Radio Bilal August 25, 2012 ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 19/2004
- በኢድ ሰላት ታስረው የተፈቱት ምዕመናን ፍረድ ቤት እንደሚቀርቡ ተጠቆመ
- ነሀሴ 21 ሊካሄድ የነበረው የመጅሊስ ምርጫ መራዘሙ እየተነገረ ነው
- ታዋቂ ሰዎችና አምባሳደሮች በጠ/ሚ መሞት ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛሉ
- የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የዋስ መብት በመከልከል መታሰሩ ተጠቆመ
በኢድ ሰላት ታስረው የተፈቱት ምዕመናን ፍረድ ቤት
እንደሚቀርቡ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 19/2004
ባሳለፍነው የኢድ ሰላት ወቅት ታስረው የተፈቱት ሙስሊም
ምዕመናን መካከል ግማሾቹ የፊታችን ሰኞ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ምንጮቻችን ጠቆሙ፡፡
ለምዕመናኑ መታሰር በምክንያትነት የቀረበባቸው የታሰሩት
ይፈቱ ፣ድምፃችን ይሰማ ፣ምርጫችን በመስጅዳችን እንዲሁም ሌሎች በበራሪ ወረቀቶችን እና መፈክሮችን በመያዛቸው እንደሆነ ይታወሳል፡፡ወረቀቶቹን
ይዘው በመገኘታቸው ህዝብ በማሸበር ተግባር ተሰማርታችኋል ተብለዋል፡፡ይህንንም ተከትሎ በእስራት ወቅት ኒቃብ የለበሱ ሴቶችን ለፎቶና
ቪዲዮ ቀረፃ መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡
የታሰሩትም ምዕመናን ተለቀው የፍርድ ሂደታቸውን በውጪ እንዲከታተሉ
መደረጋቸውን አብራርተዋል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የህግ ባለሙያ በምንም መልኩ ለክስ ምስረታ አይዳርግም ባይ
ናቸው፡፡ እንደ ህግ ባለሙያው ገለፃ ግለሰቦች በወቅቱ የአምልኮ ተግባራቸውን አከናውነው የመብት ጥያቄ ነው የጠየቁት እንጂ ጉዳዩ
በምንም አይነት መልኩ ከሽብር ተግባር ጋር እንደማይያያዝ አስረድተዋል፡፡
ነሀሴ 21 ሊካሄድ የነበረው የመጅሊስ ምርጫ መራዘሙ እየተነገረ ነው
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 19/2004
ከነሐሴ 21 እስከ መስከረም 5 እንደሚካሄድ
በተለያዩ ሚዲያዎች ተገልፆ የነበረው የመጅሊስ ምርጫ መራዘሙ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ይሄው የመጅሊስ ምርጫ መራዘም የክቡር
ጠ/ሚ ህልፈትና የሰሞኑ የህዝበ ሙስሊሙ ሠላማዊ ተቃውሞ ተከትሎ እንደሆነ ተሰምቷ፡፡ከነሐሴ 21 እስከ መስከረም 5 ሊካሄድ የነበረው
የመጅሊስ ምርጫ መስከረም 21 ሊካሄድ እንደሚችል መረጃዎች እየገለፁ
ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ ምንጮች የመጅሊሱ ምርጫ ለመስከረም 21 እና 25 እንደተራዘመ ቢገልፁም ከመጅሊስም ሆነ ከዑለማ ም/ቤት የተገለፀ
ነገር የለም ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የመጅሊስና የኡለማ ም/ቤት የሥራ ሀላፊዎችን ለማነጋገር
ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ታዋቂ ሰዎችና አምባሳደሮች በጠ/ሚ መሞት ሀዘናቸውን
እየገለፁ ይገኛሉ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 19/2004
የጠ/ሚ መለስ
ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎ ታዋቂ ሰዎችና አምባሳደሮች ብሄራዊ ቤተ መንግስት በመገኘት ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ከሀገሪቷ የተለያዩ
ከተሞችና ከውጭ ሀገራት በመምጣት የጠ/ሚ አስክሬን የሚገኝበት ብሄራዊ ቤተ መንግስት ሀዘናቸውን በሚገልፁ ሰዎች እየተጨናነቀ እንደሆነ ተገልፆዋል፡፡
የጠ/ሚ የቀብር
ስነ-ስርዓት ነሐሴ 27 እንደሚፈፀም የቀብር አስፈፃሚ ኮሚቴ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች
በቀበሌዎች አካባቢ ድንኳኖች ተጥለው ህዝቡ የተሰማውን ሀዘን እንዲገልፅ የሀዘን መግለጫ መዝገብ መዘጋጀቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጠ/ሚ መሞት የተለያዩ የአፍካ መሪዎችም በአንባሳደሮቻቸውና በሚዲያውች ሀዘናቸውን እየገለፁ
እንደሚገኙ ምንጮች አመልክተዋል፡፡ቀደም ሲል የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነረ፣የላይቤሪያ ፣የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንቶችና የኬንያው ጠቅላይ/ሚ
መሞት ማዘናቸውን እና አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የዋስ መብት በመከልከል መታሰሩ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 19/2004
ባለፈው ሐሙስ
ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በተከፈቱበት አራት ክሶች የዋስ መብት ተከልክሎ መታሰሩ ተገለጸ፡፡በዚሁ
ችሎት ባልታደሰ ንግድ ፍቃድ ተከሰው ጉዳያቸው በክትትል ላይ የሚገኙት የኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ባለቤት እና የዜድ ፕሬስ ሥራ አስኪያጅ
በፍትህ ሚኒስቴር ክሱ እንዲቋረጥ መታዘዙ ተነግሯል፡፡
ሐሙስ ነሐሴ
17 የፌደራ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ምድብ ችሎት የቀረበው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ሶስት ክሶች
ሲከፈቱ አንዱ ማስተዋል ፕሮሞሽን በተሰኘው ድርጅቱ ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የተከፈተው ክስ
በጋዜጣው ላይ በወጡ ፅሁፎች እንደሆነ ታውቋል፡፡
አቃቢ ህግ
ያቀረባቸው ክሶች ለአመፅ የሚያነሳሱ ፅሁፎች እንደሆኑ በማስረዳት ግለሰቡ ቋሚ አድራሻ እንደሌላቸውና የክሱን ክብደት በመጥቀስ የዋስ
መብቱ እንዲከለከል ጠይቋል፡፡
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጠበቃም በበኩላቸው የደንበኛቸው የዋስ መብት እንዲከበርለት
ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ በግለሰቡ ላይ የቀረቡት ክሶች ተደራራቢ በመሆናቸው ወደ ማረሚያ ቤት ወርደው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ለነሐሴ
28 ቀጠሮ መሰጠቱ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል
በዚሁ ችሎት ባልታደሰ የንግድ ፍቃድ ወንጀል ተከሰው ክስ የቀረበባቸው የኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳምሶን ማሞና ባለቤታቸው
የዜድ ፕሬስ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዘውድነሽ ክሳቸው እንዲቋረጥ በፍትህ ሚኒስቴር መታዘዙን ተናግሯል፡፡
ፍትህ ሚኒስቴርም በተከሳሾቹ ላይ የሚያጣራው ጉዳይ ስላለ ክሱ እንዲቋረጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ
ለዳኛው ቢሰጥም ፍትህ ሚኒስቴር ክስ ማንሳቱን ለፍርድ ቤቱ እስኪያረጋግጥ በተለዋጭ ቀጠሮ የዋስ መብታቸው እንደተጠበቀ ለማወቅ ተችሏል፡፡ቀደም
ሲል ሁለቱም ተከሳሾች ታስረው መፈታታቸው አይዘነጋም፡፡
No comments:
Post a Comment