- የአየር ጤና አንሷር መስጅድ ኮሚቴ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ሕንፃ ለአገልግሎት ተዘጋጀ
- በሚዛን ተፈሪ ስምንት ሙስሊም ግለሰቦች መታሰራቸው ተጠቆመ
- በሻሸመኔ ወረዳ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በመጅሊስ ምርጫ እንዲሳተፍ እየተገደደ እንደሆነ ነዋሪዎች ጠቆሙ
- ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ተጠባባቂ ሚኒስትሩ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ትኩረት እንዲሰጡ ጠየቁ
የአየር ጤና አንሷር መስጅድ ኮሚቴ በ10 ሚሊዮን ብር
ወጪ ያስገነባው ሕንፃ ለአገልግሎት ተዘጋጀ
አዲስ አበባ
ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 20/2004
የአየር ጤና አንሷር መስጅድ አስተዳደር 10 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ያሰራው ባለ አራት
ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ የግንባታው ስራ መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡አንድ የመስጅዱ አስተዳደር ኮሚቴ አባል ለሬድዮ ቢላል እንደገለፁት ላለፉት
ሶስት አመታት የግንባታ ሥራው ሲካሄድ የቆየው ሕንፃ በመስጅዱ የፊት ለፊት መግብያ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራው
ተጠናቆ ለአገልግሎት ተዘጋጅቷል፡፡
ለሕንፃው ግንባታ የአካባቢው የጀምዓ አባላትና አህለል ኸይራት
ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው በተለያየ ጊዜ ኢስላማዊ መፅሀፍትን አዘጋጅቶ በማሳተም ከሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለሕንፃው ግንባታ ሥራ እንዲውል
የጀምዓው ዓሊሞች የበኩላቸውን እገዛ መስጠታቸውንም የኮሚቴው አባል አስረድተዋል፡፡
ይኸው ባለ አራት ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ ለአካባቢው ማህበረሰብ የህክምና
አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ይህም ሙስሊሙ ማህበረሰብ በአካባቢና አገር ልማት ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆኑን
የሚያረጋግጥበት አንዱ ማሳያ ነው ያሉት የኮሚቴው አባል የሕክምና ተቋሙ ሥራ ሲጀምር ኃይማኖት ሳይለይ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች
በተመጣጠኝ የአገልግሎት ክፍያ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሌሎች መስጅዶችም
በመሰል የማህበራዊ ተቋማት ግንባታ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የህክምና እጥረትና ጥበት ለማቃለል መንግስት እያደረገ
ያለውን ጥረት በማገዝ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የአካባቢው አስተዳደር አካላትና የመሬት አስተዳደር አመራሮች
ለህንፃው ግንባታ እውን መሆን ቀና ትብብር ማድረጋቸውንም የኮሚቴው አባል ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
በሚዛን ተፈሪ ስምንት ሙስሊም ግለሰቦች መታሰራቸው
ተጠቆመ
አዲስ አበባ
ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 20/2004
በደቡብ ክልል የሚዛን ተፈሪ ከተማ ስምንት የሚደርሱ ሙስሊም ግለሰቦች የረመዷን
ፆም አገባደው ወደ መጡበት ለመመለስ ሲንቀሳቀሱ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው ምንጫችን ገልፀዋል፡፡ ለእስራታቸውም
ግልፅ የሆነ ምክንያት ከመንግስት አካላት ባይቀመጥም በአዲስ አበባ እና በደሴ ከተከሰተው ወቅታዊ የህዝበ ሙስሊሙ ጉዳይ ጋር ተዛማጅነት
ሳይኖረው እንደማይቀር አስረድተዋል፡፡ እንደ ምንጮቻችን ገለፃ የታሰሩት ምዕመናን ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዳልተጠበቀላቸው
አብራርተዋል፡፡
ይህ በንእንዲህ እንዳለ የመጀሊስ አመራሮች ምርጫን በተመለከተ የመንግስት አካላት ጺማቸውን ያሰደጉ እና ሱሪያቸውን
ያሳጠሩ ምዕመናን በስብሰባ ወቅት ለሚያቀርቡት ጥያቄዎች አይመለከታችሁም የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
በሻሸመኔ ወረዳ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በመጅሊስ ምርጫ
እንዲሳተፍ እየተገደደ እንደሆነ ነዋሪዎች ጠቆሙ
አዲስ አበባ
ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 20/2004
በሻሸመኔ ወረዳ የአባሮ ቀበሌ ሙስሊም ህብረተሰብ በመጅሊስ ምርጫ
ላይ እንዲሳተፉ በመንግስት አካላት እየተገደዱ እንደሆነ ነዋሪዎች
አመለከቱ፡፡ የቀበሌው ሙስሊም ነዋሪዎች በበኩላቸው የታሰሩት ኮሚቴዎች ሳይፈቱ በምርጫ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል፡፡ የመንግስት
አካላትም በበኩላቸው የታሰሩት ግለሰቦች ሁከት በመፍጠራቸው ነው በማለት ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡
ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ተጠባባቂ ሚኒስትሩ ለሰብዓዊ
መብቶች መከበር ትኩረት እንዲሰጡ ጠየቁ
አዲስ አበባ
ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 20/2004
ፕሬዝደንት ባራክ
ኦባማ የኢፌድሪ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሰብዓዊ መብቶችና ለቀጠናው ሰላምና ደህንነት የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩ
ጠየቁ፡፡ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የተተኩት ተጠባባቂ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝን በስልክ ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ
በሀገራቸው ስም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የሚገልፅ መግለጫ በፕሬዝዳንቱ በኩል አስተላልፈዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ነሐሴ
27 በሚፈፀመው የጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ስርዓተ-ቀብር ላይ የበርካታ ሀገራት መሪዎች እንደሚገኙ አዲስ ዘመን ዘግቧል፡፡
No comments:
Post a Comment