Sunday, October 14, 2012

ድላችንን እያጣጣምን ትግላችንን እንቀጥላለን!

ድላችንን እያጣጣምን ትግላችንን እንቀጥላለን!

ማንኛውም ህብረተሰባዊ ሰላማዊ ትግል እርከንና ደረጃዎች ይኖሩታል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እምነታቸው እስልምና ላይ የተከፈተባቸውን ዘመቻ ለመመከት ቆርጠው የተነሱበት ትግል እርከኖችና ደረጃዎች ነበሩት። ከአንዱ እርከን ወደ አንዱ ተዛውሮ ቀጣዩን እርከን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ሁለት ነገሮችን የግድ ይፈልጋል፡- ያለፈውን እርከን ውጤት ማጣጣምና ለሚቀጥለው እርከን በብርቱ መዘጋጀት።

እንደሚታወቀው ካለፈው ትግላችን ያተረፍናቸው በርካታ ነገሮች ነበሩ። በዚህ የአስር ወራት ትግላችን በአላህ ጸጋ ካልሆነ በምንም የማይገኘውን ኢስላማዊ ወንድማማችነት አትርፈናል። በዚህ ረገድ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ካሁን ቀደም የነበሩበትን ጉድለቶች በሚገባ አክሞ የመቻቻል ባህሪውን አሳድጓል። ከሙስሊሙ ህብረተሰብ አልፎም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞች ጋር የነበረውን ለዘመናት የዘለቀ ሰላማዊ አንድነት አጠናክሯል።
በዚህ የአስር ወራት ትግል በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የዲን ተቆርቋሪነት ተስተውሏል። ይህም ሁሉንም ያጠቃለለ እንጂ የጥቂቶች ብቻ አልነበረም። ከወጣቱ እስከ አዛውንቱ፣ ከሴቱ እስከወንዱ፣ ከነጋዴው እስከ አርሶ አደሩ፣ ከተማሪው እስከ ጉልበት ሰራተኛው ድረስ በጋራ ተንቀሳቅሷል። ጥቃቱን ለመመከት የተባበረ ድምጹን አሰምቷል። በዚህ የአስር ወራት ትግል ለዲን የሚከፈል መስዋእትነት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል በተግባር ታይቷል። መስዋእትነት ለመክፈል ምሉእ ጉጉት ያላሳየ የማህበረሰብ ክፍል አልነበረም። ዲናቸው ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከት በሚያደርጉት ትግል በእስር ቤት የማቀቁ፣ የቶርች ድብደባ ሰለባ የሆኑ፣ ወዳልታወቁ ቦታዎች ተወስደው የተደበደቡ፣ የጥይት አረር ሰለባ የሆኑ፣ አካላቸው የተጎዳ፣ የበርካታ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ የሆኑ ሺዎች ከምርጦቹ ኮሚቴዎቻችን ጀምሮ በትእግስት አሳልፈዋል። ለቀጣይ መስዋእትነትም ሙሉ ፈቃደኝነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።

በዚህ የአስር ወራት ትግል አማኞች ከአላህ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አድሰዋል። በጾምና በዱዓ ከፊቱ ተዋድቀዋል። ፈተናቸውን ይወጡ ዘንድ እንዲረዳቸው ለሱጁድ ተደፍተው ለምነዋል። ለአላህ ሲሉ በሚያደርጉት ትግልም በርሱ ስም እርስ በርስ ተዋድደዋል። የመተሳሰብና የመዋደድ ደረጃቸው ከፍ ብሏል። አንዱ ሌላውን ለመንከባከብ ጉጉት አሳይቷል። ለአንዱ የተሰነዘረውን እስርና ዱላ ሌላው በውዴታ ተጋፍጧል።
ከምንም ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ተረግጦና መብትን አጥቶ ከመኖር ይልቅ መብትን በድፍረት የመጠየቅን ዋጋ በሚገባ ተረድቷል፤ አጣጥሟል። ይህ ደግሞ ጭቆናን እስከናካቴው ለማስወገድ ከሚያፈልጉ ግብአቶች ዋነኛውና እጅግ አንገብጋቢው ነው። እንግዲህ እኒህ ከላይ የተጠቃቀሱት በትግላችን ካተረፍናቸው ድሎች እጅግ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ድሎች ማጣጣም በቀጣዩ ትግላችን ለድል ለመብቃት እጅግ አስፈላጊ ግብአት ነው! በትግላችን ላተረፍነው ሁሉ አላህን በሙሉ ልብ ማመስገን ከኛ የሚጠበቅ እንደሆነው ሁሉ አመስጋኝ ሆኖ ለመገኘት ደግሞ ድልን ማጣጣም ከሁሉ ይቀድማል።

ትግላችን ለዲን ልእልና መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው - በደል እያደረሱብ ላሉት ጭምር! የዲን ልእልና ማለት ደግሞ የቀልብ በአላህ ውዴታ መርጠብ፣ የመሳጂዶቻችን በጀመዓ እና በደርሶች መድመቅ፣ የስነምግባራችን መስተካከልና ሌሎችን መማረክ እንጂ ሌላ አይደለም። የእነዚህ መልካም ባህሪያት መዳበር ደግሞ አሁን ባለን አንድነትና ጽናት እነዚህን ድሎች በደንብ ለማጣጣም ጽኑ መሠረት ይሆነናል።

የትኛውንም አይነት ድል ልናሳካ የምንችለው የአላህን እገዛ ስናገኝ ብቻ ነው። የአላህን እገዛ ደግሞ እሱ በሚወዳቸው ተግባራት እንጎናጸፋለን። በመሆኑም ካሁን ቀደም በየመሳጂዶቻችን ይደረጉ የነበሩ ወርሀዊ የዳዕዋ ፕሮግራሞች ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው አሁን ነው። በፍጹም ሊቋረጡ አይገባም። በተለይ ደግሞ የሴቶች ለሴቶች ወርሀዊ ፕሮግራሞች አስፈላጊነታቸው ከምንጊዜውም በላይ ጨምሯል። ቤት ለቤት እያፈራረቁ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀትም ሆነ በየመሳጂዶቻችን ወርሀዊ ወይም ሳምንታዊ የሙሐደራ መርሀ ግብሮችን በማዋቀር ኢማናችንን ማጠናከር፣ በዱኣ መዋደቅ አስፈላጊ ነው። ቂርአቶችና ኢስላማዊ እውቀት የምናዳብርባቸው ዘዴዎች ከዱሮውም በተሻለ ሊሟሟቁ የግድ ነው። እውቀት ፍለጋ ለአፍታም ቢሆን ሊገታ አይገባም።

ከቁርአን ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከርና ማሳመርም ሌላው አስፈላጊ ነገር ነው። ቁርአን ምሉእ መለኮታዊ ምንጫችን ነው - የህይወት መርሃችንና መመሪያችን ዋነኛ ምንጭ! ለአፍታም እንኳ ልንርቀው የማይገባ የመንፈስ ምግባችን ነው። ከቁርአን መመርያ ርቆ የአላህ እገዛ አይታሰብም። በተቃራኒው ቁርአንን ስንቀርብ ስነ ፍጥረቱ የሚገዛበትን መለኮታዊ ህግ እንረዳለን። ለምናደርገው የመብት ትግል ጽናትን እና አርቆ አሳቢነትን እናገኛለን። የኢስላማዊ ወንድማማችነትን ጸጋነት በጥልቅ እናስተውላለን። አሁን አላህ ያጎናጸፈን ኢስላማዊ አንድነት ከተሰነዘረብን ጥቃት የሚታደገን ጠንካራ ጋሻ ቢሆንም ‹‹ያገኘነውን አንድነት መሰረት አድርገን ምን ሰራን? ምን አሻሻልን? በምንስ ይህን አንድነት አስጠብቀንና አሳድገን መቀጠል እንችላለን?›› ብለን ራሳችንን መፈተሸ በጫንቃችን ላይ ያረፈ ከባድ ሀላፊነታችን ነው። እርስ በርስ በመረዳዳት እና አንዱ ሌላውን በሁሉም መስክ ሊያግዝ የሚችልባቸውን መንገዶች በማመቻቸት፣ በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ላይ በመሰማራትም ልንረባረብ ይገባናል።
በጥቅሉ ዘመቻ የተከፈተብን አንድነታችንን በመፈረካከስ ኢስላምን ለማዳከም በመሆኑ መፍትሄውም ከምናደርገው ትግል ሌላ እስልምናችንን ማጠናከር፣ በእውቀት መታጠቅ እና በኢማን መጨመር ነው። ካሁን ቀደም ስናደርጋቸው የነበሩ ጤናማ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።

ይህ ሲባል አንዳንድ ሰዎች ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀሬ ነው። ‹‹አህባሽ እንዲመጣ የተደረገው ኢስላማዊ ተግባራትን በሰላም መፈጸም እንዳንችል እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ለማስመታት አይደል ወይ?›› ሊሉ ይችላሉ። ይህ ግን እንደምክንያት ሊሆን አይችልም። ኢስላማዊ ሃላፊነቶቻችንን መወጣትና አምልኮዋችንን በሰላም ማካሄድ በየትኛውም አይነት ሁኔታ ውስጥ የማይቀር የህይወት ሙሉ ትግል ነው። የትግሉ አስኳልም ይኸው ነው - የትኛውንም አይነት ተጽእኖ ተቋቁሞ በሃይማኖታችን መጽናት! ይህ ደግሞ በመዘናጋትም ሆነ በየትኛውም ምድራዊ ምክንያት ችላ የማንለው የህይወት መርሃችን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ሁሉም በነፍስ ወከፍ ይህንን መሰረታዊ አደራ ለሌሎች ወንድሞች በማሳወቅ ይረባረብ።
ትግላችንን አጠናክረን አንቀጥላለን!
መፍትሄውም ከምናደርገው ትግል ሌላ እስልምናችንን ማጠናከር፣ በእውቀት መታጠቅ እና በኢማን መጨመር ነው። ካሁን ቀደም ስናደርጋቸው የነበሩ ጤናማ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።

ይህ ሲባል አንዳንድ ሰዎች ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀሬ ነው። ‹‹አህባሽ እንዲመጣ የተደረገው ኢስላማዊ ተግባራትን በሰላም መፈጸም እንዳንችል እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ለማስመታት አይደል ወይ?›› ሊሉ ይችላሉ። ይህ ግን እንደምክንያት ሊሆን አይችልም። ኢስላማዊ ሃላፊነቶቻችንን መወጣትና አምልኮዋችንን በሰላም ማካሄድ በየትኛውም አይነት ሁኔታ ውስጥ የማይቀር የህይወት ሙሉ ትግል ነው። የትግሉ አስኳልም ይኸው ነው - የትኛውንም አይነት ተጽእኖ ተቋቁሞ በሃይማኖታችን መጽናት! ይህ ደግሞ በመዘናጋትም ሆነ በየትኛውም ምድራዊ ምክንያት ችላ የማንለው የህይወት መርሃችን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ሁሉም በነፍስ ወከፍ ይህንን መሰረታዊ አደራ ለሌሎች ወንድሞች በማሳወቅ ይረባረብ።
ትግላችንን አጠናክረን አንቀጥላለን!

ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment