒክና ሙያ ካምፓስ በተሰጠውና የመንግስት ባለሥልጣናት ስለእስልምና ጣልቃ ገብተው ሲፈተፍቱ በነበረበት የቀናት ሥልጠና የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ኃይለማርያም ሲናገሯቸው የነበሩት ንግግሮች በሙሉ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት የሚያሳዩ ናቸው። እስከማቧደንና አንዱን መዝሀብ በሌላው ላይ እስከመቀስቀስ ደርሰዋል። የሚከተለውን አስገራሚ ንግግር ተናግረዋል። በድምጽም ተቀድቷል፡- ‹‹…ቅንጅትና ኢሕአዴግ አንድ ላይ ሊደራደሩ ይችላሉ? (ሰዎች አይችሉምይላሉ) እንደዚሁም ወሐቢያና ሱኒ አንድ ላይ ሊሆኑ አይችሉም!›› • አንድ ትልቅ የመንግስት መሥሪያ ቤትን ወክሎ የተገኘ ሰው በሁለት የእስልምና ቡድኖች መካከል ‹‹ስምምነት ሊፈጠር አይችልም›› በሚል ንግግር ለመከፋፈል እንዲሞክር መብት የሰጠው ማነው? ‹‹ሱፊያ›› እና ‹‹ሱኒ›› ወዘተ መካከል ያለው ልዩነት ለምንግስት ምን አገባው? መስማማት መቻል አለመቻላቸውን የሚወስነው የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ነው? • በተሰጡት ሥልጠናዎች ‹‹በግድ›› የተካፈሉ ሰዎች ጥያቄ ለመጠየቅ መከልከላቸውን እና አቋርጣችሁ አትወጡም ተብለው መከልከላቸውን፤ ከብዙ ክርክር በኋላ ሲወጡም የስልክ ሜሞሪዎቻቸውን በፖሊሶች ተቀምተው እንደተባረሩ በወቅቱ በወጡት ኢስላማዊ ሚዲያዎች ላይ የተገለጸ መሆኑም ሌላ የጣልቃ ገብነት ማስረጃ ነው። ሥልጠናዎቹ የተካሄዱት በአገር አቀፍ ደረጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር በጀት ተመድቦ፣ በፖሊስና ደህንነቶች ጥበቃ በትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች አዳራሾች ውስጥ ነበር። አዘጋጆቹም መንግስትና መጅሊሱ ናቸው። ብዙ ሺህ የመስጊድ ኢማሞችም ስልጠናውን ካልወሰዱ እንደሚባረሩ የሚገልጹ ደብዳቤዎች ከእስልምና ጉዳዮች ተሰጥቷቸው በግዳቸው ተገኝተዋል። ትምህርቱም በአብዛኛው ሀይማኖታዊ ነበር። እኒያ ሁሉ የዩኒቨርሲቲ አዳራሾች ‹‹አህባሻዊ›› ትምህርት ሊሰጥባቸው የሚችለው በመንግስት አስፈቃጅነት መሆኑም በተደጋጋሚ ተገልጾዋል። መንግስት ምን አገባው

6. የአንዋር መስጊድ ኢማም ጣሃ መሀመድ ንግግር
የታላቁ አንዋር መስጊድ ዋና ኢማም ጣሃ ሙሐመድ ሐሩን በአህባሽ ምክንያት የተፈጠረውን ተቃውሞ ለማረጋጋት በመጅሊሱ አማካኝነት ጠርተው 400 ያህል ሰዎች በተገኙበት እና በድምጽም ጭምር በተቀዳ ንግግራቸው የሚከተለውን ብለው ነበር፡- ‹‹ከዶክተር ሽፈራው ጋርም ቢሆን እንገናኛለን በዚህ ዙሪያ። አብረን እንገናኛለን በስብሰባ ብዙ ጊዜ። በቁርአንና በሐዲስ የተረጋጋ የሱፊያ አካሄድን ይዘን መጓዝ አለብን የሚል ነው ዋና መመሪያው!›› • በቁርኣንና በሃዲስ፣ እንዲሁም በሱፊያ መንገድ እንሂድ አንሂድ ዶክተር ሽፈራው ምን አግብቷቸው ነው ከመስጊድ ኢማሞች ጋር ስብሰባ በየጊዜው የሚቀመጡት? የትኛው የህገ-መንግስት አንቀጽ ነው ይህንን ስልጣን የሰጣቸው

7. መንግስት ለመጅሊስ እያደረገ ያለው ህገወጥ ድጋፍ
ከዋነኛ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ማረጋገጫዎቹ አንዱ መንግስት መጅሊሱ ኤን..ኦ እንደመሆኑ መጠን እንቅስቃሴዎቹንና የሂሳብ ሪፖርቶቹን ሁሉ የመመርመርና የመቆጣጠር ስልጣን (ግዴታ) ያለበት ሲሆን ተቋሙ ችግር ፈጣሪ ሆኖ ሲገኝም ተገቢውን ፍትሐዊ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። እስካሁን ለበርካታ አመታት መጅሊሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን በሙስና ሲያጭበረብር እና ሲመዘብር፣ ከመተዳደሪያ ደንቡ ጋር በተጋጨ ሁኔታ ያለምርጫ በጓሮ በኩል ካድሬዎችን ሲሰገስግና ተቋሙን ሲያስመዘብር ዝም ማለቱ በራሱ ወገንተኛ ሆኖ ድጋፍ እያደረገና ጣልቃ እየገባ ለመሆኑ ማስረጃ ነው። መሪ ተብዬዎቹን ለእጅ ጥምዘዛና አጀንዳ ማስፈጸሚያ እያደለባቸው መሆኑም ሳይታለም የተፈታ ነው። በ 2003 በተደረገው የሀጅ ጉዞ ብቻ ተቋሙ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ከተጓዦች እንደመዘበረ በርካታ ኢስላማዊ ጋዜጦችና መጽሔቶች ጽፈዋል። ጠጣር መረጃዎችንም ከሰነድ ጭምር አቅርበዋል። ተቋሙ በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን ውጭ ይህን
ሁሉ በደል ሲፈጽም፣ ከዚያም አልፎ አዲስ በጥባጭ አንጃ ከሊባኖስ አስመጥቶ በግድ ሙስሊሙ ላይ ሲጭንም የመንግስት ባለሥልጣናት ካጠገቡ ሆነው ሲደግፉ፣ የተቃወመውን ሲያስፈራሩና ሲያስሩ ቆይተዋል። ባለፉት ሳምንታት ‹‹መጅሊሱ አይወክለኝም›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ቲሸርት የለበሱ ወጣቶችን በየፖሊስ ጣቢያው ሲያጉሩ ነበር። መጅሊሱን የመቃወም መብት የሕዝቡ ሆኖ ሳለ እስራቶች መፈጸማቸው ጣልቃ ገብነትን ያሳያል። ባለፉት 6 ወራት (በተለይ ደግሞ አስር ሳምንታት) የወጡትን የ‹‹ሠለፊያ›› ጋዜጦች ማየት ብቻ ምን ያህል ሰዎች በጥቃቅን ሰበብ ሲታሰሩና ሲንገላቱ እንደነበር ማስረጃ ነው። በደብረዘይት በተዘጋጀ ስልጠና የፌደራል ጉዳዮች ባለስልጣን የሆኑት አቶ እውነቱ ብላታም ‹‹መጅሊሱን መቃወም መንግስትን መቃወም ነው›› ሲሉ በድፍረት በጋዜጠኞች ፊት ተናግረዋል፡፡ 

8. ስልጠናውን ያዘጋጀው ራሱ መንግስት መሆኑ
መጅሊሱ በ04/11/03 ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በጻፈው ማህተም ያረፈበት ደብዳቤ ስልጠናው የተዘጋጀው በፌደራል ጉዳዮች እና በመጅሊስ ትብብር እንደሆነ ጠቅሷል። እንደውም አስቀድሞ የጠቀሰው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ነው። ሚኒስቴሩም በርካታ ሚሊዮን ብር በማውጣትና አገር አቀፍ የትምህርት ተቋማት አዳራሾችን በመጠቀም ሲያሰለጥኑ ቆይተዋል። ስለዚህ ‹‹ተጋብዘን ነው ህገ መንግስቱን ያስተማርነው›› ሲሉ የሰጡት ምክንያት ተቀባይት የለውም! በግልጽ ሁኔታ መንግስት ጣልቃ መግባቱንም ያረጋግጣል። በተጨማሪም ትላልቅ የመንግስት ባለስልጣናት አህባሽ የተባለው አንጃ ሌላውን ሙስሊም ክፉኛ በሚያጠቃበት፣ በሚያከፍርበት እና በሚሰድብበት ስብሰባ ላይ አንዳች ሳይቃወሙ፣ እንዲያውም እየደገፉ መገኘታቸው አላማቸው እንደተናገሩት ‹‹ጽንፈኝነትን ከህገ መንግስቱ አንጻር ለመግራት›› ሳይሆን ሙስሊሙን በቡድን ከፋፍሎ ለማበጣበጥ መሆኑን ግልፅ ያደርጋል። የተሰጡትም ትምህርቶች ጽንፈኝነትን የሚቃወሙ እና ሚዛናዊነትን የሚሰብኩ አልነበሩም። ይልቁንም አንዱ ሌላውን ሙስሊም ወንድሙን እንዲጠላ የሚጋብዙ ናቸው። ህገ መንግስት ማስተማር ከዚህ ጋር ምን አገናኘው? 9. የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በሻሸመኔ የተናገሩት ንግግር
በቅርቡ በተደረገው ስልጠና የሻሸመኔ ሙስሊም ህብረተሰብ በመቃወሙ ‹‹በአገር ልጅነት›› እንዲያግባቡ የታዘዙት አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ‹‹ስልጠናው የማይቀር የመንግስት ፕሮግራም ስለሆነ ብትገቡ ነው የሚሻላችሁ›› በማለት መሻኢኾችን ሰብስበው አስፈራርተዋል። ሌሎች የፌደራል ጉዳይ ሰራተኞችም በሻሸመኔ፣ ባሌና አርሲ ቤት ለቤት ከፖሊሶች ጋር በመዞር ኡለሞችን ስልጠና እንዲገቡ ሲወተውቱ፣ ሲያስፈራሩ ቆይተዋል። ይህም ግልጽ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው።

10. የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ንግግር
የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲ ሳዶ ሰሞኑን በትውልድ ቀያቸው ተገኝተው የአህባሽን ስልጠና መሻኢኾች እንዲቀበሉ ባደረጉት ንግግር በግልጽ ሐይማኖት ውስጥ ጣልቃ ገብተው ሲናገሩ ተስተውለዋል። ለሸህ አብደላ አል ሐረሪ ጥብቅና በመቆም ዲናዊ ጥያቄዎችን ጭምር እያነሱ ከመናገር አልፈው ‹‹ኪታብ ካላችሁ መድረክ እናዘጋጅላችሁ፤ መጥታችሁ ተከራከሩ ብለናቸዋል›› ሲሉ ተናግረዋል። መንግስት ምን አግብቶት ነው የመዝሀብ ክርክር መድረክ የሚያዘጋጀው? ‹‹በውሸትና በሀሰት አገሩን የሚበጠብጡት እንዲመረጡ አንፈልግም›› በማለትም ይደረጋል በተባለው ምርጫ ውስጥ አሁንም መንግስት በጣልቃ ገብነቱ የሚቃወሙትና እንደፈለገ የማይሆኑለት እንዳይመረጡ እንደሚያደርግ አሳይተዋል። ‹‹እኛ የምናውቀው ሸህ አብደላ አልሀረሪን ነው›› በማለትም የመንግስትን የሀይማኖት ምርጫ ጠቅሰዋል። የጅማ ከንቲባ ራሳቸውም አሊሞችን እያስፈራሩ ስልጠና ለማስገባት ሞክረዋል። የማይገቡት እንደሚታሰሩም ዝተዋል።

11. ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አንዱን መጤ ሌላውን ነባር ሲሉ መፈረጃቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሃያ አምስተኛው መደበኛ የፓርላማ ስብሰባቸው ‹‹ሱፊያ›› ብለው የፈረጁትን አካል ‹‹ነባር››‹‹ሰለፊያ›› ብለው የሰየሙትን አካል ደግሞ ‹‹መጤ›› ሲሉ ፈርጀዋል። ይህ ደግሞ በቁርአንና በሀዲስ ጣልቃ መግባት ነው። አንድ ባለስልጣን ስለሙስሊም መዝሀቦች በዚህ መልኩ የመናገርና አንዱን ነባር አንዱን መጤ እያለ የመፈረጅ፣ የመከፋፈል ስልጣን የለውም። ሀይማኖታዊ ትንተና የሚመለከተው አሊሞችን እንጂ ባለስልጣናትን አይደለም። ከዚህ በተቃረነ መፈፀሙ ደግሞ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሸህ አብደላ ሐረሪ ጥብቅና መቆማቸውና ያራመዱትም ነባሩን እስልምና መሆኑን መጥቀሳቸውም እንዲሁ ከአንድ ባለስልጣን የማይጠበቅ ጣልቃ ገብነት ነው! ‹‹ጣልቃ አንገባም!›› እያሉ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ጣልቃ መግባቱ መች ይሆን የሚቆመው? ሁላችንም ሕገ መንግሥታችን እንዳይሸራረፍ ዘብ እንቁም! (ይህንን ወረቀት የቻሉትን ያህል ኮፒ በማድረግ ላልደረሳቸው ሁሉ ያዳርሱ፡፡ በተለይም ገጠር ላሉና ሚዲያ መከታተል ለማይችሉ ዘመዶችዎ በማዳረስ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ እየተሰራ ያለውን ግፍና የመብት ጥሰት ያሳውቁ! አላህ አጅርዎን ይከፍልዎታል!)


No comments:

Post a Comment