Friday, October 12, 2012

የዜሮ ድምር ምርጫ

የዜሮ ድምር ምርጫ

"በዚህም ቅርጫ እንደ ቀዳሚው ጊዜ ሁሉ ለሃይማኖታቸው ቀናኢ ያልሆኑ፣ በመልካም ምግባራቸው የማይታወቁ፣ በጥንቁልና ስራ ላይ የተሰማሩ፣ ልጃገረድ ደፍሮ ወህኒ ቤት ከርመው የወጡ እና ድራፍት ቀጂዎችም ጭምር የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ተወካይ ተብለው ተመርጠዋል፡፡"
 
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት መጅሊስ ከተቋቋመባቸው ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ ሕዝበ ሙስሊሙን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምራትና ማስተዳደር ነበር፡፡ ከ1987 የአንዋር መስጊድ ግርግር በኋላ መጅሊስ እነዚህን ሰናይ ተግባራት የሚፈጽም ሆኖ አላገኘነውም፡፡ እንደውም በተቃራኒው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ድህረ 1987 መጅሊስ በሙስና፣ በአቅም ማነስ፣ በፖለቲካና እምነት ንፍቅና፣ በጸብ አጫሪነት …. ወዘተ የሚታመስ ሆኗል፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ለዲኔ ይጠቅመኛል ብሎ የመሠረተው ተቋም ወደኋላ ዞሮ ራሱን ሙስሊሙን መጨቆኛ መሣሪያ ሲሆን አይቶ፣ ሰምቶ፣ ታግሶ 17 አመት ዝም አለ፡፡
በሐምሌ 2003 የጀመረው ጥቃት ግን አንድ የሃይማኖት ተቋም በህዝብ ላይ ሊፈጽም የሚችለውን የመጨረሻ አጸያፊ ተግባር ከመንግስት ጋር ተባብሮ መፈጸም መጀመሩ ለዘመናት በዝምታ እና በትእግስት ተውጦ የነበረውን ሙስሊም አባነነው፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ዳግም ቃሉን ላያጥፍ፣ የተቋሙን እና ሙስሊም የመሆን ተፈጥሮአዊ ህልውናውን ለመታደግ ከጥር 2004 ጀምሮ የሕይወት እና የሞት ሽረት ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የትግሉ ዓይነተኛ ባህሪም ሰላም እና ሰላማዊነት ነው፡፡ ሰላምን ፈልገን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ሰላማዊ ትግል ብናደርግም ትግላችንን ከሚመሩት ወንድሞቻችን በተጨማሪ ዳኢዎቻችን፣ አርቲስቶቻችን እና ጋዜጠኞቻችን በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
የተቋማችንን ጉዳይ ስናነሳ መሠረታዊ ጥያቄያችን የነበረው በተቋማችን ውስጥ የተሰገሰጉ ሕገ ወጥ ግለሰቦች ከቦታቸው ተነስተው ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ ምርጫ እንዲደረግ ነበር፡፡ በየካቲት 26 የፌዴራል ጉዳዮች ለመጅሊሱ የአመራርነት ቦታዎች ምርጫ እንዲደረግ መስማማቱን ገልጾ የነበረ ቢሆንም ማን?፣ መች? እና የት? ለሚሉት ሦስት ንዑስ ጥያቄዎች መልስ አልተሰጠም፡፡ ምርጫውን የሚያደርገው ማን ነው? ምርጫው መች ነው የሚደረገው? እንዲሁም ምርጫው የት ነው የሚደረገው? የሚሉት ሦስት የጥያቄው አንኳር ጭብጦች በመንግስት አካላት ምላሽ ሊሰጠው አልተደፈረም ነበር፡፡ መሪዎቻችንም ሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ እነዚህ የጥያቄው ሦስት ንኡስ ጭብጦች በጊዜ ምላሽ አለማግኘታቸው የሚፈጥሩት ክፍተት ቀላል እንደማይሆን በአግባቡ ተረድተው ነበር፡፡ ለዚህም ነው መንግስት የጥያቄውን ሙሉ ምላሽ እንዲያቀርብ መሪዎቻችን ሳይታክቱ የጠየቁት፡፡ መንግስት ለሦስቱ ንኡሳን ጭብጦች (ምርጫው መቼ፣ በማን እና የት ይካሄዱ የሚሉት ጉዳዮች ከምርጫው ዴሞክራሲያዊ መሆን አለመሆን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡) ምላሽ መስጠት አለመፈለጉ እና የዚህም ምክንያቱ ግልጥ ማለት የጀመረው ለምርጫ መሰናዶ ሲጀመር ነው፡፡

ከምርጫው መሰናዶ መጀመር በኋላ ምርጫው የራሱን ስም ለውጦ ቅርጫ መሆን ጀመረ፡፡ ይህ በቀዳሚነት የታየው በአስፈጻሚው አካል ማንነት ነበር፡፡ መንግስት ምርጫውን የሚያካሄደው የኡለማ ም/ቤት ነው ብሎ ወሰነ፡፡ ኡለማ ም/ቤት በቁጥር አምስት እንኳ የማይደርሱ ግለሰቦች አባል የሆኑበት፣ ተጠሪነቱ በሕገ ወጥነት መጅሊስ ወንበር ላይ ለተቀመጠው የመጅሊስ ፕሬዚዳንት መሆኑ፣ ኡለማ ም/ቤቱ የአቅም ውስንነት ያለበት መሆኑ ተደማምሮ በም/ቤቱ አስፈጻሚነት የሚካሄድ ምርጫ ቅርጫ ከመባል የማይዘል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡

የምርጫው መቼነትም ወሳኝ ነበር፡፡ ይሄም ያለምንም ውይይት እና ቅድመ ዝግጅት በድንገት በኡለማ ም/ቤት የተወሰነ ነበር፡፡ የምርጫው መካሄጂያ ቦታ ሌላው ትልቅ ጥያቄ ያስነሳ ነበር፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ምርጫው የሃይማኖት ተቋምን አመራር የሚመለከት በመሆኑ መንፈሳዊ ተግባራት በሚካሄድባቸው መስጊዶች መካሄድ አለበት ቢልም መንግስት ግን የፖለቲካዊ አመራሮች ምርጫ በሚደረግበት ቀበሌ መካሄድ አለበት የሚል የመረረ አቋም ያዘ፡፡ ሕዝቡ ምርጫው በዴሞክራሲያዊ መልኩ ይካሄድ አለ መንግስት ግን ለዚህ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ በእንቢታው ገፋበት፡፡

እንዚህ ሶስት ንኡስ ጉዳዮች ሕዝቡ በጠየቀው መልኩ በሌላ አነጋገር የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት በሚያረጋግጥ መልኩ ምላሽ ሳያገኙ ነው ወደ ምርጫ የተገባው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን የምርጫ ድራማ ዜሮ ድምር ያደረገውም ይኽው እውነት ነው፡፡ ይህ ምርጫ ይህንኑ ባህሪ መላበስ የጀመረው ገና ከምዝገባ ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ካልተካሄደ ትርፉ ድካም ብቻ ነው ብሎ ያምን ስለነበር በምርጫው መሳተፉ ትርጉም አልባ ብቻ እንደሆነ ተገንዝቧል፡፡ ለምርጫው ምዝገባ ተጀምሯል ከተባለበት ጊዜ አንስቶም ኅብረተሰቡ ያለ ማንም ቀስቃሽነት የምርጫ ምዝገባ ጣቢያዎችን ላለመርገጥ ቁርጥ ውሳኔ በመውሰድ በአቋሙ ጸና፡፡ ይህንን የሕዝብ አቋም ለማስቀየር የመንግስት ብዙሀን መገናኛዎች ተከታታይ የቅስቀሳና የፕሮፖጋንዳ ስራዎች ቢያከናውኑም ውጤት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ መንግስት ይህን ስጋቱን ለመቅረፍ ከ20 ሺ በላይ የሚሆኑ የሌላ እምነት ተከታይ ካድሬዎችን ጀለቢያ እና ኮፍያ በማልበስ በምርጫው ጣቢያዎች ሄደው ምዝገባ እንዲፈጽሙ የማድረግ አሳፋሪ ድርጊት ፈጽሟል፡፡ ከዚህም ብሶ ከዚህ ቀደም በታሪክ ባልታየ መልኩ ሰአታት እስኪቀሩት ድረስ ምዝገባው እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ ምዝገባው ቤት ለቤት ቀን ከሌት በሚዟዟሩ ካድሬዎች ጫና ፈጣሪነት የታጀበ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን ውጤት አላመጣም፡፡ የዚህ ነጸብራቅም በቅርጫው እለት በቅርጫ ጣቢያዎች ኦናነት (ባዶነት) በትክክል ታይቷል፡፡
የቅርጫውን እለት ትእይንቶች እና የሕዝብ ተሳትፎውን በአራት አይነት ደረጃ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያውና በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች ልቆ የታየው ምርጫ የሚባል ነገር ከነአካቴው አለመኖሩ ነው፡፡ በብዙ የኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል እና ደቡብ ክልል ወረዳዎች ምርጫ የሚባል ሂደትም ሆነ ምዝገባ እንዳልነበር ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በተቃራኒው ግን በእነዚሁ ምርጫ ባልተካሄደባቸው ቦታዎች ተመርጠዋል ተብለው በርካታ የአሕባሽ አቀንቃኝ ግለሰቦች ወደ ዞንና ክልል እስልምና ምክር ቤቶች እንዲሳቡ ተደርጓል፡፡ በእነዚሁ አንዳንድ አካባቢዎች በምሳሌነትም በኢሊባቦር፣ በገጬ፣ በኮራ፣ በበደሌ፣ በዲዱ፣ አልጌ ሳቺ፣ በአማራ ክልል በደጀን፣ ከሚሴ፣ ጉራጌ ዞን እና ወዘተ ምርጫው በተለዋጭ ቀን ይካሄድ ቢባልም ሙሉ በሙሉ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የነበረው ትዕይንት ምርጫው ይካሄድባቸዋል በተባሉ ቦታዎች ለምዝገባም ሆነ ለመራጭነት ከነአካቴው የሰው አለመገኘት ነው፡፡ ቅርጫው ይካሄድባቸዋል የተባሉ ጣቢያዎች ላይ መራጩን ለመመዝገብም ሆነ ቅርጫውን ለማስፈጸም ከተመደቡት ሰዎች ውጪ መራጭ ሰው አለመገኘቱ ነው፡፡ ይህ በብዙ መልኩ በአማራ እና አፋር ክልል ወረዳዎችና ከተሞች ተስተውሏል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎችም ቅርጫውን ለመድገም አሁንም ሙከራ በመደር ላይ ይገኛል፡፡ ሶስተኛውና ከፍተኛ ቁጥር የሚይዘው የቅርጫ ትእይንት ቅርጫው ከ50 እና ጥቂት 100ዎች የማይበልጡ ሰዎች ብቻ ተሳትፈውበት የተጠናቀቀ መሆኑ ነው፡፡ በእነዚህ የቅርጫ ጣቢያዎች የተገኙ ቁጥራቸው አናሳ የሆኑ ሰዎች የፓርቲ አባላት፤ ካድሬዎች እና የአሕባሽ አህለ ሱና ወልጀመኣ ወሱፍያ ማኅበር አባላት ነበሩ፡፡ ይህ በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በሰበታ፣ በሱሉልታ፣ በደንቢ፣ በምስራቅ ጎጃም ቢቸና፣ ቻግኒ፣ በደሴ፣ በገርባ፣ በደጋን፣ በጉራራ፣ በዱከም፣ በሞጆ፣ በከፋ፣ ቦንጋ፣ ዲላ፣ ጉራጌ ዞን፣ ወልቂጤና ዙሪያዋ፣ በሎጊያ፣ በአሳይታ፣ በጭሮ፣ በሰንበቴ፣ በመቀሌ፣ በአድዋ፣ አላማጣ ከተሞች በስፋት የተስተዋለ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ የሙስሊም ነዋሪ ቁጥራቸው እስከ 70ሺ በሚደርሱ አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ተገኝተውበት ነበር ቅርጫው የተከናወነው፡፡ ለምሳሌነት ቦሌ ክፍለ ከተማ አቶ ኤሊያስ ሬድማን በሚኖሩበት ወረዳ ውስጥ በተካሄደ ምርጫ ተገኝተው የነበሩ መራጮች ቁጥር አቶ ኤሊያስ ሬድማንን ጨምሮ 26 ብቻ ነበር፡፡ በሌሎችም አከባቢዎች ትዕይንቱ ብዙ ምስስሎሽ ነበረው፡፡

ቀጣዩና አራተኛ አይነት ትእይንት የነበረው በጣት በሚቆጠሩ የአዲስ አበባ እና የክልል ምርጫ ጣቢያዎች ነው፡፡ እነዚህ ቅርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የነበረው አጠቃላይ ትእይንት ለካሜራ (ለኢቴቪ ፕሮፖጋንዳ) ፍጆታ በሚል ቀድሞ ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎበት የተጠናቀቀ ነው፡፡ ለዚህ ሲባልም በርካታ ካድሬዎች (ብዙዎችም የሌላ እምነት ተከታዮች ኢስላማዊ አለባበስ በመልበስ) የታደሙበት ነው፡፡ የእነዚህ ቅራጫ ጣቢያዎች ቁጥር በግምት እስከ 11 ይደርሳሉ፡፡ በእነዚህ ቦታዎች እና በሌሎችም ጥቂት ቦታዎች መንግስት ምርጫው ፍትሀዊ ነው ተብሎ እንዲታሰብ የሚረዱ አንድ አንድ ማስመሳይ ተግባራትን በማከናወን የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ ጥረት ቢያደርግም ከሕዝቡ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ የምርጫ ቦታዎች የምርጫ ሸፍጥ እየፈጸሙ በጣት በሚቆጠሩ ቦታዎች ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂጃለሁ ማለት ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ በዚህም ቅርጫ እንደ ቀዳሚው ጊዜ ሁሉ ለሃይማኖታቸው ቀናኢ ያልሆኑ፣ በመልካም ምግባራቸው የማይታወቁ፣ በጥንቁልና ስራ ላይ የተሰማሩ፣ ልጃገረድ ደፍሮ ወህኒ ቤት ከርመው የወጡ እና ድራፍት ቀጂዎችም ጭምር የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ተወካይ ተብለው ተመርጠዋል፡፡

ቅርጫው በአጠቃላይ በተደጋጋሚ ቅስቀሳ እና ፕሮፖጋንዳ የሕዘብን ልብ ያልገዛ እንኳ ተራ የፖለቲካ ድራማ ሆኖ ቢያልፍም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ግን የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጠበት ሆኖ አልፏል፡፡ ዛሬም ቢሆን እኛ ሙስሊሞች በመሰል የፖለቲካ ድራማ የማንሸወድ መሆናችንን በማረጋገጥ እስከድላችን ዋዜማ ድረስ በሰላማዊ ትግላችን እንደምንቀጥል በተግባር እናረጋግጣለን፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment