Saturday, October 6, 2012

እሁድን በሰደቃና ዱዓ!

በዕለቱም ከወዲሁ ክስረቱ የተረጋገጠው ቅርጫ ከሚደረግባቸው ጣቢያዎች እራሳችንን በማራቅ ካድሬዎቹ "አረ የመራጭ ያለህ!" እያሉ ፀሐይ እንዲሞቁ እናደርጋቸዋለን፡፡

እሁድን በሰደቃና ዱዓ!
• ሙስሊሙን ህብረተሰብ በገዛ አገሩ እምነቱን መተግበር፤መማር ማስተማር እንዳይችል አድርጎ ላይነሳ ለመቅበር የተደረገውን ሴራ የገባው ሙስሊም ማህበረሰብ ከጅማሮው ለመቅጨት በነቂስ ወጥቶ መቃወም ከጀመረ አመት ሊሞላው ነው፡፡
• ተሰባስበን ጥያቄአችን ይመለስ፤ መብታችን አይረገጥ፤ድምጻችን ይሰማ ብለን ደጋግመን ጮኽን፡፡ የመንግስት ምላሽ ሆኖ ያገኘነው ግን በማን አለብኝነት በሀሰት ውንጀላና ማጠልሸት ሆነ፤ ያኔ ውንጀላው በሬ ወለድ ነው ብለን ጮህን ወደ አላህም አለቀስን፤ አልሃምዱሊላሀ የአለህ ፍቃድ ሆኖ እኛን ማስቆም አልተሳካለትም፤
• ችላ ያለ በማስመሰል ለማሰልቸት ሞከረ፡-ሰብር እነደሚያስፈልገን አውቀን ታገስን በዚህም ጠንካራ ብርታት አገኘን፤ በዚህም የትዕግስት ውጤት የሆነውን ፅናት አጎናጸፈን፤ እኛን ማስቆምም አልታካላቸውም፡፡ አልሃምዱሊላህ!
• እኛ በትዕግስት በዱዓ ተበራትተን መልስ ስንጠብቅ ማን አለብኝ ባዩ አለኝ የሚለውን ጉልበት ሁሉ ተጠቅሞ ጸጥ ለማሰኘት ፡-ደበደበን፤ ከፊሉን ገደለ ፤አሰረን፡፡ አሁም በአላህ ፍቃድ ዋናውን የትዕግስት (በከባድ ችግር ግዜ) ካባ እንድንጎናጸፍ እና ፅናት አስተምሮን አለፈ አልሃዱሊላህ፡፡ የዱላውም፣ የጥይቱም ውርጅብኝ የአጅር ናዳና የፅናት ካባ አከናንቦን ለዛሬው ማንነታችን አበቃን፤ ወይ ፍንክች፡፡
• ህዝባዊው ተቃውሞው ሀ ተብሎ ከተጀመረ ግዜ ጀምሮ ከመንግስት ውክቢያ እና እንግልት አንጻር ሂደቱ መቀጨጭና ወደ ህዝባዊ ነውጥ መቀየር ምኞታቸው የነበረ ቢሆንም በተቃራኒው ተቃውሞው በአገር አቀፍ ደረጃ መዛመትና ሂደቱም ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ ተቀጣጥሎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
• ለዚህ ሁሉ የተቃውሞ ግዝፈት፣የህዝቡ ትዕግስት፣ ጽናት ሚስጥሩ እያንዳንደዱ ሙስሊም ህብረተሰብ አላህ ያጎናፀፈውን ማንንም ብርቱ የሚያንበረክከውንና ማንም የማይማርከውን ዱዓ የሚባለውን መሳሪያ በመጠቀም እንጂ በምንም አይደለም፡፡ እስቲ እናስታውስ የዱዓ ጥንካሪያችን ምን ይመስል ነበር?ዱዓችን ተቀባይነት እንዲያገኝ ወደ አላህ የምንቃረብባቸውን ተግባራት አስታውሱ፡፡ ህዝብን ከጫፍ ጫፍ ያነቃነቁ ነበሩ...ሰደቃ፣አውፍ መባባል፣ዚያራ...ይህ ባለበት ወቅት ነበር ሽህሩል በረካ ረመዳን መጥቶ የበለጠ ወደ አላህ ቅርበታችንን ያጠናከርንበት፡፡ በነዚህ ወቅቶች የተደረጉ ዱዓዎች ዛሬ ላይ ላለንበት የአላማ ጽናት(ዲንን የማስጠበቅ)በልኬት የማይሰፈሩ ድሎች ያጎናጸፈን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ግን ጉዞአችንን አልጨረስንም ጠላቶችም ጥቃቶቻቸውን አጠናክረው እኛንም አጠናክረውን እንገኛለን፤ በመሆኑም ይህንን የጠላት ግልጽ እና የተደበቁ ሴራዎችን ለመመከት ብሎም ድል ለማድረግ በእጃችን ያለውን ማንም የማይቀማንን መሳሪያችን--ዱዓ--ከመጠቀም የተዘናጋን ይመስላል፡፡
• ዱዓችንም የተፈለገለትን አላማ ይዋል ይደር እንጂ ግቡን መምታቱ አይቀሬ ነው ምክንያቱም ተበዳዮች ነን የተበዳይ ዱዓ ደግሞ ወይ ፍንክች ጠብ አትልም--ለሁሉም ግዜ ይፈታወል፡፡ ዱዓችን ግን ግቡን ይመታ ዘንድ ወደ አላህ ቀረብ ማለት ግድ ይለናል፡፡ በተለያዩ ኢባዳዎች በርትተን የአላህን ውዴታ እንፈልግ---ጎበዝ እያንዳንዳችን እጅ ላይ ያለውን መሳሪያ እንጠቀምበት፡፡ ቁጭ ብሎ ማውራት ሳይሆን ደበቅ ብሎ ወደ አላህ ማልቀስ፡፡ ወደ አላህ ለማልቀስም ረጠብ ያለ ልብ ያስፈልገናልና ሰደቃዎች ላይ እንበርታ፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በቅርጫ-ምርጫው እለት ሁላችንም የሚከተሉትን ተግባራት እንድከናውን መልእክት ተላልፏል፡፡

1. የምርጫውን ፍፁም ህገወጥነት ዳግም ማስተጋባት፡- ባለፉት ጁምአዎች በተለይም በቢጫው ማዕበል በምንም አይነት ጥበብ እና የተለመደ ባዶ ፕሮፖጋንዳ ተሞልተው ቅርጫውን ቢከፋፈሉት እንኳን ህጋዊ መሰረት እንደሌለው በፀና አቋም ውድቅ አድርገነዋል፡፡ ይህንኑ አቋማችንን በእለቱ እያንዳንዳችን ቢያንስ ለሶስት ሰው ህገወጥነቱን በተጨባጭ ማስረጃዎች እናስረዳለን፡፡ በአሜሪካ፤ አውሮፓ፤ መካከለኛው ምስራቅና በሌሎች ሃገራት የምትኖሩ ከአንድ ሚሊዮን የምትበልጡ ሙስሊም የዲያስፖራ አባላት እያንዳችሁ ለቤተሰቦቻችሁ በመደወል ምርጫው ላይ መሳተፍ ማለት ለአህባሻዊው መጅሊስ እውቅና መስጠት መሆኑን አስረድተን አለመምረጣቸውን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡ ቤተሰቦቻችሁንም ለጎረቤቶቻቸው እንዲያስተላልፉ ሃላፊነት ብትሰጡ ውጤቱ እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡
2. እለቱን የዚህ በላእ ገፈት ቀማሽ የሆንን መላው ሙስሊሞች እና የግፍ ቀንበሩን ከላያችን ላይ ለማንሳት የምንጥር የትግል አጋሮች በሙሉ በሰደቃና በመልካም ተግባራት እንድናሳልፍ ከባድ አደራ እንላለን፡፡ ታላቁ ነብይ ሙሃመድ (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ከሰደቃዎች ሁሉ በላጩ አንዳችሁ በባለቤቱ አፍ ላይ የሚያኖረው ጉርሻ ነው›› ብለዋል፡፡ ቢያንስ ይህንን በመተግበር ከትንሷ ሳንቲም ጀምሮ የቻልነውን የሰደቃ አይነት በመስጠት ወደ አላህ እንቃረብ፡፡ የታመመን በመጠየቅ የተቸገረን በመርዳት ወዘተ እንረባረብ፡፡ በቢጫው ማዕበል ሃላፊነታችንን የተወጣን በሙሉ ይሀንንም ሃላፊነታችንን ያለማንም ቀስቃሽ በእለቱ እንድንወጣ አደራ አደራ፡፡
በአጠቃላይ ይህንን በላእ አላህ እንዲመልስልን፤መና እና ከንቱ ያደርግልን ዘንድ እለቱን ስለ ህገ ወጥነቱ በማውራት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ሰደቃ እየሰጠን፤ ዱዓ እያደረግን አላህን ከልብ መማጸን፤ ጀምዓ ሰላቶችን በሙሉ በመስጂድ ውሥጥ ተሰብስበን በመስገድ እየተፈጸምብን ያለውን የመብት ጥሰት በጥበቡ እንዲያከሽፈው ከልብ መማጸን ይኖርብናል፡፡
• ይህ ሁሉ ኢስላምን የማዳከም ተግባር በሰላም ተጋፍጠን እዚህ ደርሰናል፡፡ ብርቅዬ ዱዓቶችና ወህኒ ተግዘዋል፡፡ የመጣብንን በላእ አላህ እንዲመልስልን ወደ እሱ ቅርብ ወደሚያደርገንና የማንንም ይሁንታ፣ድጋፍ፣ ሙገሳ፣ የማየሻውን ተግባር ነውና እንዳንዘናጋ፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሃገሪቱ የምንገኝ ሙስሊሞች የእሁዱን እለት በዚህ መሰሉ የኸይር ስራ በመሰማራት እርዳታን ከሃያሉ አላህ እንማፀናለን፡፡ በዕለቱም ከወዲሁ ክስረቱ የተረጋገጠው ቅርጫ ከሚደረግባቸው ጣቢያዎች እራሳችንን በማራቅ ካድሬዎቹ "አረ የመራጭ ያለህ!" እያሉ ፀሐይ እንዲሞቁ እናደርጋቸዋለን፡፡

 

No comments:

Post a Comment