Friday, September 21, 2012

በመዲናችን አዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጂድ የተሳካ ተቃውሞ ተካሄደ፡

ድምፃችን ይሰማ Facebook Source

በአላህ ሥም እጅግ በጣም አዛኝ እጅግ በጣም ሩሕሩሕ
በመዲናችን አዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጂድ የተሳካ ተቃውሞ ተካሄደ፡፡
ከዒድ አደባባይ የተቃውሞ ትዕይንት በኋላ አሳማኝ ምክንያቶች በመኖራቸው የተነሳ ተቃውሟችን ተቋርጦ መክረሙ ይታወሳል፡፡ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ሊያገኙ ይቅርና ተገቢ ትኩረት ተነፍጓቸው ወኪሎቻችን በታሰሩበት፣ ሕገ ወጥ የመጅሊስ አመራር አካላት ያሻቸውን እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ ተቃውሟችን ያለምን እረፍት መቀጠል ቢኖርበትም አገራችን አዲሱን ጠቅላይ ሚንስተር ቃለ መሐላ አስፈፅማ በሾመችበት ተመሳሳይ ቀን የተቃውሞ ድምፃችን በታቀደለት መርኃ ግብር መሠረት እነሆ ተካሂዶ ውሏል፡፡
በዕለቱ የተቃውሞ ውሎ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ በቦታው የተገኘው ከፍተኛ ቁጥር የነበረው ሙስሊም ሕዝብ የነበረውን አስቸጋሪ የአየር ንብረት ተቋቁሞ ያለምንም ችግር ተቃውሞውን አሰምቶ በሰላም ወደ የመጣበት ተመልሷል፡፡ ከነጫጭ ሶፍትና መሐረብ እስከ ታላላቅ መልዕክቶችን ያዘሉ ባነሮች ከፍ ብለው የታዩ ሲሆን “free our heros” ፣ “ምርጫውን አንሳተፍም” ፣ “ወኪሎቻችን ሳይፈቱ ምርጫ የለም”፣ “ምርጫው ህገ ወጥ” ነው የሚሉት የተቃውሞ መልዕክቶች ከበርካታ የተቃውሞ መልዕክቶች መካከል ይገኙበታል፡፡
ሕዝቡ በያዘው አቋም በመፅናት በምርጫው ሂደት ከመሳተፍ ራሱን ማግለሉን ይፋ ቢያደርግም ለጥቅም ባደሩ ጥቂት የመጀሊሱ አካላት በመታገዝ የመንግስት አካላት በየቤቱ እየገቡ ሕዝቡ በግድ እየወጣ እንዲመዘገብ እያስገደዱ ባሉበት በዚህ ሰዓት ሕዝቤ በመደበኛ የተቃውሞ ቦታ በመገኘት ያለ ምንም ፍርሀትና ድንጋጤ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ ዛሬም ድምፄ ይሰማ በማለት ለተቃውሞ ሲወጣ የሕዝብ ድምፅ ተከብሮ ተገቢው ምላሽ እስካልተሰጠ ድረስ ተቃውሞው እንደሚቀጥል በዛሬው እለት አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን ኃላፊነት ለተረከበው አካል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
በዲሞክራሲ መርሕ ሕዝብ ያደረበትን ቅሬታ እና እየደረሰበት ያለውን በደል ለመግለፅ አደባባይ ሲወጣ ይህን ከመተግበር ውጪ ሁከት የማስነሳትም ሆነ ረብሻ የመፍጠር አላማ እንደሌለው ሂደቱ ሲያረጋግጥ በተቃዋሚው ሕዝብ ዙሪያ የተኮለኮሉትና እዚህም እዚያም የመሸጉት የመንግስት የኃይል ክፍሎች ዛሬም ቢሆን ትምህርት መውሰድ እንዳለባቸው ይታየናል፡፡ ይህም እነሱን ከመናቅ የመነጫ ሀሳብ እንዳልሆነ ሊሰመርበት እንደሚገባ እያሳሰብን ህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞውን በሠላም አሰምቶ ወደ ቤቱ ከመመለስ ውጪ ላለፉት አስር ወራት ሲያደርገው እንደከረመው ሁሉ ይህ ሂደቱ አሁንም በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚቀጥል ሊያረጋግጥ ይወዳል፡፡ “እኔም ተቃውሞዬን በሠላም ማሰማቴን እቀጥላለሁ እናንተም ባላችሁበት ፀንታችሁ ኃላፊነታችሁን ተወጡ!” የሚለው ዛሬም የሚደግመው ቃሉ ነው፡፡
በመጨረሻም በጨዋ ሥነምግባሩ ወደር የለሽ የሆነው ሙስሊም ሕዝብ ዛሬም እንደ ትላንቱ በፅናት በሚያስደንቅ ታዛዥነት የሚገባውን ኃላፊነት በመወጣቱ የላቀ ክብርና ምስጋና በአላህ ስም ይድረሰው ለማለት እንወዳለን፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የተከበሩ ኃይለማሪያም ደሳለኝ መልካም የስራ ዘመን ይሁንላቸው፣ እኛም ተቃውሟችንን አሀዱ ብለን ጀምረናል፡፡ አላህ ይገዘን፡፡
አላሁ አዕለም

Ethiopian Muslims rally in mosques in the capital Addis Ababa and other Ethiopian states protesting the government interference in their religion freedom and demanding the release of detained leaders.

No comments:

Post a Comment