Tuesday, October 23, 2012

እንዲህ ናቸው የኛ ጀግኖች (ክፍል 1)

 ድምፃችን ይሰማ
እንዲህ ናቸው የኛ ጀግኖች (ክፍል 1)

የጠራው የእስልምና መንገድ ከኛ ለመድረስ በርካቶች ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡ ሕይወታቸውንም መሰዋእት አድርገው አቅርበዋል፡፡ አያት ቅድመ አያቶቻችን ወቅቱ የሚጠይቀውን የትግል አማራጮች አሟጠው በመጠቀም ታላቅ ጀብዱ ፈፅመው ሙስሊም ሆኖ በኢትዮጵያዊነት መኖር ያሳፍር የነበረበትን ዘመን ላይመለስ ሸኝተውታል፡፡ አሁን የምንገኝበት ትውልድ ደግሞ ወቅቱ የሚጠይቀውን የትግል ዘዬ በመከተል ንቁ ሙስሊም በመሆንና በኢትዮጵያዊነት መካከል ግርዶሽ ለማበጀት የሚያሴሩ ሃይሎችን ‹‹አይሳካላችሁም›› ሲል በአደባባይ አንገታቸውን አስደፍቷቸዋል፡፡ የቀዳሚው ዘመን ጀግኖችን የመሩ ድንቅ ስብእናዎች ብዙዎችን
እንደማረኩ ሁሉ የኛን ትውልድ የህልውና ትግል የመሩት ድንቅ ስብእናዎችን መላው ህዝባችን ‹‹እንዲህ ናቸው የኛ ጀግኖች›› እንዲል የኩራትን አክሊል ደፍቶላቸዋል፡፡

የኛ ጀግኖች ብዙ ሁነው እንደ አንድ የቆሙ፣ አንድ አካል ሁነው ለወገን የበቁ፣ ተገደው የገቡበትን የመሪነት ሚና አፍቅረው የሚሰሩ፤ እራሳቸውን ለህዝብ የሰጡ ናቸውና ለነሱ ያለንን የጠለቀ ፍቅር ሁሌም እንዘክራለን፡፡ ኮሚቴዎቻችን ከእስር በፊት በነበራቸው የአብሮነት ቆይታ በተግባር ያሳዩንን ሰናይ ነገር ሁሉ ዘርዝረን ባንዘልቀውም በፈለጋቸው ፀንተን መቆማችንን ለማውሳት በጥቂቱ ‹‹እንዲህ ናቸው የኛ ጀግኖች›› ስንል በተከታታይ ክፍሎች በመልካም እናወሳቸዋለን፡፡

የኛ ጀግኖች ነፍሳቸውን በአላህ ፍራቻ የገሩ ለአምላካቸውና ለሰው ልጆች ጥልቅ ፍቅር የሰጡ ናቸው፡፡ ለሚያፈቅሩት ሲሉ ሁሉ ነገራቸውን የሰጡ፣ ቃላቸውን የሞሉ ታማኝ መሪዎቻችን ናቸው፡፡ ያደርጓቸው በነበሩ እያንዳንዷ እንቅስቃሴ በህዝብ የስሜት ግለት እና በጠላት ተንኮል መክሸፍ ሳይኩራሩ ሁሌም የአላህን እገዛ ተደፍተው የሚማፀኑ ነበሩ፡፡ ሹራዎቻቸው በኢስላማዊ አደብ ከመቃኘታቸው በላይ ከውሳኔ በፊት ከልብ ተጨንቀው በዚክር እና በዱዓ ታግዘው ነበር የሚወስኑት፡፡ በትግሉ ሂደት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ወንድሞችና እህቶች የሚያፈልቋቸው አማራጭ ሃሳቦች ሁሌም በጸሎት እንዲታገዙ ይሹ ነበር፡፡ በየሹራቸው እለት ከአባላቱ ቢያንስ የተወሰኑቱ ቀኑን በፆም ያሳልፉ ነበር፡፡ ከፊሎቹ በሹራዎች መሃል ምላሳቸውና ቀልባቸው በዚክር ተሰብስቦ የሌላ አለም ሰው እስኪመስሉ እሩቅ ይጓዙ ነበር፡፡ ውሳኔያቸው ከምንም በላይ አላህን እንዳያስከፋ በመቀጠልም ለሙስሊሙ ኡማ የተሻለ ነገር እንዲያመጣ ሁሌም ይጨነቁ ነበር፡፡ ወጣቶቹ በእድሜ ለገፉት ያደርጓቸው የነበሩ መተናነሶች በእድሜ የገፉት ለወጣቶቹ ያሳዩት የነበረውን ፍቅር የወለደው አክብሮት በመመልከት የአብሮነት መስተጋብራቸውን በአላህ የተመራ ብለን እንድንደመድም በሩን ይከፍትልናል፡፡

የኛ ጀግኖች አላህ በምድር ላይ ሳሉ ያስቀመጠባቸውን ሃላፊነት ተወጥተው ጌታቸውን መገናኘት የሚመኙ ባላደራ መሪዎች ናቸው፡፡ ከሚጋፈጡት ታላቅ ጠላት ግዝፈት ይልቅ የሚረዳቸው አላህን እገዛና ቅርበት በፅኑ ያምናሉ፡፡ በጌታቸው ላይ ያላቸውን ፅኑ እምነት በመመካት ለአንድ አፍታ እንኳ ተስፋ መቁረጥ ታይቶባቸው አይውቅም፡፡ በተለይ በግፍ ወደ እስር ሊወረወሩ ቀናትና ሰአታትን እየቆጠሩ በነበሩባቸው ግዜያት ያሳለፏቸው የአብሮነት ጊዜያት እራሳቸውን ይበልጥ ወደ አላህ ያቃረቡበት፣ የተጣለባቸውን ሕዝባዊ ሃላፊነት ከተወጡት አላህ እንዲመድባቸው ጽኑ ዱዓእ ያደረጉበት፣ የጀመርነው የመብት ማስከበር ትግል መርህ ባደረገው እውነተኝነት (ሲድቅ) እና ሰላማዊነቱ ፀንቶ እንዲቀጥል የአደራ መልእክት ያስተላለፉበት፣ ከምንም በላይ ደግሞ ከፊት ለፊታቸው የሚታያቸውን ፈተና በስኬት ለማጠናቀቅ በስነ ልቦና ዝግጁ የሆኑበትና መስዋእትነት የከፈሉለት ህዝብ አላህ ድልን አጎናጽፎት የደስታውን እለት እንዲያሳያቸው የተመኙበት ወቅት ነበር፡፡

እኛም የተጫነንን ቀንበር ከጫንቃችን ሳናነሳ ወደ ቤታችን እንደማንመለስ እስከአሁን እያስመሰከርን እንገኛለን፡፡ ለመሪዎቻችን ያለን ጥልቅ ፍቅር ለአላማችን ካለን ፅናት ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ ሁለቱን ለይተን ማየት አንችልም፡፡ የጥያቄዎቻችንን መመለስ እስክናረጋግጥ ከኛ ጀግኖች ጋር ቃል በተጋባነው ሰላማዊ አማራጭ እንደምንፀና ሁሉ፤ ውድ መሪዎቻችንን ዳግም ከማግኘት የሚያግደንን መሰናክል ሁሉ በማለፍና መክፈል የሚገባንን መሰዋእትነት ሁሉ በመክፈል የድል ማማ ላይ እንደምንወጣ ዳግም ቃላችንን እንሰጣለን፡፡ በእነዚህ ቅን የአላህ ባሮች ላይ የምትሰነዘር ትንሿ የቅጣት ጅራፍ ዞሮ ዞሮ ሰንዛሪውን ትገርፋለች፡፡ ፀቡም ከአላህ ጋር በመሆኑ አመፀኞች የታሪክ መማሪያ ይሆኑ ዘንድ የእጃቸውን ያገኛሉ፡፡ ይህ የአላህ ቃል ኪዳን ነው፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ ክበር!

No comments:

Post a Comment