Thursday, October 4, 2012

በምርጫው የማንሳተፍበት 8 እጅግ መሠረታዊ ምክንያቶች


- በነስሩዲን ዑስማን

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ስር የተቋቋመው እና ለስሙ እንኳ የሚመጥን ቁመና (stature) የሌለው፣ በራሱ ጭንቅላት ሳይሆን በመንግሥት (በተለይም በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለሥልጣናት) ጭንቅላት እየተሽከረከረ ያለው ‹‹የዑለማ ምክር ቤት›› ባስታወቀው መሠረት (ከማስታወቅ የዘለለ ሚና ለመጫወት አቅምም ሥልጣንም የለውም) መስከረም 27፣ 2005 ሊካሄድ በታቀደው የመንግጅሊስ አመራሮች ምርጫ ላይ ኢትዮጵያውያን ሙስ
ሊሞች በመራጭነትም ሆነ በአስመራጭነት አንሳተፍም፤ ልንሳተፍም አይገባንም፡፡ በዚህ ‹‹ምርጫ›› ላይ የማንሳተፍበት በርካታ ተያያዥ ምክንያቶች አሉን፡፡ በዚህ ጽሑፌ በጣም አንኳር የሆኑትን ብቻ ለሙስሊም እና ሙስሊም ላልሆኑትም ወገኖቻችን ግልፅ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ …

1. ጉልቻ ለመለወጥ በሚካሄድ ሩጫ ላይ አሯሯጭ መሆን አንፈልግም፡፡ እኛ ሙስሊሞች አዲስ እና ነፃ የመጅሊስ ምርጫ እንዲካሄድ የጠየቅነው፣ በሥልጣን ላይ ያለው የመጅሊስ አመራር ከመንግሥት ጋር ዶልቶ የአህባሽን አስተምህሮ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ በግድ ለመጫን የከፈተው ዘመቻ እና መዘዞቹ በማያዳግም መልኩ ሊቆሙ የሚችሉት መጅሊሱ ከአህባሽ ሲፀዳ ብቻ ነው ብለን ስላመንን ነው፡፡ ነገር ግን አህባሻዊው የዑለማ ምክር ቤት እና መንግስት ሊያካሂዱ የሚሯሯጡለት ምርጫ፣ መጅሊሱ ከአህባሽ ቁጥጥር ሥር እንዳይወጣ ለማድረግ፣ አልያም እንደተለመደው ለሃይማኖታቸው ደንታ የሌላቸውን የመንግስት አሻንጉሊቶች ለማስቀመጥ የታለመ እንደሆነ በአሁኑ ሰዓት ራሱ መንግስት ቀበቶውን አጥብቆ፣ ዓይኑን በጨው አጥቦ ከሚሠራቸው በሰነድ ማስረጃ የተረጋገጡ አሳፋሪ ሥራዎች በውል ተረድተናል፡፡ ስለዚህም አህባሻዊ አመራርን በሌላ አህባሻዊ አመራር ለመተካት፣ አልያም ለኢስላምና ለሙስሊሞች ደንታ የሌለው ጥቅመኛ የመንግስት አሽከርን አስወግዶ ሌላ ተመሳሳይ አሽከር ለመተካት በሚደረግ ሩጫ ላይ በአሯሯጭነት ተሰልፈን ለህገ ወጥ ተግባር ህጋዊ መልክ የማስገኘት ሚና ለመጫወት አንፈልግም፡፡ ስለዚህም እኛ የለንበትም፡፡

2. እኛ ሙስሊሞች አዲስ እና ነፃ የመጅሊስ ምርጫ እንዲካሄድ የጠየቅነው በመጅሊሱ አመራር ላይ አህባሽ ያልሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በስነ ምግባር፣ በሃይማኖታዊም ሆነ በዘመናዊ ትምህርት፣ በአገር ወዳድነት እና በህዝብ አገልጋይነት እና ተቆርቋሪነታቸው የሚታወቁ ብቁ ሰዎችን ለመምረጥ እና መጅሊሱን ከተተበተበበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢቻል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማላቀቅ አስበን ነው፡፡ በእኛ እምነት ይህ ዕውን ቢደረግ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥትም፣ መላው ህዝብም፣ አገርም ይጠቀማሉ እንጂ የሚጎዳ አይኖርም፡፡ አሁን ምርጫው ሊካሄድ በታሰበበት መልኩ ግን ይህ የህዝቡ የጋራ ፍላጎት ዕውን ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም፣ የተጨማለቀ መንግጅሊስን በሌላ የሚጨማለቅ መንግጅሊስ ለመተካት በሚካሄድ ምርጫ ላይ አንሳተፍም፡፡

3. በተጠራቀሙ ብሶቶች አወሊያ ላይ የተሰባሰበ ህዝበ ሙስሊም ከመጅሊሱ ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎቹ ዘላቂ መፍትኄ በመሻት ኮሚቴዎችን መርጦ በእነርሱ በኩል ጥያቄዎቹን ለመንግሥት ቢያቀርብም፣ የመንግሥት ምላሽ የኮሚቴውን አባላት፣ የእንቅስቃሴው ደጋፊ ዳዒዎችን፣ ዱዓቶችን፣ የመስጂድ ኢማሞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን እና እጅግ በርካታ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አባላትን ለእስር፣ ለድብደባና ለእንግልት መዳረግ ሆኗል፡፡ እነዚህ እርምጃዎች መንግሥት የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆኑን በግልፅ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ የመብት ጥያቄዎቻችንን ለመንግሥት እንዲያደርሱልን ፈርመን የመረጥናቸው ወኪሎች ያለ አንዳች ጥፋት ታስረውና የዋስትና መብት ተነፍገው ወህኒ ቤት እየማቀቁ በሚገኙበት በአሁኑ ሰአት፣ ከፈቃዳችን ውጪ ሊካሄድ በታቀደው ምርጫ ላይ መሳተፍ ማለት የመብታችን ተሟጋቾችን መሸጥ ማለት ነው፡፡ መብትን መጠየቅ የሚያሳስር ከሆነ እኛም ተራው ደርሶን እስክንታሰር፣ አልያም ጥያቄዎቻችን እስኪመለሱ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን እንጂ፣ በምንም ዓይነት የወከልናቸውን የኮሚቴ አባላትና መብትን የማስከበር ሰላማዊ ትግላችን ደጋፊ ወንድሞቻችንን እና አባቶቻችንን ከድተን በህገ ወጥ ምርጫ ለመሳተፍ እግራችንን አናነሳም፡፡

4. የአገሪቱን ህዝቦች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በሚገዛው ሕገ መንግሥት የዜጎች መብቶች በግልፅ የተደነገጉ ሆነው ሳለ፣ መንግሥት ‹‹አክራሪነትን›› በመዋጋት ሽፋን በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 27 የሰፈሩትን የሃይማኖት ነፃነት መብቶች ለመገደብ ዳር ዳር እያለ ይገኛል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይህን ፀረ ሕገ መንግሥት ዓላማ ራሱ ፊት ለፊት ሊፈፅመው አይፈልግም፡፡ … ሙስሊም ዜጎችን በተመለከተ መንግሥት ይህን ዕኩይ ዓላማውን ተፈፃሚ ለማድረግ ለእርሱ ፈቃድ ሰጥ ለጥ ብሎ የሚያድር፣ ከመጋረጃ ጀርባ በሚቀመጥ ካድሬ የሚታዘዝ አሻንጉሊት መጅሊስ እንዲኖር ይሻል፡፡ ከዚያም የዚህን አሻንጉሊት መጅሊስ ሥልጣን እና ተግባራት በአዋጅ ደንግጎ ማንኛውንም ኢስላማዊ እንቅስቃሴ (መድረሳ መክፈት፣ መስጂድ መገንባት፣ በመስጂድ ዳዕዋ ማድረግ፣ ከመስጂድም ውጪ በሲዲ፣ በመጻሕፍት፣ በመፅሔት፣ በጋዜጣ ወዘተ. የዲን ትምህርትን ማሰራጨት) የመሳሰሉትን ተግባራት በመጅሊሱ ፈቃድና ይሁንታ ብቻ የሚካሄዱ ለማድረግ ይፈልጋል፡፡ ይህም ማለት የሙስሊም ዜጎችን በሕገ መንግሥት የተረጋገጡ መብቶች በመጅሊስ የማቋቋሚያ አዋጅ ሥር እንዲወድቁ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህ መረጃ በግምት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ኃይለማርያም በአንድ የአህባሽ ሥልጠና መድረክ ላይ፣ የመጅሊሱ ሊቀ መንበር አህመዲን ጨሎ የሰጠውን አስተያየት ተከትለው በግልፅ የተናገሩት ነው፡፡ ሚኒስትሩ እንዲያውም መንግሥት የጁሙዓ ኹጥባም በመጅሊሱ ተዘጋጅቶ ለኢማሞች እንዲሰጥ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ … የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ ይህንን የመንግሥት ሐሳብ ወደተግባር ለመቀየር በታህሳስ/ጥር 2004 የሥራ ዕቅዱ ውስጥ አካትቶት ነበር፡፡ ዕቅዱ ‹‹የምክር ቤቱን ሥልጣንና ተግባር አዋጅ በፍጥነት እንዲወጣ ማድረግ፣ በአዋጁ ውስጥ ኢስላማዊ ህትመቶችን የመቆጣጠር ስልጣን እንዲካተት ወዘተ.›› የማድረግ ዓላማ ነበረው፡፡ ነገር ግን ዕቅዱ ሊተገበር በታሰበበት ወቅት የሙስሊሙ ኅብረተሰብ የመብት ንቅናቄ በመጀመሩ ይመስላል አዋጁ እስካሁን አልወጣም፤ ወይም ስለመውጣቱ አልሰማንም፡፡

… በአሁኑ ጊዜ መንግስት የመጅሊስን ጉዳይ የራሱ ዐብይ አጀንዳ አድርጎ ከሙስሊሙ ህዝብ ፈቃድ ውጪ የሆነ የመጅሊስ ምርጫ ለማካሄድ የሚሯሯጠው እኒህን መሰል እኩይ ዓላማዎችን ሰጥ ለጥ ብሎ የሚያስፈፅም፣ ለሃይማኖቱ ደንታ የሌለው አሻንጉሊት መጅሊስ እንዲኖር አጥብቆ ስለሚፈልግ ነው፡፡ ስለዚህም ምርጫውን በማንኛውም መንገድ፣ የሰፈሬ ልጆች በፋራም በአራዳም እንደሚሉት፣ አካሂዶ የህዝበ ሙስሊሙ የምርጫ ጥያቄ ተመልሷል ለማለት ይፈልጋል፡፡ …. ከዚያ በኋላስ? ከዚያ በኋላማ የሚፈልጋቸውን ኢስላማዊ እንቅስቃሴን ለማዳከም የታለሙ ትዕዛዛት ለአሻንጉሊቶቹ እያስተላለፈ የሙስሊሙን ህገ መንግሥታዊ መብት በሙስሊም አሻንጉሊቶቹ ያስደፈጥጣል፡፡ በዚያን ጊዜ ‹‹ኧረ የመንግሥት ያለህ!›› እያልን ብንጮህ የሚሰጠን መልስ ‹‹እኔ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አልገባም!›› የሚል እንደሚሆን ቅንጣት ታህል ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ስለዚህም በመስከረም 27ቱ ምርጫ ላይ በየትኛውም ደረጃ መሳተፍ፣ ለዚህ የመንግሥት ዕኩይ ዓላማ ግብረ አበር ከመሆን የዘለለ፣ በገዛ አንገታችን ላይ የሸምቀቆውን ገመድ ከማጥለቅ የተለየ አንዳችም ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህም አንመርጥም፣ አናስመርጥም፡፡

5. በጽዮናውያን ተጠፍጥፎ የተሠራው አህባሽ በተመሠረተበት በሊባኖስም ሆነ በአውሮጳና በአሜሪካ፣ በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ስሙም በእንግሊዝኛ Association of Islamic Charitable Projects (AICP) ሲኾን፣ በሊባኖስ ወደ አንድ የታጠቀ የፖለቲካ ኃይልነት አድጓል፡፡ ድርጅቱ የሚያራምደውን አስተሳሰብ በጥልቀት የሚመለከት ማንኛውም ሙስሊም የድርጅቱ ተልዕኮ በአጭሩ ‹የኢስላምን ለምድ ለብሶ ኢስላምን መቦርቦር› መሆኑን ይረዳል፡፡ ከመቦርቦሪያ መሣሪያዎቹ አንዱ በመሠረታዊ የኢስላም አስተምህሮዎች ላይ አፈንጋጭ ብይኖችን በመስጠት ሙስሊሞችን እርስ በርሳቸው ማወዛገብ፣ ከተሳካም መከፋፈል ነው፡፡ ይህ ድርጊቱ በቁርአንና በነቢዩ (ሶ.ዐ.ወ) ሐዲስ ላይ ከተመሠረተው የአንድነት አስተምህሮ ጋር የሚቃረን ተግባር ነው፡፡ መንግሥት የጽዮናውያንን ፈቃድ ለመሙላት የተጋባው ውል ኖሮት ይሁን በሌላ ምክንያት ይህንን አወዛጋቢና ከፋፋይ አጀንዳ ያነገበ ቡድን ‹‹የኢትዮጵያ ነባሩ እስልምና›› የሚል ስያሜ ሰጥቶ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ ለማንገስ እንቅልፍ አጥቷል፡፡ ይህ ዕውን የሚሆነው ግን፣ መንግሥት እንዲህ በሃይማኖታችን ጉዳይ ውስጥ ገብቶ ሲፈተፍት እኛ ‹‹ምን ግዳችን›› ብለን ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የተኛን እንደሆን ብቻ ነው፡፡ አልሃምዱሊላህ! እስካሁን አልተኛንም፤ ኢንሻአላህ ወደፊትም አንተኛም!!! ስለዚህም አ ን መ ር ጥም!

6. የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የጋራ ተቋም እንደመሆኑ፣ የተለያዩ የአስተሳሰብ ፈለጎች (መስመሮች) ሲኖሩ (ከኢስላም ማዕቀፍ እስካልወጡ ድረስ) በእውቀት ላይ ተመሥርቶ ሁሉንም የሚያቻችል ሚዛን መፍጠር፣ መላውን ሙስሊም በእኩል ዓይን አይቶ ማስተናገድ ይጠበቅበታል፡፡ ከቶውንም ከመሠረቱ ‹‹ይሄኛው ምንትሴ፣ ያኛው ቅብጥርሴ›› እያለ የመከፋፈል ሚና የሚጫወት ተቋም አይደለም፡፡ ታላቁ የመጅሊሱ መሥራች አባት ሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ (ረሂመሁላህ) ይህንን ሚዛን ጠብቀው፣ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ አስማምተው፣ በዕውቀትና በብስለት የመሩ ሲኾን፣ ዛሬም ይህንን ማድረግ የሚችሉ የበሰሉና የበቁ ዓሊሞች (የሃይማኖትና የአካዳሚ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን) አሉ፡፡ … በአንጻሩ አላህን (ሱ.ወ) የማይፈሩ የአህባሻዊው ዑለማ ምክር ቤት ‹‹ሸኾች›› ጠንቋይ ይመስል ‹‹እንቶኔን አክራሪ ነው ብለን ፈርደናል!›› እያሉ ቴሌቪዥን ሲቀረፁ፣ የሆድ ነገር ሆኖባቸው እነሱ ባያፍሩ ስለ ደማቁ ማይምነታቸው እኛ በኃፍረት ተሸማቅቀናል፡፡ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ታዛ ሥር ያሉ አለቆቻቸውን አስደስት ብለው የተሰጣቸውን ሲያነብቡ እኛን በገዛ አገራችን አንገት አስደፍተውናል በብሽቀት፡፡ ለዚህም ነው ከፋፋዩ ‹‹አህባሻዊ መንግጅሊስ ይወገድ!››፣ ‹‹በመላው ሙስሊም የጋራ ፈቃድ፣ ፍላጎት እና ነፃ ምርጫ ላይ የተመሠረተ መጅሊስ ይመረጥ!›› የምንለው፡፡ ይህ ዕውን እስኪሆን ድረስ፣ አህባሻዊ የመንግጅሊስ አመራሮችን በሌላ አህባሻዊ አመራሮች ለመተካት ባለመ ቅርጫ ላይ በየትኛውም ደረጃ በፍፁም እጃችንን አናስገባም፤ አንመርጥም፤ አናስመርጥም፡፡

7. ትናንት (በ1950ዎቹ) ሊባኖስ ውስጥ በበጎ አድራጎት ድርጅት ስም የተፈጠረው Association of Islamic Charitable Projects (AICP)፣ በኢትዮጵያም ከ1996 ጀምሮ በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ተመዝግቦ ሲንቀሳቀስ የቆየው አህባሽ፣ ዛሬ በመንግስት ‹‹መልካም ቸርነት›› መንበረ መንግጅሊሱን ይዞ፣ የህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞ እያየለ በመጣበት ወቅት ደግሞ አዳማ ላይ በተጠራ ጉባዔ ራሱን ‹‹አህለ ሱና ወልጀመዓ ወስሱፊ ወሻፊኢይ …›› ወዘተ. ብሎ በመጥራት እነሆ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ የመፍረድ እና የመቅደድ ‹‹ሥልጣን›› ተጎናፅፏል፡፡ ስንት ታላላቅ ዓሊሞች ባሉባት በዚህች አገር ማን ሙስሊም እንደሆነ፣ ማን እንዳልሆነ፤ ማን አክራሪ እንደሆነ፣ ማን እንዳልሆነ፤ ማን በመጅሊስ ምርጫ ላይ መምረጥ፣ ማስመረጥ እና መመረጥ እንደሚችል፣ ማን እንደማይችል፤ የማን አለባበስ ኢስላማዊ እንደሆነ፣ የማን እንዳልሆነ ይፈርዳል፤ ይቀድዳል፡፡ ስንት ድንቅ ዓሊሞች ባሉባት አገራችን ይህ እንዲሆን መንግስት ‹‹መልካም ፈቃዱ›› ሆነ፡፡ የመንግጅሊሱ ታናሽ ወንድም የሆነው የዑለማ ምክር ቤትና መንግስት መስከረም 27 ሊያካሂዱ ያቀዱት ቅርጫ በአዲስ ምርጫ ስም ይህንኑ የማን ርዕይ እንደሆነ ያልታወቀ ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› የማስቀጠል ዓላማ እንዳለው ከአጠቃላይ እንቅስቃሴው በግልፅ መረዳት ይቻላል፡፡ ታዲያ እኛ የማንን ርዕይ እናስቀጥል ብለን ነው በዚህ ቅርጫ ላይ የምንሳተፈው?! …

8. እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ይህን ‹‹ኢህአዴጋዊ ቸርነት›› አንቀበልም አልን፡፡ እምቢ ስላልን ግን ስሞች ተቀጠሉብን ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ››፣ ‹‹አክራሪ››፣ ‹‹ጽንፈኛ››፣ ‹‹ነውጠኛ››፣ ‹‹እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት የሚያልሙ›› ወዘተ. ወዘተ. ተባልን፡፡ ዛሬ በእስር ላይ የሚገኘው ወንድማችን ዑስታዝ በድሩ አንድ ጁሙዓ ዕለት አወሊያ ላይ የተናረው ንግግር እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይገባዋል፡፡ ‹‹ትልቁ ነገር የሚሉንን ሁሉ አለመሆናችን ነው አልሃምዱሊላህ!›› … ፍፁም ሰላማዊ ሆነንም ግን በህገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶቻችንን አሳልፈን ለመስጠት አልፈቀድንም፤ አንፈቅድምም፡፡ በዚህ ፅኑ የጋራ አቋማችን ምክንያት አያሌ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን እና አባቶቻችን ታስረዋል፤ ተደብድበዋል፣ ጥቂቶችም አሳሳ ላይ ተገድለዋል፡፡
መንግሥት ከፅኑ አቋማችን ጀርባ ያሉትን ተጨባጭ እውነታዎች በጥሞና ለማጤን እና ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ፣ እኛን ሚሊዮኖቹን በጠላትነት ፈርጆ፣ የእኛኑ የጋራ ተቋም እርሱ እንጂ እኛ በማናውቃቸው፣ ስለዚህም በማናምናቸው ሰዎች ለመሙላት አብዝቶ ሽር ጉድ እያለ ነው፡፡ ታዲያ እኛ መንግስት ከራሱ ስውር መርኃ ግብር አኳያ በቃኘው፣ የህዝበ ሙስሊሙን ፈቃድም ሆነ ፍላጎት ከመጤፍ ባልቆጠረ ህገ ወጥ ቅርጫ ላይ የምንሳተፈው ከቶ ምን ቤት ነን ብለን ነው?!

ከዚህ በላይ ከጠቀስኳቸው ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በመንግስት ፊታውራሪነት ሊካሄድ የታቀደው ህገ ወጥ ምርጫ አራት ቀናት ብቻ በቀሩት በአሁኑ ሰአት እኒህን አንኳር ምክንያቶች በጥልቀት መረዳት ብቻ ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ላይ የማያወላዳ አቋም ለመያዝ ያስችለናል ብዬ ተስፋ አደፈርጋለሁ፡፡ እኛ አቋም ይዘን ብቻ ግን አናቆምም፡፡ የነገሩ የቅርብ እና የሩቅ ጊዜ አንድምታ ላልገባቸው ወንድም፣ እህት፣ እናት እና አባቶቻችን የነገሩን ውል በሚገባ ልናስጨብጣቸው፤ አስጨብጠንም በመስከረም 27ቱ ቅርጫ ላይ ለመሳተፍ ከቤት እግራቸውን እንዳያነሱ ልናደርግ ግድ ይለናል፡፡

በተቻላችሁ መጠን ይህን ጽሑፍ አትማችሁ በማባዛት ፌስቡክ ለማይጠቀሙ ወገኖች በማዳረስ የድርሻችሁን እንድትወጡ በአላህ ስም እንጠይቃለን፡፡ አላህ ያግዘን፡፡ ወሏሁ አዕለም፡፡

No comments:

Post a Comment