Monday, September 24, 2012

ታላቅ የሰደቃና የዱዓ ዘመቻ


ታላቅ የሰደቃና የዱዓ ዘመቻ
በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ሙስሊም በዒድ አደባባይ፣ ከዚያም በፊትና በኋላም በማያሻማ ሁኔታ በመስጂድ ካልሆነና ኮሚቴው ካልተፈታ ምርጫ የሚባል ነገር መስማት እንደማይፈልግ ቢገልጽም መንግስትና ጀሌው መጅሊስ የህዝቡን ድምጽ ደፍጥጠው መስከረም 27 ምርጫ ለማድረግ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡ እንደነሱ አሰተሳሰብ ምርጫ ጠይቃችሁ ነበር ይኸው ተደረገ በማለት እንቅስቃሴያችንን ለማስቆም የሞኝ ህልም ያልማሉ፡፡ ለልማት መጨነቅ ይገባቸው የነበሩ በየክፍለከተማውና በየቀበሌው ያሉ ካድሬዎች ሁሉ ስራቸውን እርግፍ አርገው ትተው ቅርጫውን ለማሳካት ሌት ተቀን ይለፋሉ፡፡ በግድ ይሰበስባሉ፣ ያስፈርማሉ፣ ያስፈራራሉ፡፡ ኮሚቴዎቻችንን እጅግ አረመኒያዊ በሆነ ሁኔታ በእስር እንዲማቅቁ በማድረግና የነሱን ሜዳው ላይ አለመኖር እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ አይደለም ከመንግስት ከሽፍታ የማይጠበቅ የውንብድና ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህን ሁሉ ግፍ ሲፈጽሙ እነሱ ያላቸውን ሃይልና የሚወረወርላቸውን ዶላር ተማምነው ሲሆን ሙስሊሙ ትንሽ ቢጮህም ምንም አያመጣም ብለው ያስባሉ፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችን በተዋጉበት ዘዴ እኛን ሊያጠፉ ይፍጨረጨራሉ፡፡ እነዚህ አካላት ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር ጦርነቱን የከፈቱት ሙስሊሙ ላይ ሳይሆን አላህ ላይ መሆኑን ነው፡፡ ሙስሊሙ ያለፉትን ወራቶች በሙሉ እጅግ በላቀ ጽናት ያካሄደው ትግል ውጤታማ ሊሆን የቻለው በአላህ እገዛ ነው፡፡ ሙስሊሙ ሁሉ በዱዓ፣ በሰደቃ፣ በቁኑት፣ በጾም፣... ልዩነቱን ወደ ጎን ትቶ ወደ አላህ አለቀሰ፡፡ ወንዱ፣ ሴቱ፣ ሽማግሌው፣ አሮጊቱ፣ ህጻናቱ ሁሉ " ያ አላህ! እኛ ደካሞች ነን፡፡ የመጣብንን መከራ ካንተ ውጪ የሚመልስልን የለምና እርዳታህ አይለየን፡
፡  በዳዮችን ያዝልን" ብለው ለአላህ ስሞታ አቀረቡ፡፡ በዳዮች የሞቀ ፍራሻቸው ውስጥ ሲተኙ እነሱ በውድቅት ሌሊት ተነስተው " ያ አላህ!" አሉ፡፡ እርስ በርስ ይቅር ተባባሉ፡፡ በዱዓ ብቻ ሳይብቃቁ እንደሰው የሚችሉትን መስዋዕትነት ሁሉ ከፈሉ፡፡ ይህኔ የአላህ እገዛ መጣ፡፡ የሙስሊሙን አቅም በመናቅ እንደቀልድ ሊያስፈጽሙት የተሰጣቸው የቤት ስራ ሙሉበሙሉ ባይቆምም በከፍተኛ ሁኔታ መገታት ቻለ፡፡ ሊከፋፍሉትና ሊያባሉት ያሰቡት ህብረተሰብ ታይቶ የማታወቅ አንድነት ፈጠረ፡፡ ከከተማ በጣም ርቀው የሚገኙ ገጠሮች ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ ይሄን አዲስ ሃይማኖት ወዲያ በሉልን አሉ፡፡ ህብረተሰቡ ለእምነቱ ያለው ተቆርቋሪነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ…፡፡ ይህ ሁሉ ድል ሊገኝ የቻለው በርግጠኝነት በአላህ እገዛ ነው፡፡ አሁንም እስከመጨረሻው ልንታገል የምንችለው በራሳችን ጥረት በመተማመን ብቻ ሳይሆን የአላህ እገዛ እንዳይለየን አላህን በመለመን፣ በሰደቃና መልካም ተግባራት ወደ እርሱ በመቃረብ ነው፡፡ በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ ምርጫው ይደረግበታል ተብሎ እስከታሰበው መስከረም 27 ድረስ ለሁለት ሳምንት የሚቆይና ተከታዮቹን ስራዎች ያካተተ ፕሮግራም እንዲሰራ ተወስኗል፡፡
• የሰደቃ ፕሮግራም፡- ሰደቃ በላእ (መከራን) እንደሚያነሳ የተለያዩ ሐዲሶች ይጠቁማሉ፡፡ ሰደቃ ምን ያህል መከራ እንዳነሳልንና የሰራውንም ተዐምር ከሐዲስ ባለፈ በተግባርም ሁላችንም ያየነው ነው፡፡ ሰደቃውን እንዳካባቢው ሁኔታ በመስጂድ፣ በየቤታችን ሚስኪኖችን ጠርቶ በማብላት፣ ከጎረቤቶቻችን ጋር በመሆን…ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚያም አልፎ ቤታችን ምግብ በመስራትና በፌስታሎች በመቋጠር ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ መስጊድ በሮች አካባቢ ለሚገኙ ሚስኪኖች መስጠት ይቻላል፡፡
• የሰኞና ሐሙስ ፆም፡- ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጾመኛ ሰው እስኪያፈጥር ድረስ የሚያደርገው ዱዓእ በፍጹም እንደማይመለስ ነግረውናል፡፡ በተቻለ መጠን መጪዎችን ሰኞና ሐሙሶች በመጾም ከልባችን አልቅሰን ዱዓ እናድርግ፡፡ የመጣብንን መከራ አላህ እንዲይዝልንና በዳዮችን መቀጣጫ አድርጎ እንዲያሳየን እንለምነው፡፡
• የለሊት ሰላትና ዱዓ፡- ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) አላህ የለሊቱ አንድ ሶስተኛ ሲቀር "ማነው የሚጠራኝና የምመልስለት? ማነው የሚጠይቀኝና የምሰጠው?" እያለ እንደሚጣራ ነግረውናል፡፡ ታዲያ እኛ አላህን የምንለምነው በርካታ ጉዳዮች የሉንም እንዴ? በደሉ ድንበር አልፏል፡፡ ኮሚቴዎቻችን ለኛው ጉዳይ ሲሉ በጨለማና ቀዝቃዛ ክፍሎች ታስረዋል፡፡ ተገርፈዋል፡፡ እነሱን እስር ቤት ጥለን እንዴትስ ፍራሻችን ይመቸናል፡፡ ሁላችንም ከፈጅር በፊት ትንሽ ቀደም ብለን ተነስተን ሁለት ረከዓ ሰግደን ወደ አላህ እናልቅስ፡፡ "ያ አላህ!" እንበል፡፡
ይህ የሰደቃና ዱዓ ፕሮግራም ገጠር ድረስ ላሉ ሰዎች ጭምር እንዲደርስና እንዲተገበር በየመስጂዱ በመናገር፣ በወረቀት ኮፒ በማድረግ፣ ሜሴጅ በመላክ፣ ለምናገኘው ሰው ሁሉ በአፍ በመንገር፣…የበኩላችንን ጥረት እናድርግ፡፡ እራሳችንን ከወንጀል እናርቅ፡፡ ሰደቃ አውጥተን በንጹህ ልብ የምናደርገው ዱዓ በአላህ ፈቃድ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ የጠላቶቻችንንም ድካም ሁሉ ከንቱ ያስቀራል፡፡ አላህ ይወፍቀን!

No comments:

Post a Comment