Monday, August 27, 2012

Radio Bilal August 27, 2012 ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 21/2004


Radio Bilal August 27, 2012 ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 21/2004

  • ዛሬ ይጀመራል የተባለው የመጅሊስ ምርጫ መራዘሙ ተገለጸ
  • በማልታ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ቢላል ኮሚኒኬሽንና ዓለም  አቀፍ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ም/ቤትን ለመደገፍ ቃል መግባታቸው ተገለጸ
  • አወሊያ ኮሌጅ ግልፅ ባልሆነ ምክኒያት ምዝገባ እንዳልተጀመረ ተጠቆመ
  • በደሴ በተከሰት ግርግር ላይ የታሰሩ ምዕመናን ነገ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተገለፀ
ዛሬ ይጀመራል የተባለው የመጅሊስ ምርጫ መራዘሙ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 21/2004
በኡለማዎች ምክር ቤት አስፈፃሚነት ዛሬ ሐምሌ 21 ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የመጅሊስ የወረዳ ምርጫ መራዘሙ ተጠቆመ፡፡
ቀደም ሲል በኡለማ ምክር ቤት ለዛሬ ሐምሌ 21 የወረዳ አመራሮች ምርጫ እንደሚካሄድ መገለፁ ይታወሳል ፡፡ይሁን እንጂ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መሞትን ተከትሎ ህብረተሰቡ ሀዘኑን እየገለፀ በመሆኑና የቀብር ስነ ስርዓቱ እስኪፈፀም ምርጫው እንደተራዘመ ተነግሯል፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችም መጅሊሱና የኡለማ ምክር ቤቱ ምርጫውን ለማራዘም የተገደዱት በጠ/ሚኒስትር ሀዘን ሳይሆን ሙስሊሙ ህብረተሰብ ባደረሰባቸው ጫና ነው ብለዋል፡፡

በማልታ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ቢላል ኮሚኒኬሽንና ዓለም  አቀፍ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ም/ቤትን ለመደገፍ ቃል መግባታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 21/2004
በማልታ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች  በትላንትናው ዕለት ከቢላል ኮሚኒኬሽን የበላይ ጠባቂ ከአቶ መሐመድ ሐሰን ጋር የስራ ስብሰባ ካካሄዱና በአገራችን ስለሚገኘው ተጨባጭ ሁሜታ እንዲሁም የሚዲያና የመደራጀት አስፈላጊነት ላይ ከተወያዩ በኋላ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት፡፡
          በስብሰባ ላይ ስለ ቢላል ኮሚኒኬሽን የስራ ዘርፎችና በቅርቡም ተመርቆ ስለሚከፈተው አለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ም/ቤት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማካሄዱ ተገልፆዋል፡፡
የማልታ ኢትዮጵያዊያን ሙስሞች ቢላል ኮሚኒኬሽንንም ሆነ ዓለም አቀፍ ም/ቤቱን ለመርዳት በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ሰፊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አወሊያ ኮሌጅ ግልፅ ባልሆነ ምክኒያት ምዝገባ እንዳልተጀመረ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 21/2004
የአወሊያ ኮሌጅ ግልፅ ባልሆነ ምክኒያት እስከ አሁን ምዝገባ እንዳልተጀመረ ተገለፀ፡፡ ሐምሌ 6/2004 ምሽት በፀጥታ ሐይሎች በአወሊያ መስጂድ ተወስዶ በነበረው እርምጃ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ግቢው ተዘግቶ እንደነበርም ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ምንጮች አክለው እንደገለጹት የኮሌጁ የደረጃ 1,2,3,4 ፈቃድ ከመንግስት ተሰጥቶታል፡፡የኮሌጅ ምዝገባም በቅርቡ ሊጀመር እንደሚችል የሚመለከታቸው የመጅሊስ ህዝብ ግንኙነት የአወሊያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰዒድ አስማረ አስታውቀዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ ይህን ቢሉም የኮሌጁ ይሁን የመደበኛ ትምህርቱ ስለመቀጠሉ ተጨባጭ ዋስትና እንደሌለው ነው አንዳንድ የኮሌጁ ሰራተኞች የሚገልፁት

በደሴ በተከሰት ግርግር ላይ የታሰሩ ምዕመናን ነገ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተገለፀ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ነሐሴ 21/2004
በደሴ በተከሰተው ግርግር ላይ የታሰሩ 12 ሰዎች በነገው ዕለት ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተገለፀ፡፡በደሴ አረብ ገንዳ መስጂድ በተፈጠረው ግርግር በርካታ ምዕመናን መታሰራቸውና በግርግሩ አዛውንትና ሴቶች ድብደባ እንደደረሰባቸው መገለፁ አይዘነጋም ፡፡በግርግሩ ማግስትም በርካታ የመስጂዱ ኢማሞችና ዳዒዎች ከቤታቸው እየታፈኑ ወደ ማረሚያ ቤት መወሰዳቸው ተጠቁሟል፡፡ ለእስር ከተዳደረጉት በርካታ ኢማሞችና ዳዒዎች መካከል 12ቱ በነገው እለት ለፍርድ እንደሚቀርቡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለሬዲዮ ቢላል ገልጸዋል፡፡ በደሴ አረብ ገንዳ መስጂድ ተካሂዶ የነበረውን ሰላማዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment