Monday, October 29, 2012

“ድንቅ ስብዕናዎች...ኮሚቴዎቻችን”

“ድንቅ ስብዕናዎች...ኮሚቴዎቻችን”

በዚህች ምድር ላይ ከሚያስደስቱ ነገሮች አንዱ ከራሳቸው አልፈው ለህዝብ የሚኖሩ ሰዎችን ማየት ነው።ራሳቸውን ሁነው ቤተሰባቸውን በፍቅርና በስነ-ልቦና ገንብተው ለህዝብ ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ “ጀግኖችን” እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም። እንደነዚህ አይነት ሰዎችን ብዙዎች ያፈቅሯቸዋል።ብዙዎች ስለ እነርሱ መስወዓት መሆንን ይመኙላቸዋል። ስለነርሱ መልካምነት ይዘክሯቸዋል። ብቻ ሳር ቅጠሉ ሳይቀር ስለነሱ የሚያስብ ይመስላል። ትንሽ ትልቁ፡ሴት ወንዱ፡ ወዳጅ ጠላቱ የሚያወራው ስለነርሱ ነው። አዎን! ግልፅ የሆነ የህይወት ግብን አስቀምጦ ለርሱ ኖሮና በርሱ ኖሮ ለዚሁ ግብ ሲሉ መክፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል ሃሴትን ያሰገኛል። በዚሁ ግብ ላይ መሞትም ህያውነት ነው።ሁልጊዜ በሰዎች ልብ ውስጥ መታወስ ነውና። አዎን! የህዝብን ልብ መግዛት የሚቻለው በወሬና በፕሮፖጋንዳ አይደለም- ይልቁንስ ሆኖ በመገኘት እንጂ። በጠመንጃም አይደለም- በመልካም ስነ-ምግባር እንጂ። እንደ አንዳንድ ሗላ ቀርና ተምረው ያልተማሩ የስነምግባር ችግር ያለባቸው ባለስልጣናት ሰውን በሃይልና በሞት በማሰፈራራት የሚገኝ ታዛኝነት የለም-ውርደት እንጂ። ለእንደነዚህ አይነቶቹ ሰዎች የምንላቸው ነገር ቢኖር ስው እንዴት መፈቀር እንደሚችል ከ “እኛ ጀግኖች” ተማሩ ነው። የሰውን ልጅ ልብ እንዴት መግዛት እንደሚቻል ከ “እኛ ጀግኖች” ኮርጁ አይጎዳችሁም። ማንነታችሁን መጀመሪያ ፈልጉና አግኙት እንደኛው “ጅግኖች”።ለእራስ ሳይሆኑ -ለሃገርም ለህዝብም መሆን አይቻልምና!!!።

የእኛ ጀግኖች በ21ኛው ክ/ዘመን እኛ ስለናንተ እኛ ስለህዝብ አንገታችንን እንሰጣለን።እናንተ ሰላማዊና ሰለማዊ መንገድን ብቻ ተከተሉ። ቢያስሯችሁ፡ቢደበደቡችሁ እናንተ በፍቅር አሸንፏቸው። እነርሱ መሳሪያ ቢመዙባችሁ እናንተም ወደ አላህ ፊታችሁን አዙሩ። የህዝብና የሃገር ሰላም ይቀድማል።መብት እየጠየቅን የማንንም መብት እንዳንጋፋ።አደራ-ሰላማዊነታችሁን እጅ ለእጅ በመያያዝ በመተቃቀፍ ቃል ግቡልን።እኛ ስለ ኢስላምና ስለሙስሊሙ ኡማ መሆን ያለብንን ነገር ሁሉ እንሆናለን።በእርግጥ “የምንገደልበት ምክንያት የለም የምንሞትለት አላማ ግን አለን-ኢስላም”፤ “ለኢስላም ስንል አይደለም ግዚያችንን አንገታችንን እንሰጣለን”፤ “መኖር ካለብን በክብር- መሞትም ካለብን በክብር ነው”፤ “ለጠላቶቻችሁ ፈገግ በሉላቸው- ሶደቃ ነው”...የሚሉ መሪዎችን እንደማግኘት ምን የሚያስደስት ነገር አለ? ወላሂ!ይህ ትልቅ ፀጋ ነው።አልሐመዱሊላህ። ዛሬ እነዚህ ጀግኖች የትም ይሁኑ የት፡ምንም አይነት ችግር ይጋፈጥባቸው አንድ የማይፈቅ እውነታ ግን አለ ቢያንስ ከ40 ሚሊዩን በሚበልጥ ሙስሊም ልብ ውስጥ አሉ።እነሱን መሆን የሚሻ፡የእነርሱን ድንቅ ስብዕናና መንገድ አጥብቆ የያዘና መያዝም የሚፈልግ አለ።

አዎን! እነኝህ የህዝብን አደራ በታማኝነትና በሚያሰደምም ብቃት የተወጡት ጀግኖች አሁንም የሚሰቃዩት ለትልቅ አላማ ነው።የሚገረፉት የሚደበደቡት የሰነ-ልቦና ጫና የሚደርስባቸው ለተራ ነገር አይደለም። ለትልቅ አላማ ነው--ለኢስላም። መስዋዕትነት ዝም ብሎ አይከፈለም።መጀመሪያ ስለ ኢስላም ጠንቅቆ ማወቅን ይጠይቃል። ኢስላም ያለፈባቸውን ሂደቶችን ጠንቅቆ መገንዘብን ይሻል። አዎን!ብዙ ነቢያት የተሰቃዩበት ዲን ነው። የመጨረሻው ነቢይ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መከራ ያዩበት ዲን ነው።ሶሃባዎችና ታቢኢዮች ከዚያም በሗላ የመጡ መልካም የአላህ ባሪያዎች ተገርፈውለት፡ተገድለውለታል-ለኢስላም። እርግጥ ነው አንደ ሰው በኢማኑ ልክ ይፈተናል።የእኛም ጀግኖች ይኼው ነው እየደረሰባቸው ያለው። ኢስላምን ሲረዱ የተረዱት አስተምህሮቱን ብቻ አይደለም።በኢስለም ውስጥ ያለፉ ስብዕናዎች ያጋጠሟቸውንም ችግሮችና መከራዎችንም ጭምር እንጂ። እነዚህን ድንቅ የኢስላም ስብዕናዎች አላህ በሂክማው እንዲጠብቃቸው የዘወተር ዱዓየ ነው።
እንኝህ ጀግኖች ናቸው ታሪክን ተምረውና አንብበው ታሪክ የሰሩት፤መልካም ስነ-ምግባርን አስተምረው በመልካም ስነ ምግባራቸው እንኳን ወዳጅን ጣላትንም ያሸነፉት፤ በመልካም ፈገግታቸው ጥላትን ያከሱት፤ስለ ዕውነተኝነት አስተምረው እውነተኛ ሆነው በቃላቸው ፀንተው ለእውነት ሲሉ ዘብጥያ የወረዱት። ከአንደበታቸው የሚወጡ ቃላቶች ሲበዛ ጣፋጮች ናቸው። በርግጥ ሲባዛ ብርቅየ የኢስላም ሰብዕናዎች ናቸው።ሁሉም ሰው ንግግራቸውን ሰምቶ ይወዳቸዋል። ፊታቸውን አይቶ አይጠግባቸውም።ተለይቶ ይናፍቃቸዋል።ትልቁም ትንሹም ያከብራቸዋል።ፈገግታቸው ይማርካል። መልካም ሰብዕናቸው ብዙዎችን ያማልላል። ሲበዛ መልካም መካሪዎች ናቸው።ሲበዛ ለህዝብና ለሃገር ሰላም ያስባሉ።ለመልካም ማህበራዊ ኑሮ ይጨነቃሉ። በእርግጥ አላህ የወደዳቸው ባሪያዎች እንኳን በወዳጅ ዘንድ በጠላትም ቢሆን እንድወደዱ ያደርጋቸዋል። መልካም ስራቸውን ያበዛላቸዋል። አዎን! ከገጠር እሰከ ከተማ በአካል ባይታወቁም መልካም ስራቸው ብዙ ሙስሊም ልብ ውስጥ ገብቷል። ለአላህ ስትሆን አላህ ለአንተ ይሆንሃል። ለአላህ ስትተናነስ አላህ ያግዝሃል። በትክክለኛው መንገድ እሰከተጓዝክ ድረስ አላህ ከጎነህ ነው። ዋናው ነገር መልካም መንገድ ላይ መሆንን ጠንቅቆ ማወቅ ነው።መልካም ነገር ለማግኘት ብዙ መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ታግሶና በጥበብ ማለፍን ይጠይቃል። ኢንሻአላህ!አላህ ሁልጊዜም ቢሆን ትክክለኛ መንገድ ላይ ያሉ ህዝቦችን ይረዳቸዋል።ይህ የእርሱ ተፈፃሚ ቃሉ ነው። ሰዎች አምነናል ስላልን ብቻ ነፃ አንተውም ፈተና አለብን። እስኪ እነዚህን የቁርአን አንቀፆች እንመልከታቸው።
“..ሰዎቹ አምነናል በማለታቸው ብቻ እነሱ ሳይፈተኑ የሚተው መኾናቸውን ጠረጠሩን? እነዚያንም ከእነሱ በፊት የነበሩትን በእርግጥ ፈትነናል።እነዚያንም እውነት የተናገሩትን አላህ በእርግጥ ያውቃል።ውሸታሞቹንም ያውቃል።ይልቁንም እነዚያ መጥፎዎችን ስራዎች የሚሰሩት ሊያመልጡን ይጠረጥራሉን? ያ! የሚፈርዱት (ፍርድ) ከፋ። የአላህን መገናኘት ተስፋ የሚያደርግ ሰው (ይዘጋጅ)። የአላህ ቀጠሮ በእርግጥ መጪ ነውና። እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው።” (አል-አንከቡት(29)፡ 2-5)
“...በእውነቱ አላህ ከናንተ እነዚያን የታገሉትን ሳያውቅ (ሳይለይ) ታጋሾቹንም ሳያውቅ ገነትን ልትገቡ አሰባችሁን? (አል-ኢምራን(3)፡142)
“...በእውነቱ የእነዚያ ከበፊታችሁ ያለፉት (ምዕመናን መከራ) ብጤ ሳይመጣችሁ ገነትን ልትገቡ ታስባላችሁን? መልዕክተኛውና እነዚያ ከእርሱ ጋር ያመኑት “የአላህ እርዳታ መቼ ነው?” እስከሚሉ ድረስ መከራና ጉዳት ነካቻቸው። ተርበደበዱም። ንቁ! የአላህ እርዳታ በእርግጥም ቅርብ ነው (ተባሉም)።” (በቀራህ (2)፡ 214)
ይኼው ነው እንገድህ እውነታው ኢስላምና ነው-ሃይማኖቱ።ድንቅ እምነት። ድንቅ የህይወት መስመር። ስለዚህ ገነትን ለማገኘት ይህ ድንቅ ዕምነት የሚጠይቀውን መስዋዕትነት መክፈል ግድ ይላል። በተለይም እነዚህን አንቀፆች የዘንጋችዃቸው አንዳንድ ወንድሞቼ አስታውሷቸው። ስለማዊ ትግል ይውለዳል፤ ያድጋል፤ ያረጃል ይሞታል እያላችሁ ይምትደሰኮሩኝ ወንድሞቼ---የምላችሁ ነገር ቢኖር ቢያረጅና ቢሞት ኖሮማ 1433 አመታትን ተጉዞ እኔና እናንተ ጋ ዛሬ ባለደረሰ ነበር። ሰላማዊ ትግልን ጥብብ እድርጎ በማየት ዕድሜውን መገድብ ትክክል አይመስለኝም። ውድ ነገር ሁሉ ትግል ይፈልጋል። አራት ነጥብ። ሰላማዊ ትግልን መንገድ ላይ ወጥቶ መቃወም ብቻ ነው ብላችሁ ትርጉሙን እስካላጠበባችሁት ድረስ-ሙስሊሞች እስከ ዕለተ ቂያማ ድረስ በስላመዊ ትግል ውስጥ ነን።
ለእኔ የሶሃባዎችን ታሪክ ብቻ አንብቤ የምረካበት ጊዜ አልፎ የሶሃባዎች ታሪክ በ21ኛክ/ዘመን በሃገሪም ጀግኖች በተግባር አይቸዋለሁ። በ“ኢልመል የቂን” ሳይሆን በ “አይነል የቂን” በአይኔ በብረቱ ተመልክቻለሁ።የሶሃባዎችን ታሪክ አንብቦ...ይህ ሁሉ ግን በሰው ልጅ ሊፈፀም ይችላልን ብሎ የሚጠይቅ ህሊና ዛሬ በእኛው ልጆች-ሙሉ መልስ አግኝቷል።አዎን! ይቻላል።አዎን!ዛሬም እንደ ትላንቱ ለአመኑበት አላማ-ኢስላም-የስቃይ፡የሰቆቃንና የግፍን ውርጅብኝ መሸከም ይቻላል።
ወንድሞቼ እህቶቼ እኔ ስለእነዚህ የኢስላም ድንቅ ስብዕናዎች ከዚህ በላይ ማለት ቢቻልም ትልቁ ቁምነገር ግን እነዚህ ሰዎች ይህን ሁሉ ነገር ሲሆኑ እኛ ትምህርት ልንወስድ ይገባል። ወጣቶች እነዚህን ድንቅ ስብዕናዎች ለመተካት እስልምናን በስርዓት መማር እንጀመር። እናትና አባቶች ልጆቻችን በ ተርቢያ እናሳድግ። ለምን ፈለጋቸውን አንከተልም።የኢስልምና እውቀት መሳሪያ ነው። ይህን ከሰራን አሁንም ቢሆን ኮሚቴዎቻችን የደከሙለትና እኛም የተጨነቅንለትን አላማ ከግብ እያደረስን ለጣላቶቻችን ደግሞ ሽንፈትን እያከናነብብ ጉዟችንን ወደፊት እንበል ለማለት ነው።
መልካም ነገር ከፃፍኩ በአላህ እርዳት ነው። አግባብ ያልሆነ ነገርም በፅሁፉ ውስጥ ካለበት ከ እኔው ስህተት ነው። አላህ ሁላችንንም በኢስላም ላይ ኖረን በኢስለም ላይ የምንሞት ያድርገን። አሜን!

No comments:

Post a Comment