ሲኖዶሱ እና መጅሊሱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማጥመቂያ?
በተመስገን ደሳለኝ
ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ሼህ፣ ኢማም፣ ኡላማ፣ ደረሳ፣ ፓስተር፣ ዘማሪ፣ ካድሬ፣ ጠርናፊ፣ ተጠርናፊ፣ ሊግ፣ ማህበር፣ ፎረም፣ ግንባር ቀደም አርሶአደር፣ ልማታዊ ባለሀብት፣ ልማታዊ ጋዜጠኛ፣ ልማታዊ አርቲስት፣ ልማታዊ ማስታወቂያ ሰራተኛ፣ ልማታዊ እድር፣ ልማታዊ ማሀበር፣ ልማታዊ… ማን ቀረ? ማንም፡፡ እናም በዛሬ ጊዜ እመንም አትመንም የእነዚህ ሁሉ ምንጭ መለስ እና ኢህአዴግ ናቸው፡፡ በተቀረ የእምነት/ሀይማኖት መገኛ ቤተክርስቲያን እና መስጊድ መሆናቸው ከቀረ ዘመን አልፎበታል፡፡ ስብከትም ሆነ ዝማሬ አሊያም ዝየራ ከመፃሀፍ ቅዱስና ከቅዱስ ቁራን ሳይሆን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከተሰኘው እስታሊናዊ መፀሀፍ ነው፡፡ መምህሩም አንድ እሳቸው ‹‹ዘላለማዊው›› ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ለሲኖዶሱም ሆነ ለመጅሊሱ እየሱስና ነብዩ፤ ወይም ሙሴና ሙሳ ቦታ የላቸውም፡፡ ሆኖም በዚህ ቅር አትሰኝ፣ ምክንያቱም ለአብዮታዊ ዲሞክራሲና ለ‹‹ሰውየው›› ገለታ ይድረሳቸውና አብዮታዊያን ‹‹ሙሴ›› እና ‹‹ሙሳ››ን አዘጋጅተውልኻል፡፡
አፅመ-ታሪክ
እንዲህም ይጀምራል፡- ከዕለታት አንድ ቀን ጠረፍ ጠብቁልን ያልናቸው ወታደሮች ተሰባሰቡና መንግስት መሰረቱ፡፡ የተመሰረተው መንግስትም ምድራዊ አይደለምና ሊተች፣ ሊነቀፍ፣ የስራ ማቆም አድማ ሊደረግበት፣ የተቃውሞ ሰልፍ ሊወጣበት… አይገባም ሲሉ አዋጅ አወጁ፡፡ አዋጁም እንዲህ እንደዛሬው መወንጀያ ከመሆኑ በፊት ‹‹የኢትዮጵያ ትቅደም አላማን የሚቃወም…›› በሚል የሚጀምር ‹‹አማላይ›› እንደነበር ወደዚንባቤ ጎራ ብለህ ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡ ምናአልባትም ዚንባቤ የሚርቅህ ከሆነ በቅርቡ ከእስር የተፈቱትን ‹‹የቀድሞ ትናንሽ አማልክት››፣ የደርጉ መስራች ባለስልጣናትን ፈልገህ ጠይቃቸው ‹‹ተፀፅቼአለሁ›› ብለዋልና ሳይደብቁ ይነግሩሀል፡፡
የሆነ ሆኖ ባለፈው መንግስት ውስጥ የነበረው ‹‹ሀይማኖት››አንድ ነው፡፡ መጠሪያውም ‹‹ሶሻሊዝም›› የተሰኘ ሲሆን አማልክቱም ከፍ ሲል ሌኒንና ጓደኞቹ፤ ዝቅ ሲል መንግስቱ ኃ/ማርያምና ግብረ አበሮቹ ነበሩ፡፡ በተረፈ እግዚአብሔር፣ አላህ፣ ኢየሱስ፣ ቡድሃ፣ ባሂ… ጂኒ ቁልቋል በ1967ቱ አዋጅ ተሽረዋል፡፡ መሻራቸውንም ተከትሎ መቀጣጫ ይሆን ዘንድ ከጳጳሳቱ፣ ከሼሁ፣ ከፓስተሩ ተመርጠው መስዋዕት ሆኑ፡፡ ከዚህ በኋላም እውነት እውነት እልሀለው ለ17 አመታት ያህል ምድሪቱን ሞልተዋት የነበሩት መንጌ እና ጓደኞቻቸው ብቻ ነበሩ፡፡
እነሆም ይህ ከስጋም ከነፍስም የተጣላው የመንግስቱ ኃ/ማርያም መንግስት በመለስ ዜናዊና ጓደኞቻቸው ብርቱ ትግል፤ተራራ መውጣትና መውረድ (ማንቀጥቀጥም) ተጨምሮበት፣ እንዲሁም የእነአሞራውና የእነቕሺ ገብሩ መስዕዋትነት ታክሎበት እንዳይሆን እንዳይሆን ሆኖ ወደቀ፡፡ ከውድቀቱ በኋላም በአዋጅ የተሻረው ፈጣሪ በህገ-መንግስት ተመለሰ ተባለ፡፡ እነሆም ሰለፈጣሪ መመለስ የተበሰረበት ህግ ምዕራፍና ቁጥር፡-
‹‹ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ የመቀበል፤ ሃይማኖትና እምነቱን ከሌሎች ጋር በመሆን ወይም ለብቻው በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለፅ መብትን ያካትታል፡፡›› (የኤፈዴሪ ህግ-መንግስት አንቀጽ 11፣ ንዑስ አንቀጽ 1)
በእርግጥም አሸናፊዎች ባለጎፈሬ ታጋዮች የሃይማኖት ነፃነትን በተመለከተ ይህንን ብቻ አይደለም በህግ የደነገጉት፡፡ ሌላም አላቸው፤ በግልፅ እንዲህ የሚል፡-
‹‹በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማደራጀት፣ ለማስፋፋት የሚያስችላቸውን የሃይማኖት ትምህርት፣ የአስተዳደር ተቋም ማቋቋም ይችላሉ›› (የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 11፣ ንዑስ አንቀፅ 2)
መቼም ይሄ እፁብ ድንቅ አዋጅ ነው፡፡ ያውም ራሳቸውን የምድር አማልክት ባደረጉ ወታደሮች የተመሰረተ መንግስት በወደቀ ማግስት የተሰማ አዋጅ! ግና ምን ዋጋ አለው! ‹‹ነበር ባይሰበር›› ሆነ እንጂ? (‹‹ነበር ባይሰበር››ን ወደታች እናየዋለን)
…ከዚህ ቀደም ደግመን ደጋግመን እንድተነጋግርነው ደርግና ኢህአዴግ በአፈፃፀም እንጂ በአካሄድ ፍፁም የተለያዩ ናቸው፡፡ ደርግ አንጃ ግራንጃ አያበዛም፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃ ፕሬስ፣ ሰብዓዊ መብት፣ ሰማያዊ መብት… ቅብርጥሶ የሚባል ‹‹ግርዶሽ››ም የለውም፤ ወይም አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም ደርግ ‹‹ነፍሴ›› ምንም ይሁን ምን መቀበል እንጂ መቃወም እንደማይቻል በግልፅ ‹‹እኛ ወታደሮች ነን ደማችን ቶሎ ይፈላል›› ብሎሃልና፡፡ እንደአየኸውና እንደሰማኸውም ህዝባዊ መንግስት፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሃይማኖት ነፃነት… ያሉ ሀገር ወዳዶች፣ ሀገር ወዳድ ነን ባሉ ወታደሮች እንደወጡ ቀርተዋል፡፡
ኢህአዴግ ‹‹ነፍሴ›› ጋ ስትመጣ ግን ይኼ የለም፡፡ ሲጀመርም የኢህአዴግ ልጆች ወታደሮች አይደሉም-ታጋዮች ናቸው፡፡ በቃ! ታጋይ ማለት አንተ ስትራብ አብሮ የሚራብ (በእርግጥ አመራሩ ለረሃብተኛ የመጣ ስንዴን፣ ረሃብተኛው እንደቅጠል ቢረግፍም ሸጦ ጠመንጃ ከመግዛት አይመለስም፡፡ ይሄ ግን ሁልጊዜ አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ ነው፣ ሁልጊዜማ ዕርዳታም የለ)፤ ብቻ ታጋይ ማለት ድርጅትን እንጂ መሪውን የማያመልክ፣ የማያንቆለጳጵስ (የዛሬን አያድርገውና) ነው፡፡ የትኛውም ታጋይ በበረሃ ቆይታው ያለውን ችግር ፊት ለፊት ይናገር ነበር፡፡ መለስም ላይ እንኳ ቅሬታ ቢኖረው ‹‹ተጋዳሊ መለስ…›› ብሎ ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ በግምገማ ይተቻቸዋል፡፡ በረከት ስምኦንንም ሆነ አዲሱ ለገሰንም እንዲሁ ታጋዩ እኩል ምክንያት ጠቅሶ ይከራከራል፡፡ ይህ የሆነው ለምን መሰለህ? ታጋዩ እርሻውንም ሆነ ትምህርቱን ትቶ የተሰባሰበው ‹‹የተጨቆኑ ህዝቦች›› አሉ ተብሎ ሲነገረው ‹‹ነፃ ላውጣ›› በሚል ስለሆነ ነው፡፡ በተቀረ ማንንም ጠይቅ ወይም የትግሉን ታሪክ (ሚዛናዊ ሆነው የተፃፉትን) አንብብ ያ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ከቤቱ የወጣው አንተና እኔን ስልት በቀየረ አዲስ ጨቋኝ ለመጨቆን አልነበረም፡፡
የሆነ ሆኖ ኢህአዴግ እና መለስ ወይም መለስ እና ኢህአዴግ የሃይማኖት ነፃነት አውጀዋል አልኩህ እንጂ በሃይማኖት ጣልቃ አይገቡም አላልኩህም፡፡ እንዲህማ ልልህ አልችልም፡፡ እንዴትስ እልሃለሁ? ለምሳሌ እነ መለስ ደርግን አሸንፈው አዲስ አበባ ሲገቡ ከበረሃ ይዘው የመጡት የብሔር ፖለቲካ እና በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን የፌዴራሊዝም ስርዓት ብቻ አይደለም፡፡ ለኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ‹‹ፓትርያርክ››ም ይዘውላቸው ነው የመጡት፡፡ ያውም ዶ/ር ብፁኡ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን፡፡
በእርግጥ እኒህ ብፁኡ አባታችን ‹‹እግዚአብሔር የለም›› በሚለው ደርግ ወደእስር ቤት ተወርውረው ምድራዊ መከራን ተቀብለዋል፤ ሆኖም ይህ ብቻውን ከእምነቱ ቀኖናና ዶግማ (Dogma) ውጭ በሆነ ሁኔታ ‹‹እግዚአብሔርም አላህም ከወዴትም አይደለም፣ ከሰማይም አይደሉም፣ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እንጂ›› በሚለው እምነት የለሹ ኢህአዴግ ፓትርያርክ ሆነው ሊያሾማቸው አይችልም፡፡ ነገር ግን ተሾመዋል-ጊዜው የአሸናፊዎች ነውና፡፡ መቼም የአቡኑ ወደመንበሩ መምጣት ከኢህአዴግ ጋር መያያዙ አከራካሪ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ ማስረጃ የሚፈልግ ዊክሊክስን መጎብኘቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ አዎን! በወቅቱ የኢህአዴግ ሁለተኛ ሰው፣ በዚህ ዘመን ደግሞ ‹‹ፓስተር›› የሆኑት ታምራት ላይኔ ለአሜሪካው አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ ‹‹እኛ ከጫካ አዲስ አበባ ስንገባ በስልጣን ላይ የነበሩት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ከስልጣናቸው እንዲባረሩ የተደረጉት በእኔ ፊርማ ነው›› ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋልና፡፡
በዚህ ብቻ የሚገታ እንዳይመስልህ የአባታችንና የፓርቲያችን ፍቅር፤ ምክንያቱም ‹‹የግንቦት 20 ፍሬ›› የሆኑት አቡነ ጳውሎስ ከእምነቱ ተከታዮች እና ከአንዳንድ ጳጳሳት የሚደርስባቸውን ተቃውሞ ሁሉ እያፈኑ እና እየደፈጠጡ እዚህ የደረሱት በማን ድጋፍ ይመስልሃል? መቼም ‹‹ሚካኤል በሰይፉ ጠብቋቸው ነው›› እንደማትለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሌላው ቢቀር ድህረ ምርጫ 97ን ተከትሎ የተነሳውን ተቃውሞ አስታኮ በ1998 ዓ.ም. የጥምቀት በዓል ሲከበር፤ ሾላ አካባቢ የሚገኘውን የካ ሚካኤል ያጀቡ ምዕመናኖች የዘመሩትን መዝሙር ትረሳዋለህ ብዬ አላስብም፡፡ ምንአልባት ማስታወሱ አስፈላጊ ከሆነም መዝሙሩ ይኸው፡-
‹‹ጳጳሱ ፌዴራል ናቸው
ሚካኤል ፍረድባቸው››
እሺ! እንግዲያስ ብፅዑ ወቅዱስነታቸውን ሚካኤል ካልጠበቃቸው የጠበቃቸው አንድ ሀይል አለ ማለት ነው፡፡ እናም እኔ እልሃለሁ እመነኝ ያ ሀይል የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እንጂ የሌላ የማንም አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰኔ 29 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹በስም›› ከፓትርያርኩም ስልጣን በላይ እንደሆነ የሚነገርለት ‹‹ሲኖዶሱ›› ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጎ ነበር፡፡ የእድል ጉዳይ ሆኖም በዛ ጉባኤ አቡነ ጳውሎስ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሲኖዶሱ ሰምትውት የማያውቁት ብርቱ ተቃውሞ ቀረበባቸው፡፡ በወቅቱም ስለነበረው ሁኔታ አዲስ ነገር ጋዜጣ የሰራውን ዜና እንደወረደ ላቅርብልህ፡-
