Tuesday, November 13, 2012

“የሰላማዊ ትግላችን... ሰላማዊ ቦምቦች”


“የሰላማዊ ትግላችን... ሰላማዊ ቦምቦች” (ቁጥር 1)

ደነገጣችሁ እንዴ ቦምቦች ስል? አውፎን? አብሽሩ! ሰላማዊ ቦምቦች ነው ያልኳችሁ...የምን መፍራት! ስለ ኢስላም እያወሩ መሸበር የለም። ኢስላም...ለ ‘ሰላማዊ ቦምቦች’ እንጂ...ዛሬ አለማችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች ተጠቅማ ላበረከተችልን ‘ጂምላ ጨራሽ’ መሳሪያዎች ቦታ የለውም።ኢስላም...ሰላም ነውና!

ዛሬ ሚዲያ ሞልቶ ቢተርፋቸው...ሰላማዊ ስምህን ቢያጠለሹት እውነት እንዳይመስልህ። ኢስልምናን ከአሸባሪነት ጋር እያገናኙ ሲለፍፉልህ አመንካቸው እንዴ? ለዘመናት ቢለፍፉ...መመሪያውን ‘ስሜት’ ሳይሆን ‘ቁርአንንና ሃዲስን’ ያደረገ ትውልድ ይህን ነገር ከመጤፍ አይቆጥረውም። ስኳርን ትሪሊ
ዮን ግዜ... ‘ጨው’ እያልክ ብትጠራው ከጣፋጭነቱ ይቀየራል እንዴ? አይቀየርም! ኢስልምናንም ትሪሊዩን ጊዜ አሸባሪ ቢሉት ከሰላማዊነቱ አይቀይሩትም። ኢስላም ሁልጊዜም የሚሰብከው ስለ ሰላም ነውና! ኢስላም...የአንድን ንፁህ ሰው ነፍስ ያለበቂ ምክንያት ማጥፋት...የሰው ዘርን በሙሉ እንደማጥፋት ይቆጠራል ብሎ አስተምሮህ። አንድን ንፁህ ነፍስ የታደገ...የሰው ዘርን እንደማዳን ይቆጠራል ብሎ ገስፆህ...ለምን ቦምቦች ስልህ ትደነግጣለህ? አብሸር! የምን መሸበር ነው...ኢስላም የሽብር ዲን አይደለም!...የሰላም እንጂ። አቦ ሆድ ይብሰኛል... ወዴ አሸባሪነት ርዕስ ከገባሁ... አይክፋቸሁና ቶሎ ልውጣ ከዚህ። በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ርዕስ ውስጤ ያለውን ሁሉ አካፍላችሁ አላሁ...ኢንሻአላህ። ለዛሬው ግን...እምኑኝ የማወራችሁ ሰለ ሰላማዊ ቦምብ ነው። ያለ ክፍያ...ስለሚገኘው ቦምብ። በጥንቃቄ...ከተጠቀምንበት የ21ኛው ክ/ዘመንም ይሆን ማንኛውም ቴክኖሎጂ ከሚያፈሯቸው ‘ጂምላ ጨራሽ’ ቦምቦች በውጤታማነቱ በእጂጉ ይልቃል። የአላህ ፍቃዱ ከሆነ...በተከታታይ ክፍሎች “የሰላማዊ ትግላችን ...ሰላማዊ ቦምቦች” በሚለው አምድ ስር...ትንሽ ነገር ለማስነብብ ፈልጌ ነው። ይኼው...የመጀመሪያውን ጀባ ብያለሁኝ! ተቀብሎ መተግበር የሁላችንም ሃላፊነት ነው!


ሰላማዊ ቦምብ ቁጥር 1፡ ዱዓ

ዱዓ ህይወታችንን ወደ መልካም ነገር የመቀየር ሃይል አለው። ዱዓ የሰውን ውጫዊና ውስጣዊ ማንነት ያስተካክላል።ዱዓ ቀደርን ሳይቀር የመቀየር ሃይል አለው። ዱዓ እንደ ኢስላም አስተምህሮ በችግርም ይሁን በድሎት ጊዜ የሚጠቅም የሙሰሊሞች ቦምብ ነው። በአንድ ውቅት ነቢዮ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሆነ ቦታ ሲያልፉ ሰዎች ችግር ውስጥ ሆነው ተመለከቱና “ለምንድነው እነዚህ ሰዎች ወደ አላህ ዱዓ የማያደርጉት ከዚህ ችግር እንዲጠብቃቸው።” ሲሉ ተደምጠዋል። ዛሬ ላይ ሆነን በሁሉም የአለማችን ክፍል ሙስሊሞች ትልቅ ችግር ውስጥ ነን። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ከጎናችን ቢኖሩ ከላይ ያሉትን ነገር ዛሬም ይሉት ነበር። በእርግጥ እርሳቸው በአካል ባይኖሩም አስተምህሮታቸው ሳይበረዝና ሳይደለዝ በሁለችንም ቤት አለ። ተቀብሎ መተግበር ሃላፊነቱ የተጣለው ከእያንዳንዳችን ላይ ነው።

በእርግጥ ዛሬ ዱዓን ሙሉ በሙሉ እረስተነዋል ማለት አይደለም። በየጊዜው እጆቻችንን ወደላይ አንስተን እያነባን ነው። ለዱዓ ያለን ምልከታና ትግበራ ግን ብዙዎቻችን ላይ ትክክል አይመስልም። ብዙዎቻችን ዱዓ ኢባዳነቱን የዘነጋነው ይመስላል። ለዱዓ ያለን ምልከታ ዱዓ ‘ለደካሞች’ና ‘ተስፋቸው ለደከመ’ ሰዎች መፅናኛ እስኪመስለን ድረስ ዱዓን የመጨረሻ አማራጭ አድርገን ወስደናል። ምንም ነገር ለማድረግ አማራጭ የሌላቸው ሰዎች መጠለያ መስሎ ታይቶናል። እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። ከሰው ሰራሽ መሳሪያዎች ሁሉ በላጩ መለኮታዊ ትዕዛዝ ያለበትን ዱዓ አጥብቆ መያዝ ነው። ከሃብት ሁሉ በላጭ የዱዓ ሃብት ነው። እንደ ኢስላም አስተምህሮ...ዱዓ አመራጭ ያላቸውም ይሁን አማራ የሌላቸው ሰዎች በእኩልነት የሚያስፈልጋቸው መሳሪያ ነው።

በእርግጥ በዚህ ዘመን ዱዓን ከደካማነትና ምንም ማድረግ ካለመቻል ጋር ሲገናኝ ማየት በጣም ያሳዝናል።ዱዓ የኢባዳዎች ሁሉ መሰረት መሆኑ ሲዘነጋ ሆድ ይብሳል። ለአንድ ሙስሊም ከዱዓ የተሻለ መሳሪያ የለውም። በችግርም ይሁን በድሎት ጊዜ ያስፈልገዋል። ኢባዳ ያለ ዱዓ ጣዕም የለውም። ያለ ዱዓ ኢባዳ መልካም መዓዛ ይርቀዋል። ያለ ዱዓ ተግባራችን ሁሉ ውስጣዊ ሃሴትን አይሰጥም። ዱዓና ኢባዳ የማይለያዩ የኢስላም መሰረቶች ናቸው። አንዱን ይዞ ሌላውን መተው አያስኬድም። ዱዓን መሳሪያው አድርጎ የያዘ ኡማ (ማህበረሰብ) ፈፅሞ አይወድቅም። ያለ ዱዓ ደግሞ በራስ ሃይል አንድ እርምጃ የሚራመድ የሙስሊም ኡማ የለም። ስለዚህ በአንድ ሙስሊም ህይወት ውስጥ በእያንዳነዱ የህይወት ጉዞው በሚያቅዳቸውና በሚተገብራቸው ደርጊቶች ውስጥ ዱዓ ትልቅ ስፍራ አለው።

<አስተማማኝ... የመገናኛ መስመር>

ዱዓ ከአለማቱ ፈጠሪ፤ከሃያሉ አምላክ፤ ሁሉን ሰሚ፡ አዋቂና ተመልካች፤ የፍጡራን ሁሉ አምላክና የንግስና ባለቤት ከሆነው አላህ ጋር ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሚያገናኝ የሙዕሚን መሳሪያ ነው። የበዳዮችም የተበዳዮችም አምላክ...ከሆነው አላህ ጋር የሚያገናኝ መስመር ነው። ፍጡራን ሁሉ ወደውም ይሁን ሳይወዱ የሚገዙት የሆነው አላህ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው።አማላጅ ሳያስፈልግ፡ የ ‘ነብስ አባት ሳንሻ’ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ከአላህ ጋር ቀጥተኛ ቃለ ምልልስ የምናደርግበት ጊዜ የማይሽረው የመገናኛ ዘዴ ነው። ወላሂ! ምን ያማረ መገናኛ..ዱዓ! ዱዓ...ከማንኛውም ፍጡራን የባርነት ቀንብር ተላቀን በነፃና ያለምንም የፍጡራን ጣልቃ ገብነት ከአላህ ጋር በቀጥታ የሚያገናኘን መስመር ነው። ወደ አላህ ዱዓ የምናደርገው ከእርሱ ጋር ሁሉም መከራዎችና ችግሮች የተሟላ ምላሽ እንዳላቸው ስለምናምን ነው። ይኼ በራሱ...ተውሂድ ነው። ሁሉን ነገሮች በተሟላ መልኩ መፈፀም የሚችለው አላህ መሆኑን የምናረጋገጥበት ተውሂድ!
ችግሮቻችንን ለአላህ ካቀረብን በሗላ...ውስጣችን ቅልል ይለዋል። ጭንቀታችን ይወገዳል። ውስጣችን...ይረጋጋል። በዙሪያችን የአላህ እዝነት መኖሩን እንረዳለን። አላህ ያሳየንን መንገድም አጥብቀን ይዘን በእርሱው ላይ ለመጓዝ በእያንዳንዱ ዱዓ ቃል ኪዳናችንን ለእራሳችን እንዳሳለን። በሁለቱም አለም ስኬታማነት የሚገኘው በዚሁ መንገድ ላይ መሆኑን እንረዳለን። ይኼም...የትክክለኛ ተውሂድ መገላጫ ነው። አስተማማኝ...የመገናኛ መስመር ማለት ይኼው ነው። በማንኛውም ወቅትና ሁኔታ ኔትወርክ አያስቸግርህም። በተደጋጋሚ ያለ ክፍያ ደውለህ ችግርህን ማወያየት ትችላለህ።ስንፍና ካልተጫነህ በስተቀር!

<የመጀመሪያውም...የመጨረሻውም ተግባር>

እንደ ሙስሊም በእያንዳንዱ ጉዳያችን ውስጥ የመጀመሪያው ነገር ዱዓ ነው። በጉዳያችን ሂደት ውስጥም ትልቅ ቦታ ያለው ዱዓ ነው። ጉዳያችን ሲፈፀምም...በዱዓ ይፈፀማል። የሙስሊም ህይወት የሚያምረው...በዱዓ ሲጌጥ ነው። ጣዕምና ለዛም የሚኖረው...በጉዳዮቻችን ላይ ሁሉ የአላህ እርዳታ ሲኖርበት ነው። የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንዴት መቋቋምና ከችግሩ እንዴት መውጣት እንደሚቻል አላህ የመፍትሄ በሩን እነዲያሳየን እንጠይቀዋለን። የአላህን እርዳታ እንሻለን። በጥቅሉ በኢስላም ላይ ኑረን...በኢስላም ላይ ለመሞት የአላህን እገዛ እንሻለን። የሰው ልጆች...በእኛ ‘ብስለት’ ና ‘ብልጠት’ ምንም ማድረግ አንችልም። በምድር ላይ ጥረታችን ሁሉ ስኬታማ እንዲሆን የአላህን እገዛ እንሻለን። ለሁሉም ነገራችን በመጀመሪያውም...በሂደቱም ውስጥ...በመጨረሻውም ሰዓት ሁሉ ውጤታማ መሳሪያችን ዱዓ ነው።

<የአምልኮ...አስኳል>

ዱዓ የኢባዳ መቅኔ ነው። በዱዓ ላይ ዘውታሪ ሰዎች በአላህ ብቸኝነት ጥልቅ እምነት ያላቸው ናቸው። በተውሂድ ግንዛቤያቸው ላቅ ያለ ሰዎች ዱዓ ያበዛሉ።ሽርክን በብዙ የራቁ ሰዎች ናቸው። አዎን! በዱዓ ተውሂድ ይረጋገጣል። በዱዓ...’ቁሳዊይም ይሁን አሰተሳሰባዊ’ ..ከሆኑ ጣዖታት ይራቃል። በዱዓ...ኢማን ይጨምራል። በዱዓ ሰዎች ከኩራት ይርቃሉ። ሰዎች ከግላዊ ኢጎ () ይላቀቃሉ። እስኪ ይህን ዱዓ አንብቡት፦ “አላህ ሆይ! እኔ ራሴን ከማውቀው በላይ አንተ እኔን በደንብ ታውቀኛለህ። እነዚህ ሰዎችም እኔን ከሚያሞግሱኝ በላይም ራሴን በተሻለ ሁኔታ አውቀዋለሁ። እነርሱ ከሚያሞግሱኝና ከሚያስቡኝ በላይ የተሻለኩ አድርገኝ። እነርሱ የማያውቋቸውን ወንጀሎቼንም ማረኝ። እነርሱ በሚሉት ነገር ላይም ተጠያቂ አታድርገኝ” አቡበከር አል ሲዲቅ ናቸው ይህን ዱዓ ያደረጉት። ምን ያክል መተናነስ እንዳለበት በዱዓው ውስጥ በግልፅ ይታያል። ዛሬ ላይ ሆነን ስንቶቻችን ነን በሰዎች ዘንድ መሞገስን ይምንሻ። ስንቶቻችን ነን ለግለዊ ክብራች ቅድሚያ ሰጥተን ከእውነታዎች ጋር የምንላተም። በሰዎች መሞገስ... በውስጣችን ያለውን እውነታ አይቀይርም። እራስን ሳይዋሹ መመርመር ያስፈልጋል።

በዱዓ መልካም ስነ ምግባር ይታነፃል። የሻከሩ ልቦች ይለሰልሳሉ። የተራራቁ ልቦች ይቀራረባሉ። ኢስላማዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ይጠናከራል። የሙስሊሞች አንድነት ይጠናከራል። መካራና ችግር ይወገዳል። ሰዎች ፅናት ያገኛሉ። የአላህ ታላቅነት ይመሰከራል። የሰው ልጅ ካለ አላህ እገዛ ምንም መሆኑን ይረዳል። ይህ የተውሂድ መሰረት ነው። በዱዓ ዘወትር እራሱን የሚያሳትፍ ሙስሊም በአላህና በእርሱ መካካል ያለውን ግንኙነት በአንክሮ የተረዳ ሙስሊም ነው። ይህ ነው የእምነት ዓላማም...ችግሮችን ሁሉ ለአላህ ማቅረብ። ፍፁም በቂና የተሟላ ምላሽም ያለው ከእርሱ ዘንድ ብቻ መሆኑን መገንዘብ። ለዛም ነው...ዱዓ የኢባዳ አስኳል ነው የሚባለው።

<ትልቅ...ትንሽ>

ለትንንሽም ይሁን ለትልልቅ ጉዳዮች በአላህ መታገዝ የሙዕሚኖች ትክከለኛ መንገድ ነው። ለትንሽም ይሁን ለትልቅ ጉዳያችን አላህን መያዝ የጥበብ መጀመሪያ ነው። ከምንጠይቀው አምላክ በኩል ምንም ነገር የማይቻል የለም። ከጠያቂዎቹ በኩል ደግሞ የአላህ እገዛ ከሌለበት በሰተቀር በራሳችን አቅም ትንሽንም ነገር መስራት አንችልም። ይህ ትልቅ የተውሂድ አስተምህሮ ነው።ፊታችንን ወደ አላህ ስናዞር በተናነሰና ስርዓት ባለው መልኩ ሲሆን ነገሮች ሁሉ ምላሻቸው ያምራል። አላህንም ስንጠይቀው ምላሽ እንደምናገኝ በሙሉ ተስፋና የቂን መሆን አለበት። አላህም በኢህላስና በኹሽኡ እጆቹን የዘረጋን ባሪያ አይመልስም። እርሱ አዛኝ አምላክ ነውና። “ምንም ነገር ለአላህ የቀረበ የለም...ወደርሱ ዱዓ ከሚያደረግ ባሪያው የበለጠ” ነው እንደ ኢስላም አስተምህሮት።

<በማንኛውም ጊዜ ... በሁሉም ፍላጎቶች>

ሙስሊም በማንኛውም ወቅት ዱዓ ያደርጋል። ለማንኛውም ጉዳዩ ዱዓ ያስፈለገዋል። በችግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን...በድሎትም ጊዜ ያስፈልጋል። ዱዓ የሙስሊም ባህሪው ነው። የኢባዳው አስኳል በመሆኑ። ነቢዮ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል “አላህ በችግርና በመከራ ጊዜ ዱዓውን እንዲቀበለው የሚፈልግ ሰው በምቾትና በድሎት ጊዜ ዱዓ ያብዛ”። ከአላህ በማንኛውም ወቅትና ለማንኛውም ጉዳይ ዱዓ ማድረግ አለብን። “ከአላህ ምንም ነገር የማይጠይቅን ሰው አላህ ይቆጣበታል።” አህመድና ቲርሚዚ እንደዘገቡት። በቁርአንም አላህ እንዲህ ይላል፦

“ጌታችሁም አለ “ለምኑኝ እቀበላችሗለሁና፡ እነዚያ እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ገሃነም በእርግጥ ይገባሉ።” (ጋፊር(40)፡60)

አሁን በግልፅ የገባን መሰለኝ።ዱአ አለማድረግ መዘዙ ብዙ መሆኑን የተረዳን መሰለኛ። ስለዚህ ዱዓ ያለማድረግ የአላህንም ቁጣ ሊያስከትል ይችላል። ዱዓ ያለማድረግ በሂደት በራስ መብቃቃትና ወደ ኩራት ሊወስድም ይችላል። ለዱኒያዊይም ይሁን ለአኺራ ጉዳያችን አላህን መጠየቅ አለብን። ለሁለቱም አለም ስኬት የሚገባቸውን ነገር ማድረግ ይጠበቃል። በኢስላም ለዱኒያ ብቻ መኖር የተጠለ ነው። ዱኒያን ረስቶ ለአኼራም ብቻ መመነንም የተጠላ ነው። መካከለኛ ሆኖ ለሁሉም የሚገባውን ሃቅና ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

<ለሁሉም...ሰዎች>

ዱዓን ከእራሳችን አለፍ ብለን...ለወላጆቻችን፤ለወንድሞቻችንንና ለእህቶቻችን፤ ለባለቤቶቻችንና ለልጆቻችን፤ ለዘመዶችና ለጓደኞች፤ ለኡለማዎችና ለኡስታዞች ለምናውቃቸውም ለማናውቃቸውም በየትኛውም የአላማችን ክፍል ይሁኑ ለኢስላም ሲሉ የሚታገሉ ወገኖችን በዱዓችን ማስታውስ ይጠበቅብናል። በዱኒያም በአኼራም መልካም ነገር እንዲለግሳቸው መማፀን ያስፈልጋል። “አንድ ሙስሊም ለሙስሊም ወንድሙ በሌለበት ዱዓ ሲያድረግ ተቀባይነት ያገኛል። ለዚሁ ስራም የተመደበ መላዒካ አለ። ለውንድሙ መልካምን ዱዓ ሲያደርግለት...መላኢካው “አሜን” ይላል።አንተም ለወንድምህ በጠየከው ነገር ተባርካሃል ይባላልም” (በሶሒህ ሙስሊም እንደተዘገበው)። ዱዓን አደቡንና ሸርጦቹን ጠብቀን ካደረግን ተቀባይነት እንደምናገኝ የቂን ሊኖረን ይገባል። አላህም የለማኞችን ዱዓ እንደሚቀበል እንዲህ ሲል ነግሮናልና፦

“ባሮቼም ከእኔ በጠየቁህ ጊዜ (እንዲህ በላቸው)፦እኔ ቅርብ ነኝ። የለማኝን ፀሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ። ስለዚህ ለእኔ ይታዘዙ፡ በእኔም ይመኑ፡እነሱ ሊመሩ ይከጀላልና” (በቀራህ(2)፡186)

አላህ ሆይ! አንተን በአደብ ጠይቀው ምላሽ ካገኙ ህዝቦች አድርገን። አላህ ሆይ! ይህንን የሰላም ቦምብ አንግበው ጠላቶቻቸውን ድል ከሚያደርጉ ኡማዎች አድርገን። አንተን ለምነው ካሉበት ችግርና መከራ ከተላቀቁ ሰዎች አድርገን፤ ይህንን የሰላም ቦምብህን አንተ በፈለግከው መልኩ ተጠቅመው አሸናፊ ከሚሆኑም ህዝቦች ውስጥ አድርገን። ለአንተ ምንም የሚሰንህ ነገር የለምና! አሜን።


“የሰላማዊ ትግላችን... ሰላማዊ ቦምቦች”  ቁጥር 2

የዛሬው... “ሰላማዊ ቦምባችን” ሰፊና የኢስላም ወሳኙ አስተምህሮ በመሆኑ ትንሽ ሰፋ ይላል። በትዕግስት አንብቡኝ...በእርግጥ ስለዚህ ርዕስ በዚህች አጭር ፅሁፍ ብዙ ማለት አይቻልም። የፅሁፉ አላማ መጠቆም ብቻ ነው።ስለ ርዕሱ በቂ ግንዛቤ ለማገኘት የግል ጥረትን ይጠይቃልና...ቁርአንን...ሃዲስን...ሲራን...ሃያቱ ሶሃባን ማገላበጥ ስለሚጠይቅ ትንሽ ጊዜ እንስጠው።

*ሰላማዊ ቦምብ ቁጥር 2፡ መልካም ስነ-ምግባር*

በዚህች ምድር ላይ የሰዎችን ልቦና አስበርክኮ የሚገዛ ነገር አምባገነናዊ ስርዓት አይደለም።ጉልበት፡ ስልጣን ወይም ገንዘብም አይደሉም። ታዲያ ሰዎቸን ለሰዎች እጂ እንዲሰጡ
አንዳቸው ለአንዳቸው አርአያ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ምንድነው ብትሉኝ? መልካም ስነ ምግባር እላችሁለሁ ምንም ሳላቅማማ! መቼም አትጠይቁኝም እንጂ እንዴት አውቅክ ካላችሁኝ ደግሞ? ዛሬ ላይ በአለማችን ወደ 1.7 ቢሊዮን የሚሆኑ ሙሰሊሞች ከሰዎች ሁሉ በላይ የሚወዱት ማንን ነው? ሰዎች ሁሉ በአካል ሳያዩት እኔ ስለ እረስዎ የሚሉት ለማን ነው? ማንነታቸውን የኢስላም ጠላቶች ሊያጎድፉት ሲነሱ በእንባ እየተራጩ እኔ ስለ እርሰዎ የሚባልላቸው ማን ናቸው? በአካል ሳይታዩ በመካከላችን ብዙ የዘመን ግርዶሽ ተቀምጦ ይህን ያክል የሚፈቀሩትና የሚወደዱት ሰው ማን ናቸው? የ14 ክ/ዘመናትን የዘመን ጂረት ተጉዞ በእኛ ልብ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው የሰዎች ሁሉ ፈረጥ ማነው? ሱብሃንአላሀ! አንድን ነገር ላይጨረሱ መጀመር እንዴት ይከብዳል? የኢስላም ሊቃውንቶች ከሚጠቀሙት አባባል በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ “የነቢዮ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ጉዞ በየትኛውም መስክ ለመግለፅ ብትሞክር አንድ ነገር እርግጠኛ ሁን ይላሉ። ትጀምረውለህ...እንጂ አትጨረሰውም!” ድንቅ የሆነ አባባል! አዎን!...ይህ ሰው ያለ ጥርጥር ነቢዮ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ናቸው። የመፈቃራቸውንም ሚስጥር ቁርአን በግልፅ እንዲህ ሲል ገልፆታል።

“አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ” (አል-ቀለም(68)፡4)
“(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጂ አልላክንህም።” (አል.አንቢአ (21)፡107)

ይህ መልካም ስነ ምግባርና አዝነት በነቢዩ ላይ ባይኖር ኖሮ...ዛሬ ላይ ምናልባት በኢስላም ጥላ ስር ባልተሰበሰብን ነበር። አላህም እንዲህ ሲል ይገልፃል፦
“ከአላህ በኾነች ችሮታ ለዘብክላቸው።ዐመለ መጥፎ፡ልበ ደረቅም በኾንክ ኖሮ ከዙሪያህ በተበተኑ ነበር። ከእነርሱም ይቅር በል። ለእነርሱም ምህረትን ለምንላቸው። በነገሩም ሁሉ አማክራቸው።...” (አል.ኢምራን(3)፡159)

መልካም ስነ ምግባር ሰዎችን ይሰበስባል ተቃራኒው ግን ሰዎችን ከዲኑ ያባራል። የመላካቸውንም አላማ ሲገልፁ “እኔ የተላኩት በሰዎች ዘንድ መልከም ስነምግባርን ለመሙላት ነው” ብለዋል። የአቡበከር ሲዲቅን፤የኡመር ኢብን አል ኸጣብን፤ የኡስማን ኢበኑ አፋንን፡ የአሊይ ኢብን አቢጧሊብንና የአነዚያን የከዋክበት ሶሃቦች (ረ.ዐንሁም) ምንነት ስትገመግም የመልካምነታቸው ሁሉ መሰረቱ መልካም ስነ ምግባራቸው ነበር፡፡

የእነዚህ ስብዕናዎች ስነ-ምግባር የሻከረ ቢሆን ኖሮ...ኢስላምና ገና ከመካ ሳይወጣ በጃሂሊያ ጊዜ ሴቶች ልጆችን ከነሂዎታቸው እንደሚቀበሩት እዛው በእንጭጩ ተቀብሮ በቀረ ነበር። ኢስላም ዛሬ ሁሉንም የአለማችንን ክፍሎች ባልዳሰሰው ነበር። ዛሬ ላይ ኢስላም የተስፋፋው በሰይፈ እንጂ በሰላም አይደለም እያሉ...መርዝ ባረገዘው ብዕራቸው ‘ኦሬንታሊስቶች’ ከትበው ቢያሰራጩልህ አትመናቸው። ህሊና ላለው ሰዎ ሁለት ተቃራኒና እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ሀሳቦች አብረው እንደማይሄዱ ይረዳልና።በአንድ በኩል ኢስላም የተስፋፋው በሰይፍ ነው አስተምህሮቱም የሸብር ነው እያሉህ በሌላ በኩል ደግም በአለማቸን ላይ በጣም በፍጥነት እያደገ ያለ እምነት...ኢስላም ነው ሲሉ ይለፍፉልሃል። ታዲያ እነርሱ እንደሚሉት ኢስላም የሽብር እምነት ከሆነ ለምን ይሆን በእየቀኑ ሰዎች የኢስላምን ብር የሚያንኳኳት? መቼም ለመሸበር አትሉኝም! አይደለም...ለመዳን ነው! የሰላምን ...ሂይወት በኢስላም ለመኖር ነው። ህይወት የሚጣፍጠው በኢስላም ነው። መልካም ስብዕና የሚገነባው በኢስላም ነው። ለነገሩ ኢስላምን ያጠኑት በመልካም ንያ ስላልሆነ አንፈርድባቸውም። ስራ የሚለካው በኒያ አይደል እንደ ኢስላም አስተምህሮ!

የኢስላም አስትምህሮ ሁሉ የሚያጠነጥነው ስነ.ምግባርን በማነፅ ላይ ነው። የኢስልምናን መሰረቶችና የኢማንን አርካኖች ብንመለከታቸው በሁሉም ማመን የሚጨረሻው ውጤት መልካም ስነ.ምግባርን ማሻሻል ነው።

<የኢስልምና መሰረቶችና...መልካም ስነምግባር>

<ሸሃዳ፡- ላኢላሃ ኢለላህ ሙሀመዱን ረሱሉላህ>
የመሰከረ ሰው አላህን ከሚያስቀይሙ ነገሮች ሁሉ ይርቃል። እሱን የሚያሰደስቱ ተገባሮች ላይ ብቻ ዘወትር እራሱን ያሳትፋል። የነቢዩን መልዕክተኛነት ያፀደቀ ሰው..ሱናቸውን ይተገብራል። የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሱና ደግሞ መልካም መዓዛ እንጂ ሌላ ምንም ጉድፍ የለውም።በመልካም ማዘዝ ከመጥፎ መከልክል..የነቢዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ኡማ ተልኮው...ይኼው ነው!

<ሶላት>
አላህ በቁርአኑ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል።
“...ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ።ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና።...” (አል አንከቡት(29)፡45)
የሰላት አላማው ከመጥፎና ከሚጠሉ ነገሮቸ ሁሉ ለመራቅ ነው። መጥፎ ነገሮችን የማይዳፈር ሰው የሰላቱ ውጤት ነው። ሁላችንም ለሶላታችን ዋጋ እንስጥ! ለሶላት ዋጋ መስጠት ለሒይወት ዋጋ መስጠት ነውና።

<ዘካ>
“ከገንዘቦቻችሁ ስትሆን በእርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምፅዋት ያዝ። ለነሱም ፀልይላቸው...” (ተውባህ(9)፡103)
ዘካ ለሚያወጣው ሰው ራስ ወዳድነትንና ስስትን ያስወግድለታል።ቀሪ ገንዘቡንም ያጠራለታል። ዛካ የሚቀበሉ ሰዎች ከምቀኝነት፡ ከቅናትና ከጥላቻ ይርቃሉ። ከዚህ በላይ የስነምግባር ምጥቀት ምንድነው? አላህ ምፅዋት (ሶደቃ) የሚያወጡ ሰዎችን እንዲህ ሲል በቁርአን ውስጥ በስዕላዊ መንገድ ይገልፃቸዋል፦
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እንደዚያ ገንዘቡን ለሰዎች ማሳየት ሲል እንደሚሰጠውና በአላህና በመጨረሻውም ቀን እንደማያምነው ሰው ምፅዋቶቻችሁን በመመፃደቅና በማስከፋት አታበላሹ። ምሳሌውም በላዮ ላይ አፈር እንዳለበት ለንጣ ድንጋይ ሐይለኛም ዝናብ እንዳገኘውና ምልጥ አድርጎ እንደተወው ብጤ ነው።ከሰሩት ነገር በምንም ላይ (ሊጠቀሙ) አይችሉም።...(በቀራህ (2)፡264)
አዎን...የሁሉም ሰራዎች ውበት ለአላህ ብቻ ተብሎ በመሰራቱ ላይ ነው።

<ፆም>
አላህ በቁርአኑ ውስጥ “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ፆም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ህዝቦች) ላይ እንደተፃፈ በናንተም ላይ ተፃፈ (ተደነገገ) ልትጠነቀቁ (አላህን ልትፈሩ) ይከጀላልና።” (በቀራህ(2)፡183
አዎን! የመራቡ የመጠማቱ የመጨረሻ ግቡ መጠንቀቅን (ተቅዋን) ማስረፅ ነው።በዱኒያ ላይ የሚያጋጥሙ የህይወት መሰናክሎችን ሁሉ ተጠንቅቆ ማለፍ። ተቅዋ ደግሞ ሁሌ መልካም ነገር እንጂ መጥፎ ፍሬ የለውም።

<ሃጂ>
“ሐጅ (ጊዜያቱ) የታወቁ ወሮች ናቸው። በእነርሱም ውስጥ ሐጅን (እንዲሰራ) ነፍሱን ያስገደደ ሰው በሐጅ ውስጥ ሴትን መገናኘት ማመፅም ክርክርም የለም። ከበጎ ስራ የምትሰሩትን ሁሉ አላህ ያውቀዋል። ተሰነቁም፡ ከስንቅም ሁሉ በላጩ ጥንቃቄ (አላህን መፍራት) ነው። የአእምሮዎችም ባለቤቶች ሆይ ፈሩኝ።” (በቀራህ(2)፡197)
አላህን መፍራት መልካም ስነ ምግባሮችን ሁሉ ይወልዳል። ሐጅ የሰዎችን እኩልነት በተግባር ያረጋግጣል። አረቡ አረብ ካልሆነው ጋር፡ጥቁሩ ከነጩ ጋር፡ ባለ ስልጣኑ ከተራው ሰው ጋር...ነጭ ለብሶ ትካሻ ለትካሻ ሆነው...ለአለማቱ አምላክ ባርነታቸውን ይመሰክራሉ።በሐጅ በጎሳና በዘር መኩራራት የሚባሉ መርዘኛ በሸታወች ይታከማሉ።

<የኢማን እርከኖችና...መልካም ስነ ምግባር>

<በመጨረሻው ቀን ማመን> ሰዎች አላህ ፊት ቆመው መጠየቅን ስለሚፈሩ መልካምን እንጂ መጥፎ ነገርነ ላለማሰብ ጥሩ ስራን እንጂ መጥፎ ተግባርን ላለመላመድ ጥረት ያደርጋሉ። በአኼራ የማያምን ሰው የሚመራው በስሜቱ ብቻ ነው።ደስ ሲለው መልካም ይሰራል ሲደብረው ይዘርፋል ወይም ይገድላል ማንንም ስለማይፈራ።ተጠያቂነትና ሃላፊነት ስለማይሰማው። <በመላኢካዎች ማመንን> ብንወስድ...ሁል ጊዜም ለአላህ ታዛዥ መሆን እንዳለብን እንማራለን። እነርሱ ሁልጊዜም ቢሆን አላህ ያዘዛቸውን ነገር ዘወትር ፈፃሜዎች መሆናቸውን ስትረዳ አላህን የማያምፁ መሆናቸውን ስትገነዘብ...እኔስ ብለህ ራስህን ትጠይቃለሀ? <በነብያቶች ማመን>...ለአላማ ፅናትን፡ተስፋ አለመቁረጥን፡ጥበብን፡ሰዎች መጥፎ ሲያስቡብህ አንተ ሁልጊዜ መልካም መሆንን፡ በመልካም ማዘዝን ከመጥፎ መከልከለን ትማራለህ። <በመለኮታዊ መፀሃፍቶቹ> ስናምን...ከሚከለክሉት እንታቀባለን የሚያዙትን ደግሞ ተግባራዊ እናደርጋለን። መለኮታዊ ናቸውና...የሚከለክሉን ለስው ልጅ ከማይጠቅሙና የሞራልም ይሆን የስነ ምግባር መላሸቅ ከሚያስከትሉ ነገሮች ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ እንድንተገብራቸው የሚያዙን የሞራል ምጥቀትን የሚያጎናፅፉ ነገሮችን ብቻ ነው። አያችሁ...ኢስላም...እንዴት ስነ...ምግባርን ከኢስልምና መሰረቶች ና ከኢማን አርካኖች ጋር እንዳቆራኘው? <በቀደር ማመንን> ብንወስድ...ጀግንነትን ያጎናፅፋል። በላይህ ላይ ለሚያንዣብቡ አደጋዎች በሞሉ በብራታት ትወጣቸዋለህ። አላህ ከወሰነው ነገር ውጭ ምንም ነገር እንደማይደርስብህ ስትረዳ...ፈሪ አትሆንም..ሰዎችን ታከብራቸዋለህ እንጂ በፍራቻ አትሰግድላቸውም። በአንተ ላይ እንዲከሰት የወሰነውን ነገር የሰው ዘር በሙሉ ቢሰበሰብ እንደማያሰወግድልህ ስተረዳ በተቃራኒውም አላህ ለአንተ የፃፈልህን ጉዳይ ማንም እንደማይነጥቅህ ስትረዳ ልብህ ይረጋጋል እምነትህም ይጨምራል።

አዎን! ቀደምት የኢስላም ትውልዶች ይህንን እስተምህሮ በቲወሪ ብቻ ሳይሆን በተግባር ኑረውት በተግባር ስለመሰከሩ ነው ዛሬ ላይ መልካም ስብዕናቻው ጉልቶ የሚወሳው። ለዛም ነው ዛሬ ላይ ሆነን ከ 1430 ዓመታት በሗላ የእነርሱን የስብዕና ምጥቀት ስንረዳ በእዝነ ህሊናቸን ያን መልካም ጊዜ እያስታወስን የምናነባው።

<የሐበሻው ንጉስ ና የጃዕፈር ንግግር>

ቁረይሾች በኢስላም የተሃድሶው መጀመሪያ ላይ ያለደረሱት ጥቃትና ሙከራ አልነበረም። በመልካም ስነ ምግባሩ አሸንፎ በአንድ ሰው ተሃድሶ የተጀመረው ኢስላም ዛሬ ለ1.7 ቢለዮን የአለም ሙስሊሞች ደርሷል። መልካም ስነ ምግባር የማያሸንፈው ጠላት የለምና! ኢስላም በእንጭጭነቱ አደጋ ሲበዛበት ነቢዮ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ሃበሻ ሂዱ ከዚያ ሰዎች የማይበደሉበት ንጉስ አለ ብለው ልከዋቸው ነበር።የመጀመሪያው ሂጅራ...የሉኡኩ መሪ ጃዕፈር... ለንጉስ አስሃማ (ነጃሽ) ያደረገው ንግግር...ምን ያክል ኢስልምና ለመልካም ስነ ምግባር ትልቅ ቦታ እንዳለው ስለሚያሳይ ...ይኼው..ጀባ ብያለሁ።
“ንጉስ ሆይ! እኛ በጃሂሊያና በዘቀጠ ስነ ምግባር ውስጥ ነበርን። ጣኦታትን የምናመልክና የሞቱ እንሰሳዎችን ስጋ የምንመገብ ህዝቦች ነበርን። አስቀያሚና አሳፋሪ የሚባሉ ወንጀሎችን ሁሉ የምንደፍር ህዝቦች ነበርን።ዝምድናን የምንቆርጥ፡እንግዳን የማናከብርና ከእኛው ውስጥ ጠንካሮቹ ደካሞቹን ይመዘብሩ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳለን ዘሩን ጠንቅቀን የምናውቀው፡ዕውነት ተናጋሪነቱን፡ታማኝነቱንና ማህበራዊ ውሎውን በድንብ የምናውቀውን ሰው አላህ መልዕክተኛ አድርጎ ላከልን።ከአላህ ውጭ ስንገዛቸው የነበሩ ድንጋዮችንም ሆነ ጣኦታትን እንድንርቅና አላህን በብቸኝነት እንደንገዛ ጠራን። እውነት እንድንናገር፡ቃል-ኪዳናችንን እንድናከብር፡ማህበራዊ ውሏችን ያማረ እንዲሆን፡ለጎረቤቶቻችንም ረዳቶች እንድንሆን፡የተከለከሉ ነገሮችን ሁሉ ከመፈፀም እንድንታቀብ፡ ደም ከመፋሰስ እንድንታቀብ፡በሃሰትም እንዳንመሰክር፡የየቲምን ገንዘብ እንዳንቀርብና የንፁሃን ሴቶችን ክብር እንዳናጎድፍ አዘዘን።”

ሰማችሁት አይደል...የጃዕፈርን የመጀመሪያ ዳዕዋ...በኢትዮጵያ። ይህ ነው ኢስላም...ሰዎችን ከነበሩበት ድርብርብና ውስብስብ ብዙ ጨለማዎች አውጥቶ ወደ አንድ ብርሃናዊ ጎዳና የሚጠራ ዲን ነው...ኢስላም።

“አሊፍ ላም ራ (ይህ ቁርአን) ሰዎችን በጌታቸው ፈቃድ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን አሸናፊ ምስጉን ወደ ኾነው ጌታ መንገድ ታወጣ ዘንድ ወዳንተ ያወረድነው መፅሃፍ ነው።” (14፡1)
ይህንን መፅሃፍ...ተጠቅሞ...በብራሃናዊ ጎዳና መኖር ወይም እርሱን ትቶ በድርብርብ ጨለማዎች ውስጥ መጓዝ? መርጫው ለእኛው የተተው...ጉዳይ ነው።

<እኛነታችን...በእኛው ሲዳሰስ>

ወንድሞች እህቶች፡ አሁን ያለነው የት ነን? ዱኒያ ላይ። ዱኒያ ዘላለማዊ ቤታችን እንዳልሆነች ማንም ያውቃል። ከሚገርመው ነገር መቼ እንኳን ትተናት እንደምንሄድ አናውቅም።ዘላለም ለማንኖርባት ዱኒያ የዘላለም ሃገራችንን..ጀነትን እንዳናጣ ስንቶቻችን እየተጨነቅን ነው? ዛሬ ላይ የእኛ ስብዕና ስንቶችን ይማርካል? የመልካም ስነ ምግባራችን ሞዴል ማን ነው? ዛሬ በዕኔ መልካም ስነ ምግባር ስንት ሰው ከጉኔ ከቦኛል? በእኔስ እኩይ ስራ ስንቶች ከኢስላም ራቁ? ውስጣችን ለስንቶች ግልፅ ነው? ለእኛ የምንወደውን ለወንደሞችም ሆነ ለእህቶች የምንመኝ ስንቶቻችን ነን? በመልካም የምናዝ ከመጥፎ የምንከለክል ስንቶቻችን እንሆን? የሙስሊሞች ጉዳይ የሚያሳስበን የሙስሊሞች ችግር ውስጣችንን ነክቶን ያነባን ስንቶች ነን? ጎረቤቶቻችንም ጋር ይሁን ቤተሰቦቻችን ጋር ያለን ግኙነት ምን ያክል ያማረ ነው? የውንደማችንን መሻሻል የምንመኛስ ስንት ነን? ያንን የነቢዩን ስብዕና ስንስማው የሚያስነባንን ማንነት ወደኛ ለማምጣት ምን ያክል ጥረናል? ለሙስሊም ወንድሞቻችን ምን ያክል እናዝናለን? ምን ያክልስ እንከባበራለን? አሊይ ኢብን አቢጧሊብ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “ስለ አላህ ባጣም ብዙ እውቀት አለው የሚባለው ሰው ‘የላኢላሃ ኢለላህን’ ህዝቦች የሚያከብረው ነው።” ሙስሊም ላልሆኑ ወገኖችስ የምናሳያቸው የትኛውን የኢስላም ባህሪይ ይሆን? ቤታችን ውስጥ ያለው የስነ ምግባር ድባብስ ምን ይመስላል? በመካከላችን ምን ያክል መተዛዘን አለ? ጓደኝነታችን እንደ ሽቶ ነጋዴ ወይንስ እንደ ብረት ቀጥቃጭ? የሙስሊም ወንድማችን ችግር የሚያሳስበን ስንቶቻችን ነን? አዎን!...የሙስሊሞች አንድነት መሰረቱ መልካም ስነ ምግባር ነው። ለሙስሊሞች ወንድማማችነት ማገሩማ ሚስማሩም መልካም ስነ መግባር ነው።

<14 ክ/ዘመናትን...ወደሗላ በእዝነ ህሊናችን>

እስኪ 14ክ/ዘመናትን ወደሗላ መለስ በሉና የአንሶሮችን ሆደ ሰፊነት አስተውሉ...ሙሐጂሮችን እንዴት እንደተንከባከቧቸው? ለወንድሞቻቸው ሲሉ...የሚወዷቸውን ሚስቶቻቸውን ሳይቀር አሳልፈው ለመስጠት ሲዘጋጁ? እኛስ...ይህ ቢቀር ለሙስሊም ወንድሚ ከውስጤ የሆነን ፈገግታ አሳይቸው ይሆን? እነዚያን በጂሃድ ላይ በውሃ ጥም የሞቱ ሶስት የኢስላም ወንድማማቾች እስኪ በእዝነ ህሊናችሁ አስተውሉ? ሶስቱም ወደቀው...በውሃ ጥም ምላሳቸው ተሳስራ...የሚጠጣ ነገር ሲያገኙ..አንድኛው ሲቀበል..ወንድሜ ይብሳል ? ሁለተኛውም ለሶስተኛው አንተ ትብሳለህ ጠጣ ሶስተኛውም ለአንደኛው ሲመልስ ሁሉም ሳይጠጡት ሲተዛዘኑ ህይወታቸው ያለፈውን ድንቅ የሶሃባዎች ታሪክ ረስተነው ይሆን ወይንስ እውነት አልመሰለንም? እኛ ዛሬ እንኳን ችግር ውስጥ ሆነን ይቅርና በምቾት እንኳ ውስጥ እያለን ለውንድምና ለእህቶቻችን ችግር ምን ያክል ደራሾች ነን? ከራስ በላይ ለራስ አጥጋቢ መልስ የሚሰጠን የለምና ሁላችንም እስኪ ራሳችንን ለእነዚህና መሰል ጥያቄዎች መልስ ሰጥተን ስብዕናችንን ለማስተካከል እንሞከር።
ዛሬ...የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከመቼውም ጊዜ በላይ ስነ ምግባራችንን ፈትሸንና አስተካክለን የራቁን ወንድምና እህቶችን ማቅርብ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ከጎናችን ያሉትን ሙስሊሞች በሻከረ ስብዕናችን እንዳናርቃቸው ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን። አዎን! የሙስሊሞች መርህ መሆን ያለበት በመካከላችን መተዛዘን።መተዛዘን መልካምን እንጂ አይጨምርም።መተዛዘን...ጥላት ያኮስሳል።አንተ ትብስ አንተ ትብስ መባባል...አንድነትን ያጠነክራል። አንድነቱን የጠበቀ ኡማ ደግሞ ተሸናፊ አይሁንም!
አላህ በመልካም ስብዕናቸው ሰበብ ድል ከሚጎናፀፉት ያድርገን። በፅሁፊ ውስጥ ግድፈት ካለ ከእኔው ስህተት ሲሆን መልካሙ ነገር ሁሉ ደግሞ በአላህ እገዛ ነው። ለጊዜው...በዚሁ ይብቃኝ!


የሰላማዊ ትግላችን...ሰለማዊ ቦምቦች (ቁጥር 3)


“...አላህ በህዝቦች ዘንድ ያለውን ፀጋ በነፍሶቻቸው ያለውን (ኹኔታ) እስከሚለውጡ ድረስ አይለውጥም።...”(አረዕድ(13)፡11)
“እኔ እያለሁ በኢስላም ላይ አንዲትም ጠባሳ አያርፍም” አቡበከር ሲዲቅ (ረ.ዐ)
“ኢስላም ሃያል ሆኖ መሞት እፈልጋለሁ” በራዕ ቢን ማሊክ (ረ.ዐ)
“ኢስላም ሃያል ሆኖ እንጂ አልሞትም።ለዚህ አላማም የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ።” (ዑቅበት ቢን ናፊዕ)
“ከቻልክ ሺ ሰዎችን የመትመጥን ሁን። ካልቻልክ አንድ ሰው የምትመጥን ሁን ግማሽ ሰው አትሁን” አንድ ታቢእይ

የዛሬው የሰላማዊ ቦምባችን ይዘት በእነዚህ ድንቅ ስብእናዎች አባባል ውስጥ በቀጥታም ይሁን
በተዘዋዋሪ ተንፀባርቋል። ከሁሉም ነገር በላይ ደግም...የስብዕናዎቹ አባባል ከላይ የቀረበውን የቁርአን አንቀፅ በትክክል ከመረዳትና ከመተግበር የመነጨ መሆኑ የአንቀፁን ሃሳብ ከዛሬው ፅሁፋችን ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያሳያል። መልካም ንባብ፦

*ሰላማዊ ቦምብ ቁጥር 3፡ የግለሰባዊ ሃላፊነትና ተጠያቂነት...እኔ ለኢስላም...!*

ማህበረሰብ የግለሰቦች ድምር ውጤት ነው። ማህበረሰብ ራሳቸውንና በዚህ ምድር ላይ የሚኖሩበትን ግብና አላማ ጠንቅቀው በሚረዱ ግለሶች ሲመሰረት ያ...ማህበረሰብ ታሪክ የማይረሳውና ዘመን ያማያደበዝዘው ተምሳሌታዊ ስራን ሰርቶ ያልፋል። የሶሃባዎችን ታረክ አውሳ።የታቢኢዮችንም ተመልከት።ከዚያም በዃላ ለአለም የበረከቱ ኢስላማዊ ስልጣኔዎችን ፈትሽ። ማን እንደስራቸውና እንዴት እንደተሰሩም ገምግም። የምታገኘው መልስ አንድ ነው። የሚኖሩበትን አላማ ጠንቅቀው የሚያውቁ ግለስቦች ግላዊ ሃላፊነታቸውንና ተጠያቂነታቸውን ተገንዘበው የሰሩት የስራ ውጤት መሆኑን ትረዳለህ።

አዎን...ፍጥረት የጀመረው ከግለሰብ ነው። ከሰው ልጆች አባት አደም (ዐ.ሰ)። ከዚያም እናታችን ሐዋ...ሲወረድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ ወደ 7 ቢሊዮን ህዝብ ምደራችንን ምልቷታል። እንደ ኢስላም እይታ ግለሰቦች የራሳቸው የሆነ ሃላፊነትና ተጠያቂነት አለባቸው።ይህንን ሃላፊነትና ተጠያቂነት በውል ተረድተው ለራሳቸው ሆነው ለማህበረሰብ እንዲያገለግሉ አጥብቆ ይሻል። አላህ (ሱ.ወ) ከሞት በሗላ መቀስቀስና በሚቀጥለው አለም በአለህ ፊት ለፍርድ እንድንቆም ማደረጉ ግለሰባዊ ሃላፊነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ለማሳየት ነው።

ዛሬ ላይ በሃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት ያልተኖረ ህይወት ያን ቀን...ፀፀት ነው። በሁለቱም አለም ኪሳራ ነው። ያለ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ስሜት የሚኖር ህይወት በዚህች ምድርም ‘ለዛ’ የለውም በአኼራም ኪሳራን ያስከትላል። የሰው ልጅ በዚያች ቀን የለማንም ረዳትነት ብቻውን አላህ ፊት ይቆማል። ያን ቀን...እናትም...አባትም...ውንድም...እህት...ጓደኛ...ብሎ ነገር የለም። ሁሉም የራሱ ጉዳይ ያሳስበዋል። ከእናት በላይ...ለልጁ የሚጨነቅ ማን አለ በምድር ህይወት? ማንም! ያን...ቀን ግን እናትም የሚያሳስባት የእራሷ እጣ ፈንታ ብቻ ነው።ልጇን ትርቃለች።ልጅም ከእናቱ ይርቃል። እስኪ...የአላህን ህያው ቃል...ከቁርአን እንስማው፦

“ሰው ከወንድሙ በሚሸሽበት ቀን፡ከእናቱም ከአባቱም፡ከሚስቱም ከልጁም ከእነርሱ ለየሰው ሁሉ በዚያን ቀን (ከሌላው) የሚያብቃቃው ኹነታ አለው።” (አበሰ(80)፡34-37)

ዛሬ ኢስላም አደጋ ላይ ሲወድቅ ሃላፊነቱን ዘንግቶ ለኢስላም ሌሎች አሉት በሚል ስሜት ዳር ላይ ቆሞ የሚይመለከት ወገን...ያን ቀን ይከፋዋል።ያን ቀን ይለደማል። በእርግጥ ልክ ነው ለኢስላም በየዘመኑ የሚነሱ ብዙ ጅግኖች አሉት። እነዚህ ጀግኖች ግን ...ኢስላምን ከመጥቅም በላይ የሰሩት ነገር ቢኖር የራሳቸውን መልካም ስራ ማካበት ነው። “መልካም ብትሰሩ ለነፍሶቻችሁ መልካምን ሰራችሁ። መጥፎም ብትሰሩ (በነርሱ( በነፍሶቻችሁ ላይ ነው፡(አልን)።...” (አል ኢስራዕ (17)፡7) ይህ ነው የቁርአን አስተምህሮ። ግለሳባዊ ህላፊነታቸውንና ተጠያቂነታቸውን እየተወጡ...ለመጭው አለም ደጎስ ያለ የመልካም ስራ ስንቅ እያዘጋጁ ነው። አዎን! ለኢስላም ዘበኛ መሆን ማለት ለእራስ ማሰብ ነው።አላህ ፊት ስንቆም የሚጠቅመንን ስንቅ መሰነቅ ማለት ነው። ለኢስላም ሁሉም ሰው ዘበኛ ቢሆን ተጠቃሚው ራሱ ነው። በእርግጥ ኢስላምን የጠላቶች ተንኮልና ሴራ አይደለም የሚያሸንፈው...ለዚህ ብዙ የታሪክ ማሰረጃዎች አሉት። ኢስላም አደጋ ላይ የሚወድቀው ግለሰባዊ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሌላቸው ብዙ ተከታዮች በሚኖሩት ሰዓት ብቻ ነው።

ኢስላም ለኡለማዎች፡ ለዳኢዎች፡ ለኢስላማዊ አሳቢዎች፡ ለኢስለማዊ አማካሪዎች፡ ለአርቲስቶች፡ለጋዜጠኞች፡ ለባላሃብቶች...ብቻ የሚተው ዲን አይደለም። ምንም እንኳን ግለሰቦቻ በማህበረሰባቸው ውስጥ ባላቸው ቦታ ለኢስላም የሚጨዋቱት አስተዋፅኦ እንደዚያው ክፍ ቢልም...ለኢስላም የራሱን አሻራ ግን ትንሽም ቢሆን የማያስቀምጥ ግለሰብ በኢስላማዊ ማህበረሰብ ውስጥ አይገኝም። ምንም ትንሽ ነገር ብትሆን እያንዳንዱ ግለሰብ የሚጫወተው አስተዋፅኦ አለው። በኢስላም የስራ ትልቅነት የሚታየው በግዝፈቱና በስፋቱ አይደለም...በኢህላሱና በትክክላኛው የዲን ግንዛቤ መሰራቱ ላይ እንጂ። ምናልባት ዛሬ ላይ ግለሰቦች የአለምን ማህበረሰብ ያስጨበጨበ ስራ ሊስሩ ይችላሉ...በአለህ ዘንድ ግን ምንም ቦታ የሌለው በኢህላስ ያልተሰራ ስራ ሊሆን ይችላል። ከአላህ ውጭ የማያውቃቸው ግልሰቦች ደግሞ...ከቤታቸው ውስጥ ቁጭ ብለው ለኢስላም በሚያደሩጉት ዱዓ...እንደ ተራራ የገዘፈ አጅር ሊፃፍላቸው ይችላል በአላህ ዘንድ። ለዚህም ይመስላል...ድንቅ ና ብርቅየ ቀደምት የኢስላም ልጆች...ተራራ የሚያክል ወርቅን ሶደቃ ከመስጠት...ከአላህ ፍራቻ የተነሳ የምናነባት አንድት ጠብታ እንባ...ለውስጣችን ደስታን ትሰጠናለች ሲሉ የተደመጡት።

ሁሉም ሙስሊም ለኢስላም አስተዋፅኦ ሊያበረክትበት የሚችለው የስራ መስክና ችሎታ አለው። ዋናው ነገር ውስጥን በስርዓት አናግሮ ማድረግ የሚችለውን ነገር መገንዘቡ ላይ ነው። እኛም ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ለሰላማዊ የትግል ጉዟችን አስተዋፅኦ ማበርከት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አንዱ የመፃፍ ችሎታ ሊኖረው ይችላል። ሌላኛው የተፃፉትን ፁሁፎች ላልድረሳቸው ማዳረስ...ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ተርጎሞ ማሰራጨት። ሃሳብ ማፍለቅ ና ምክር መስጠት። ስለ ትግሉ አሳስቦት መወያየት። የሙስሊሞችን አንድነት መጠበቅ። ቤተሰብ ውስጥ ጥሩ የዲን ግንዛቤን መፍጠር። ለሌሎች የእምነት ተከታዮች በግልፅ ስለ ጥያቄችን ስለማዊና ግልፅነት ማስረዳት። በትግሉ ሂደት ውስጥ ችግር ለሚደርስባቸው ወገኖች በገንዘብም በሞራልም ማገዝ። ሙስሊሞችን አደጋ ላይ የሚጥሉ ክስተቶችን በንቃት መከታተል። የሙስሊሞችን አንድነት ሊበታትን የሚችል ነገርን ከመናገርም ሆነ ከመፃፍ መቆጠብ። ስሜትን ተቆጣጥሮና ገርቶ በሙስሊሙ መካከል የሚነሱ ተራ የሃሳብ ልዮነቶችን እንደ ፀጋ ተቀብሎ መኖር...ምናልባት ይህ ነገር ለኢስላም ትልቁ አስተዋፅኦ ሊሆንም ይችላል። የሃሳብ ልዮነት እያለን...የሙስሊሙን አንድነት ለመጠበቅ ብለህ የምታሳየው ስሜትን መግራትና ዝምታ...ከአላህ ዘንድ ትልቅ ምንዳ እንደምናገኝበት ጥርጥር የለውም። በእንቅስቃሴያችን ውስጥ ትልቅ ስራ የሚሰሩ ወንድሞችንም ሆነ እህቶችን ከሃሜት ከስድብና ከአላስፈላጊ አጉል ጥርጣሬዎች ርቆ ማበረታታት ትልቅ ስራ ነው። መልካም ጎናቸውን አጎልቶ ማሳየት ለሙስሊሞ ብረታት ነው። ይህ ማለት ግን ጥፋታቸው አይነገራቸው ማለት አይደለም። ቀስ ብለን በጥበብና በተረጋጋ መንፈስ በግለሰብ ደረጃ ውይይት ማድረግን እንድንመርጥ ለማለት ነው።

ስለዚህ በየትኛውም የኢስላም ታሪክ ውስጥ ሙስሊሞች አሸናፊ የነበሩበትን ሁኔታ ስንገመግመው የምንረዳው አንድ እውነታ አለ። ይኼውም...ሁሉም ግለሰቦች የሚሰሩትን ነገር ጠንቅቀው የሚውቁ መሆናቸው ነበር። ዛሬ ላይ ሆነን ታሪክ የሚያስነብበንን የኸሊፋዎች ታሪክ፡ የታቢኢዮች ታሪክ፡ ብርቅየ የሚባሉ ኢስላማዊ ስልጣኔዎችን ታሪክ ስንዳስስ የተወስኑ ግለሰቦች የመሪነቱን ቦታ ይዘውት እናገኛለን። ይህ ማላት ግን የታረኩ ባለቤቶች እነዚህ ግለሰቦች ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። አዎን! በአቡበከር ሲዲቅ (ረ.ዐ) አሰተዳድረ ዘመን...እነ ኡመር አል ፋሩቅን የመሰሉ ጀግኖች፡ ኡስማን ኢብኑ አፋንን የመሰሉ አላህን ፊሪዎች፡ አሊይ ቢን አቢጧሊብን የመሰሎ ጥበበኞችና ለመጥቀስ የሚያዳግቱ ሰብዕናዎችን ያቀፈ አስተዳደርን እናያለን። የዚህ ታሪካዊ ድርሻ ባለቤቶች በጊዜው የነበሩ ግለሰቦች ግለሰባዊ ድርሻቸውን ተረድተው ያበረከቱት አስተዋፅኦ ድምር ውጤት መሆኑን እንረዳለን።

ሁላችንም...”አል-ቁድስን” የከፈታትን ጀግናውን ሰለሃዲን አል አዩቢን እናውቃለን። ታሪክ ይህን አስነብቦናል። ይህ ማለት ግን ወታደሩ ሰለሃዲን ብቻ፡ በለሃብቱም እሱ ብቻ፡ የትግሉ እቅድ አውጭና አስፈፃሚ እሱ ብቻ ነው ማለት ግን አይደለም። ብዙ ወታደሮች፡ ብዙ ባለሃብቶች፡ ብዙ የሰነ -ፅሁፍ ሰዎች፡ ብዙ ሴቶች፡ ብዙ አሳቢዎችና እቅድ አውጭዎች፡ ብዙ አማካሪዎችንና...የብዙ ተራ ግለሰቦችን አስተዋፅኦ የጠየቀ የትግል ውጤት እንጂ። አዎን! በሁሉም የታሪክ ክስተቶች ውስጥ በአላህ ዘንድ ትልቅ ቦታ ያላቸው በሰዎች ዘንድ ግን የማይታወቁ ታሪክ በስም ያላደረስን ብዙ ግለሰቦች እንደሚኖሩ ግን ጥርጥር የለውም።

ዛሬ ላይ በሰላማዊ ትግላችን ውስጥ ለምናበረክተው እያንዳንዱ አስተዋፅኦ...በአላህ ዘንድ ምንዳ ይኖረናል ኢንሻአላህ።
ለምናስመዘግበውም ድል...ታሪክ እንደ ትውልድ ክሽን አድርጎ መዝግቦ ያስቀምጠናል። አዎን! ምናልባት በታሪካዊ ድርሳኑ ውስጥ ፋጡማ...አሊ...ሙሐመድ ተብለን ላንመዘገብ እንችላለን። ነገር ግን የ21ኛው ክ/ዘመን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያደረጉት የሰላማዊ ትግል ተብሎ በማይደርቁና በማይፋቁ የታሪክ ቀለሞች ይፃፋል።

አዎን! እራሳቸው ተሸብረው አሸባሪ እየተባሉም እንኳን ሰላማዊ ትግልን የመረጡ ምርጥ ትውልዶች፡ እየተገረፉና እየተገደሉ እንኳን ሰላምን ያበሱረ ብልህ ትውልዶች፡ መንግስት አርቅቆ ያፀደቀወን የሃገሪቱን የህጎች ሁሉ የበላይ ተብሎ የሚወሰደውን “ህገ-መንግስት” በተግባር አፈፃፀሙን ያሳዩ ብርቅየ ትውልዶች፡ ጭቆናንና በደልን ለመቃወም ከአምባገነኖች ፊት ለፊት የቆሙ እውነተኞች ና የሰላም አምባሳደሮች ተብለን ግን በታሪክ መወሳታችንን እርግጠኛ ሁኑ!

በመጨረሻም ይህን የቁርአን አንቀፅ እናንብበው፦
“የምንገስፃችሁ በአንድት ነገር ብቻ ነው። (እርሷም) ሁለት ሁለት አንድ አንድም ኾናችሁ ለአላህ እንድትነሱ...” (ሰብዕ(34)፡46)

አዎን!...ጥሪው ይኼው ነው። የአላህን ዲን ለመጠበቅ በግለስበም ይሁን በጀማዓ ውስጥ ተሳታፊ መሆን! ኢስላም ለተውሰኑ የማህበረሰባችን ከፍሎች የተተው ዲን ሳይሆን የሁሉም ሙስሊሞችን የጋራ ስራ የሚፈልግ ዲን መሆኑን መገንዘብ። ይህ ሲሆን አሸናፊዎቹ እኛው ነን-ኢንሻአላህ።

አላህ ሆይ! በዚህች ምድር ላይ ሲኖሩ የሚኖሩበትን ግብና አላማ በውል ተረድተው ከራሳቸው አልፋው ለማህበረሰባችው መልካም የሚሰሩ ብርቅየ ትውልዶች አድርገን። በመካከላችንም መግባባትን እንጂ መለያያትን አንተው አርቅልን። አንተ ሰሚም ዐዋቂም ቻይም አምላክ ነህና! አሜን።

የሰላማዊ ትግላችን...ሰለማዊ ቦምቦች (ቁጥር 4)
ባለፉት 3 ክፍሎች ስለ ዱዓ፡ መልካም ስነ ምግባርና የግለሰባዊ ሃላፊነትና ተጠያቂነት መንፈስ ማዳበር አይነተኛ የሰላማዊ ትግላችን መሳሪያዎች እንደሆኑ ለማየት ሞከረናል። ዛሬ በአላህ ፈቃድ ስለ “ፅናት” በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን።

ቁጥር 4፡ *ፅናት*

ከሳምንት በፈት “ያን ቀን...የበረዶ ክፍሎቹ ይመሰክራሉ” የሚል አጥር ያለ ፅሁፍ አስነብቤ ነበር። በዚሁ ፅሁፍ ውስጥ ሙእሚኖች በዱኒያ ላይ ሲኖሩ በጣም ብዙ ፈተናዎች በሁሉም አቅጣጫዎች እንደሚደቀኑባቸው ለመጥቀስ ሞክሪያለሁ። ሙእሚኖቸ እነዚያንና ተመሰሳይ ፈተናዎቸን ለማለፍ ከሚያሰፍልጓቸው መሳሪያዎች አንዱ “ፅናት” ነው። ፅናት በአጭሩ ሲገለፅ ሰዎቸ የሆነን አላማ አስቀምጠው እርሱን እውን ለማድረግ በሚንቀሳቀሱበት ሰዓት ለሚያጋጥሟቸው እያንዳንዱ ፈተናዎች ያለምንም ወደሗላ መመለስ ፈተናዎቹን በጥበብና በትዕግስት አያለፉ አላማን ከግብ ማድረስ ወይም የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት ማለት ነው። ሙስሊሞች ለአመኑበት ዲን ኢስላም መክፍል የሚገባቸወን መስዋፅትነት በፅናት ሲከፍሉ የተነሱለት አላማ እውን ይሆናል። የእኛ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችም የአጭር ጊዜ ግባችን አሁን ከሚደርሱብን ዘርፈ ብዙ የመብት ረገጣዎቸና ሰብአዊ እንግልቶች ራሳችንን አላቀን በሀገራችን ላይ ሙሉ መብታችን ሳይሸራረፍ ተክበሮ በክብር መኖር ሲሆን ይህም መንገድ መክፍል የሚያሰፈልገውን መስዋዕት እየከፈሉ በፅናት እሰከመጨረሻው መቀጠልን ይጠይቃል። ሌላው የእኛ የሙስሊምች ትልቁና የረዥም ጊዜ ግባችን በሙስሊምነታችን (በእምነታችን) በምድር ላይ ቆይታችን የሚጋረጡብንን ብዙ ፈተናዎች ጠንቅቀን ተረድተን ፈተናዎቻችንን በፅናት መወጣት ነው። እርግጥ ነው! ምንም ሌሊቱ ቢረዝም መንጋቱ አይቀርም። በኢስልምናችን ላይ የሚመጣ አደጋ ምንም ያክል ዋጋ ቢያስከፍለንም ውድን ነገር.. “ጀነትን”... ለማገኘት እንጂ ለተራ ነገር ስላልሆነ ብዙም አይከብደንም...ኢንሻአላህ።

በጥቅሉ ፅናት ሁልጊዜ በህይወት ዑደታችን ውስጥ ከፊትለፊታችን የሚያጋጥሙንን አያሌ “መሰናክሎችን” ወደ ሰኬት ጓዳና “መረማመጃ ደረጃነት” ለመቀየር ፅናትን ይጠይቃል። ፅናት ለማንኛውም የህይወት እንቅስቃሴያችን ከግብ መድረስ ወሳኝ መሳሪያ ነው። ትንሽም ይሁን ትልቅ ስራ ተጀምሮ ለመጨረስ ፅናትን ይጠይቃል። መልካም ስነ ምግባራችንን ለመገንባት የዘወትር ፅናት ይጠይቃል። እውቀትን ለማካበት ፅናት ያስፈልጋል። እምነትም በምላስ ተለፍፎ ብቻ ጣዕም እንደሌለው የኢስላም ታላላቅ ስብዕናዎች አስመስከረዋል። ብዙ ሶሃባዎች ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ ተደብድበው ተሰቃይተው ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ሁሉም የሚስማሙት ነገር ድብደባው ኢማናቸውን ጨመረላቸው እንጂ ወደ ሗላ አልመለሳቸውም። ፈተናው ቀላል ሆኖ ሳይሆን ጀነትን ለማግኝት መከፈል ያለበትም መስዋፅትነት ከባድ እንደሆነ ስለተረዱ እንጂ። ፈተና የሙዕሚኖችን ልብ ያረጋጋል እንጂ አይረብሽም። በኢማን ብርሃንም ይሞላል። የሙዕሚን ዱዓ ከኢማኔ በላይ አትፈትነኝ ነው እንጂ መቼም ቢሆን ፈተናን አርቅልኝ አይደለም። ያለ ፈተና እንዴት ጀነት ይገኛል? ይህ ሁሉ...ፅናትን...ይጠይቃል።

አላህ (ሱ.ወ) በቁርአን ውስጥ ስለ ፅናት በብዙ ቦታዎቸ ከትዕግስት ጋር እያቆራኘ ይገልፃል። እስኪ የተውስኑትን አንቀፆች እንመልከት፦

“ እነዚያ “ጌታችን አላህ ነው” ያሉ ከዚያም ቀጥ ያሉ “አትፍሩ፡አትዘኑም በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ” በማለት በነሱ ላይ መላዕክት ይወርዳሉ።” (41፡30)

“አላህ እነዚያን ያመኑትን በቅርቢቱም ህይወት፡በመጨረሻይቱም በተረጋገጠው ቃል ላይ ያረጋቸዋል።...”(14፡270)

“ለጌታህም (ትዕዛዝ) ታገስ።” (74፡7)

“ከችግርም ጋር ምቾት አለ። ከችግር ጋር በእርግጥ ምቾት አለ።” (94፡5-6)

ዛሬ የኢትዩጵያ ሙስሊሞች ላይ በጣም ካባድ ፈተና ተደቅኗል። ወጣቶች ከመኖሪያ ቤታቸው እየተፈናቀሉ በየጫካው እየተሰደዱ ነው። ሰዎች እየተገረፉ እየተደበደቡ ነው።ግለሰባዊ ህይዎታቸው እንኳን በቤታቸው ውስጥ ሳይቀር ሰላም ተነፍጎታል። ንብረታቸውም እየተዘረፈ ነው። ሙስሊሞች በቀንም በሌሊትም እየተሸበሩ ነው “ለሰላም ቀናኢ” በሆነው መንግስታችን! ብዙ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳትም እየደረሰባቸው ነው።... ሁልጊዜም የማይቀየረ አንድ እውነታ ግን አለ። ይኸውም መጨረሻው...ለእውነተኞችና አላህን ፈሪዎች መሆኑ። ይህ ጉዳይ ዘመን የማይሸረው እውነት ነው። እመኑ እውነትነ የያዙ ህዝቦች አሸናፊዎች ናቸው። ከአላህ በላይ ንግግሩ ታማኝ ማነው? ወላሂ! ማንም። አላህ በቁርአኑ...በማይነጥፈውና በህያው ቃሉ እንዲህ ብሎናል፦

“ ሙሳ ለሰዎቹ፦ “ለአላህ ተገዙ ታገሱም። ምድር ለአላህ ናትና። ከባሮቹ ለሚሻው ያወርሳታል። ምስጉንዋም ፍፃሜ ለጥንቁቆች (አላህን ፈሪዎች) ናት” አላቸው።” (7፡128)

“ቤተሰብህንም በስግደት እዘዝ። በእርሷም ላይ ዘወትር (ፅና)። ሲሳይን አንጠይቅህም።እኛ እንሰጥሃለን። መልካሚቱም መጨረሻም ለጥንቁቆቹ (አላህን ፈሪዎቹ) ናት።” (20፡132)

“...በችግር በበሸታና በጦር ጊዜም ታጋሾችን (እናወድሳለን)። እነዚህ እነዚያ እውነትን የያዙ ናቸው። እነዚያም ተጠንቃቂዎቹ (አላህን ፈሪዎቹ) እነርሱ ናቸው።”(2፡177)

ሰለማዊ ትግላችን የብዙ ህይወቶችን ዋጋ እያስከፈለን ቢሆንም መጨረሻ ግን አሸናፊዎቹ እኛው ነን። እውነት ከእኛ ጋ ስለሆነች...ኢንሻአላህ፡፤

ፅናትን ለማዳበር የሚረዱን ነገሮች፦
1) ቁርአንን ማንበብ ማሰተንተን
2) መልካም መስራት ከመጥፎ መከልከል
3) ሱና ነገሮችን ማዘውተር
4) የነቢያቶችንና የሶሃባዎችን ታሪክ ማንበብና መከተል
5) ዱዓ
6) ዚክር (አላህነ አብዝቶ ማውሳት)
7) ስልጠናዎችን በመውሰድም ሆነ ኢስላማዊ እውቀትን በመማር ፅናትን ማዳበር
8) ኢስልምና የክብራችንና የማነነታችን መሰረት መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ
9) ከጠንካራ ሙእሚኖች ጋር ጓደኝነት መፍጠር
10) የአላሀ እርዳት ሁለጊዜም እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን
11) የውሸተን ምንነት ጠንቅቆ መረዳትና የእውነትን ዋጋ መገንዘብ
12) የትልልቅ ኡለማዎቻችንን ምክር መቀበል
13) አሚሮቻችንን መታዘዝ
14) ፅናትን የሚያላብሱ ባህሪያቶችን ማወቅና መተግበር
15) ስለ ጀነት ድሎት ማሰብ፡ስለ ጀሃነም ቅጣት መፍራትና ሞትን አብዝቶ ማስታወስ
16) ...
አላህ...የተጋረጠብንን ፈተና በድል የምንወጣው ያድርገን! አሜን።

የሰላማዊ ትግላችን...ሰላማዊ ቦምቦች (ቁጥር 5)

ወሳኝና መሰረታዊ የትግላቸን መሳሪያ የሆነውን “ኢስላማዊ ወንድማማችነት” በዚህ ክፍል እንመለከታለን። ወንድማማችነት ምን ያክል በኢስላም ትልቅ ቦታ እንዳለው ሁላችንም ጠንቅቀን እናውቃለን። ምንም እንኳን እንደ ኢስላም እይታ ወንድማማችነት በሶስት ትልልቅ ክፍሎች ቢከፈልም (የስጋ/የደም ወንድማማችነት፡ የአጠቃላይ ሰው ልጆች ወንድማማችነትና ኢስላማዊ ወንድማማችነት)። ይህ ክፍል የሚያተኩረው በኢስላማዊ ወንድማማችነት ላይ ብቻ ይሆናል። ወንድማማችነት በሚለው ቃል ወስጥ ሁሉ እህትማማችነትም እንደለ በቅድሜ ተገንዘቡልኝ! መልካም ንባብ፦

ቁጥር 5፡ *ኢስላማዊ ወንድማማችነትን ማጠንከር”

< ፅንሰ ሃሳብ>

በአጭሩ ሰዎች ኢስላማዊ ወንድማማቾች ናቸው ስንል አንድ አይነት እምነትን (ኢስላም) የሚጋሩ፡ ለአንድ ግብ የሚሰሩ (ጀነት) ና አንድ አይነት የስነ ምግባር (አኽላቅ) መርህን የሚጋሩ መሆናቸውን ለመግለፅ እንደሆነ ብዙ ኢስላማዊ መፅሃፍቶች ያስነብባሉ።

<ታሪካዊ ዳሰሳ>

ኢስላም ሙስሊሞች እምነታቸው የተሟላና ኢባዳቸውም ፍሬ ያፈራ ዘንድ በሙስሊሞች መካከልም ጠንከር ያለ ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባ ያስገነዝበናል። ይህንን ግንኙነትም የምናጠናክርባቸውን የተለያዩ መንገዶችን አስቀምጧል። ለምሳሌ፦ በቀን አምስት ወቅት ሶላት በጀመአ መስገድን፡ የጁማአን ሶላት....እስከ ሐጂ ድረስ ያሉ ኢባዳዎችን ብንመለከት የሙስሊሞችን ግንኙነት ማጠናከሪያ ተደርገው ይወሰዳሉ።

በዚሀ መንገድ በቀደምት የኢስላም ትውልዶች በውል ተተግብሮ ጠንካራ የኢስላማዊ ወንድማማችነትን ትስስር ተጎናፅፈውበት አልፈዋል። በወንድማማችነት መንፈስ የሚሰራ ስራ ደግሞ የማህበረሰብን ህይወት ይለውጣል። መስርተዋቸው የነበሩት ኢስላማዊ ኢምፓየሮች ለዚህ አይነተኛ ማሳያዎች ነበሩ። ለአለም ማህብረሰብ ያበረከቷቸው ስልጣኔዎችና የመቻቻል ባህሎችም እንዲሁ። በየጊዜው ይነሱ የነበሩ የኢሰላም ጠላቶች በሙስሊሞች በጠንከረ ኢስላማዊ ወንድማማችነት ክንድ ተመክቷል። አያሌ የማህበረሰባቸው ችግሮች ተፈተዋል። ሰላምና ፍትህ እዲሰፍን አስችሏል። የሰውን ልጆች ሰብዓዊ ክብር አክብረው አስከበረዋል። አዎን! ሰፔንን ወደ 800 ዓመታት ሙስሊሞቸ ሲያሰተዳድሯት ከእስልምና ወጭ ያሉ ማህበረሰቦችን በዋነኛነት አይሁዶችና ክርሲቲያኖች ፍትህን ተጎናፅፈው ነበር። በሙስሊሞች መካካል የነበረው ኢስላማዊ ወንድማማችነት ሌላውን ማህበረሰብ እንዲረሱትና እንዲንቁት ሳይሆን እንዲንከባከቡት ነበር ያደረጋቸው ምክናያቱም ኢስላም ተማግሮ የተለሰነው በእዝነትና በፍትህ ስለሆነ።ለዚህ ደግሞ ‘ኦሬንታሊስቶች’ ራሳቸው የምስክርነት ቃላቸውን በፃፏቸው መፅሃፍት ሰጥተዋል።

ነቢዮ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሶሃባዎች መሃል ሲኖሩ አንዱ ቤት ተበልቶ ሌላው ቤት ፆም አይታደረም ነበር። አንዱ ሰው ተጨንቆ ሌላው ሲደሰት ውሎ አያድረም ነበር። አንዱ ታርዞ ሌላው ልብስ አያማርጥም ነበር። ሲበዛ መተዛዘን የነበረበት ወቅት ነበር። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከሁሉ ነገር በፊት መካ ውስጥ በነበሩበት ወቀት ኢስላም ገና ተሃድሶውን ሲጀምር በሙስሊሞቹ ላይ ሲጋረጥ የነበረው ችግርና ድብድባ በጣም የጠነከረ ነበር። ይህ ጉዳይ ደግሞ የስጋ ዝምድና እንኳን አልገደበውም ነበር። አባት ልጁን ያሰቃይ ነበር ኢስልምናን በመከተሉ ብቻ። ይህንን ጉዳይ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የፈቱት በሙስሊሞቹ መካክል በኢስላማዊ ወንድማማችነት በማስተሳሰር ነበር። ከዚያም ወደ መዲና ሲሰደዱ ሙሃጂሮቹን ከአንሷሮች ጋር እንዴት በኢስላማዊ ወንድማማችነት እንዳስተሳሰሯቸው በኢስላማዊ ታሪካችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ተስጥቶት እናገኛለን። ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ከሞቱ በሗላ እንኳን ሳይቀር በኸሊፋዎቹም ከዚያ በሗል በመጡ ኢስላማዊ ትውልዶች ላይ ኢስላማዊ ወንድማማችነት መንፈስ በጉል ተስተውሎ አልፏል። በነ ኡመር የአስተዳደር ጊዜ አይደለም ለሰው ልጆች በእንሰሳዎች ሳይቀር በአላህ ፊት እጠየቃለሁ ብለው ሲጨነቁ እንደነበር ታሪክ አስተምሮናል። ለሳይንስና ለስነጥበብ እድገት ሳይቀር ጥለውት ያለፉት አሻራ ቀደምት የኢስላም ትውልዶች በታሪክ እንዲታውሱ ከማድረጉም በላይ ለ21ኛው ክ/ሙሰሊሞችም ኩራታችንና የጥንካሬያችንም መሰረት ነው። ስለዚህ ኢስላማዊ ወንድማማችነት ከሃይማኖታዊ መንፈሱም አልፎ የኢስላማዊ ታሪካችን አንዱና ትልቁ ክፈል ተደርጎም ይወሰዳል።

<ኢስለማዊ ወንደማማችነት...ከቁርአን፡ ከሱናና ከሲራ>

ዛሬ ላይ አብዘሃኛው ሙስሊም ማለት በሚያስችል ሁኔታ ኢስላማዊ ወንድማማችነትን እንደ ተራ ነገር እየተመለከትን ነው። ሶሃባዎች ኑረው የሞቱበትን፡ በታሪክ የሚታወሱበትን ይህን ድንቅ የኢስላማዊ ወንድማማችነት መርህ በቀላልና ውሃ በማያነሱ ምክናያቶች ስናሻክረው ይስተዋላል። አብዘሃኛውን ጊዜ ደግሞ ይህ ወንድማማችነት የሚሻክረው ሃይመኖታዊ ባልሆኑና በዱኒያዊ ነገሮች መሆኑ ያሳዝናል። ኢስላማዊ ወንድማማችነት...መሰረቱ እምነት ሆኖ ሳለ፤ መሰረቱ የኢስላም አሰተምህሮ ሆኖ ሳለ፤ መሰረቱ ሰማያዊ ትዕዛዝ፤ መሰረቱ የነቢዩ ህይወት፤ መሰረቱና መገለጫዎቹ የሶሃባዎች ህይወት የታቢኢዮች ውሎ ሆኖ ሳለ ዛሬ ላይ ብዙም ቦታ አልተሰጠውም። ግን ለምን? ሁላችንም ራሳችንን እንጠይቅ!

<ከቁርአን>

“ምእመናኖች ወንድማማቾች ናቸው።በሁለት ወንድሞቻችሁም መካካል አስታርቁ።ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ።” (አል-ሁጁራት፡10)
“ምእምንና ምእመናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው።...” (አልተውባ፡71)
“አላህንና መልክተኛውንም ታዘዙ። አትጨቃጨቁም ። ትፈራላችሁና ሐይላችሁም ትኼዳለችና/ይዳከማልና።ታገሱም አላህ ከትዕግስተኞች ጋር ነውና” (አል አንፋል፡46)
“በልቦቻችሁም መካከል ያስማማ ነው። በምድር ያለውን ሁሉ (ሀብት) በለገስክ ኖሮ በልቦቻቸው መካከል ባላስማማህ ነበር። ግን አላህ በመካከላቸው አስማማ። እርሱ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና።” (አል አንፋል፡63)
“የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ፡፡ አትለያዩም። ጠበኞችም በነበራችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (የዋለውን) የአላህን ፀጋ አስታውሱ። በልቦቻችሁም መካከል አስማማ። በፀጋውም ወንድማማቾች ኾናችሁ። በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ። ከእርሷም አዳናችሁ። እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀፆቹን ያብራራል።” (አልኢምራን፡103)
...
ወንድሞችና እህቶች ከዚህ በላይ ምን አይነት ትዕዛዝ እንጠብቅ ይሆን? ኢስላማዊ ወንድማማችነታችንን የምናጠነክርበት ሰዓት አልድረስም ነው የምትሉት? ወይስ ምን?

<ከሱና>

ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ኢስላማዊ ወንድማማችነት በብዙ ንግግሮቻቸውና ውሏቸው ውስጥ አስገንዘበዋል። የተወሰኑትን ንግግሮች ለትውስታ ያክል እንጥቀስ፦

“እስክታምኑ ድረስ ጀነትን አትገቡም አንዳችሁ አንዳችሁን እስከምትወዱም ድረስ አታምኑም” (ሶሂህ ሙስሊም)
“ለራሳችሁ የወደዳችሁትን ነገር ለወንድማችሁ እስካልወደዳችሁ ድረስ አማኞች አትሆኑም” (ሶሂህ ቡኻሪ)
“...በፍርዱ ቀን አላህ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፦ ለእኔ ሲሉ ሲዋደዱ የነበሩት የት አሉ? ዛሬ በእኔ ጥላ ስር ይሁናሉ ከእኔ ውጭ ሌላ ጥላ በሌለበት” (ሶሂህ ሙስሊም)
“በዱኒያ ችግር ላይ የወደቀን ሰው አግኝቶ ችግሩን የቀረፈ ሰው አላህ የፍርዱ ቀን የእርሱን ችግር ይቀርፍለታል። በችግር ውስጥ ያለን ሰው ችግር ያቀለለ ሰው አላህ የዱኒያውንም የአኼራውንም ህይወት ያቀልለታል። የሙስሊሞችን ነውር/ስህተት/ የደበቀ አላህ የእርሱን ነውር በዱኒያም በአኼራም ይደብቅለታል። አላህ ባሪያው ወንድሙን በመርዳትና በማገዝ ላይ አስከሆነ ድረስ አላህ እርሱንም ያግዘዋል ይረዳዋል።” (ሶሂህ ሙስሊም)
“ለአንድ ሙስሊም ወንድሙን አሳንሶ መመልከቱ ከወንጅል በቂው ነው። የአንድ ሙስሊም ህይወት፡ገንዘብና ክብር በሌላ ሙስሊም አይደፈሩም።” (ሶሂህ ሙስሊም)
...
አሁንስ...ምን እንጠብቅ ይሆን?

<ከሲራ>

በኢስላማዊ ታሪክና ሲራ ውስጥ ከኢስላማዊ ወንድማማችነት ጋር በተያያዘ በጣም ብዙ የሚያስደምሙና ልብን የሚያረጥቡ ብዙ ክስተቶችን መጥቀስ ይቻላል። ግና ፅሁፉን በጣም ላለማርዘም ስል አንድ ታሪክ ብቻ ይኼው ጀባ ብያለሁ። ወላሂ! በጣም የሚያስነባ ክስተት ነው። በድንብ አስተውለን ራሳችንን እንገምግምበት ይህንን ያክል እንኳን ባንሆን የቻልነውን ነገር ለማድረግ የሚያነሳሳን ይመስለኛል። አላህ ያገዘን! አሜን።

ታሪኩን የሚተረክልን ሁዘይፋ የሚባለው ሶሃባ እንዲህ ይላል “የየርሙክ ጦርነት ወዲያውኑ እንዳበቃ በጦር ሜዳው በሸሂዶችና በተጎዱት መካክል ‘በማንቆርቆሪያ’ ውሃ ይዤ እዞር ነበር። በዚሁ አጋጣሚ የአጎቴን ልጅ ተመለከትኩኝ። በሚያቃጥለው አሻዋ ላይ በደም ተለውሶ ወድቋል። ሊሞት ምንም አልቀረውም። ዉሃ ይፈልግም እንደሆን ጠየኩትኝ።መናገር ስለማይችል ውሃ እንደሚፈልግ በምልክት አሳየኝ።ውሃውን እየሰጠሁት ባለሁበት ቅፅበት በጣም በሚያዛዝን ድምፅ “ውሃ! ውሃ! እባካችሁ የውሃ ጠብታ” ሲል አስተጋባ። የአጎቴ ልጅ ‘ሃሪስ’ ይህን የሚያሳዝን ድምፅ እየሰማ ለራሱ መጠጣት አልፈለገምና ውሃውን ለሚጮኸው ሰው እንድሰጠው በምልክት ነገረኝ። እኔም ፈጠን ብየ ወደ ድምፁ አቅጣጫ አመራሁኝ...‘ኢክሪማ’...ነበር። ውሃውን ለኢክሪማ ልሰጠው እያልኩኝ አሁንም ሌላ የሚያሳዝን ድምፅ ጮኸ፡ ውሃ! ሲል አስተጋባ።ኢክሪማም ምላሱ በውሃ ጥም እንደታሰረች ለሚጮኸው ወንድሙ በቅድሚያ እንድሰጠው አመላከተኝ። እኔም ፈጠን ብየ ወደዚያው ሄድኩኝ ሰውየው... ‘ኢያሸ’... ነበር። ዱዓ እያደረገም አገኘሁት እንዲህ በማለት “አላህ ሆይ! ለእምነታችን ስንል የህይዎታችንን መስዋዕትነት ለመክፈል ምንም አላቅማማንም። የሸሂድነትንም ክብር ለግሰን ወንጀሎቻችንም ይቅር በለን!” ይህንን ዱዓ እንደጨረሰ ‘ኢያሽ’ በእጄ የያዝኩትን ዉሃ እንዳየው ሳይጠጣው በዚያችው ቅፅበት ህይወቱ አለፈች። ሸሂድ ሆነ። ወዲያውኑ ወደ ኢክሪማ በፍጥነት ተመለስኩኝ። ነገር ግን ኢክሪማም ሸሂድ ሆኖ አገኘሁት። ከዚያም በፍጥነት ወደ አጎቴ ልጅ ሃሪስ ጋ አመራሁኝ። በሚያሳዝን ሁኔታ እርሱም በዚያ በሚያቃጥለው አሸዋ ላይ ህይወቱ እያለፈች አገኘሁት። በህይወቴ በጣም ከሚያሳዝኑኝ ክስተቶች ውስጥ ትልቁ ይሄ ነበር። እንደዚህ እንዲተዛዘኑ ያደረጋቸውም ነገር ቢኖር በኢስላም ላይ የነበራቸው ስር የሰደደ እምነት ነበር። ይህንን የመሰለ ኢስላማዊ ወንድማማችነትም የመሰረተው ኢስላም ነበር።” ይለናል!

ወንድሞችና እህቶች ይህ ታሪክ ውስጣችንን የማይንጠው ሙስሊሞች ካለን ራሳችንን እንፈትሽ። በተለይም በዚህ ወቅት የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ይህንን ታሪክ ልንደግመው ይገባል። በወንድሞቻችንን ላይ በሚደረሰው እያንዳንዱ ክስተት ላይ ተቆርቋሪዎች መሆን አማራጭ ሳይሆን ግዴታች ሊሆን ይገባል። ታዲያ..ይህንን ትልቅ ነገር እንዴት በቀላሉ ሊታረቁ በሚችሉ ምክናያቶች እንንደዋለን? እስኪ ስንቶቻችን ነን ለኢስላማዊ ወንድማማችነት ለሶላታችን የምንስጠውን ቦታ ያክል የምንሰጠው? ስንቶቻችን በእኛ ህይወት ውስጥ እንዲገጥመን የምንፈለገውን መልካም ነገር፡ እንዲርቀን የምንሻውን መጥፎ ነገር በሙስሊም ውንድሞቻችን ላይ መልካሙ እንዲገጥማቸው መጥፎው ደግሞ እንዳይነካቸው የምንመኘው? የውንድሞቻችን መቸገርና በተለያዩ መከራዎች ውስጥ መሆን ምን ያክል ይሰማናል? ስንቶቻችንስ ነን ለሙስሊሙ አንድነት ተጨንቀን በቀላል ምክናያቶች የተራራቁ ወንድሞችን ለማቀራረብ የምንጥር? ስንቶቻችን ነን ወንድሞቻችንን በዱአችን ውስጥ የምናስታውሳቸው? ስንቶቻችንስ ነን የኢስላማዊ ወንድማማችነትን ሃቆች የምናውቀው?

በፅሁፊ ውስጥ ስህተት ካለ ከእኔ ሲሆን ትክክል ከሆነም በአላህ እርዳታ ነው። አስተያየትና ሃሳብ ካላችሁ ልታደረሱኝ ትችላላችሁ። በሌላ ፅሁፍ እስከምንገነኝ ለጊዜው በዚሁ ላብቃ።

ቁጥር 6፡ <የሃሳብ ልዩነት...በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ቢላዋ!>

<የበሽታዎቻችን... ጥቅል ዳሰሳ>

በ21ኛው ክ/ዘመን በኢስላማዊ ማህበረሰብ ማንነት ላይ የተለያዩ አደገኛ በሸታወች ተስተውለዋል።እየተስተዋሉም ነው።የስብዕና ግድፈት፡የሞራል መላሸቅ፡ ከምሁራዊ ምልከታ እጦት፡ ከውስጥ በስሜቱ ከውጭ በኢስላም ጠላቶች ሽንፈት፡ ፍትሃዊና አግባብ የሆነ ማህበራዊ ኑሮ ርቆናል፡ሙስናና ምዝበራ በዝቷል፡ መሃይምነትም ቢሆን ቀላል አይደለም፡ ድህነትና ብክነት፡ ስግብግብነት፡ በራስ ያለመተማመንና ጥገኝነት፡ በጥቃቅን ነገሮች ውዝግብና ንትርክ፡ አለመከባበር፡ በእውቀት ሳይሆን በስሜት መመራት፡የሙስሊሙ አንድነት መቀጨጭ፡ ግደለሽነትና ሃላፊነት አለመውስድ...የበሽታው ዝርዝር ብዙ ስሜቱም አስቃቂ ነው። የበሽታዎቻችን ብዛትና የችግራቸውን ጥልቀት ስንገምግመው ደግሞ የሙስሊሙን ኡማ ከምድረ ገፅም ጭምር የማጠፋት ሃይል አላቸው።
ታዲያ የሙስሊሙ ማህበረሰብ በነዚህ በሽታዎች ሳቢያ ከምድረ ገፅ ለምን አልጠፋም? የዘመናችን የኢስላም ‘አሰላሳዮች’ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሁለት ታላላቅ ምክናያቶችን ያስቀምጣሉ። 1ኛ) ሙስሊሙ "ኡማ” ከምድረ ገፅ ከመጥፋት የዳነውና አሁንም ያለው ቁርአንና ሃዲስን መመሪያቸው አድርገው ያያዙ የማህበረሰባችን ክፍሎች በቁጥር ይነሱም ይብዙ በመኖራቸውና 2ኛ) በማህበረሰባችን ውስጥ ምንም እንኳ የችግሮቹ ብዛት አያሌ ቢሆንም መልካም ስራዎችና መልካም ስሪዎች፡ በአላህ የሚመኩ፡ አላህን ቀጥተኛውን መንገድና ከወንጀላቸው ምህረት የሚጠይቁ ሙስሊም የማህበረስብ ክፍሎች መኖራችውን ያመላክታል ይላሉ። አላህ (ሱ.ወ) በህዝቦች መካከል መልካም የሚሰሩና አላህን ፈሪዎች አስካልጠፉ ድረስ ያንን ኡማ እንደማያጠፋ ለነቢዮ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አላህም አንተ በውስጣቸው እያለህ (ድንጋይ በማዝነብና ባሳማሚ ቅጣት) የሚቀጣቸው አይደለም ። አላህም አነሱ ምህረትን የሚለምኑ ሲኾኑ የሚቀጣቸው አይደለም።” (አልአንፋል፡33)

<የሃሳብ ልዩነት...የቢላዋው የላይኛው ጠርዝ ስለት>

በአሁኑ ሰዓት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ካጠቁት ከባባድ በሽታዎች መካከል ታላቁን ድርሻ የሚይዘው <የሃሳብ ልዩነት>...አለምግባባትን ሲፈጥር...ይህ ደግሞ የሙስሊሙን አንድነት አደጋ ላይ ሲጥል ነው።ይህ አለመግባባት ተውሳክ ነው።በሽታው በጣም አደገኛ ወረርሽኝ ነው።ከዚህም የተነሳ ይመስላል ያልገባበት አከባቢ፡ ያልዞረበት ከተማና ያላመሰው የማህበረስብ ክፍል የለም።ይህ ያለመግባባት ተፅዕኖም በሰዎች አመለካከትና እምነት፡ ስብዕናና ፀባይ፡ የአነጋገር ዘይቤያቸውም ላይ ይሁን ከሰዎች ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ሳይቀር ሰርፆ ገብቷል። ይህም በሽታ የሙስሊሙን ኡማ የአጭርም ይሁን የረዥም ጊዜ ግብና አላማዎቹን ጎድቷል። የብዙዎችን ልብ አቁስሏል፡ አድምቷል ብሎም አጨልሟል። አካባቢን በክሏል። ልብን መካንና ብቸኛ አድርጓል።ብዙ ሰዎችን አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር አናክሷል። ብዙ ትዳሮችን አፍርሷል። አባትና ልጅን አጣልቷል። ኢስላማዊ ወንድማማችነትን አቀጭጯል። የሃሳብ ልዩነት አደጋነቱ የሚመነጨው ኢስላማዊ ስርዓትና አደብን ሳንከተል በምናስተናግድበት ወቅት ነው። በዚህን ጊዜ የሙስሊሙ ህብረተስብ አንድነት ፀር ይሆናል። ማህበረሰብ አውዳሚ በሽታ ይሆናል። በመወዛገብ ጊዜ ይባክናል። ይህ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይህ አይነቱ ድርጊትም ከቁርአንንና ከሱና አስተምህሮ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ማወቅ ይኖርብናል።

<ኢስላማዊ...እውነታው>

ሙስሊሞች በተውሂድ ትክክለኛ እምነት ከተላበሱ በሗላ አላህ በቁርአኑ ነቢዮ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሃዲስ በስፋት ያስገነዘቡትና ያስተማሩት ጉዳይ ቢኖር የሙስሊሙ “ኡማ” አንድነት ላይ ነው። የቁርአንና የሱናም አስተምህሮ ዋነኛ ትኩረትም የሙስሊሙን ማህበረስብ አለመግባባት ማከምና አላስፈላጊ ነገሮችን በቀዶ ጥገና አስወግዶ የሙስሊሙን “ኡማ” አንድነት ማስጠበቅ ነው። በዚሁ ሳቢያ የሙስሊሙን ህብረተስብ ሰላምና ግንኙነት የሚያሻክሩ አለመግባባቶችን ከስራቸው ነቅሎ መጣል ነው። ከአላህ ጋር ምንም ከለማጋራት ቀጥሎ በሙስሊሞች ዘንድ አላስፈላጊ አለምግባባቶችን ቀርፎ ሙስሊሙ ህብረተሰብ አንድነቱን ማስጠበቅ ትልቅ ቦታ አለው። የአላህም ትዕዛዝ ሆነ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አብዘሃኛው ጥሪ ሙስሊሙን ማህበረስብ ወደ አንድነትና አጋርነት እንዲመጣ ማድረግ፡ ልቦቻቸውን በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር ሞልቶ በፍቅር ማስተሳሰርና ሃይላቸውን ለአንድ አላማ በጋራ እንዲሰሩና እንዲጠቀሙ ማስቻል ነው።

<የሃሳብ ልዩነት...የቢላዋው የታችኛው ጠርዝ ስለት>

የሙስሊሞች አምላክ አንድ አላህ፡ ነቢያቸው ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)፡ መመሪያቸው ቁርአን፡ ቂብላቸው ካዕባ፡ የመኖር አላማቸው አላህን መገዛት እስከሆነ ድረስ በነዚህ የጋራ አጀንዳዎች ላይ እንዳይስማሙና በጋራ እንዳይሰሩ ሊያደርግ የሚችል ነገር በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም። አላህም እንዲህ ይላል፦ “ይህች (ህግጋት) አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት። እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ” (አል አንቢዕ፡92)። ለጋራ ግብ ሲባል በሃሳብ ልዩነት ውስጥ አንድነት ይፈለጋል። ለማህበረሰባችን አንድነትና መሻሻል ስንል የሃሳባችንን ልዩነት ለጥንካሬያችን መሰረት ማድረግ ይገባል። ልዩነታችንን የምናስተናግድበትን መንገድ በኢስላማዊ ስርዓትና አደብን ተከትልን ከሆነ ልዩነት ፀጋ ነው። ሶሃባዎች የሃሳብ ልዩነታቸው ወደ አለመግባባት አልውሰዳቸውም ነበር። የሃሳብ ልዩነታቸውን ፀጋ ተጠቅመውበታል። ለጋራ ግባቸው እንደ ግብዓት ተጠቅመው አውለውታል።ማህበረሰባቸውን ቀይረውበታል። ስልጣኔን ገንብተውበታል። ጠላትንም አሽንፈውበታል። መንግስታትን መስርተውበታል።

ሁሉም ሰው ከሌላው የሚለይበት ልዩ የሆኑ ተፈጥሯዊ ባህሪያት አሉት። ከአከባቢአችንም ይሁን ከልምድ ወይም ከትምህርት ያገኘናቸው ልዩ ችሎታዎችም አሉን። እነዚህን የተለያዩ የተፈጥሮና በጥረት የተገኙ ክህሎቶች በአንድ ላይ ሲመጡ ጥሩ ማህበረሰብን ለመገንባት ያስችላል። ተመሳሳይ አመለካከት። ተመሳሳይ ችሎታ፡ ተመሳሳይ ዝንባሌ፡ ተመሳሳይ ልምድና ሁሉም ነገራቸው ተመሳሳይና አንድ አይነት በሆኑ ማህበረሰቦች መካከል ማህበራዊ ግንኙነት መፍጠር ካባድ ነው።ይህ ሲሆን ለማህበራዊ መስተጋብር ቦታ አይኖርም። ለመስጠትም፡ ለመቀበልም፡ ለመማርም፡ ለማስተማርም ለመሻሻልም ክፍተት አይኖርም ማለት ነው። ምክናያቱም ሁሉም ተመሳሳይና አንድ አይነት ናቸውና። ሰለዚህ የሃሳብ ልዩነት በስርዓት ከተጠቀምነበት የለውጥ ሚስጠር ነው።

<ታሪካዊ...ምልከታ>

የቁርአን ወደ አንድ ሶስተኛው የሚሆነው ክፍል በብዙ ታሪኮች የተሞላ ነው። ቁርአን የቀደምት ነብያት ተከታዮችን ታሪክ ከእነርሱ ትምህርትና ተግሳፅ እንድንወስድ ይተርክልናል። ማህበረሰብ እንዴት እንሚያድግ፡ ስልጣኔ እንዴት እንደሚገነባና እንደሚፋፋ ያስነብበናል። በተቃራኒው ደግሞ ማህበረስብ እንዴት እንደሚንኮታኮትና ስልጣኔም እንዴት እንደሚከስም ተግሳፅ ይሰጠናል። ማህበረሰብ የሚንኮታኮተውና ስልጣኔ የሚከስመው ሙስሊሞች አንድነታችው ሲዳከም፡በሙስሊሞች መካከል አለመግባባት ሲሰፍንና ወደ <ሰፍር ጎጠኝነት> ሲዘነበል መሆኑን በግልፅ ያስተምራል።

“ከእነዚያ ሃይማኖታቸውን ከለያዩትና ክፍልፍሎች ከሆኑት (አትሁን)። ሁሉም አነርሱ ዘንድ ባለው ነገር ተደሳቾች ናቸው።”(አር-ሩም፡32)

በጭቅጭቅና በንትርክ ሰበብ የሙስሊሞች አንድነት ከላላ የነቢዩን መንገድ በትክክል ያለመከተል መገለጫ ነው። አላህም በቁርአን ውስጥ እንዲህ ይላል፡- “እነዚያ ሃይማኖታቸውን የለያዩ አህዛብም የኾኑ በምንም ከእነሱ አይደለህም። ነገራቸው ወደ አላህ ብቻ ነው። ከዚያም ይሰሩት የነበሩትን ሁሉ ይነገራቸዋል።” (አል አንዓም፡159)

አንድ ማወቅ ያለብን ጉዳይ ቀደምት ሙስሊሞች መካከልም የሃሳብ ልዩነት ነበር። ለእነርሱ ግን ልዩነታቸው የሃሰብ ብቻ እንጂ የሙስሊሞችን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል አልነበረም። ሶላትን በሚያከል የኢስልምና አስተምህሮ ላይ ሳይቀር የሃሳብ ልዩነት አሳተናግደው አብረው ኖረዋል።አልተጣሉም።ተከባብረዋል። ተደጋግፈዋል። ተማምረዋል። በነሱ ጊዜ ስሜት ሳይሆን መመሪያቸው እውቀት ነው። እውነት ካለበት ቦታ ሁሉ ያሸንፋል በእነሱ ዘመን። ለእውነት ተገዥ ነበሩ። ነፍስያ ቦታ አልነበራትም በእነሱ ግዜ።በሃሳብ ተለያይተው በአካል ጀርባ አይሰጣጡም። አይኮራረፉም። አይተማሙም። ችግራቸው ሲነገራቸው በፍጥነት ያስተካክላሉ ከየትኛውም በኩል ይምጣ። እንደኛ ስህተታቸውን የሚጠቁማቸው ሰው በጠላትነት አይፈርጁም ይልቁንስ ሲበዛ ያከብሩት ነበር። ምክናያቱም ለዕነሱ አላማቸውና በመካከላቸው ያለው ትስስር ከፊትለፊታቸው ሁል ጊዜም የሚታያቸው ትልቁ ስዕል ስለነበር ነው። የልባቸው አንድ መሆን ከሁሉም በላይ ስለሚያስጨንቃቸው ነበር። በአንድ ወቅት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለሶቦቻቸው ከእነርሱው መካከል በጣም ጥሩ ስለሆነ ሰውና እርሱም የጀነት እንደሆነም ነገሯቸው። ሶሃባዎች ሁልጊዜም ቢሆን ስራቸውም ይሁን ምኞታቸው መልካም ነገር ስለነበር ስለዚህ ሶሃባ መልከም ስራ ለማወቅ ፈለጉ ነቢዮም እንዲህ አሉ “ሰውየው በልቡ ውስጥ የማንንም ሙስሊም ጥላቻ ይዞ አይተኛም ሁልጊዜ ከመተኛቱ በፊት ሁሉንም ሰው ይቅር ብሎ ስለሚተኛ ነው” አሏቸው።

<እኛነታችን...በእኛው ሲፈተሽ>

ሱብሃንአላህ...ከላይ የቀረበው ስብዕና ምን ያምር? ምን ያማረ..ችሎታ? ሰዎች በድለዎት...የለምንም ማቅማማት ይቅር ማለት? የእኛስ ጉዳይ ወንድሞች እህቶች? ስንት ወንድሞቻችን ጋር ተቀያይመናል? ስንቶቻችን ነን ሁሉንም የበደለንን ሰው ይቅር የምንለው? ልባችን ውስጥ የስንት ወንድሞችና እህቶች ጥላቻ ይነድ ይሆን? ስንቶቻችን...እንሆን...ያስቀየሙንን ወንድሞችና እህቶች ይቅር የምንላቸው? ስንቶቻችን ነን ከውንድማችንና ከእህቶቻችን ጋር መጣላታችን አስጨንቆን እንቅልፍ የሚነሳን? ሰውን ይቅር የማለትስ የውስጥ ጉልበት ያለን ስንት ነን? መቼም ለራስ ከራስ በላይ መፍትሄ የሚሰጥ የለምና ራሳችንን እንፈትሻት።

< ኢስላማዊ... መፍትሄዎች>

በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን።

<አጠቃላይ...መፍትሄ>

ሁላችንም ሙስሊሞች በትንሽ በትልቁ እየተጨቃጨቁ በሚፈጠር አለመግባባት በሙስሊሞች አንድነት መፍረክረክ ላይ ያለውን ታላቅ ድርሻ በውል ልንረዳ ግድ ይላል። ከዚህ ችግር ለመውጣት ያለን ብቸኛው መፍትሄ ኢስልምናን ከትክክለኛው ምንጭ በትክከለኛው ግንዛቤ መረዳት ነው። ኢስላማዊ እውቀት አማራጭ የሌለው የሙስሊሙን ማህበረስብ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊፈታ የሚችል መሳሪያ ነው። የመጀመሪያወ መስተካከል ያለበት “አቂዳችን” ነው። እምነታችን በቁርአንና በሱና ላይ መመስረት አለበት።በእውቀት እንጂ በስሜት የማይመራ ማህበረስብ መገንባት ያስፈልጋል። ትክክለኛውን ኢስላማዊ ግንዛቤ በማህበረሰባችን ላይ የማስረፁ ስራ ሊሰራ ይገባል።ይህ ሲሆን ግንኙነታችንና መስተጋብራችን ይሻሻላል። ልዩነታችን ግብዓትና ውበት ይሆናል። በልባችን ውስጥ ያለው ጥላቻ ይወገዳል።
ትክክለኛ የዲን ግንዛቤ ሃራሙን ከሃላል፡ ሱናውን ከሙባህ፡ ሙባሁን ከመክሩህ ያስለያል። የሚቀድምና የሚከተለውን ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። ትልቁን አላማችንን እንዳንስት ያግዘናል። ኢስላማዊ ስብዕናችንንና ፀባያችንን ይሞርደዋል። ትክክለኛውን ስነ ምግባር ያለብሰናል። ከመበታተንም ይታደገናል።የቁርአንም አስተምህሮ ይሄው ነው። የመጨቃጨቅ የመነታረክ ያለመከባበር ትርፉ አንድነትን ማጣት። አንድነትን ማጣት ደግሞ ትርፉ ፍርሃት። የፍርሃት ትርፍ የሽንፈትን ካባ መላበስ። መጨረሻው ተወርዶ መኖር!

“አላህንና መልክተኛውንም ታዘዙ። አትጨቃጨቁም። ትፈራላችሁና ሐይላችሁም ትኼዳለችና። ታገሱም። አላህ ከትዕግስተኞች ጋር ነውና።” (አል አንፋል፡46)

<ዝርዝር የመፍትሄ አቅጣጫዎች>

1. ሰዎች የቆዳ ቀለማችን፡ ቋንቋችን፡ ባህላችን፡ ወጋችን፡ የአመጋገብ ስርዓታችን፡ የአለባበስ ስርዓታችን እንደሚለያየው ሁሉ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ የሃሳብ ምልከታ እንደሚኖረን አምኖ መቀብል ወሳኝ ጉዳይ ነው።
2. ሁልጊዜም ቢሆን ትልቁንና የጋራ የሚያደርግንን አጀንዳችንን...ኢስላማዊ አንድነትን..ከፊትለፊታችን በማስቀመጥ...ለጥቃቅን ነገሮች ቦታ ሰጥተን አንድነታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መታደግ ያስፈልጋል።
3. የሃሳብ ልዩነት መኖር የለውጥ ወሳኝ መሳሪያ መሆኑን መገንዘብ። ነገር ግን የሃሳብ ልዩነታችንን የምናስተናግድበት መንገድ ኢስላማዊ አደብና ስርዓት የተከተለ መሆን አለበት።
4. ኢስላማዊ አደብ ያልተከተለ የሃሳብ ልዩነትን ማንፀባረቅ ለሙስሊሙ አንድነት አደጋ መሆኑን በመገንዘብና ሓላፊነት ተሰምቶን ኢስላማዊ አደብን በተላበሰ መልኩ ለማቅረብ መሞከር።
5. ማንኛውንም ነገር ስንሰራም ሆነ ስንተው ለአላህ ብሎ የመስራት ባህልን ከማንነታችን ጋር ማቆራኘት አለብን። ይህ ሲሆን በስሜት ሳይሆን በእውቀት እንመራለን።
6. ትክክለኛውን ኢስላማዊ አስተምህሮ ማወቅና ራስን ሁልጊዜ ለቁርአንና ለሱና ቅርብ ማድረግ።
7. ኢስላማዊ ታሪኮችን ማንበብ። ሶሃባዎች በሱና ሳይሆን በፈርድ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር የተለያየ ሃሳብ ኑሯቸው ግን በአንድነታቸውም ላይ ይሁን በወንድማማችነታቸው ላይ ምንም ችግር አልተፈጠረም ነበር። ስለዚህ ሶሃባዎች ለማህበረስብ የኑሮ መሻሻል ብሎም ለስልጣኔ ግንባታ የተጠቀሙበት የሃሳብ ልዩነት በእኛ ጊዜ እንዴት ለአንድነታችን የስጋት ምንጭና በመካከላችን ጥላቻን ይዘራል ብሎ ራስን መጠየቅ?
8. የሙስሊሙ አንድነት በሙስሊሞች ህልውና ላይ ያለውን ትልቅ ድርሻ በመገንዘብ ካላስፈላጊ ንትርኮችና ውዝግቦች ራስን መቆጠብ።
9. ዱዓ ማድረግ አላህ የሙስሊሙን አንድነት እንዲጠብቅና ከማይጠቅም የሃሳብ ልዩነት እንዲጠብቀን ዘወትር በዱዓ መበርታት።
10. ይቅር ባይ መሆን። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በትንሽ በትልቁ አለመቀየምና የተከፋንበት ሰው እንኳን ካለ ለአላህ ሲሉ ይቅር ማለት። ለምንም ሳይሆን ለአላህ ስንል ይቅር ማለት፡ ይህ ጉዳይ ቢያንስ 3 ትርፎች አሉት ሀ) አላህን ያስደስታል ለ) ይቅር የሚለው ሰው ስብዕናው ይሻሻላል ሐ) ይቅር የተባለው ሰው ደስ ይለዋል። የምን መዘግየት ነው? አሁኑኑ...ለአላህ ስንል ይቅር መባባል እንጂ! ከእራሴ ጀመሬ ይቅር ብያለሁ...ሁላችሁንም ሙስሊም ወንድሞች እህቶች ለአላህ ስል እውዳችሗለሁ። በአንድነታችን ላይ አላህ ያግዘን!አሜን

በፅሁፊ ላይ ስህተት ካለ ከእኔ ችግር ሲሆን...ትክክል ከሆነ በአላህ እገዛ ነው።

1 comment:

  1. ከላሊው የኢንሊሉአኒቲ ትዕዛዝ ወደ አሜሪካ እና በመላው ዓለም ሰላምታ ስንሰጥ, ይህ የጠፋውን ህልማችንን መልሰው ማግኘት የሚችሉበት የ Illuminati ወንድማማችነት ለመሳተፍ እና እንዲሁም የሀብትንና ደስታን ብርሃን ማየት የሚችሉበት አጋጣሚ ነው. ያለ ደም የሚቀርብ. በተጨማሪም ሁሉም አዲስ አባላት በእውነተኛው ማህበር ውስጥ እና በሚመርጡበት እና በሚኖሩበት አካባቢ የሚኖሩበት ኢንቨስትመንቶችን ለመቀበል እና እነሱን ለመሰደድ የሚያስችለውን ይህን እድል ለመቀበል $ 650,000 ዶላር እንከፍላለን.

    ነፃ ሕጐች ውስጥ ለሚገቡ አዲስ አባላት ይሰጥ ነበር.
    1. የአሜሪካ ዶላር የ 650 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሽልማት ነው.
    2. በአሜሪካ ዶላር 150,000 የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያለው የ Sleek Dream AG
    3. በመረጡት አገር የተገዛ የሕልም ቤት.
    በአለም ውስጥ ከ 5 ቱ ቀጠሮ ጋር ቀጠሮ.
    መሪዎቹ እና በዓለም ላይ ያሉ አምስት ዋና ዋና ዝነኞች. ፍላጎት ካሳዩ እባክዎ ቀዳሚውን ኢሜይል አድራሻ = ትልቅilluminate99@gmail.com ያነጋግሩ



    ማስታወሻ; በዚህ የዓለም ህንድ ውስጥ ቱርክ, ቱርክ, አፍሪካ, አሜሪካ, ማሌዥያ,
    ዱባይ, ኩዌት, ዩናይትድ ኪንግደም, ኦስትሪያ, ጀርመን, አውሮፓ. እስያ, አውስትራሊያ, ወዘተ,


    ሰላምታ TEMPLE ILLUMINATI ዩናይትድ ስቴትስ

    ReplyDelete