Wednesday, September 12, 2012

ድምፃችን ይሰማ · 14,655 like this
9 hours ago ·
“ከአማኞች በእርሱ ላይ ለአላህ ቃል ኪዳን የገቡበትን በእውነት የፈጸሙ ወንዶች አሉ….”
ቁርዓን (ምዕራፍ 33፡23)
በታሰሩ ወንድሞቻችን ላይ የሚፈፀመው የህግ ጥሰት ተቀባይነት የለውም!!
በመንግስት ስም የተደራጁ ቡድኖች እየፈፀሙት ያለው ህገወጥ ተግባር በአስቸኳይ ይቁም!!
ኢስላማዊ ታሪካችን ታሪክ በወርቃማ ብዕሩ እጅግ በጣም ብዙ ትርክቶችን በከተበላቸው ጀግኖች ገድል ያበበ ነው፡፡ የሰውልጅ ሊሰራቸው የከበዱ የሚመስሉ ስራዎችን በሰሩና በሚገርም ፅናት ከሀሰት ፊት በቆሙ ልጆቹ አኩሪ ታሪክ የደመቀ ታላቅ ሃይማኖት ነው፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብም ጌታቸው ጋር የገቡትን ቃል በእውነት በሚፈፅሙ፤ለህዝባቸውም የገቡትን ቃል በማያጓድሉ የመጨረሻውን (የፍርዱን) ቀን የሚናፍቁ የጌታቸውን ውዴታ በሚሹ ከቅርቢቱ ህይወት አኼራን በመረጡ ወንዶች ታሪክ የተሞላ ነው፡፡
ከፍጡሩ ሁሉ ካላቃቸው ከታላቁ የአላህ መላእክተኛ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ጀምሮ ብልቷን በእሳት በጋለ ጦር እየወጓት በፅናት ከጌታዋ ጋር ከተገናኘችው ሱመያ (ረድየሏሁ ዐንሃ) አልፎ በአሐዱን አሐድ ድምፁ የነኡመያን ልብ ያሰነፈ የቁረይሽ አለቆችን በትዕቢት የተወጠረ ማንነት ባለመቻል ያስቃተተ የኛው ኢትዮጵያዊው ቢላሉል ሐበሽን (ረድየሏሁ ዓንሁ) ጨምሮ ከዛም እየሰለሱ………በማያልቀው ዝክር ውስጥ መንጎድ ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዛሬ ላይም ባነሱት የመብት ጥያቄ ምክንያት እየደረሰባቸው ያለው የመብት ጥሰት ገደቡን አልፎ እየፈሰሰ ነው፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ጩኸቶች ተበራክተዋል፡፡ በአሳሳ ወንድሞቻችን በየትኛውም መልኩ ለመቀበል በሚከብድ ሁኔታ ድንጋይ ወረወራችሁ በሚል ተልካሻ ምክንያት ግንባራቸው በፖሊስ ጥይት ተመቶ ወደ አኼራ ከጌታቸው ጋር ሊገናኙ የዚህችን በግፍ የተሞላች ዓለም መጋረጃ አወረዱ፡፡ በአወሊያ መስጊድ የህዝብን ደህንነት እነዲጠብቁ ሀገራዊ ግዴታና ሞራላዊ አደራ የተሸከመው የሀገሪቱ የፖሊስና የፌደራል ወታደራዊ ሃይላት ጨለማን ተገን አድርገው በወሰዱት የሃይል እርምጃና በፈጸሙት አሰቃቂ ድብደባ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ እህትና ወንድሞቻችን ላይ ከባድ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ሲያደርስ ጥቂት የማይባሉትም አካለ-ስንኩላን ሆነው የቀሩበት ተጨባጭ ተፈጥሯል፡፡ የ 60 ዓመት ባልቴት ሳይቀር ሰደቃው ላይ ቀን ተሳትፈሽ አይተንሻል በሚል ደብድበዋል፡፡ በተከበረው የአላህ ቤት ላይ የተጠለሉ ምእምናንን በር ሰብረው በመግባት የመስጅዱን ክብር ደፍረዋል ፡፡ ምእመናኑን በአስለቃሽ ጭስ እራሳቸውን ስተው እንዲወድቁ በማድረግ ኢፍትሃዊ ድርጊት ፈፅመውባቸዋል፡፡ በድብደባው ሰዓት የመስጂዱ ጣራ ላይ ተደብቀው ያመለጡ 6 የአይን ምስክሮች ሰዉን ሁሉ ደብድበው ጨርሰው አለመርካት ይታይባቸው የነበሩ ወታደሮች የመስጊዱን የመስኮትና የበር መስታወቶች በእግራቸው እየመቱ ይሰባብሩት እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለሙስሊሙና ለሃይማኖቱ ያላቸውን የውስጥ ጥላቻና ንቀት ለመወጣት ሞክረዋል፡፡ በቄራ መስጅድ ውስጥ በተፈጸመ ድብደባም የአይን ብሌናቸው የፈሰሰ እስከዛሬ ካልጋ መውረድ ያልቻሉ ብዙ ጉዳተኞችን አፍርተናል፡፡
በታላቁ አንዋር መስጊድም በተመሳሳይ “ አላህን ብቻ ነው የምንፈራው ስትሉ አልነበር ? ጀግናዎቹ! እሰኪ አሁን አለመፍራታችሁን ታሳዩናላችሁ!” እያሉ በስላቅ የእምነት መብታችን ላይ ግፍ ፈፅመውብናል፡፡ በደሴ የ80 ዓመት ኢማምን ከማሰር ጀምሮ ሁሉንም ዓይነት የመብት ጥሰት ያለማን አለብኝነት ፈፅመውብናል፡፡ ለዚህም ተግባራቸው በደሴ ያሉ ክርስቲያን የፖሊስ አባላትን ባለማመን ለግፍ ተግባራቸው ከጎጃም አካባቢ ስለጉዳዩ ምንም መረጃ የሌላቸውን ፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶች በማስመጣት ዋይታዎቻችንን አብዝተውታል፡፡
ዛሬም መሰል ድርጊቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ከምሰራቅ እሰከምዕራብ ከደቡብ እሰከ ሰሜን በማን አለብኝነት በየቀኑ እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ሙስሊሙ እንደባእድ በሀገሪቱ በደህንነት ያለስጋት የመኖር የዋስትና መብቱን ተነፍጎ የጥቃት ሰለባ እየሆነ ይገኛል፡፡የመስጅድ ኢማም እየተጠራ ለሊት ስግደት ላይ ምን እያልካቸው ነው የምታስለቅሳቸው ተብሎ የሚጠየቅበት፤ ለመስጊድ መጠገኛ የሚዋጣ ገንዘብ ወንጀል ሆኖ የሚያሳስርበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ፡፡ መብት በጠራራ ፀሀይ የሚነጠቅበት ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ሙስሊሙ የህግ ከለላ እንኳ ተነፍጎት ያለፍርድ ቤት ክስ በሀገሪቱ ባሉ እስርቤቶች ሁሉ ይታጎራል፡፡ በእስር ቤቶችም ውስጥ ኢሰብኣዊ ድርጊት በስፋት ይፈፀምበታል፡፡ በአንዋሩ አላሁ አክበር ብላችሁዋል በሚል ታስረው ከነበሩ ወንድሞች መካከል ዳዒ ሙሃመድ ሳኒ ፍርድቤት በቀረበበት ሰኣት ልብሱን አውጥቶ የተገረፈ ጀርባውን ለዳኞች በማሳየት እኔ ኢትዮጵያዊ አየደለሁምን??? እኔ ኢትዮጵያዊ አየደለሁምን !!! ኢትዮጵያዊ ላይ መሰል ግፍ ይፈጸማልን ??? በማለት ጠይቋል፡፡ በፍ/ቤቱ ውስጥ የነበሩ ሁሉ ተላቅሰው፣ የነበሩ ዳኞችም አንብተው ጉዳዩን ከአሁን በሁዋላ እንደማያዩ ጭምር በመግለፅ ፖሊስ ልጁንና ሌሎች ከሱ ጋር የነበሩ 70 ያህል ልጆችን በነፃ እንዲያሰናብት ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
በተለይ ደግሞ ባለፉት ሳምንታት በማዕከላዊ በግፍ ታስረው በሚገኙ የኮሚቴ አባሎች ፤ ዳዒዎች ፤ ጋዜጠኞች….. ላይ እየደረሰ ያለው አሰቃቂ ግፍን ስንመለከት ይቺ ሀገር በህግ የምትመራ ሳትሆን መንግስት ውስጥ የተደራጁ ቡድኖች በፈለጉት መልኩ የሚመሯት እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ የዚህኑ ቡድን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል የኮሚቴው ዓላማ ኢስላማዊ መንግስት መመስረት እንደነበር መርማሪዎች የግድ ማረጋገጥ ስለሚጠበቅባቸው በታሳሪዎች ላይ የደረሰው ስቃይና ጫና የሰው ልጅ በሰውነቱ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እንደነበር ከታማኝና ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
• ኮሚቴዎቻችንና ዳዒዎቻችንን ከ10 ቀን በላይ በቀዝቃዛና ምንም ብርሃን በሌለው ጨለማ ክፍል ለብቻ በማሰር ሌሊት ሌሊት በመግረፍ ሲያሰቃዩዋቸው ከርመዋል፡፡ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ያለምንም እረፍት በተከታታይ ለ18 ሰዓታት እንዲቆም በመደረጉ ኩላሊቱን በጠና ታሞ ሆስፒታል ሂዶ ታክሞ እንደነበር ታውቋል፡፡ ሸህ መከተ ሙሄ ሰውነታቸው አባብጦ ታይተዋል፡፡
• ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸውን በገቡ በወጡ ቁጥር የጻፋቸውን ጽሁፎች እያመጡ ይህንን ምን ለማለት ፈልገህ ነው የጻፍከው በሚል እየደበደቡት ይገኛሉ፡፡
• የተወሰኑ እስረኞችን እርቃናቸውን በማድረግ እንደገረፉ ተረጋግጧል፡፡
• ለሚመሰርቱት ክስ ማስረጃ እንዲሆን የቢንላደንን ፎቶና ብር በማስያዝ ፎቶ እስከማንሳት የደረሰ አረመኔያዊ የጭካኔ ተግባር እተፈጸመባቸው ይገኛል፡፡
• ኮሚቴዎቻችንና ዳዒዎቻችን ለዳዕዋና ለንግድ ጉዳዮች ከአገር የወጡባቸውን መረጃዎች በመያዝ ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት ከውጪ ሃይሎች ለመገናኘት ያደረጉት ጉዞ መሆኑን እንዲያምኑና እንዲፈርሙ ለማድረግ ከፍተኛ ግርፋት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በአዲሱ የፀረሽብር ህግ በስቃይ ብዛት የሚፈረሙ መረጃዎች ሁሉ ለፍ/ቤት ተገድጄ ነው የፈረምኩት ቢባል እንኳ ተቀባይነት እንደሌለውና በመረጃነት እንደሚቀርብ ልብ ይሏል፡፡
• የፍ/ቤት ዳኞች ከህጋዊ ጠበቆቻቸው ጋር ለመገናኘት እንዲችሉ ትዕዛዝ በያስተላልፉም የፍ/ቤቱን ትእዛዝ ባለማክበር እሰካሁን ከህጋዊ ጠበቆቻቸው ጋር ለመገናኘትና ማማከር አልቻሉም፡፡

ውድ ኮሚቴዎቻችንና አስተማሪዎቻችን! እናንተ የዘመኑ ፈርጥ ልትሆኑ ከጌታችሁና ከኛ ጋር የገባችሁትን ቃልኪዳን ፈጽማችኋል፡፡ እኛም በፊርማችን ወክለን ጥያቄያችንን እንድታደርሱልን የላክናችሁን እንደራሴዎቻችንን ከውድ ቤተሰቦቻችሁና ልጆቻችሁ ነጥለን ጥያቄያችን በአግባቡ ሳይመለስና ነጻ ሳትወጡ ወደቤታችን ላንመለስ የገባነውን ቃል የምናጥፍ አይደለንም፡፡ ድምጻችንን የሚሰማን መንግስት ብናጣ እንኳ የሩቅንም የቅርብንም ሰሚ፣ የውስጥንም የውጭንም ተመልካች ወደሆነው አንድ አላህ ድምጻችን ያስተጋባል ፡፡ለነብዩላህ ኢብራሂምን (ዓለይሂ ሰላም) አላህ የሰው ልጆችን ወደ ሃጅ ተጣራ አላቸው፡፡ ጌታዬ ሆይ! እንዴት አድርጌ ለሰው ልጆች ሁሉ ማሰማት ይቻለኛል? በማለት ጌታቸውን ጠየቁ፡፡ አላህ አንተ ሃላፊነትህ ጥሪውን (አዛኑን) መፈጸም ሲሆን ማድረሱ በኛ ላይ ነው አላቸው ፡፡

በታሰሩ ወንድሞቻችን ላይ የሚፈፀመው የህግ ጥሰት ተቀባይነት የለውም!!
በመንግስት ስም የተደራጁ ቡድኖች እየፈፀሙት ያለው ህገወጥ ተግባር በአስቸኳይ ይቁም!!

No comments:

Post a Comment