Sunday, October 7, 2012

ከምርጫው ጀርባ ያሉ እውነቶችና የኢቲቪ ቅጥፈት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህና አዛኝ በሆነው እጀምራለሁ::
ከምርጫው ጀርባ ያሉ እውነቶችና የኢቲቪ ቅጥፈት
መንግስት የልማት ስራውን ላለፉት በርካታ ወራት ሙሉ ለሙሉ በመተው በመጅሊስ የምርጫ ጉዳይ መጠመዱን አቶ ኩማ ደመቅሳ በግልፅ ቋንቋ አስረድተውናል፡፡ ለነገሩ ከዚህም በላይ የምርጫው ባለቤት ህዝቡ ሳይሆን መንግስት እራሱ መሆኑን በየመስጂዳችን፤ በየመንደራችንና በየመስሪያ ቤታችን ሲደርስብን በነበረው ማዋከብና ማሸማቀቅ እናውቀዋለንና ሌላ መስካሪ አንጠብቅም፡፡ በሙስሊሙ ጉዳይ ላይ ህገ መንግስቱን የሚጣረሱ አካሄዶች በመብዛታቸው ህገመንግስቱ የወረቀት ላይ ነብር ብቻ እየሆነ መምጣቱን ሁሉም እየተገነዘበው ነው፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ግን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ከወራት በፊት በሬዲዮና በቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግራቸው ‹‹የምርጫ ቦታን አስመልክቶ ውሳኔው የህዝቡ ነው፡፡ ቢፈልግ ቀበሌ ያድርገው፤ ቢፈልግ በመስጂድ ያድርገው፤ የመንግስት ስራ የህዝብን ምርጫ ማስከበር ነው›› ያሉት ቃል እንዲህ በጠራራ ፀሃይ በክህደት ሲለወስ ማየት የእሳቸውን ሳይሆን የወከሉትን ስርአት ለህግና ለስርአት ተገዥ የመሆን ብቃትና ፍላጎት እጦትን ነው የሚያመላክተው፡፡ የዛሬውን ምርጫ ህገወጥነቱን ማወጅና አለመሳተፍን መወሰን ጥርጣሬ የሌለው ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን በበርካታ ማሳያዎች ማስረዳት ይቻላል፡፡ እውነት ከተናገረ ልሳኑ የሚዘጋ የሚመስለው ኢቲቪ ግን ዛሬ የምርጫውን ‹‹ፍትሃዊነት›› እና ‹‹በህዝብ ነፃ ፍላጎት›› መካሄድ ሊነግረን መዘጋጀቱ ግልፅ ነው፡፡ እኛ ግን ስለ ምርጫው ገሃዳዊ ድራማዊነት በጥቂት ነጥቦች ብቻ ለማሳየት እንሞክር
ህዝበ ሙስሊሙ የጀመረው የመብት ማስከበር ሂደት እያደገ መጥቶ በወከላቸው መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች አማካይነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በቀጥታ በየመስጂዱ የአስመራጭ ኮሚቴ በመምረጥ በአዎልያ ሶደቃ ፕሮግራም ላይ ለማስተዋወቅ ዝግጅት በመደረጉ በተቀደምን ስሜት የተበሳጩት የፌዴራል ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ዶ/ር ሽፈራው ( ከባል ደረቦቻቸው ጋር በመሆን ) በመጅሊሱ ቅጥር ግቢ አንድ ቡድን በማደራጀት ለሁለት ቀን ምርጫውን ሶስት ሰው ብቻ ቢሳተፍ እንኳን እነዴት እነደሚያስፈጽሙት፣ ደራማውንም እነዴት አድርገው ለህዝብ እነደሚገልጹ ጭምር ስልጠና እንደሰጡ ሁሉም የሚያውቀው የአደባባይ ሚስጥር ነው ፡፡ ይህ በርሳቸው የተደራጀው ቡድን ከሀገሪቱ የደህንነቱ ቢሮ የተመለመሉ 27 አባላት ያሉት ሲሆን ከዘጠኙ የክልል መስተዳደሮች እንዲሁም ከድሬዳዋ እና ከአዲስ አበባ ተወክለውበታል፡፡ እንግዲህ መንግስት ( የፌደራል ጉዳዮች ) በእነዚህ አካላት ነው ለአህባሾች ‹‹የአህለሱና ወልጀመአ ማህበር›› በሚል ስያሜ የሚታወቀውን መዋቅር በፌዴራል ና በክልል ደረጃ ማቋቋም የቻለው ፡፡ ቀድሞ በመጅሊሱ ፕሬዚዳንት አህመዲን አብዱላሂ በበላይ ጠባቂነት ተዋቀሮ የነበረውን ‹‹የኡለማ ምክር ቤት›› እነደሽፋን በመጠቀም እነዚህ የመንግስት ምልምሎች ናቸው እንግዲህ ዛሬ የሚጀመረውን ቅርጫ ያለ አቅማቸው እንዲያስፈጽሙ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው የነበረው :: (ልብ በሉ የመንግስት ጣልቃ ገብነትስ ከዚህ በላይ በምን ሊረጋገጥ ይቻላል ?? ) :: የዚህ ቡድን አባላት በይበልጥም በአስተባባሪነት የተመረጡ አምስቱ( መሐመድ ረሺድ፤ እስማኤል፤ አብዱልፈታህ፤ አብዱልማሊክ፤ ሚሊዮ)ና በየክልሉና በየክፍለ ከተማዎቹ ያደራጇቸው አባላት ማንነት እና የስልክ ቁጥርን የያዘ አድራሻ በግልፅ የታወቃል ( ፌስቡክ ላይ ከዚህ በፊት የወጡ ከፊል ዝርዝሮችን ይመልከቱ ) :: በተጨማሪም የመንግስት ተገዳጅ ካድሬዎችን በመያዝ በብዙ ሚሊዮኖች ጩኸት ምክንያት ህገ-ወጥነቱ ታውጆ የወደቀውን የመጅሊስ አመራር በሌላ ህገ-ወጥ ቅርጫ መስከረም 27/2005 ለመተካት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ ::
በመሆኑም በዚህ መሰል የሸፍጥ አደረጃጀት በተዋቀረ ቡድን በሚመራ ምርጫ የሚመጣው ውጤት እና አመራር አስቀድሞ የታወቀ በመሆኑ የዚህ ህገ-ወጥ ድርጊታቸው ተባባሪ ላለመሆን መወሰናችን ተገቢና ትክክለኛ ነው፡፡
እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ የዛሬውን ምርጫ ኢቲቪ በምን መልኩ ሊዘግበው እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ድምፃችንን ለማሰማት የሚጥሩ ሁለት የቪኦኤ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሌሎች በርካቶችን ያፈነው መንግስት እና ልሳኖች እነኢቲቪ እውነት እንደማይናገሩ ግልፅ ነው፡፡ የመብት ጥያቄአችንን ገና ከጅምሩ ከሽብር ጋር በማያያዝ የፍረጃ ዘገባዎቻቸው ዛሬም አልተረሱምና ከእነሱ የተለየ ነገር አንጠብቅም፡፡ ለሃሰት ፍጆታቸው እንዲውል በካድሬዎች የተሞሉ ጥቂት ጣቢያዎችን በመቅረፅ ‹‹ጉሮ ወሸባቸውን›› ሊያሳዩ ቋምጠዋል ፡፡ እውነታውን ግን ህዝብ ከማንም በላይ ያውቀዋልና ትርፉ ድካም ነው ፡፡ በመሰረቱ ምርጫው በመላ ሃገሪቱ የተወገዘ ከመሆኑም በላይ ለሚዲያ ፍጆታ የሚውለውም ምስል የሚገኘው ከጥቂት አካባቢዎች ብቻ ነው ፡፡ ድራማው ( ቅርጫው ) ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ የሚፈለግ እንጂ ከዛ ያለፈ ነገር አለመኖሩን ደግሞ ከ10 ሺህ በላይ ቀበሌዎች ባሉበት ሀገር ውስጥ 500 በማይሞሉ አካባቢዎች ብቻ ለይስሙላ እነደሚካሄድ ይታወቃል :: የህገ-ወጡን ምርጫ ድራማዊነት በበለጠ ለመረዳት አንድ ታላቅ እውነታን ብቻ ለማየት እንሞክር ለምሳሌ በሀገሪቱ በጠቅላላ እንደሚኖር ከሚገመተው 30 ሚሊዮን (እነደ መንግስት ቆጠራ ነው) ሙስሊም ማህበረሰብ ውስጥ 5 ሚሊዮን የሚጠጋው የሱማሌ ሙስሊም የህገወጡ የምርጫ ሂደት ከጅማሮ ጀምሮ ግልፅ ተቃዋሚ በመሆን የራሱን የምርጫ ሂደት ይከተላል :: 2 ሚሊዮን የሚጠጋው የአፋር ህዝብ ህገ-ወጡን የቀበሌ ምርጫ ውድቅ አድርጓ በመስጅዱ ያካሂዳል ፡፡ ከ14 ሚሊዬን በላይ ሙስሊም ማህበረሰብ የያዙት የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ ከጅማ እስከ መቱ ከነቀምት እስከ በደሌ ከአርሲ እስከ ባሌ ከኣዳማ እስከ ሻሸመኔ በምርጫው እንደማይሳተፉ በአደባባይ ገልጸዋል ፡፡ ከ 3 ሚሊዮን በላይ የሚልቀው የደቡብ ክልል ሙስሊምም ከወራቤ እስከ ወልቂጤ በአንድ ድምጽ የምርጫውን ህገ-ወጥነት በማጽደቅ ላለመሳተፍ ወስኗል ፡፡ የአማራ ክልል ሙስሊምም ቢሆን ከጎንደር እስከ ጎጃም፣ ከሰንበቴ እስከ ወልዲያ በማያሻማ መልኩ አቋሙን አሳውቋል፡፡ በትግራይ ከአላማጣ በመቀሌ እስከ አድዋ በአንድ ድምጽ ‹‹የህዝብ ድምጽ ይሰማ›› ምርጫው ህገ ወጥ ነው ሲሉ አውጀዋል፡፡ ቀላል ቁጥር በሌላቸው በአዲስ አበባ፣በሐረርና ድሬዳዋ ያለው እውነት ከሌሎች ክልሎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ታዲያ ኢቲቪ ሆይ ስለሚሊየኖች ድምጽ ወይንስ ስለ ድራማዊ ቅርጫ ማውራት የሚቀለው ???
እውነታው ይህ ሆኖ እንኳን በምርጫው የሚሳተፉ ሰዎችን በመመዝገብ፣ የምርጫ ካርድ በመስጠት ሂደት የታዩ አስጨናቂና አሳፋሪ የማስገደድ ስራዎች ውጤት በመሆኑ ጭምር ቅርጫው የጭቆና መገለጫ እንጂ የፍትሃዊ ምርጫ ተሳትፎን በጭራሽ አይወክልም ሊያሳይም አይችል ፡፡ መራጮችም የግዳጅ ዘመቻው ሰለባዎች መሆናቸ ጥያቄ የለውም ፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ ‹‹ምርጫችን በቀበሌያችን›› ብሎ የጠየቀ ህብረተሰብ ሳይኖር ‹‹ምርጫው ህዝቡ በመረጠው ቦታ ተካሄደ›› ብሎ ቢዘግብ አይገርመንም፡፡ ዛሬም ይህ እንደሚሆን ነው የምንጠብቀው፡፡ የኢቲቪ ቅጥፈት ግን የምርጫውን ገመና አይጋርደውም፡፡ የዛሬው ቅርጫም ለህዝብ ክብር የሌላቸው ለሆዳቸው ያደሩ ሹማምንትን መሰየሚያ በመሆኑ የምናወግዘው የሂደቱን ህገወጥነት ብቻ ሳይሆን ውጤቱንም እንደማንቀበለው ጭምር ነው፡፡ በተሳሳተ አቅጣጫ ተጉዞ ትክክለኛ ቦታ መድረስ ስለማይቻል በዚህ ህገ-ወጥ መንገድ የሚመጡ ሹማምንቶችን እውቅና እንደማንሰጥ ከወዲሁ እናስታውቃለን፡፡ ባለፉት ግዜያት ሃይማኖታዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ በየመስጂዶቻችን የጀመርናቸውን ሂደቶች ከዳር አድርሰን ለህዝብ ሰላምና ለሃገር ደህንነት የሚበጁ መሪዎችን እስከምንመርጥም ትግላችን በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል፡፡
“ ድልም መንሳት አሸናፊ ጥበበኛ ከሆነው አላህ ዘንድ ብቻ እንጂ ከሌላ አይደለም ”(ሱረቱ ኣለ ዒምራን-126 )

No comments:

Post a Comment