Sunday, August 19, 2012

በድምጻችን ይሰማ
በአላህ ሥም እጅግ በጣም አዛኝ እጅግ በጣም ሩህሩህ

ኢትየጵያዊያን ሙስሊሞች አኩሪ ታሪክ ሠሩ
አዲስ አበባ ስታዲየም ልዩ የተቃውሞ ትዕይንት አስተናግዶ ዋለ፡
ሙስሊሙ ሀዝብ ለ9 ወራት ይዞት የዘለቀውና ተገቢ ምላሽ ሳያገኝ ንቀት በተሞላበት ሁኔታ እያስተናገደ የሚገኘውን ሀይማኖታዊ የመብት ጥያቄ አካል የሆነው ተቃውሞ በታሪኩ ልዩ እና ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መልኩ ተካሂዷል፡፡ ሰፊውን ህዝብ ያቀፈ መሰረታዊ የመብት ጥያቄ ባግባቡ በማስተናድ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “ጥቂቶች” በሚል አባዜ ተጠምዶ ለከረመው አካል ትልቅ ትምህርት የሰጠ የተቃውሞ ውሎ ሆኗል፡፡ ገና በማለዳ ወደ ስቴዲየም መጉረፍ የጀመረው ሙስሊም ህዝብ አመጣጡ እንደ
እስከዛሬ ዒድን ብቻ ለመስገድ እየመጣ እንዳልነበረ ከአብዛሃኛው ሙስሊም ገፅታ በቀላሉ ማንበብ ይቻል ነበር፡፡ ትላንት የመግሪብ ሰላት መሰገድን ተከትሎ በየመስጂዱ እና አካባቢው ያለውን የጠነከረ ቁጥጥር በማለፍ የዛሬውን የዒድ የተቃውሞ ውሎ አቅጣጫ የሚያሳዩ ወረቀቶች ሲበተኑ ያመሹ ሲሆን ይህም በስታዲየም ለሚኖረው የተቃውሞ ሂደት መልክ ያበጀ እና ሂደቱ በተፈለገው መንገድ ተጉዞ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነበር፡፡

ከወትሮው የዒድ ሶላቶች በተለየ ሁኔታ በስታዲየም አራቱም አቅጣጫዎች ከፍተኛ የፌዴራል ፖሊስ ቁጥር ማየት ተችሏል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ እያካሄዱት የነበረው የአፈታተሸ ስርዓት እጅግ የሚገርም የነበረ ሲሆን መርፌ የጠፋቸው ያክል የጠነከረ የሰውነት ፍተሻ ሲያደርጉ ለሚመለከት ሰው ድፍን የአዲስ አበባን ሙስሊም በዚህ መልኩ መፈተሸ አዳጋች እንደሚሆን እንዴት እንዳልገመቱት ግራ ያጋባል፡፡ በዚህ ሁኔታ የነበረውን ፍተሻ ያለፉ በርካታ ከአቡጀዲ እና ሸራ የተዘጋጁ መፈክሮች፣ ነጫጭ ወረቀቶች እና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሶፍቶች የተቃውሞው ማድመቂያ ነበሩ፡፡
የመጅሊሱ ሕገ ወጥና ሙሰኛ አመራሮች መድረኩን በመቆጣጠር እንደለመዱት ዲስኩራቸውን ለማስተላለፍ ዝግጅት አድርገዋል፡፡ ይህንንም ባገኙት የሕዝብ የመገናኛ ብዙኃን ሁሉ ሲለፍፉ ሰንብተዋል፡፡ “ሙያ በልብ ነው” ያለው ሰፊ ሕዝብ ግን ይህ ሁሉ እንደማይበግረው በመተማመን የልቡን በልቡ ሰንቆ ከመድረኩ ፊት ለፊት ጀምሮ የስታዲየምን ዙሪያ በሙሉ ተቆጣጥሮታል፡፡
የዒድ ተክቢራውን ጋብ በማድረግ “የተከበራችሁ ምዕመናን ኢድ ሙባረክ” የሚል ንግግር ከመድረኩ ሲሰማ የመጅሊስ ሰዎች መድረኩላ መውጣታቸውን ያረጋገጠው ሕዝብ የተቃውሞ ድምፁን በሚገርም አንድነትና ሞገድ ለመቆጣጠር በማይቻልበት ሁኔታ ለቀቀው፡፡
“አላሁ አክበር!”፣ “አሻዕብ ዩሪድ ኢስቃጠል መጅሊስ!” የሚል የድምፅ ማዕበል ንፁኃን ኮሚቴዎቻችን የታሰሩበት ቦታ ድረስ ይሰማል ብለን እስከምንጠረጥር ድረስ ከባቢውን አጥለቀለቀው፡፡ በዚህም የእለቱ ከሶላት በስተፊት የተቃውሞ ድምፅን የማሰማት ስትራቴጂ አኃዱ አለ፡፡ የመጅሊሶች ላንቃ እከወዲያኛው ተዘጋ፡፡ በሁኔታው እጅግ መደናገጣቸው ያሳበቀባቸው መድረክ አካባቢ የነበሩ የመጅሊሱ ሰዎች መሯሯጥ ጀመሩ፡፡ ወደ ቀኝ ወደ ግራ በመዘዋወር በቅርብ ከሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ጋር የሚነጋገሩት ነገር እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ምናልባትም “አንድ በሉን እንጂ!” ለማለት ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡ የተቀየረ ነገር ሳይኖር ሕዝቡ ድምፁን በማውጣቱ ቀጠለ፡፡ የሕዝቡን ድምፅ የገታው ነገር የመድረኩ መነጋገሪያ (ማይክራፎን) ከመጅሊሱ ሰዎች ተክቢራ ሲያሰሙ ወደ ቆዩት ሸኾች ተላልፎ የወትሮ ተክቢራዎችን መቀጠላቸው ነበር፡፡ ሆኖም አንዴ የጀመረው የህዝቡ የተቃውሞ ድምፅ መቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡
በሰሞኑን የመንግስት መገናኛ ብዙኃን አማካይነት የዒዱን ዝግጅት አስመልክቶ የመጅሊሱ ሰዎች መቆጣጠር ይችሉ ዘንድ ከ 1,000 (አንድ ሺህ) በላይ ወጣቶችን እንዳሰማሩ ሲደሰኩሩልን እየሰማን ብንቆይም ይህንን ይቅርና ዩኒፎርም ለብሰው ከፊት ለፊቱ የተከመሩትን ወታደሮች (የፌዴራል ፖሊስ) ከቁብ ሳይቆጥረው ሕዝቡ ተቃውሞውን አሰማ፡፡
የተለመደው የተክቢራ ድምፅ በኑር መስጂድ ምክትል ኢማም ቢባልም ከቁጥጥር ውጭ የነበረው የተቃውሞ ድምፅ ማስተጋባቱን ቀጠለ፡፡ ሼኹም ይህንን እየሰሙ እንዳልሰሙ ሆነው ተክቢራ ማለታቸውን ቀጠሉ፡፡ የሳቸው ተክቢራ ድምፅ የተቋጨው ከአንደበታቸው የወጣው “አሶላቱ ጃሚዓ!” የሚለው ጥሪ ሕዝቡን ለሶላት እንዲቆም ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ ነበረ፡፡ ሀጂ ጠሐ ወደ ሚሕራቡ ሲጠጋ ያስተዋለው ሕዝብ የጀመረውን የተቃውሞ ድምፅ ይበልጥ ማስተጋባት ቀጠለ፡፡ እስከ አምስተኛው የሶላቱ ተክቢራ ድረስ ከሁሉም አቅጣጫ የሚያስተጋባው የተቃውሞ ድምፅ እንደ ቀጠለ ነበረ፡፡ ሐጂ ጠሐ ሶላቱን አሰግዶ ማጠናቀቁ ክፍል ሁለት የተቃውሞ ድምፅ የማሰማት ሂደት ማወጂያ ነበርና ሕዝቡ በጉጉት ይጠባበቃል፡፡ በፍጥነት ሶላቱን ማጠናቀቁን ተከትሎ ሁሉም ከመቀመጫው በመነሳት ተቃውሞው በቃላት ለመግለፅ በሚያዳግት ሁኔታ ቀጠለ፡፡ ወንድ፣ ሴት፣ ሕፃን፣ አዋቂ፣ ወጣት፣ አዛውንት ባጠቃላይ ስታዲየምና ዙሪያ ገባዋ ተናወጠች፡፡ ሶፍቶች፣ ነጭ ወረቀቶች፣ ነጫጭ ጥምጣሞች ሁሉም በእጁ የያዘውን ወደላይ በማውጣት አውለበለበ፡፡ አልፎ አልፎ በእስር ላይ የሚገኙት የኮሚቴዎቻችንን ፎቶግራፍ የያዘ ባነር መታየት ቻለ፡፡ ሀጂ ጠሐ ኹጥባ ለማሰማት መድረክ ላይ በድፍረት ቢወጣም ሕዝቡ ወደ አንድ ቦታ በመሰባሰብ የተቃውሞ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ የህዝቡን ቁጣ ከቁብ ሳይቆጥር ዙሪያውን በተደረደሩት ወታደሮች የልብ ልብ ተሰምቶት ኹጥባውን ለመቀጠል ቢሞክርም ከአፍታ ቆይታ በኋላ ቁጣ በተቀላቀለው ድምፅ “አሠላሙአሌይኩም” የሚል የመጨረሻ ቃል አውጥቶ መድረኩን ተሰናበተ፡፡
ቀድመው የተዘጋጁና የጠነከረውን ፍተሻ አልፈው በሕዝብ እጅ የነበሩ የተቃውሞ ወረቀቶች ይፋ ወጡ፡፡ “የታሰሩት ይፈቱ!”፣ “ድምፃችን ይሠማ!”፣ “ምርጫችን በመስጂዳችን!”፣ “ፍትሕ ናፍቆናል!”፣ “ኢስላም ሠላም!”፣ “Free All Prisoners!”፣ “ሳይፈቱ ምርጫ የለም!”፣ “ሕገ መንግስቱ ይከበር!”፣ “ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ!” እና የመሣሠሉት በጉልህ ከሚታዩት እና ከሚሰሙት መፈክሮች መካከል ይገኙበታል፡፡
በመካከላችን እና በዙሪያችን የሚገኙት የፀጥታ አካላት ሁኔታውን ፈዝዘው በአግራሞት ከመመልከት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ተሰልፈው ወደ ውስጥ (ወደ ስታዲየሙ) መግባታቸውን ብናስተውልም የለመዱትን ድብደባ ሊፈፅሙ ነው የሚል ስሜት ከመጫሩ ባለፈ የፈጠሩት ነገር አልነበረም፡፡ ስታዲየሙ ውስጥ የነበረው የተጨናነቀ ሕዝብ በቡድን በቡድን በመሆን በአራቱም የስታዲየሙ ማዕዘናት ተሰባስቦ ሲያበቃ ተጀምሮ የነበረው የተቃውሞ ድምፅ ተጠናክሮ እንዲቀጠል አደረገ፡፡ ይህ ሁሉ በሚሆንበት አጋጣሚ ኋላ ላይ ምን እንደሚሉ የምንታዘበው ጉዳይ ቢሆንም የመጅሊስ አመራሮችን ጨምሮ ኹጥባ ለማድረግ መድረክ ላይ የወጣውን ሐጂ ጠሐን ዞር ብሎ የተመለከታቸውም አልነበረም፡፡ ሂደቱ ፈፁም ሰላማዊ የመሆኑ መገለጫ የሆነው ይህ አጋጣሚ እስካሁን ድረስ ሕዝብን እንደፈለጋቸው ሲያንጓጥጡ፣ ሲሰድቡ እና ሊከፋፍሉ ሲሞክሩ የነበሩትን ሙሰኛ የመጅሊስ አካላትንም ሆነ ተለጣፊ ግለሰቦችን የመጉዳት ፍላጎት ኖሮት አያውቅም፡፡ ይህንንም ዛሬ በይፋ አሳየቷል፡፡ በስታዲየሙ ውስጥ የነበረው የተቃውሞ ሂደት ዙሪያ ገባውን በተኮለኮለው ኡማ ታጀቦ ነበር፡፡ ሂደቱን ይበልጥ የተቀናጀ እንዲመስል ያደረገው ዋና ጉዳይ ቢኖር ኡማው ልብ ውስጥ ያለው የመተሳሰር ስሜት ሲሆን ይህን ተከትሎ ሕዝቡ በርካታ ቁጥር ባለው የተለያዩ ጎራዎች በመከፋፈል ፍፁም ሠላማዊ የሆነውን ትዕይንት ተመልካቹን በማስደመም አሳይቷል፡፡ ስታዲየምን ያማከለው ይህ ትዕይንት በሜክሲኮ አቅጣጫ፣ በቸርችል ጎዳና፣ በሳሪስ መስመር እና ወደ መገናኛ መስመር የነበረው የተቃውሞ ትዕንይንት እጅግ ማራኪ ነበር፡፡ ይህም ያለምንም አስገዳጅ ኃይልና መገፋፋት የወጣውን ህዝብና የተቃውሞውን ሕዝባዊነት አሳይቷል፡፡ “ጥቂቶች” እየተባለ የሚወራውንም ፕሮፓጋንዳ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደረገ መሆኑን ዳግም አስመስክሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ የሄደው የተቃውሞ ትዕይንት ፍፁም ሠላማዊ የነበረ መሆኑ የሚያሳየውን እውነታ ለአንባቢው ብንተወውም በምንም ዓይነት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሊውል እንማይችል የሚያስማማ ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምናልባትም ቀድሞ የተጠነሰሰው ሴራ አካል መሆኑ የተገመተና የተቃውሞውን ሰላም የማድረስ ሂደት ተሞክሯል፡፡ በሁሉም አቅጣጫዎች በሕዝብ ተቃውሞ የታጀበው ጉዞ መልኩን ወደ ሠላማዊ ሰልፍነት ቀይሮ በቀጠለበት ሁኔታ አብዮት አደባባይ ወደ መገናኛ አቅጣጫ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በቦታው የነበሩ ጥቂት ፖሊሶች በሌላ አካባቢ ከነበሩት በልደረቦቻቸው በተለየ መልኩ አባዚያቸው ተነስቶባቸው በሠላማዊ መንገድ ተቃውሞውን እየገለጠ የነበረውን ሕዝብ ድንገት በያዙት ቆመጥ መደብደብ ጀመሩ፡፡ ይህም ምናልባትም በቅርብ የነበሩትን የቤትክርስትያን አማኞች ረብሸዋል ብሎ በመወንጀል አንድም በሂደቱ ለመጠቀም በማሰብ በሌላም በኩል ክርስትያን አማኞችን በኛ ላይ በማነሳሳት ረብሻ ለማቀጣጠል የታሰበ ቢሆንም “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሠናል ” ያለው ሙስሊም ሕዝብ ከረብሻው ራሱን በማራቅ ምንም ዓይነት አፀፋ ሳይመልስ ከፊሉ ወደ ቤተ ክርስትያኗ በመጠለል ከፊሉም ወደ ሌላ አቅጣጫ ለጊዜው ገለል በማለት ሊፈጠር ታስቦ የነበረው ረብሻ በቅፅበት ወደ መረጋጋት ተለውጦ ህዝቡ ተቃውሞውን በሠላማዊ መንገድ እየገለጠ ጉዞው ወደ የቤቱ አድርጓል፡፡
ከስታዲየም በመነሳት በኢቴቪ በኩል የተጓዘው አንደኛው እና እጅግ በርካታ ቁጥር የነበረው የተቃውሞ አጀብ አቴቪ ላይ ሲደርስ ጉዞውን ጋብ በማድረግ “ኢቴቪ ውሸታም!” በማለት ኢቴቪ እስከዛሬ ድረስ በሙስሊሙ ሕዝብ ላይ ሲሰራ የቆየውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመቃወም አውግዘዋል፡፡
ከዚህ አገራችን ኢትዮጵያ ካስተናገደችው ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን የተላበሰ እና እጅግ ቁጥሩ በርካታ ሙስሊም በሙሉ ፈቃደኝነት የተሳተፈበት የዛሬው ታላቅ የተቃውሞ ውሎ ለሕዝበ ሙስሊሙ የድል አውድማ ሆኖ ከመዋሉም ባሻገር ኢትዮጵያ በታሪክ ድርሳኗ በደማቅ ቀለም የምታሰፍረው እውነታ ይሆናል፡፡ ሙስሊሞች በእነ ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ አማካይነት የዒድ በዓሎቻቸው ብሔራዊ በዓል ሆነው መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብ ዕውቅና የነፈጋቸው የመጅሊስ አመራሮች በሕዝብ ተዋርደው መድረክ ሳይኖራቸው የደከረተ ዲስኩራቸውን ሳያሠሙ የቀሩበት ልዩ አጋጣሚ ሆኗል፡፡ በእስከዛሬው የዒድ አከባበር በዓል ላይ በመገኘት ንግግር ያሰሙ የነበሩት የመንግስት አካላትም በዛሬው ዕለት በቦታው አልተገኙም አሊያም ተመልሰው ሄደዋል፡፡
መንግስት ለዘጠኝ ወራት ያክል የቆየውን የሙስሊሙን ሕዝብ የተቃውሞ ሂደት ባግባቡ ማስተናገድ ሳይችል በመቅረቱ የተነሳ ሕዝበ ሙስሊሙ ተቆጥቷል፡፡ ፍፁም ሠላማዊነታችን ከአገራችን አልፎ ለዓለም ኅብረተሰብ ይፋ በሆነበት በዚህ አጋጣሚ መንግስት ዳግም ራሱን እንዲፈትሽ እንጠይቃለን፡፡ ጥቂት ሙሰኛና ሐይማኖቱንና ሕዝቡን የማይወክሉ የመጅሊሱ አመራሮች ከመንግስት ጋር እንደመዥገር ተጣብቀው ሲያበቁ የሚያተርፉለት ነገር ቢኖር የህዝብን ቁጣ ይበልጥ መቀስቀስ እና ከሕዝብ ጋር መለያየትን ነው፡፡ እጅግ የሚያስገርመው ነገር ሙስሊሙ በገፍ ወጥቶ ተቃውሞውን እንዲህ እንዲገልጥ ያስገደዱትና ተገቢ ምላሽ ያልተሰጠባቸው ጥያቄዎች በባሕሪያቸውም ሆነ በይዘታቸው ከአገር ሁለንተናዊ ጥቅም አኳያ እጅግ ቀላል እና ቀላል ምላሽ የሚያሻቸው ናቸው፡፡ እነኚህን ጥያቄዎች በአግባቡ ተመልክቶ ከሕዝብ ጎን በመቆም ምላሽ ይሰጥባቸው ዘንድ ሕጋዊ አግባብን በመከተል ይወክሉናል ባልናቸው ወንድሞቻችን አማካይነት ለመንግስት አቀረብን፡፡ የዚህ ሂደት መጨረሻው ከውልደት እስከ ዕድገት በቅርበት የምናውቃቸውን እና ከኛ ይሻላሉ በማለት የወከልናቸውን ወገኖች “አሸባሪ” በማለት እስር ሆነ፡፡ እነሱ በዕስር ላይ ባሉበት ሁኔታ ተቃውሞው በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉ “አሸባሪዎቹ” እነሱ ሳይሆኑ ሰፊው ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡
መንግስት መንግስት ነው፡፡ እንደ መንግስት እና እንደ ሕዝብ ማሰብ ይገባዋል፡፡ ሕዝብ ያቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ባልተሰጠበት ሁኔታ ሠላማዊ እና ሠላማዊ መንገድን ብቻ ተከትሎ ሲያሰማ የቆየውን የተቃውሞ ድምፅ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኢንሻ አላህ፡፡
መልካም የዒድ በዓል፡፡ ዒድ ሙባረክ!

No comments:

Post a Comment