Wednesday, September 12, 2012


እጅግ በጣም አዛኝ እጅግ በጣም ሩሕሩሕ በሆነው በአላህ ስም
ሙስሊሙ ህብረተሰብ የጀመረውን የድምጻችን ይሰማ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን ለመግለጽና እና ተያይዞ ለተፈጠረው የስልጣን ሽግግር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል ጋብ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ኮሚቴዎቹ ታስረው እየተሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ ይህንን ከባድ እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው ከመዳከም ሳይሆን ይልቁንም ጥንካሬው ጫፍ ደርሶ ከታየበት ከዒድ አገርአቀፍ የተቃውሞ ዕለት ማግስት ነበር፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትና የ"ደህንነት" አካላት ከህዝብም በላይ የሃዘኑ ዋነኛ ተካፋዮች እንደመሆናቸው ሃዘኑን ተረጋግተው እንዲያሳልፉ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ፋታ መስጠትም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚሁ አካላት ሙስሊሙ የሰጠውን የእፎይታ ጊዜና የሃዘኑን ድባብ እጅግ ኢሞራላዊ በሆነ መልኩ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ በተለይ የደህንነት ሰዎች ለጊዜው የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት በመጠቀም ከግል ጥቅማቸው ጋር በተያያዘ ይሁን ከመንግስት አመራሮች በተሰጠ መመሪያ በማናውቀው ሁኔታ በርካታ ህገወጥ እርምጃዎችን ሲወስዱ ከርመዋል፤ አሁንም እየገፉበት ይገኛሉ፡፡ በዚሁ የሀዘን ወቅት በመላ አገሪቱ ለመቁጠር የሚያዳግቱ በደሎች በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የተፈጸሙ ሲሆን ጥቂቶቹን ለመዘርዘር እንሞክራለን
• ህብረተሰቡ በየአካባቢው በተጣሉ ድንኳኖች ተሰብስቦ ሲያለቅስ እነሱ የታሰሩ ኮሚቴዎቻችንና ዓሊሞቻችን ያለምንም ርህራሄ አንዴ ጨለማ ክፍል በሌላ ጊዜ ቀዝቃዛ ክፍል ለረጅም ቀናት በማቆየትና በግድ ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት ተንቀሳቅሰናል ብላችሁ ፈርሙ በማለት ሲገርፏቸው እንደቆዩ በተጨባጭ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
• አዲስ
አበባን ጨምሮ በብዙ ክልሎች በርካታ ዓሊሞችና ዳዒዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ሸኽ ሐጂ፣ ሸኽ አብዱሰላም፣ ኡስታዝ ሙራድ ሽኩር፣ ኡስታዝ ሙሐመድ ሳኒ፣ ኡስታዝ አቡበክር ዓለሙ …ተጠቃሽ ናቸው፡፡
• ከአንድ ዓመት በፊት ያወጡት የነበረውን ኢስላማዊ ተቋማትን የመዝጋት ፕላን ማስፈጸም ጀምረዋል፡፡ ከ12 በላይ የሚሆኑ ኢስላማዊ የዳዕዋና የልማት ተራድዖ ድርጅቶች የባንክ ሂሳብ ተዘግቷል፡፡ አንዳንዶቹ የሰራተኛ ደሞዛቸውን እንኳ መክፈል ባለመቻላቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡
• በየክልሉ ከመጅሊስ ባለስልጣኖች ጋር በመሆን ህዝቡን ሃዘን መግለጫ ፕሮግራም በሚል ሽፋን በመጥራት ካድሬዎቻቸውን ለመጅሊስ አስመራጭነትና እጩነት እንዲቀበላቸው ሲያስፈራሩ ቆይተዋል፡፡
• ሙስሊሙን ህብረተሰብ ለይተው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት አላዘናችሁም በማለት ፍትሃዊ ጥያቄውን ለማደናቀፍ የማሸማቀቅ ስራ በሰፊው ሰርተዋል፡፡
• በየመስጊዱ የሚደረጉ የነበሩ ዳዕዋዎችን የተለያዩ ምክኒያቶችን በመፍጠር እንዳይቀጥሉ አድርገዋል፡፡
• ኢስላማዊ መጽሄቶችና ጋዜጦች እንዳይወጡ እገዳውን ቀጥለዋል፡፡

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለአገር አሳቢነቱንና ያለውን አለመረጋጋት ተጠቅሞ ሊያስፈጽም የሚፈልገው ምንም አይነት ፖለቲካዊ አጀንዳ እንደሌለው ከበቂ በላይ ለሆነ ወቅት ተቃውሞውን አቁሞ ማሳየት ችሏል፡፡ ነገር ግን የ"ደህንነት" ሰዎች ይህንን ወቅት ሃዘኑን ባግባቡ ለማሳለፍና ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ጋር የተፈጠረውን ቅራኔ ተረጋግቶ መፍትሄ ለመስጠት ከመጠቀም ይልቅ በሚያሳዝን ሁኔታ ሃዘኑን ህብረተሰብን ለማሸማቀቂያነት በመጠቀም ስራቸውን ሲሰሩ ከርመዋል፡፡ በመሆኑም በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንደማይቻለው ሁሉ መረጋጋትም ህብረተሰብ ስለፈለገው ብቻ ስለማይፈጠርና ዝምታውን ተገን አድርጎ የመብት ረገጣው በሰፊው መቀጠሉን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቆሞ የነበረው የሙስሊሙ ህብረተሰብ ተቃውሞ ከመጪው ጁሙዓ ጀምሮ እንዲቀጥል ሹራ ተደርጎበት ተወስኗል፡፡ መጪው ጁሙዓም አንዋር መስጂድን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የተመረጡ መስጂዶች በአላህ ፈቃድ በተቃውሞ ተክቢራ ደምቀው ይውላሉ፡፡ ነገ ሐሙስና ጁሙዓም ኮሚቴዎቻችን ፍርድ ቤት ስለሚቀርቡ ሁላችንም አራዳ ፍርድ ቤት በመገኘት አጋርነታችንን እናሳያለን፡፡ የቀጠሮው ሰዓት በውል ስለማይታወቅ ከጠዋቱ 2፡00 ጀምሮ በመገኘት በትእግስትና ምንም ዐይነት ሁከት እንዳይፈጠር ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ኮሚቴዎቻችን ቢታሰሩም ትግላችን እንዳልታሰረ ለኮሚቴዎቻችንም ሆነ ልቦና ላለው ሁሉ እናሳያለን፡፡ በቀጣይም በተለይ በኮሚቴዎቻችን ላይ መስከረም 3 እና 4 የሚሰጠውን የመንግስት ውሳኔን ከግምት ያስገቡ ቀጣይ እርምጃዎች በተከታታይ የምንገልፅ ይሆናል፡፡
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment