Tuesday, October 9, 2012

“ነፃ ምሳ የለም!” or “There is no free lunch”

እኔ በግሌ እስካሁን ድረስ ሙስሊሙ ህብረተሰብ እያደረጋቸው ባሉት እንቅስቃሴዎች አንድም ቀን እንኳ ተሳታፊ አልነበረኩም።ምንም እንኳ እንደሙስሊምነቴ በሙስሊሙ ላይ የሚፈፀሙ ብዙ ነገሮች ቢያሳስቡኝና ቢያበሳጩኝም ዝምታን መርጨ ነበር። ነገር ግን ሚዲያዎችን ስከታተልና ሰገመግም አይን ያወጡ ውሸቶች ውስጤን ረበሹት።በተለይም ደግሞ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በኩል እየቀረቡ ያሉ ጉዳዮች ኢትዮጵያን ወደፊት ወደ አልተፈለገ አቅጣጭ እንዲሚወስዷት ሳስብ የተሰማኝን ነገር ለመፃፍ ወሰንኩ። እነሆ ለዛሬው ይህችን ነገር ማለት ወድጃለሁ። በሙስሊሙ ማህበረሰብ የስነ-ምግባር ምጥቀትና አሰተዋይነት እንደኮራሁበት ግን ሳልገልፅ አላልፍም።ኢንሻአለህ ደግሞ ከአሁን በሗላ አንዱ የትግል አባል መሆኔን ለእራሴ ቃል ገብቻለሁ።
“ነፃ ምሳ የለም!” or “There is no free lunch”
አዎን!ኢስላም አሁን እኛ እጅ የደረሰው በምድር ላይ አሉ የሚባሉ ውድ፡ ክብርና ዕንቁ ነገሮች መስዋዕት ሆነው ነው። ታሪካችን በብዙ ውጣውረዶች የተሞሉ ክስተቶችን በጥንቃቄና በሰፊው ዘግቦ ለእኛ አድርሶናል። ይህ ታሪካችን ደግሞ የጥንካሪያችን ምንጭ፡የተስፋችን መሰረት፡የራዕያችን ጉልበትና የማንነታችን መገለጫም ጭምር ነው። እርግጥ ነው ታሪክ የሌለው ትውልድ ታሪክ አይሰራም።ኢስልምና እንደ እምነት ብዙ ታሪኮችን አሳልፎ አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል።በኢስልምና ላይ የተቃጡና ሲጋረጡ የነበሩ ፈተናዎች የጀመሩት “የተሃድሶው” መሪ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ገና ሰዎችን ወደ ኢስላም መጥራት በጀመሩበት ጀንበር ነበር።ሁሉም ሙስሊም ጠንቅቆ እንደሚረዳው እስልምና ከዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከሰው ልጆች ሁሉ በላይ የሆኑትና የመልካም ስብዕና ባለቤት የሆኑት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመከራ ዓይነቶችን ሁሉ ተሸክመውና አይተዉበት ነው።ከረሃብ ና ጥም፡እርዛት፡ስደት፡ ስድብ፡ድብደባ፡ዕንግልትና የግድያን ሙከራዎች ጨምሮ አሉ የሚባሉና ለማሰብ የሚከብዱ ችግሮችን አሰተነግደውበታል። ለዚሁ ዲን ሲሉ የተሰውለትን ሶሀባዎች፡ታቢኢዮች፡ቀደምት ታላላቅ ኡለማዎችና እሰከ ዘመናችን ድረስ ብዙ የአላህ ቅን ባሪያዎችን ብዛትና ማንነት ለማወቅ ኢስላማዊ የታሪክ ማህደርን ያገላበጥ ሙስሊም በእንባ የሚያስንጡ ክሰተቶችን ያገኛል።
ይህ ጉዳይ ደግሞ በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ቦታ አለው። ኢስልምና መጀመሪያ ከመካ ቀጥሎ የገባባት ሃገር ከመሆኗ አንጻር ኢትዮጵያዊይን ሙስሊሞች ታሪካችን ዕድሜ ጠገብ ነው።የዛሬን አያድረገውና!-አዎን!ያኔ!ጠዋት ሃገሬ ኢትዮጵያ የአለም የፍትህ ተምሳሌት ነበረች።የተበደሉ ሙስሊሞችን እንባ አብሳለች-የያኔየዋን ኢትዮጵያን ነው የምላችሁ ፍትሃዊዩ መሪ የነበረበትን ዘመን። የዛሬዋን አይደለም እንባየን በለሊትም በቀንም የምታፈሰውን፡ ተናንሸ እየለመንኳት የምትረግጠኝን፡መልካም ነገሪ ብዙ ሆኖ ሳለ የሌለብኝን መጥፎ ባህሪ አለብህ እያለች የምትደበድበኝንና የምታሰለቅሰኝን አይደለም የምላችሁ።ሰላም ስላት ‘ብትር የምታነሰብኝን’ አይደለም እያልኳችሁ ያለሁት!። “ብርቱካን ስሰጣት ድንጋይ የምትወረውረብኝን” ማለቴም አይደል።የአሁኗን ባለውለታይን “አሸባሪ” ብላ ‘የመዓረግ’ ስም የሰጠችን ከመሰላችሁም ተሳሳታችሁል። የዛሬዋን ኢትዮጵያን “ባለ ራዕዩ ና ፍትሃዊዩ መሪ!” ያለባትን ኢትዮጵያ ማለቴም እንዳልሆነ ትረዱኝላችሁ። ያልኳችሁ ግን ባለውለታየን የነጋሺ ዘመን ኢትዮጵያ ነው! በርግጥም እሷን ነው-እመኑኝ!!!
ግን ብዙም ሳያመሸ ይህ ጉዳይ ተገልብጦ ኢትዮጵያዊይን ሙስሊሞች አሉ የሚባሉ የግፍ አይነቶችን አጼ ሄዶ አጼ ሲተካ ንጉስ ወረዶ ንጉስ ሲሾም እየቀመሱ የዲናችንን መሰረት አሁን ላለው ትውልድ በክብር አስረክበውናል።ቀን ‘ክርስቲያን’ ለሊት ከአላህ ፊት ተደፍተው ‘እንባ የሚያነቡ ሙስሊሞች’፡ስማቸውን ከ ‘ሙሐመድ’ ወደ ‘ከበደ’፡ልጆቻቸውን ከትምህረት ገበታ አርቀው፡ምላሳቸውን እየተቆረጡ፡ሴቶች ጡታቸው ‘እየተጋጠጠ’...የግፍ ዓይነቶችን ሁሉ ቀምሰው አባቶቻችን ይህን ዲን (ኢስላምን) እኛ እጅ ላይ አድርሰውልናል። አልሐምዱሊላህ! አባቶቻችንና ቅድመ-ዓያቶቻችንን እናከብራችሁለን!እንወዳችሁለንም!አለህ ጀነትን እንዲወፍቅልን ዘወትር እንማፀነዋለን! አዎን-ውድ ሃብት አውርሳችሁናልና።ኢስላምን ብሩህ የህይወት መንገድ፤የመረጋጋት፡የደስታና የስኬት ምንጭ፤ያማረ ማህበራዊ ኑሮ መገንቢያ መሰፈረት ባለፀጋ፤ የማይደረቅ የህይወት ምንጭ፤ ለሰው ልጆች ችግር ሁሉ ቁልፍ መፍትሄ አመላካች የሆነውን ኢስላምን- በጠራ መንገድ ላይ ሳይበረዝና ሳይደለዝ ስላደረሳችሁን ውለታችሁ ከብዶናል።አሁንም እናመሰግናችሁለን።ታላቅ አክብሮትም አለን።ለዚህ ውድ ዲን የተከበረ ህይወታችሁን አሳልፋችሁ ሰጥታችሁ በተግባር የመስዋዕትን አከፋፈል አስተምራችሁናል።አልሃመዱሊላህ!

የኢትዮጵያዊይን ሙስሊሞች ታሪክ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ‘ነፃ ምሳ እንደሌለ ነው’።እንኳን ዛሬ ‘ኑሮ ሰማይ በነካበት’ ጊዜ ይቅርና በድሮ ዘመንም ነፃ ምሳ አልነበረም። ምሳ ለመብላት ዋጋ መክፍልን ይጠይቃል።ገንዘቡንም ለማገኘት ቢሆን ‘ነጭ’ ላብ እስኪወጣ መስራትን ይጠይቃል። የኢትዮጵያዊይን ሙስሊሞችን ታሪክ ወደሗላ መለስ ብይ ስመለከት የአንድ ንጉስ ታሪክ ከኢትዮጵያዊይን ሙስሊሞች ታሪክ ጋር ሲመሳሰልብኝ ነው የዚህችን አጭር ፅሁፍ ርዕስ “ነፃ ምሳ የለም” ያልኳት።ታሪኩ እንዲህ ነው፦ “አንድ ንጉስ ብዙሪያው ለነበሩት አማካሪዎቹና ረዳቶቹ አንድ የቤት ስራ ይሰጣቸዋል።የቤት ስራውም በንጉሱ የአሰተዳደር ዘመን አሉ የሚባሉ መልካምም ይሁን መጥፎ ተሞክሮዎች እንዲሰበስቡና እንዲያቀርቡለት ነበር።አላማውም ተሞክሮዎቹን ለትውልድ በውርስ መልክ ለማሰተላላፍ ነበር።አማካሪዎቹና ረዳቶቹ የቤት ስራቸውን በፍጥነት በመስራት በርከት ያሉ ባለብዙ ቅፅ ‘ጥራዞችን’ አዘጋጅተው ለንጉሱ አቀረቡለት። ንጉሱም ጥራዞቹ ስለበዙ የሚያነባቸው ስለማይኖር ከእንደገና እንዲቀንሱት ያዛቸዋል። ከዛም አንድ ቅፅ አድረገው ይሰጡታል። አሁንም ቀንሱት ይባላሉ። አንድ ምዕራፍ ያቀርባሉ። አሁንም እንዲቀንሱት ይታዘዛሉ። ከዚያም አንድ አንቀፅ አድረገው አቀረቡለት። ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያሳጥሩት ሲጠየቁ አንድት አረፍተ ነገር ብቻ ይዘውለት ይመጣሉ።ንጉሱም በአረፍተ ነገሯ ተስማምቶ ለትውልድ አስተላለፋት።አረፍተ ነገሯም “ነፃ ምሳ የለም” or “There is no free lunch” የምትል ነበረች።”
አዎን! ኢትዮጵያዊያን ሙስሊም አባቶቻችን ከማንምና ከምንም በላይ “ነፃ ምሳ የለም” የሚለውን መርህ በተግባር ኑረው አሳይተውናል።መብት በነፃ አይገኝም፤መብት እንዲከበር ይጠየቃል እንጂ አይለመንም፤መብት በህልም ቅዥት ሳይሆን በገሃዱ አለም በትግል ይከበራል፤መብት የሚገኘው በማያቋራጥና በትክክለኛ መንገድ በፅናት በመታገል ብቻ ነው ሲሉ በተግባር ገስፀውናል። ስለዚህ ‘የኢህአዲግ’ መንግስት ማወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ጥያቄ የ ‘ካርታ ጨዋታ’ አለመሆኑን ነው። እኛ ሙስሊሞች ጠራራ ፀሃይ ብሎም በዶፍ ዝናብ ሳይቀረ ‘ድምፃችን ይሰማ’ የምንለው ለትረፍ ነገር አይደለም። መሰረታዊ የማንነት ጥያቄ ነው።“ነፃ ምሳ የለም” ብለው ያወረሱንን አባቶቻችን ቃል በማክበር እስከ ዕለተ ህልፈታችን ድረስ የህይወታችን መርህ አድርገን ለልጆቻችንም “ነፃ ምሳ የለም የማይጣፍጥ ምሳም ቢሆን” የሚለውን ጨምረን እናስተላልፍላቸዋለን። ይልቁን መንግስት ረጋ ብሎ ወደ ህሊናው ተመልሶ፡አስቦ፡አስተውሎ ለጥያቄያችን መልስ ሰጥቶ፤ይህችን ድሀ ሃገራችንን ካለችበት ድህነት አብረን እንታደጋት እላለሁ። በቅርቡ ደግሞ ስለሰላማዊ ትግላችን ትንሽ ለማለት እሞክራለሁ።ኢንሻአላህ!

1 comment: