Monday, August 27, 2012

ድልን የምንፈልጋት በኛ ጥንካሬ ውስጥ እንጂ በጠላቶቻችን ድክመት ውስጥ አይደለም

ድልን የምንፈልጋት በኛ ጥንካሬ ውስጥ እንጂ በጠላቶቻችን ድክመት ውስጥ አይደለም
አላህ (ሱ.ወ) ይህችን አለም የፈጠረው የሰውን ልጅ ለመፈተን መሆኑን እናውቃለን፡፡ አንዳንዴ መልካም ነገሮችን በመዋል ሲፈትነን ሌላ ግዜ ደግሞ በችግርና በመከራ ይፈትነናል፡፡ ትክክለኛ እምነትና ፅናት ላላቸው ግን ለእያንዳንዷ ችግር መውጫ ቀዳዳ ተበጅቶላታል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የእምንት ጥንካሬያችን እና ፅናታችን የሚፈተንበት ግዜያዊ ፈተና ከወደቀብን አመት ሊሞላን ነው፡፡ ግዜው አመት መሙላቱ በአንድ በኩል የፈተናችን ግዜ በአጭር አለመቀጨቱን ሲያመላክተን በሌላ በኩል ደግሞ በተደቀነብን ፈተና ሳንሸነፍ ለአመት መፅናታችንን ያሳያል፡፡ ካሉት ነባራዊ ኩነቶች አንፃር የሁለተኛው መላምት ይበልጥ ለእውነት የቀረበ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እኛ እንደወደቀብን የተረዳነው ፈተና የትልቁ ፈተና መገለጫ ብቻ እንጂ የፈተናው የመጨረሻ ጫፍ አይደለም፡፡ የመጨረሻው ጫፍማ አላህና ያሴሩብን ጠላቶቻችን ያውቁታል፡፡ እኛና እናንተም ቢሆን ሳንረዳው አልቀረንም፡፡ የሆነ ሆኖ ሁለ ነገራችንን እርግፍ አድርገን ጥለን ምንም ተሞክሮ ሳይኖረን ከተኛንበት የአመታት እንቅልፍ ድንገት በመባነን ያደረግነው መንፈራገጥ ለመቆም እያገዘን እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በዘመናችን ከሚገኙ ከየትኛውም አለም ሙስሊሞች ልዩ የሆነ ውብ ባህሪ እንዳላቸው እኛው ምስክር ሁነናል፡፡ የድንበር፤ የፖለቲካ፤ የስልጣን፤ የጎሳ፤ የንብረት---እና ሌሎች አለማዊ አጀንዳዎች ያልተቀላቀሉበት ዲንንና ዲንን የመጠበቅ አላማ ብቻ አንግበው በፅናት የሚታገሉ ተስፋ የሚጣልባቸው መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡ በዚህ የእውነት መንገድ ላይም ቀላል የማይባሉ ህይወታቸውን ሰጡ፤ ሺዎች ለእስር እና ግርፋት ተዳረጉ፤ ሺዎች ለከፋ እንግልትና ድብደባ ተዳረጉ፤ ሚሊዮኖች በእድሜአቸው አይተውት ለማያውቁት ጭንቀት ተዳረጉ፡፡ ግና ዛሬም ፅናት ድንቅ መለያ ባህሪያቸው እንደሆነ ነው፡፡ ድል ማድረግም ለነርሱ የተገባ ሃቅ መሆኑን በተጨባጭ እያስመሰከሩ ነው፡፡ ፈሊላሂል ሃምድ!!!
ያለነው በአላህ ዲን ላይ ነው፤ የተሳሰርነው በአላህ ገመድ ነው፤ የቆምነው አላህ ባዘዘን መንገድ ላይ ነው፤ የምንታገለውም አላህ ለደነገገልን አላማ ነው፡፡ የነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ ከአላህ የሆነ ሃይልና ብርታት እንዲሁም ብልሃትና ፅናት እንድናገኝ አድርጎናል፡፡ ሱመ አልሃምዱሊላህ!!! በአላህ እገዛ ያገኘነውን ብርታት እንደዋዛ ልንቆጥረው አይገባም፡፡ ቀጣይ ድልም በዚያ ውስጥ እንደሚኖር ለአፍታም መዘንጋት የለብንም፡፡ ይህን የብርታት ስሜታችንን ከግትርነት፤ ከሃይል ተጠቃሚነት፤ ከጉልበተኝነት