Friday, September 7, 2012

Radio Bilal September 7, 2012 ሬዲዮ ቢላል ጳጉሜ 2/2004



Radio Bilal September 7, 2012  ሬዲዮ ቢላል ጳጉሜ 2/2004

  1. የሼህ ሆጄሌ መስጂድ ኢማም ትላንት መታሰራቸውን የጀመዓው አባላት አመለከቱ
  2. በደሴ የታሰሩ ምዕመናን እስከ አሁን ክስ አልተመሰረተባቸውም ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ
  3. በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል አሜሪካ ስጋቷን ገለፀች
  4. የኮሚቴ አባለት ሳይፈቱ በምርጫ እንዳይሳተፉ የሻሸመኔ ነዋሪዎች አቋም መያዛቸው ተጠቆመ
የሼህ ሆጄሌ መስጂድ ኢማም ትላንት መታሰራቸውን የጀመዓው አባላት አመለከቱ
  • ኢማሙ የፊታችን ሠኞ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሠጥቷል
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ጳጉሜ 2/2004
ላለፉት 10 ዓመታት በሼሆጀሌ መስጅድ በኢማምነት በማገልገል የሚታወቁት ሼህ አብዱልሰላም አቤ ትላንት በድንገት ለእስር መዳረጋቸውን የአካባቢው ምንጮች አስታወቁ፡፡የአካባቢው ምንጮች ዛሬ ለሬድዮ ቢላል እንዳስታወቁት ኢማሙ ለእስር የተዳረጉት ባለፈው ጁምዐ ከኹጥባ በፊት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከእስር ይፈቱ በኃይማኖታችን ላይ የሚደርሱ ጫናዎች ይቁሙልን የሚል ገለፃ በመስጠታቸው ነው፡፡አክራሪና አሸባሪ በሚል የሚካሄደው መዋከብ ተገቢ እንዳልሆነም ጭምር በመናገራቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ይህን የሕዝበ ሙስሊሙን ሀሳብና አቋም በመግለፅ መናገራቸው ለእስር የሚዳርግ እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ገልፀዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ዛሬ ኢማም ሼህ አብዱልሰላም በጉለሌ የመጀመሪያ ደረጃ ፍረድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡ጠበቃቸው አቶ ተማም እንደገለፁልን የኢማም ሼህ አብዱልሰላምን ጉዳይ የተመለከተው የጉለሌ የመጀመሪያ ደረጃ ፍረድ ቤት ነበር፡፡
በዚሁ ወቅት ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ መጠየቁን ጠቅሰው ይህ የዋስትና መብት የማያስከለክልና ለክስ የማያበቃ ጉዳይ እንዳሆነ መከራከሩንም ጠበቃው አስታውቋል፡፡ችሎቱም ግራ ቀኙን ካደመጠ በኋላ ጉዳያቸውን የፊታችን ሰኞ ለማየት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ኢማሙ እስከ ሰኞ በጉለሌ ክ/ከ ፖሊስ ጣቢያ በእስር እንደሚቆዩ ተገልፆዋል፡፡


በደሴ የታሰሩ ምዕመናን እስከ አሁን ክስ አልተመሰረተባቸውም ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ጳጉሜ 2/2004
በደሴ ከተማ ባለፈው ወር መጀመሪያ ሳምንት በአረብ ገንዳ መስጂድ ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ግርግር ተከትሎ ለእስር ተዳርገው ከነበሩት ምዕመናን መካከል 12ቱ እስከ አሁን ምንም አይነት ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ተገለፀ፡፡
የታሳሪ ቤተሰቦች ዛሬ በደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት የእስረኞችን ሁኔታ ለመከታተል ተገኝተው ነበር፡፡ ይሁንና በስፍራው የነበሩ የሬዲዮ ቢላል ምንጮች እንዳሉት በፍርድ ቤት ይገኛሉ የተባሉ እስረኞች አልቀረቡም ችሎትም አልተካሄደም፡፡
በአካባቢው የነበሩ የፖሊስ አባላት ግን ለጳጉሜ 5/2004 እንደሚቀርቡ እንደገለፁላቸው ነው ምንጮቻችን ያደረሱን መረጃ የሚያመለክተው፡፡
በወቅቱ በተከሰተው ሁከትና ግርግር በ100ዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ምንጮች በማያቁት ምክኒያት 12ት ሰዎች እስከ አሁን ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር መቆየታቸው አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡


በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል አሜሪካ ስጋቷን ገለፀች
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ጳጉሜ 2/2004
በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተፈጠረውን የድንበር ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የቀረበውን ሀሳብ ሱዳን አልቀበልም በማለቷ በሀገራቱ መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል አሜሪካ አስታወቀች፡፡
ይህን ስጋቷን አሜሪካ የገለፀችው በተባበሩት መንግስታት አምባሳደር በሆኑት ሱዛን ራይስ ለፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ባቀረቡት ሀሳብ ነው፡፡
ደቡብ ሱዳን በአፍሪካ ህብረት የቀረበውን የድንበር ውዝግብ የሚፈታበት መነሻ ሀሳብ ስትቀበል ሱዳን እንቢተኛ መሆኗ ተነግሯል፡፡ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በዚህ ዓመት ጦርነት ለመግጠም የተፋጠጡት በድንበር ጥያቄና በነዳጅ ገቢ ይገባኛል ምክንያት ነው፡፡
የነዳጁ 75 በመቶ ከሱዳን በህዝብ ውሳኔ በተገነጠለቸው ደቡብ ሱዳን ይሁን እንጂ ሁሉም የነዳጅ መተላለፊያዎቹ የሚያቋርጡት በሱዳን ነው በደቡብ ሱዳንም ሆነ በካርቱም በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩና በተለይም በደቡብ ሱዳን ጁባ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ኢትዮጵያዊያን ኑሮአቸውንና ስራቸውን እዚያ እንዳደረጉ ይታወቃል፡፡ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡


የኮሚቴ አባለት ሳይፈቱ በምርጫ እንዳይሳተፉ የሻሸመኔ ነዋሪዎች አቋም መያዛቸው ተጠቆመ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ጳጉሜ 2/2004
በሻሸመኔና አካባቢዋ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የመጅሊስ ምርጫ የሚሳተፉት የታሰሩት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ሲፈቱ ብቻ መሆኑን አብዛኛው ነዋሪዎች አቋም መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡የአካባቢው ምንጭ እንዳመለከቱት አብዛኞቹ የሻሰመኔ ከተማ መስጅድ አስረዳደር ኮሚቴዎችና ኢማሞችም ይህንኑ የሕዝበ ሙስሊሙን አቋም ተስማምተውበታል፡፡
የመስጅዱ ኮሚቴ አባላትና ኢማሞች ሠሞኑን በየአካባቢያቸው ባካሄዱት ውይይት ምርጫው መስጅድን ማዕከል አድርጎ መካሄድ እንዳለበት ተስማምተዋል፡፡ይህንኑ ስምምነታቸውን በአቋም ደረጃ በደብዳቤ ለሻሸመኔ ከተማ አስተፈዳደር ማስታወቃቸውንም ነው የአካባቢው ምንጭ ለሬድዮ ቢላል ያመለከተው፡፡

No comments:

Post a Comment