Thursday, November 15, 2012

ታላቅ የዚያራ ቀን



ታላቅ የዚያራ ቀን

ውድ የአላህ ባሮች! የዚህ ሳምንት የተቃውሞ ሂደታችን ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሁሉ የተለየና በዓይነቱ አዲስ መሆኑን እናበስራለን፡፡ ሁሉም ምእመናን በየአካባቢው ባሉት መሳጂዶች የጁመዓን ስግደት እንዲፈፅም እና ጁመዓ ሊካሄድ የነበረው ከፍተኛ ተቃውሞ መልኩን ቀይሮና በተጠናከረ ከፍተኛ ህዝባዊነት ታጅቦ የፊታችን እሁድ ኮሚቴዎቻችን በሚገኙበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ‹‹ታላቅ የዚያራ ቀን›› በሚል እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡
በመደበኛ ግዜ ከሰኞ እስከ እሁድ ስናደርጋቸው የነበሩ ዚያራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ለታሳሪ ቤተሰቦች በሞራልና በምንችለው አቅም ሁሉ የምናደርገው እንክብካቤ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ታስረው ለተፈቱ ወንድሞች የምንቸረው ፍቅር፣ ድጋፍና እንክብካቤ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የፊታችን እሁድ ግን በልዩ ሁኔታ ሁላችንም ሴቱም ወንዱም፣ ወጣቱም ጎልማሳዉም፣ አባቶችም እናቶችም በአንድ ላይ በመሆን የምንዘይርበት ታላቅ ቀን ነው፡፡
በዚህ መሰረት የፊታችን እሁድ ከዚህ ቀደም እናደርገው የነበረውን የተቃውሞ ሂደት መልኩን በመቀየር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመዲናችን አዲስ አበባና አካባቢዋ ሙስሊም ነዋሪዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቅ ግዙፍና እጅግ ሰላማዊ የዚያራ ፕሮግራም በማከናወን ይሆናል፡፡
የሚሊዮኖች ተወካይ የሆኑትን መሪዎች ማሰር ህዝብን ማሰር መሆኑን ለማሳየት በነቂስ በመውጣት በቃሊቲ ዚያራ እናደርጋለን፡፡ እነርሱ ንፁህ የኛ፣ የህዝበ ሙስሊሙ ተወካዮች እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም፡፡ እነሱ ማለት እኛ ነን፤ እነርሱን በማሰር ውስጥ የታሰርነው እኛ ነን፡፡ በመሆኑም ታስረናልና ሁላችንም ከህሊና እስረኞቹ ተወካዮቻችን ዘንድ ሄደን ህዝባዊነታቸውን ለመላው ዓለም ዳግም እናረጋግጣለን፡፡ ለዲናችን መከበር የምንቆጥበው ግዜ የለንም፤ በመሆኑም እሁድን በእግርም በትራንስፖርትም፣ በግልም በጀመዓም ተጉዘን ውድ ኮሚቴዎቻችንን እንዘይራለን፡፡ በዚህ ልዩ የዚያራ ቀን ‹‹መሪዎቻችን ማለት እኛ ናቸው›› ስንል በተግባር የምናሳይበት ታላቅ የአንድነት መድረክ ነው፡፡

ይህ ቀን አለኝታነታችንን የምንገልፅበት ቀን ነው፡፡ የፊታችን እሁድ ያቀድናቸውን ፕሮግራሞች ሁሉ ሰርዘን ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ሳይገድበን በዚያራው ቦታ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በአንድነት ሄደን በመዘየር እነርሱ ላሸከምናቸው ውክልና ሲሉ አካላቸው እስኪጎዳ፣ የግል ሕይወታቸው እስኪናጋ ድረስ በእስር ያዩትን ስቃይና መከራ እንደምንጋራ እናመላክታቸዋለን፡፡ ይህን ሁሉ ገፈት የቀመሱለት ትግላቸው ትልቅ ፍሬ እንዳፈራ ተመልክተው ልቦናቸው እንዲረጋጋ፣ መንፈሳቸው እንዲረካና ፅናታቸው እንዲጎለብት በጉጉትና በናፍቆት ልናያቸው የቋመጥንላቸው ኮሚቴዎቻችንን ከረጅም ግዜ ወዲህ በአንድነት ሆነን በብዙ መቶ ሺዎች ሆነን ከፊታቸው በመቆም እንዘይራቸዋለን፡፡ የፊታችን እሁድ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእድሜው አይቶት በማያውቀው ፍፁም ሰላማዊነትን የተላበሰ የሰው ማዕበል ይጥለቀለቃል፡፡

ወንድሜ ሆይ! በኮሚቴዎቻችን ላይ የተፈፀመው እስርና ስቃይ በቁጭት አላንገበገበህም? የተቃጣባቸው ከእውነት የራቀ የአሸባሪነት ክስስ ውስጥህን አላቆሰለውምን? እንግዲያውስ አጋርነትህን ልታሳይ፣ እህት ወንድምና ጓደኞችህን ይዘህ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመገኘት በልብህ አላህ እንዲፈርጃቸው ልትማፀን፣ በአካልህ አጋርነትህን ልታስመሰክር ለዚህ ታላቅ ሰላማዊ የዚያራ ጥሪ ሀላፊነትህን በመወጣት ታሪክህን አድስ!
እህቴ ሆይ! አንቺስ የመሪዎቻችን እንግልትና መከራ የእግር እሳት አልሆነብሽም? ይህን ሁሉ ዘግናኝ ስቃይ ስትሰሚ የሴትነት አንጀትሽ ተላውሶ አይኖችሽ አላነቡምን? እንግዲያውስ በዚህ ታላቅ ሰላማዊ የዚያራ ቀን ጌታሽ ነስሩን እንዲያወርድና ሁሉንም ነገር እንዲያስተካክል እየተማፀንሽ ከወዳጅ ዘመድና ቤተሰብሽ ጋር በአካል ቃሊቲ በመገኘት አጋርነትሽን ልታስመሰክሪና አለኝታነትሽን ልታሳዪ የድርሻሽን በመወጣት ታሪክን አድሺ!

ሁላችንም ለዚህ ሰላማዊ ታላቅ የዚያራ ፕሮግራም በደመቀና ሰላማዊ በሆነ መልኩ መሳካት የድርሻችንን እንወጣ፡፡ ምናልባት በዚያን ቀን ከሚኖረው የህዝብ ብዛት አኳያ ከፊሎቻችን ኮሚቴዎቻችንን የማየት እድል ላይኖረን ይችላል፡፡ ይሁንና በጥሩ ኒያ ለመዘየር በማረሚያ ቤቱ መገኘታችን ነውና ዋናው ቁም ነገር ምንም ዓይነት ግብረገብነታችንን ከሚያውኩ ተግባራት ፍፁም ርቀን፤ ይህን ሰላማዊ የዚያራ ፕሮገራም የሚያደበዝዙ ግፍያ፣ ግርግርም ይሁን ሌላ ነገር ስንመለከት እራሳችን እንደለመድነው ስርዓት ልናሲዝና ሰላማዊ የዚያራ መንፈስን ብቻ ልናንፀባርቅ ይገባል፡፡ ይህ የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ የመዘየር እድሉን ያገኘን ላልዘየሩት ቶሎ ቦታ በመልቀቅና ውጪ በመጠባበቅ አንድ ላይ ሆነን ወደየመጣንበት በሰላም እንመለሳለን፡፡ የፀጥታ አካላትም ከምንም ዓይነት ትንኮሳ ርቀው ይህን ሰላማዊ የዚያራ ፕሮግራም በመልካም ግብረገብነትና በጥሩ የመግባባትና የመተባበር መንፈስ ህዝቡ ዘይሮ እንዲመለስ የሚጠበቅባቸውን ትብብር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም የዚያራው ሰዓት ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ሁላችንም የትራንስፖርት እጥረት ሊኖር እንደሚችል ግንዛቤ በመውሰድና ሰዓቱን አክብረን በግዜ በመገኘት ለኮሚቴዎቻችን ያለንን አለኝታነት ለጥቂት ሰዓታት በአንድ ላይ በመሆን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ አክበር!!

No comments:

Post a Comment