ጋር አንድ አድርገው የሚገነዘቡ ካሉ ተሳስተዋል፡፡ ጥያቄን ግልፅ በሆነ መንገድ ማስቀመጥ፤ ትክክለኛ ሃሳብን በመግለፅ የሚመጣ ተቃውሞን ለመቋቋም ዝግጁ መሆን፤ በሂደት ውስጥ ስህተት መስራትን አለመፍራት (ቢሰራ እንኳን ለማረምና ከስህተት ለመማር መዘጋጀት)፤ በአስቸጋሪ ሁነቴዎች ውስጥ መፍትሄዎችን ማሰብ ቅንጣት ታህል ጉልበተኝነት የሌለበት ድንቅ ብርታት ነው፡፡ ቀጣይ ድላችንንም ይህን የመሰለው ብርታታችን ሊወልደው እንደሚል ተስፋ አለን፡፡
በትግል ሂደት ላይ ትግሉን የሚረታ እና በትግሉ የሚረታ መኖሩ ግድ ነው፡፡ እኛ የጀመርነው ትግል ቁሳዊ እና የሃይል ባለመሆኑ የአሸናፊነታችን መገለጫም በቁስ እና በሃይል ሚዛን የሚለካ አይደለም፡፡ የተከፈተብን ጦርነት የስነ ልቦና፤ አንድነትን የመፈረካከስ፤ በዲናችን እንድናፍር የማድረግ በመሆኑ በብርታታችንም የተቀናቃኝ ወገንን ስነ ልቦና የማንኮታኮት፤ ጥላቻ ያስተሳሰረውን አንድነታቸውን የመፈረካከስ፤ እኩይ አላማና ሴራ ያንጠራራውን አንገታቸውን ማስጎንበስ በቁስ የማይለካ ግን ደግሞ ወደር የማይገኝለት ድል ነው፡፡ በትግሉ ሂደት ተቀናቃኞቻችን የተዳከሙባቸው በርካታ ሁኔታዎችን ብናይም ቀጣይ ድላችንን ግን የምንፈልጋት በኛ ብርታት ውስጥ ነው፡፡ በነፈሱበት ሳንነፍስ በአላማችን ፀንተን ብርታታችን ካጠነከርን የሚደገስልን ሴራ ፈፅሞ ሊበግረን አይችልም፡፡ እስኪ እነዛ በወታደር እንደተከበቡ ሳለ በመቶ ሺዎች ተክቢራ የደመቁ የአንዋር መስጂድ ውሎዎቻችን ይመስክሩ፤ እስኪ በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የተቃውሞ ትእይንቶች እድል ይሰጣቸውና የብርታታቸውን መጠን ያካፍሉን፤ እስኪ በመላው አለም የሚገኙ ወገኖቻችን ቁርጠኝነታቸው ወደር የለሽ መሆኑን ይንገሩን፤ ከምንም በላይ ደግሞ እልፍ ሆነን፤ ባማረ አንድነትና ህብረት፤ ኢስላማዊ ውበትና ጥንካሬ እንዲሁም ለማሰብ እንኳን በሚከብድ ጀግንነትና ቅንጅት ያደረግነው ለሃገራችን ብቸኛው ሰለማዊ ግን ደግሞ ብርቱ የድምፃችን ይሰማ ጥሪ የተስተጋባበት የዒድ አደባባይ ውሎውን ያካፍለን፡፡ ይህ ታዲያ የኛ ብርታት ውጤት እንጂ የተቀናቃኞቻችን ድክመት አይደለም፡፡ የነገው ጉዟችንም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በያዝነው አላማም ሆነ ባለን ፅናትና አንድነት ከነርሱ እንሻላለን፡፡ እኛ የተነሳነው የሚሊዮኖች ንፁሃን ሙስሊሞችን ድምፅ ለማሰማት እና ሊደርስ የሚችለውን መከራ ለማስወገድ ነው፡፡ ዛሬ አርቆ ማሰብ በጎደለው ጭፍንነት ሊያጠፉን የሚቻኮሉ ሰዎችን እያየን ነው፡፡ ልብ ሊሉ የሚገባው ነገር ግን ነገ ይፀፀቱበታል፡፡
አላህ በተከበረው ቃሉ እንደነገረን ለአማኞች ከጭንቅ በኋላ ፈረጃ እንደሚያደርግ ነግሮናል፡፡ በተጨማሪም መሰረታዊ ሃይማኖታዊ መርሆዎችን በመረዳት፤ ለአብነትም፡- መመካትን በአላህ ላይ ማድረግ፤ የቀደርን ምንነት መረዳት ሁሉንም ጭንቆች ያስወግዳል፤ የችግር፤ የስቃይ እና የጫና ሰበቦችን ያመክናል፡፡ ይህን ደግሞ በአይናችን ማየታችን የማይቀር ነው፡፡

No comments:

Post a Comment