Sunday, October 7, 2012

በመላው ኢትዮጵያ ቅርጫ ጣቢያዎች ወና ሆነው ዋሉ

• እፍረት የመንግስት ሰዎችንና ሚዲያዎቹን ጥላ ኮብልላለች!!!
• ሴኩላሪዝምና ሕገ-መንግታዊነት ገመናቸው በአደባባይ ተጋልጦ ውለዋል
• በመላው ኢትዮጵያ ቅርጫ ጣቢያዎች ወና ሆነው ዋሉ
• ትግላችን ስኬቱን እያጣጣመ በአዲስ ጉልበት ይቀጥላል!!!
መስከረም 27/2005 በ80 ሚሊዮኑ ሕዝባችን የኃይማኖትና የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስገራሚ፣ ለሰፊ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ትናታኔ የሚጋብዝ ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን በተለይም ለሙስሊሙ ሕብረተሰብ ፈጽሞ የማይረሳ ቀን ነው፡፡ መንግስት በእጁ ያለውን ኃይልና ጉልበት እንጂ ሕግና ስርዐትን የማክበር ወኔ እንደሌለው ተረድተናል፡፡ ይህን ለማስረዳት የመራጭነት ካርድ ባይወስዱም በዛሬው የሕገ-ወጥ ምርጫ ካልተሳተፋችሁ ተብለው ሲደበደቡና እስር ቤት ሲታጎሩ ከዋሉት በላይ ምስክር ማግኘት ከባድ አይደለም፡፡ በሕመም የተያዙ ሰዎች ከሐኪም ቤት ተጎትተው እንዲመርጡ ተገደዋል፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰዎች ሙታቸውን ለመቅበር ተከልክለው ወደ ቅርጫ ጣቢያዎች እንደ እንስሳ እየተገረፉ ሲነዱ ጎጃሜ ሁሉ ታዝቧል፡፡ በጉራጌ ዞን፣ በአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ በውልቂጤ፣ ደሴ፣ ወዘተ ወዘተ አልመርጥም ያሉ መታሠራቸውን አውቀናል፡፡ ከሁሉ አሳፋሪው ግን ከኤች አይ ቪ ጋር የሚኖሩ ወገኖቻችንን ‹‹ካልመረጣችሁ ሲዲ4 (እድሜ ማራዘሚያ መድሃኒቱ) አይሰጣችሁም›› የሚል ከሠብዐዊነት እጅግ የራቀው ማስፈራሪያና ወከባ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ቢጫው ካርድ የተሠጠን ባልታጠቀ ኃይል ነው›› የሚል ከንቱ ቀረርቶ በአንዳንድ የደህንነትና የመንግስት ሰዎች አንደበት ተደምጧል፡፡ የሠው ሕይወት ክቡር በሆነበት ዓለምና ዘመን እየኖርን ‹‹መብታችሁን ጫካ ግቡና አስከብሩ›› ያሉ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮችም ስለ ሐገር ጸጥታና ደህንነት የማውራት የሞራል ብቃት የላቸውም፡፡
ሆኖም አልሃምዱሊላህ፤ ጉልበት መቼም ሕዝብን አሸንፋ፤ እውነት መቼም በውሸት ፊት ተዋርዳ አታውቅምና አቶ ኩማ ያለ እፍረት ‹‹ሕዝቡ የጣለብንን ኃላፊነት ትተን የሙስሊሙን ጉዳይ ስናቦካ ልማቱ ቆመ›› ያሉለት ቅርጫ ያለ ስኬት ተጠናቋል፡፡ ሙስሊሙም አሸናፊነቱን አረጋግጧል፡፡ በሺ የሚቆጠሩ ሠዎች ባሉበት ወረዳና ቀበሌ አስሮችን አስገድደው ስለተሰበደቡ ምርጫ ተደርጓል ማለት አይደለም፡፡ ምርጫው ተቀባይነት የለውም፡፡ እንደ አህመዲን ጨሎ ያለ ሰው በቢጤው ቢተካም እኛ እንደሆን ምላሽ እስክናገኝ ድረስ ሰላማዊ ትግሉን ጨርሶ አናቆምም፡፡ መንግስት ሆይ! የህዝብ ድጋፍ የሌለው ሽባ መዋቅር መዘርጋት አይደለም ቁምነገሩ፡፡ ቁም ነገሩ ሕዝቡ የቱ ጋር ነው ብሎ ማሠብ ነው፡፡ መጅሊስ ድሮም የሕዝብ ድጋፍ ያልነበረው ለልማትም ሆነ ለጥፋት ማስተባበር የማይችል ነበር፡፡ ዛሬም ከዛ ቢብስ እንጂ አዲስ ነገር አይኖርም፡፡ ትግላችን ይዘግይ እንጂ የዛሬው ሕገ-ወጥ ቅርጫ ሳይቆይ በቅርቡ ተሽሮ መብታችን እንደሚከበር እናረጋግጣለን፡፡
መንግስት ሆይ! ሕዝብ በህግና ስርዐት፣ በፍቅርና በመደማመጥ እንጂ እርርርርርር ትክን ባለ የውሸት ፕሮፓጋንዳ አይመራም፡፡ በመላው ሐገሪቱ 70 ሺ ሰው እንኳ በቅርጫው ባልተሳተፈበት ሁኔታ ‹‹7 ሚሊየን ሕዝብ በምርጫው ተሳተፈ›› ብሎ በሚዲያ ማስወራት፤ 80 ሚሊዮኑ ህዝብ አልቋል፤ አሊያም ‹‹የማያይ፣ የማይሰማ ደንቆሮ ነው›› ማለት ሲሆን፤ እውነት ቢሆን እንኳ ከ40 ሚሊየን ሕዝብ ‹‹7 ሚሊየን ሰው ተሳተፈ›› ብሎ በኩራት ማውራት ትርጉሙ አስቂኝ ነው፡፡ ስለዚህ፤ መንግስት ከነ አጫፋሪ አህባሾቹ በዝረራ ተሸንፏል፡፡ ትግሉ ይቀጥላል!!! ተስፋ መቁረጥ አይታሰብም!!! አሸናፊነታችንን ሁላችንም እያጣጣምን ተሸናፊው አካል መሸነፉን አውቆ ጥያቄያችንን በመመለስ አብሮን የአሸናፊነቱን ጽዋ እንዲቋደስ እንጋብዘዋለን፡፡ ከ40 ሚሊዮን ሙስሊም በቅርጫ አልሳተፍም ብሎ 65 ወይም 70 ሺህ ሰው መረጠልኝ ብሎ መሮጥ ሩቅ አያስኬድም፡፡ ትግሉ ይቀጥላል፡፡ ሁላችንም ይበልጥ ውጤታማ የሚደርጉ መንገዶችን እያሰብን እንቆይ፡፡

No comments:

Post a Comment