Tuesday, October 23, 2012

ድምጻችን ይሰማ እያልን 10 ወራት ተቆጠሩ፡፡

ድምፃችን ይሰማ
ዒድን አስመልክቶ ወደ ገጠር ለሚሄዱ ወገኖቻችን የተዘጋጀው የአማርኛ ፓምፍሌት


ድምጻችን ይሰማ እያልን 10 ወራት ተቆጠሩ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከጥንትም ጀምሮ በእስልምናችን በሰላም እና በክብር እንዳንኖር አያሌ አጥፊ ተግባሮች ሲፈጸሙብን ቆይቷል፡፡ ይህ በነብዩ ሙአዚን አያታችን ቢላል ላይ የደረሰውን ስቃይ እና እንግልት ያስታውሰናል፡፡ ቢላል በአላህ በማመኑ ብቻ ሕይወቱን በስቃይ እንዲመራ ተገዷል፡፡ ቢላል እስልምናውን እንዲለቅ የአረቢያ የበረሐ አሸዋ ላይ በጠራራ ጸሐይ እንዲተኛ ተደርጎ ተገርፏል፡፡ ጀርባው ላይ ድንጋይ ተጭኖበት የስቃይን ጣሪያ ተመልክቷል፡፡ የአባታችን ቢላል ምላሽ ግን ‹‹አሀዱን አሀድ›› ብቻ የሚል ነበር፡፡

ይህ በአረቢያ ምድር በቢላል ላይ የተጀመረው የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስቃይ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ደርሷል፡፡ በየዘመኑ
በእናት አገራችን ሙስሊም በመሆናችን ብቻ ይፈጸምብን የነበረው የመብት ጥሰት ዛሬም መልኩን ቀይሮ እየተመለከትነው
ነው፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግስት ‹‹አክራሪነትን እዋጋለሁ›› በሚል የሐሰት ሽፋን ሙስሊም መሆንን ከወንጀል በመቁጠር
ስቃያችንን እያበዛው ነው፡፡ ዲናችንን ለማስፋፋት እና ለማስተማር በውድ አባቶቻችን በእነ ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ የተቋቋመው መጅሊስ ለእኛ ለሙስሊሞች አንዳች ኽይር ነገር ከማከናወን ይልቅ በጸረ እስልምና እንቅስቃሴ ውስጥ ዋነኛ ኃይል ሆኗል፡፡ መጅሊስ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት አመራሮቹ በየአምስት አመቱ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሕዝበ ሙስሊሙ እንዲመረጡ ቢደነገግም ለ13 ዓመታት ያህል ምንም ኣይነት ምርጫ ሳይደረግ ተቋሙ በሕገ ወጥ አመራሮች ሲበዘበዝ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ሕገ ወጥ አመራሮች በቂ የአካዳሚክም ሆነ የዲን እውቀት ሳይኖራቸው ሕዝበ ሙስሊሙን በዲኑም በዱንያውም ሲበድሉት ኖረዋል፡፡ የእነዚህ አመራሮች ግላዊ ስብእናም አንድ የሃይማኖት ተቋም አመራር ሊኖረው የሚገባውን የሞራል ብቃት ሊይዙ ቀርቶ ብዙዎቹ
በማኅበረሰባችን ውስጥ መልካም ባልሆነ ስም የሚታወቁ ናቸው፡፡
መጅሊስ ሙስሊሙን አንድ አድርጎ በአብሮነት እንዲመራ ቢመሠረትም በተቃራኒው ግን ሙስሊሙን ኅብረተሰብ በተገኘው አጋጣሚ አንድ እንዳይሆን በርካታ በደል ሲፈፅም ቆይቷል፡፡ የመጅሊስ አመራሮች ይህ ሱፊ ነው ያኛው ወሃቢያ ነው ወዘተ በማለት በኛ በሙስሊሞች መካከል አንድነትና መዋደድ እንዳይኖር ሲጥር ቆይቷል፡፡ መስጂዶቻችን ፍቅር እና ኢስላማዊ አንድነት እንዳይሰበክባቸው በተቃራኒው ጥላቻና ቂም ብቻ የመስጂዶቻችን አጀንዳዎች እንዲሆኑ መጅሊስ ሌት ተቀን ሰርቷል፡፡

መጅሊስ ሙስሊሙን ስለ እምነቱ እንዲያስተምር፣ ዲኑን የማያውቅና ለዲኑ ተቆረቋሪ ሙስሊም ሕብረተሰብ እንዲፈጥር ቢቋቋምም መጅሊሱ በተቃራኒው ለዲኑ ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ ከማድረግ በመቆጠብ ለዲኑ የሚሰሩ ግለሰቦችንና ተቋማትን ለማጥፋት ሌት ተቀን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለዲን እሰራለሁ የሚለው መጅሊስ በታሪኩ በኢትዮጵያ ምድር አንድም መስጂድ አስገንብቶ አያውቅም፡፡ መጅሊሱ በየአመቱ በሀጅ እና ዑምራ ሰበብ የሚሰበስበው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ግለሰብ ኪስ እየገባ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ምንም ዓይነት የዲን ተቋም ባለቤት እንዳይሆን ተደርጓል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ሌሎች የዕምነት ተቋሞች እንዳሏቸው ኢስላማዊ ት/ቤት፣ ሆስፒታል፣ ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎችም ተቋማት ያስፈልጉት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ሊያደርግ ይገባ የነበረው መጅሊስ ምንም በጎ ነገር ሊፈፅምልን አልቻለም፡፡

መጅሊስ በአቅም አልባነት፣ በሙስና፣ በተዝረከረከ አሰራር እና ኋላ ቀር አስተሳሰብ የተተበተበ ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ተተብትቦ ሰርቶ ማሰራት ያቃተው መጅሊስ ያለበትን ችግር አሻሽሎ ለጥሩ ተግባር እንዲንቀሳቀስ ጥረት የምናደርገውን ወገኖች በአክራሪነትና በአሸባሪነት እያስፈረጀ ወህኒ ሲያስወርድ ቆይቷል፡፡ መጅሊሱ ብቃት የለውም፣ በተሻሉ አመራሮችም ይተካ የሚለውን ህዝበ ሙስሊም ለከፍተኛ ችግር ሲዳርግ መቆየቱ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግር እያደረሰ ያለውን መጅሊስ እና አመራሩን ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለ17 ዓመታት ያህል ቢታገስም ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ መጅሊስ ጸረ እስልምና አካሄድን እያጎለበተ ከመጣው መንግስት ጋር በመተባበር አዲስ ከእስልምና አስተምህሮት የወጣ አስተሳሰብ ካልተቀበላችሁ ብሎ ማስገደድ ያዘ፡፡ ይህ አሕባሽ የተባለ መጤና ከፀረ ሙስሊም ኃይሎች ጋር ተባብሮ የሚሰራ ቡድን የያዘውን ፀረ- ኢስላም ዓላማ የኢትዮጵያ ሙስሊም ላይ በግድ ለማጫን መንግስትና መጅሊስ ከሐምሌ 2003 ጀምሮ ዘመቻ ማድረግ ጀመሩ፡፡ የዚህ ጥረታቸው ዋነኛ ዓላማ በዲኑ ፀንቶ የኖረውን የኢትዮጵያ ሙስሊም በመከፋፈል ለሌሎች ተጨማሪ ዓመታት አስተኝቶ መግዛት ነበር፡፡ ሆኖም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ይህንን ሴራ ቀድሞ ተገንዝቦት የነበረ መሆኑ ድርጊቱን እንደ ድፍረት በመቁጠር ሀይማኖቱን ከጥቃት ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
 
መንግስት ህገ መንግስቱን በመጣስ ከህግ በመተላለፍ  በሀይማኖታችን ጣልቃ በመግባት የመጅሊሱን መሪዎች ሲሾምና ሲሽር ከመኖሩም በላይ ዛሬ ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሎት  አዲስ መጤ ኃይማኖት ካልተቀበላችሁ ብሎ ቁም ስቅላችንን እያሳየን ይገኛል፡፡ ይሄ ሁሉ የመንግስት በደል ያስመረረው የኢትዮጵያ ሙስሊም ከጥር 2004 ጀምሮ የአሕባሽን የግዴታ አስተምሮ በመቃወም፣ የመጅሊስ አመራሮች ፍትሃዊ ምርጫን በመጠየቅ እና ትልቁ ተቋማችን አወሊያ ለምን ለአህባሽ ይሰጣል በማለት ተቃውሞውን ሲያሰማ ቆይቷል፡፡ መንግስትና መጅሊስ በሃይማኖታችንና በተቋማችን ላይ እያደረሱ ያሉትን ህገ ወጥ ተግባር ለመቃወም እናንተን ጨምሮ መላው ሕዝብ 17 ታዋቂ ዳዒዎችን፣ ኡስታዞችንና ምሁራንን በመወከል ወደ መንግስት አካላት ጥያቄውን አስይዞ ልኳል፡፡ እነዚህ ብልህ አመራሮች ጥያቄዎቻችንን በመያዝ ከመንግስት አካላት ጋር ውይይት ሲያደርጉ ቢቆዩም ከመንግስት ወገን አንዳችም ጠብ የሚል በጎ ነገር አልነበረም፡፡

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ግን ያነሳቸውን መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎች በማንገብ በሰላማዊ መንገድ ለ አስር ወራት ያህል ንቅናቄውን አሳይቷል፡፡ በእነዚህ አስር ወራት ሙስሊሙ ህዝብ የእርስ በርስ አንድነቱን በማሳደግ የሶደቃና የአንድነት ፕሮግራሞችን መሳተፍ፣ መረጃዎችን በተለያዩ አቅጣጫዎች ዳር እስከዳር በማዳረስ ወዘተ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት አድርጓል፡፡ ውጤቱም በጣም የሠመረ ሆኗል፡፡ አገር አቀፍ ሠላማዊ ንቅናቄያችንን ለማዳከም መንግስት በኦሮሚያ-አሣሣ፣ በአማራ ክልል-ደሴ፣ በአዲስ አበባ-አወሊያና በአንዋር መስጊድ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል ገርባና ደጋን ላይ በርካታ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በተለያዩ ጊዜያት ሙትና ቁስለኛ አድረጎብናል፡፡ የመረጥናቸውን ውድ ኮሚቴዎቻችንን ጨምሮ በርካታ ዳዒዎችን፣ ኡስታዞችን፣ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን እና አርሰቲስቶቻችንን ለእስር ዳርጎብናል፡፡

መንግስት ያሰረብንን የሰላም ተምሳሌት የሆኑ ኮሚቴዎቻችንና ዳዒዎቻችንን አሸባሪ ናቸው በማለት እየወነጀላቸው ይገኛል፡፡
ኮሚቴዎቻችን እኛም ሆነ ሰፊው ሙስሊም ኅብረተሰብ የሚያውቃቸው በሰላም መልዕክተኛነታቸው ነው፡፡ ፍጹም ሰላማዊ የነበረውን ትግላችንን የመሩት እነዚሁ ውድ የኢስላም ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ መሪዎቻችን እርስበርሳችን እንዲሁም ከሌሎች እምነቶች ጋር እንዴት በሰላምና በመከባበር መኖር እንዳለብን ሲያስተምሩን የነበሩ የሰላም ዘቦች ናቸው፡፡ ኮሚቴዎቻችን ሊታሰሩ ሠኣታት እስኪቀራቸው ድረስ በደል እየደረሰባቸው ሁላ ሰላምን ሲሰብኩና ሕዝቡንም ለሰላም ቃል ሲያስገቡት ነበር፡፡ ዛሬ ግን መንግስት የሚሰራውን ሕገ ወጥ ሃይማኖት ነክ አጀንዳ ለማስተው መሞከራቸው አሸባሪ አስባላቸው፡፡ ኮሚቴዎቻችንን ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታችን ፈርድ የተደረገብንን አንድነታችንን ለማጠናከር ስናካሄደው የነበረው የአንድነትና የሶደቃ ፕሮግራም እንኳ በመንግስት እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የሽብር ተግባር ማስፈጸሚያ ተብሏል፡፡ ምን ይሄ ብቻ በየአካባቢው የሚገኙ ኡስታዞች፣ ዳዒዎች፣  ሙአዚኖች፣ ኢማሞችና ኡለማዎች ሁላ መጅሊስ የሚሰራውን ተግባር አንቀበልም በማለታቸው ብቻ አሸባሪ አክራሪ እየተባሉ ወደ እስር ቤት እየተወረወሩ ይገኛሉ፡፡

መንግስት በአጠቃላይ በየአቅጣጫው ሙስሊሞች ላይ የጀመረው ጥቃት ማብቂያው መቼ እንደሆነ በውል አይታወቅም፡፡ መስጊዶች በየአካባቢው ሕገ ወጥ እየተባሉ በፖሊሶች ይፈርሳሉ፡፡ ተማሪዎች ሶላት አትሰግዱም፣ ሂጃብም አትለብሱም እየተባሉ ከት/ቤት ይባረራሉ፡፡ ግን ይሄ ሁሉ በደል በእኛ ላይ ለምን? ለዚህ ሁሉ መንግስት ምላሹን እንዲሰጠን ለ10 ወራት ያህል በሰላማዊ መልኩ ብንጠይቀውም መልስ ሊሰጠን አልቻለም፡፡ አሁንም መንግስት ምላሽ እንዲሠጠን በተባበረ ክንድና ድምጽ ሰላማዊ ትግላችንን በማጠናከር እንጠይቀዋለን፡፡

ትግሉ የሁላችንም ነው፡፡ ገጠርና ከተማን አይለይም፡፡ በእድሜ፣ በጾታ፣ በስራ ባህሪ፣ በማህበራዊ ደረጃ፣ ከባህር መለስ እና ከባህር ማዶ ተብሎ አይለይም፡፡ ሙስሊም የተባለን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ ትግሉም የሚጠይቀው የሁላችንንም አስተዋጽኦ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት ያነሳናቸውን ሰላማዊ የመብት ትያቄዎች በአግባቡ እስኪመልስልን ድረስ በትግላችን በመጠናከር፣ ጥያቄያችን ላልገባቸው ወገኖች ጣያቄችንን በማስረዳት፣ ከመንግስት አካላት የሚመጣብንን ግፊት በመቋቋምና ሰላምን መርህ በማድረግ በአላህም ዱዓእ በመታገዝ ወደ ፊት እንጓዝ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ ክበር!

No comments:

Post a Comment