ይህ የሪፖርቱ አካል ሙሉ በሙሉ ከአምናው ሪፖርት ላይ ቃል በቃል የተገለበጠ ሲኾን፣ ልዩነቱ የዓረፍተ ነገሮች ቅደም ተከተል መለዋወጡ ብቻ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ድረ ገፅ ላይ የሚገኘው የአምናው (የ2011) የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት እንዲህ ይነበባል:-
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በሳዑዲ የሚረዱ የወሐቢ ቡድኖች በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥ እያሳደሩ ያለው ተጽዕኖ እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ጉባዔው ይህንኑ ወገን በሙስሊሞች እና በክርስቲያኖች መካከል ውጥረትን ያባብሳል በሚል ስጋቱን ገልጿል፡፡ በብዙኃኑ ነባር የሱፊ ሙስሊሞች እና በከፊል በሳዑዲ አረቢያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚደገፉት ሙስሊሞች መካከል ውጥረት ይታይ ነበር፡፡
ሪፖርቱ ‹‹የአሜሪካ መንግሥት፣ የመንግሥት የፀረ አክራሪነት ሥልጠና አተገባበርን ጨምሮ፣ በሃይማኖት ነፃነት ጉዳይ ከ[ኢትዮጵያ] መንግሥት ጋር ተወያይቷል›› ይላል፡፡ በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ‹‹የፀረ አክራሪነት ሥልጠና›› የሚለው ሐረግ ከሐምሌ 2003 ጀምሮ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና መጅሊስ በጋራ ሲያካሂዱ ለከረመሙት የአህባሽ ስልጠና የተሰጠ ገራገር ስያሜ መሆኑ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ጋር ተወያይቻለሁ ቢልም፣ ስለውይይቱ ዝርዝር የተነገረን ነገር የለም፡፡ ‹‹ተወያይቶስ ምን አቋም ያዘ?!›› ብለን ከጠየቅን ግን የዘንድሮው ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት›› ተብዬ በራሱ ብዙ ይነግረናል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የ2011/12 ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት›› በሪፖርቱ ዓመት ውስጥ፣ በተለይ ከታህሳስ ወር 2004 (Dec. 2011) አንስቶ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሙስሊሞች በየሳምንቱ አርብ በአወሊያ ሲያካሂዱት ስለከረሙት ያልተቋረጠ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝበ ሙስሊም የመብት ጥያቄዎቹን ለመንግሥት እንዲያደርሱለት ስለመረጣቸው ኮሚቴዎች፣ ኮሚቴዎቹ የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች ይዘው ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ስላደረጉት ውይይትና ስለተሰጣቸው ምላሽ ምንም የጠቀሰው ነገር የለም፡፡ አንድ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ብቻ የቀሩትን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ አስመልክቶ እጅግ ጥቅል በሆነ መልኩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ እርሱም ከሁለት ዓ/ነገሮች በተዋቀረ አንድ አጭር አንቀፅ የተገደበ ነው፡፡ እንዲህ ይላል:-
"በዓመቱ መንግሥት በሃይማኖት ቡድኖች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ገብቷል የሚሉ ክሶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፣ መንግሥት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራርና እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ ገብቷል የሚሉ ሪፖርቶች እና፣ የተባለው ጣልቃ ገብነት ሕገ መንግሥቱ ለሃይማኖት ነፃነት የሰጠውን ጥበቃ ጥሷል የሚሉ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡"
በሪፖርቱ ዓመት በኦሮሚያ ክልል፣ አሩሲ ዞን፣ አሳሳ ወረዳ ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ስለተፈፀመው ግድያ የአሜሪካ መንግሥት የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት አንድም ነገር ትንፍሽ አለማለቱ ሌላው በአሳዛኝ መልኩ የሚጠቀስ የሪፖርቱ ገጽታ ነው፡፡
እነዚህን ሁኔታዎች ስናስተውል እና ይበልጡንም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የሚወጡትን ዓመታዊ ሪፖርቶች ስናይ በአጠቃላይ የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊ ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት›› የሚያወጣው የሰው ልጆች መሠረታዊ ነፃነት አካል ለሆነው የሃይማኖት ነፃነት በመቆርቆር ነው ብሎ ለማለት አዳጋች ይሆንብናል፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ድረ ገፅ ላይ የሚገኘውን የ2011 ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት›› ስናይ፣ ዓመታዊ ሪፖርቱ እንዲያውም የኢስላምን ገፅታ የማጠልሸት ዓላማ ያለው ሳይሆን አይቀርም ያሰኘናል፡፡ በአምናው ሪፖርት ውስጥ፣ በኢትዮጵያ አንዳንድ ክልሎች በግለሰብ ሙስሊሞች ተፈፅመዋል የተባሉ ጥቃቅን ነገሮች ‹ኢትዮጵያ ውስጥ የአለመቻቻል አባዜ እያቆጠቆጠ ነው› የሚል አንድምታ ባለው መልኩ ተዘርዝረው ተጠቅሰዋል፡፡ ይህም አለመቻቻልን ወይም ጽንፈኝነትን ከኢስላም እና ከሙስሊሞች ጋር በማቆራኘት ዓላማ የተደረገ ይመስላል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ወይም Wikileaks በተሰኘው ድረ ገፅ አማካይነት ይፋ ከተደረጉ የአሜሪካ ኤምባሲ ኦፊሴላዊ ሰነዶች ለማወቅ እንደተቻለው፣ የአሜሪካ መንግሥት ኢስላምን በተለይም የሰለፊ አስተምህሮን የስጋት ምንጭ አድርጎ ይመለከታል፡፡ ስለዚህም የሰለፊ አስተምህሮ እንዳይስፋፋ ጠንክሮ ይሰራል፡፡ ይህን አስተምህሮ ለመዋጋት የመረጠው መንገድ ደግሞ ባህላዊ እስልምናን ማስፋፋት፣ ወይም እንዲስፋፋ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ማድረግ ወይም ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ … አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኦሮሚያ ክልል፣ ባሌ ዞን ውስጥ ለሚገኘው ድሬ ሸኽ ሑሴን የመቃብር ስፍራ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ወሎ ውስጥ ለሚገኘው የጀማ ንጉስ መስጂድ እድሳት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይህንን ያደረገው ግን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ባህላዊ እሴቶች በመንከባከብ ዓላማ አይደለም፡፡ ዊኪሊክስ (Wikileaks) ይፋ ያደረጋቸው የኤምባሲው ሰነዶች እንዳጋለጡት የዚህ ድጋፍ ዓላማ ‹‹የሳዑዲ ባህላዊ ኢምፔሪያሊዝም››ን መዋጋት ነው፡፡
ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸውን ሰነዶች ያዘጋጁት የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ ‹‹የሳዑዲ ባህላዊ ኢምፔሪያሊዝም›› የሚሉት የሰለፊይ አስተምህሮን ነው፡፡ እርሳቸው ‹‹ወሐቢያ››ም ይሉታል፡፡ እናም ‹‹ወሀቢያን›› ለመዋጋት ቦታዎችን፣ ቁሳቁሶችንና ስርዓተ አምልኮዎችን ማዕከል ያደረገ ባህላዊ ቅየዳ (Cultural programming) ሁነኛ መፍትኄ እንደሆነ አምባሳደሩ ያትታሉ፡፡ በሌላ አነጋገር የአምባሳደሩ ስትራቴጂ ባህላዊ እስልምና የሚከተሉ ማኅበረሰቦች ባህላዊ እስልምናቸውን አጥብቀው በመያዝ የ‹‹ወሀቢያን›› ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ መርዳት፣ በዚህም መንገድ የ‹‹ወሀቢያ››ን መስፋፋት መግታት ነው፡፡
ይህ የአሜሪካ ፍላጎት በመሆኑም፣ ምንም ዓይነት ፍጥጫ ባልተፈጠረበት፣ ይልቁኑም መላው ሙስሊም ኅብረተሰብ ‹‹ሱፊ›› እና ‹‹ሰለፊ›› ሳይባባል፣ ከራሱ አልፎ ክርስቲያን ወገኖቹንም ያሳተፈ የአንድነት እና የሰደቃ ፕሮግራሞችን እያካሄደ ያሳለፈውን ዓመት በሚመለከት የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት፣ ‹‹በብዙኃኑ ነባር ሱፊ ሙስሊም እና ‹‹ወሀቢያ›› በሚሰኘው የኢስላም ወገን መካከል ውጥረት ሰፍኖ ነበረ›› ብሎ ማላዘን ለትዕዝብት ይዳርጋል፡፡
በዓምናው ሪፖርት ላይ ‹‹የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሳዑዲ የሚረዱ የወሀቢያ ቡድኖች በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥ እያሳደሩ ያለው ተጽዕኖ እንደሚያሳስበው ገልጿል›› ይል የነበረው ዓ/ነገር ዘንድሮ ‹‹መግለፁን ቀጥሏል›› በሚል እንዳለ ሰፍሯል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹ምክር ቤቱ ይህንኑ ወገን በሙስሊሞች እና በክርስቲያኖች መካከል ውጥረትን ያባብሳል በሚል ወቅሶታል›› የሚለው ዓ/ነገር እንዳለ ከአምናው ተገልብጧል፡፡ እዚህ ላይ በጣም የሚገርመው እኒህ ዓ/ነገሮች ከአምናው ሪፖርት ላይ መገልበጣቸው አይደለም፡፡ ይልቅ የሚገርመው በዚህ ዓመት ህዝበ ሙስሊሙ ለበርካታ ወራት በሥልጣን ላይ ላለው የጠቅላይ ምክር ቤት አመራር እውቅና ነፍጎ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ በማለት እያሰማ ስላለው ጩኸት አንዲት ዓረፍተ ነገር እንኳ አለመጻፉ ነው፡፡ ይህ የሆነው በአጋጣሚ አይደለም፡፡ ጽንፈኝነትን በመዋጋት ሽፋን በኢስላም ላይ በተከፈተው ጦርነት ውስጥ አህባሻዊው መጅሊስ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር በመሆኑ እንጂ፡፡ … በዚህ ጦርነት ውስጥ መንግሥታችን እስካሁን ከሰፊው ህዝበ ሙስሊም ጋር ሳይሆን ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጋር እንደቆመ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ይመስላል እነሆ በዘንድሮው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት›› ላይ መንግሥታችንም የተወሰነ ወሮታ ተከፍሎታል፡፡
“The constitution and other laws and policies protect religious freedom and, in practice, the government generally respected religious freedom; however, some local authorities, acting independently, occasionally infringed on this right. The government did not demonstrate a trend toward either improvement or deterioration in respect for and protection of the right to religious freedom.”
ትርጉም:- ሕገ መንግሥቱ፣ እንዲሁም ሌሎች ሕጎች እና ፖሊሲዎች ለሃይማኖት ነፃነት ጥበቃ ያደርጋሉ፤ በተግባርም መንግሥት በአጠቃላይ የሃይማኖት ነፃነትን አክብሯል፡፡ ሆኖም፣ አልፎ አልፎ አንዳንድ ባለሥልጣናት በራሳቸው የግል ውሳኔ ይህንን መብት ተጋፍተዋል፡፡ በመንግሥት የሃይማኖት ነፃነትን በማክበር፣ እንዲሁም ለሃይማኖት ነፃነት መብት ጥበቃ በማድረግ ረገድ የማሻሻልም ሆነ የማፈግፈግ ዝንባሌ አላሳየም፡፡
በገፅ 3 ላይ ደግሞ ስለ መንግሥታችን ለሕግ ተገዢነት እንዲህ ተብሎ ተመስክሯል፡
“The government generally respected constitutional protections of religious freedom and separation of church and state. However, there were reports of abuses of religious freedom.”
ትርጉም:- በአጠቃላይ መንግሥት የሃይማኖታዊ ነፃነት እና የመንግሥት እና ሃይማኖት መለያየትን ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃዎች አክብሯል፡፡ ነገር ግን የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡
በአምናው ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በ‹‹ወሀቢያ›› ላይ ያቀረበውን ጽንፈኝነትን የማባባስ ክስ በማስከተል እንዲህ የሚል ጽሁፍ ሰፍሮ ነበር፡
አንድ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለሥልጣን እንደተናገሩት፣ አዲሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሕግ፣ የውጭ አገር መያዶችን በመመዝገብና ከውጭ የሚያገኙትን ገቢ ጣሪያ በመወሰን ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎችን በመጠኑም ቢሆን ለመግታት አስችሏል፡፡
ይህ የባለሥልጣኑ መረጃ ‹‹ወሀቢያ›› እና ጽንፈኝነትን ባጣመረ ሀተታ ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ፣ በዘወርዋራ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት አወሊያን ሲያስተዳድር በኖረው International Islamic Relief Organization (IIRO) ላይ የወሰደውን እርምጃ ያመላክታል፡፡ ያንን እርምጃ ተከትሎም ነው አወሊያ በመጅሊሱ ሥር እንዲሆን የተደረገው፡፡ መጅሊሱ ደግሞ ተቋሙን የ‹‹ወሀቢያ›› ማስፋፊያ እያለ በመኮነን የ‹‹አህባሽ›› አስተሳሰብ ማስፋፊያ ሊያደርገው ተንቀሳቀሰ፡፡ የመጀመርያ እርምጃውም 15 የአወሊያ ኮሌጅ መምህራንን፣ የአወሊያ መስጂድ ኢማምን እንዲሁም ለምረቃ ጥቂት ወራት የቀራቸውን የኮሌጁ ተማሪዎች ማሰናበት ነበር፡፡ … ይህ በአህባሻዊ ጀብደኝነት የተወሰደ እርምጃ ግን ዕውን አልሆነም፡፡ ተማሪዎቹ የረሃብ አድማ ጭምር በማድረግ ተቃውሟቸውን አሰሙ፡፡ የእነርሱ ብሶት ለዓመታት የተዳፈነውን የሙስሊሙ ህዝብ ብሶት ቀሰቀሰው፡፡
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ህዝብ አወሊያ ግቢ ተሰብስቦ ‹‹አሽአብ ዩሪድ ኢስቃጠል መጅሊስ!›› [ወጣቱ የመጅሊሱ (አመራር) እንዲወገድ ይሻል!] እያለ ይፎክር ጀመር፡፡ ከአወሊያ ግቢ የተነሳው የህዝብ ቁጣ ከአዲስ አበባ አልፎ በየክልሎችም ተስተጋባ በደሴ፣ በጂማ፣ በአዳማ፣ በኮምቦልቻ፣ በሻሸመኔ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረር ወዘተ. ‹‹አሽአብ ዩሪድ ኢስቃጠል መጅሊስ!›› ተብሎ ተጩኋል፣ እየተጮኸም ነው፡፡ ይህንን የህዝብ ጩኸት አሜሪካ ‹‹አልሰማሁም›› እያለች ነው ከዘንድሮው ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርት›› እንደተረዳነው፡፡ …
… መንግሥት ግን በሰላማዊ መንገድ ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች ያውቃቸዋል፡፡ ጥያቄዎቻችን ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ መንግሥት ጥያቄዎቻችንን ለመጠምዘዝ አልያም የጥቂቶች ብቻ ለማድረግ ሞክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን በዕለተ ዒድ አል ፊጥር በየከተሞቻችን አደባባይ በነቂስ ወጥተን ጥያቄዎቹ የመላው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች መሆናቸውን ጩኸን አሰምተነዋል፤ አሳይተነዋል፡፡ አሁን ከመንግሥት የምንጠብቀው ለጥያቄዎቻችን ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ህዝባዊነቱን እንዲያሳየን ብቻ ነው፡፡ አላህ ደግ ነገር ያሰማን አሚን፡፡
* * * * * * *
የ2010 እና የ2011 የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርቶችን ቅጂ ለማግኘት የሚከተለውን ድረ ገጽ ይመልከቱ፡
http://ethiopia.usembassy.gov/
No comments:
Post a Comment