ታድያ ይህንን ሃሳባቸውን ለአንድ ሽማግሌ ጠቢብ ሰው ነግረው ገንዘብ እና ሃሳብ እንዲሰጣቸው ፈለጉ፡፡ ሄደውም አማከሩት፡፡ ያም ሽማግሌ ሃሳባቸውን ሁሉ ከሰማ በኋላ እንዲህ አላቸው፡፡
«ልጆቼ ልክ ናችሁ ሩቅ ሀገር ሄዳችሁ፣ የምትችሉትን ያህል እየሠራችሁ፣ የራሳችሁን ኑሮ በመኖር ችግሩን ሁሉ መርሳት እና መገላገል ትችላላችሁ፡፡ ምን ያስጨንቃችኋል? ቤት ያለው እዚህ ብቻ ነው እንዴ? ግን አንድ ነገር አስቡ፡፡ እንዲህ ማድረጋችሁ ራሳችሁን ብቻ ከችግሩ ታወጣላችሁ እንጂ ችግሩን አትፈቱትም፤ እናንተ ችግሩን ትረሳላችሁ እንጂ ችግሩን አታስወግዱትም፡፡ «ደግሞም የእንጀራ አባታችሁ እናታችሁን የበደለውን ያህል እናንተም ትበድሏታላችሁ፡፡ እስኪ አስቡት ለዚህች ለእናታችሁ ከእናንተ በቀር የደስታዋ ምንጭ ማን ነው? ሁሉም ነገርዋ የሚያሳዝን እና የሚያስመርር ነው፡፡ እናንተ ግን የደስታዋ ምንጮች ናችሁ፡፡ የእንጀራ አባታችሁ እናታችሁን ያሳዝናታል፤ የእናንተ ጥላችኋት መሄድም ያሳዝናታል፤ እርሱ ብቻዋን እንድትለፋ ትቷታል፤ እናንተ ጥላችኋት ስትሄዱም ያለ አጋዥ ትተዋታላችሁ፤ እርሱ በመስረቅና በድደባ አስከፋት፣ እናንተም ችግር ውስጥ ትታችኃት ከጎኗ በመራቅ አሳዘናችኃጽ ታድያ ከእርሱ በምን ተሻላችሁ?
እናንተኮ ያሰባችሁት ለእናታችሁ ሳይሆን ለራሳችሁ ነው፡፡ እናታችሁ ስለተቸገረች አይደለም ያዘናችሁት፣ ችግሩ እናንተን ስለነካ ነው፤ እናታችሁ ስለተራበች አይደለም ያዘናችሁት ረሃቡ ስለነካችሁ ነው፡፡ በእናታችሁ ላይ የደረሰው ችግር ሳይሆን ስለችግሩ ከየሰው አፍ መስማት ነው የሰለቻችሁ፤ ችግሩን ለመቅረፍ አይደለም መሄድ የፈለጋችሁት፤ ችግሩን ላለማየት እና ላለመስማት ነው፡፡
ከዚያ ይልቅ ሥራ ሠርታችሁ ገንዘብ አግኙ እና ለእናታችሁ ምግብ ስጧት፤ የሚያስርባትን የእንጀራ አባታችሁን በዚህ ትቃወሙታላችሁ፣ ልብሷን ቀይሩላት፣ የሚያሳርዛትን አባታችሁን በዚህ ትረቱታላችሁ፣ ስትታመም አሳክሟት፣ የሚያሳምማትን የእንጀራ አባታችሁን በዚህ ትቃወሙታላችሁ፤ የወግ እቃዎቹን ሰብስቡና አስቀምጡላት፤ዝክረ ታሪኳን ሊያጠፋ የተነሣውን የእንጀራ አባታችሁን በዚህ ታወግዙታላችሁ፤ እርሱ እያረጀ ሲሄድ እናንተ ግን እያደጋችሁ ነው፡፡ እንደዚያ ካደረጋችሁ እናንተ የእናታችሁ ልጆች ናችሁ፡፡ ያለ በለዚያ ግን የእንጀራ አባታችሁ ተባባሪዎች ናችሁ፡፡ ሸረሪት ታውቃላችሁ፡፡ ከሰው ቤት ግድግዳ ላይ ድር አድርታ፤ ወልዳ ከብዳ ትኖራለች፡፡ ቤቱ በእሳት ሲያያዝ ግን ከቤቱ ወጥታ ቀድማ የምትሮጥ እርሷ ናት፡፡ ቤቱ የኖርኩበት ነው፡፡ ወግ መዓርግ ያየሁበት ነው፤ እሳቱን በማጥፋት አስተዋጽዎ ማድረግ አለብኝ አትልም፡፡ መሸሽን ብቻ ነው የምትፈልገው፡፡ ለራስዋ ብቻ ነው የምታስበው፡፡ ይህ ከሸረሪትነቷ የመጣ ነው፡፡
እናንተ ግን ሰዎች እንጂ ሸረሪቶች አይደላችሁም፡፡ ታዲያ እንዴት እንደ ሸረሪቷ በክፉ ቀን ትሸሻላችሁ፡፡አዎ በናታችሁ ጉዳይ አያገባንም ልትሉ አትችሉም፡፡ እሳቱን ማጥፋት ትታችሁ ከእሳት ለማምለጥ ብቻ ልትሮጡ አይገባም፡፡ ይህንን ካደረጋችሁ ሸረሪቶች እንጂ ሰዎች አይደላችሁም፡፡»” አሏቸው ይህንን ሰምተው ልጆቹ ወደ እናታቸው ተመለሱ፡፡
አዎ አወሊያን እናቴ ብላት አይበዛባትም፡አሳዳጊ ተንከባካቢ፡ሳትሰስት ፍቅሯን የምትለግስ ውድ እናት ፡፡ታዲያ እማማ አወሊያ ዛሬ በእንጀራ አባት መዳፍ ውስጥ ነች፡፡እኛም ትላንት በመዳፏ የጎረስን፡ጭኖቿን የተንተራስን ልጆቿ የእንጀራ አባት ያደረሰባት በደል እኛንም ነካን ብለን እሷን ጥለን ከእሷ ሸሸተን ፡ርቀን ለመኖር አሰብን፡፡ያቺ እናት ልጆቼ እያለች እየተጣራች እኛ ግን ሰምተን እንዳለሰማን መኮብለል ጀመርን፡፡ታዲያ እኛስ ከእንጀራ አባቷ በምን ተለየን?ዊንጌት አወሊያ አስኮ የሚለው የወያላው ድምፅ አይናፍቃችሁም ? እንደ ልብ የሚያስቦርቀው ሜዳ፡ ካፌው፡ መምህሮቹ፡ ውቡ መስጂድ ፡ዋጋ የማይወጣላቸው የክላስ ጓደኞቻችሁ ትዝ አላሏችሁም ? ያ ውብ መስጊድስ ፡የሸህ ዑመር ምክር ፡የሱለይማ ድምፅ ጆሮአችሁ ላይ አያስተጋባም ? ልጅነት ይናፍቃል ሲባል እሰማ ነበር፡ዛሬ ግን የምር ልጅ በሆንኩ አልኩ፡ቦርሳዬን አንግቤ ወደዛ የእውቀት አውድማ ቤት በሄድኩ፡ግን ምን ዋጋ አለው ? እሱስ ይቀር ምናለ ልጅ ወልጄ በሆነ? ያን ወይነ ጠጅ ዩኒፎርም አልብሼ፡ምሳ እቃ ቋጥሬለት ግንባሩን ስሜ ወደዛ የፍቅር ማሳ በላኩት፡፡ ግና ምን ዋጋ አለው…………………………………….
ቆይ ለስምንተ ወር የለፋንለት ውድ ኮሚቴዎችችንን ከሰዋንለት 3 ጥያቄያችን አንዱ የአወሊያ ጉዳይ አልነበርን ? ከዛሬ በኃላ ጥያቄያችን ሁለት ሊሆን ይሆን ? ይመሰላል ዛሬ ሁላችንም አወሊያን እየሸሸናት ነው፡ትላንት ምዝገባ በወረፋ ነበር፡ዛሬ ግን በልመናም የሚመጣ ጠፋ፡፡
እስኪ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ የዚህች እናታችን አወሊያ ጠላቶች ፍላጎት ምንድን ነው? ያለ ረዳት እንዲትቀር ማድረግ አይደለምን? እናንተም እንተዋት፣ እናቁም፣ እንሽሽ ስትሉ ያለ ረዳት እያስቀራችኋት ነው፡፡ የእነርሱ ፍላጎት አወሊያን ተስፋ ማስቆረጥ አይደለምን? እናንተም ተስፋ ከቆረጣችሁ ተሳካላቸው ማለት ነው፡፡ ልጆችዋን እያስመረሩ ማስኮብለል አይደለምን እቅዳቸው? እናነተም ከኮበለላችሁ ተሳካላቸው ማለት ነው፡፡ ታሪክን፣ክብርን፣ ልዕልናን ማውደም መመዝበር እና ማራከስ አይደለምን አላማቸው ? እናንተም ታሪኩንና ክብሩን ርግፍ አድርጋችሁ ትታችሁ በራሳችሁ ዓለም ብቻ ስትቀሩ የእናንት ፍላጎት ሳይሆን የእነርሱ ፍላጎት ተሳካ ማለት ነው፡፡
ታድያ አሁን እናንተ መመለስ ያለባችሁ አንድ ጥያቄ ነው፡፡ የምትፈልጉት የጠላቶቿ ፍላጎት እንዲሳካ ነው ወይስ በመከራ ውስጥ ያለችውና ቀን የጣላት የእናታችሁ ፍላጎት እንዲሳካ ? ምረጡ፡
No comments:
Post a Comment