‹‹ለሳምንታት በውዝገብ ውስጥ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤው ትናንት አርብ ሐምሌ 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ተጠናቀቀ፡፡ ጉባኤው ለዚህ ሳምንት ከተያዙለት አጀንዳዎች ብዙዎቹን አልተመለከታቸውም፡፡ ፓትርያርኩ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ላይ የጣሉትን እገዳ ሲኖዶሱ ማንሳቱ የተገለጠ ሲሆን ፓትርያርኩ ከአስተዳደር ስራ እንደወጡ ቀርቦ የነበረው ሀሳብ ሳይነሳ ቀርቶ ፓትርያርኩ በነበሩበት ሁኔታ ቀጥለዋል›› ይልና የጋዜጣው ዘጋቢ ሶኖዶሱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበትን ምክንያት እንዲህ ሲል ያቀርበዋል፡፡ ‹‹ጉባኤው ሐሙስ ጠዋት ይመለከተዋል ተብሎ የነበረው አጀንዳ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳሙኤልን ጉዳይ ነበር፡፡ ይህን አጀንዳ እያሰላሰሉ ወደየማረፊያቸው ከተበታተኑት ጳጳሳት አምስቱ ግን ሌሊቱን ያሳለፉት እንዳሰቡት አልነበረም፡፡ ረቡዕ ምሽት ከ4፡00 ጀምሮ አምስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ያልጠበቋቸውን እንግዶች ለማስተናገድ መገደዳቸውን ለጳጳሳቱ ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡ በውዝግቡ ሰሞን የሲኖዶሱ ጊዜያዊ ስብሳቢ ሆነው ተመርጠው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ማረፊያ ቤት ባልታወቁ ሰዎች መገንጠሉን የቤተ ክህነቱ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ማንነታቸው ያልታወቁት ሰዎች በአካባቢው በተሰማው ድምፅ ጳጳሱ ወደነበሩበት ውስጠኛ ክፍል ሳይገቡ መሄዳቸውን ብፁዕነታቸው ለፖሊስ በሰጡት ቃል ማረጋገጣቸውንም እነዚሁ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ቤቶች በሮችም መደብደባቸውንና የማስጠንቀቂያ ንግግሮች ከውጭ መሰማታቸውን ለጳጳሳቱ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ባለቤቶቹን ዋቢ በማድረግ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ እና የሥራ አስፈፃሚው አባል የሆኑት ብፁዕ አቡነ መልከፃዴቅ ግን መታወቂያ አሳይተውናል ባሏቸው ሰዎች ከቤታቸው ተወስደው መመለሳቸውን የሲኖዶሱ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡›› ብላለች ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ፡፡
መቼም እነዚያ ዛሬም ድረስ ቢሆን ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በር የገነጠሉት መቋሚያና ፅናፅን ታጥቀው እንዳይመስልህ፡፡ ወይም ሁለቱን ጳጳሳት ‹‹መታወቂያ በማሳየት›› የወሰዷቸው ግለሰቦች ያሳዩአቸው መታወቂያ የቲዎሎጂ (የመንፍሳዊ ኮሌጅ) መታወቂያ ነው የሚል ቀልደኛ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ እናም ደግሜ ደጋግሜ እጠይቃለሁ፡፡ ከዚህ በላይ የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ማለት ምን ማለት ነው? እመነኝ ይህ አይነቱ አሰራር በሁሉም ሃይማኖት የሚተገበር ነው፡፡ …ሌላ ተጨማሪ መረጃ ለማቅረብ ያህል በነገስታቶቹ ይገፋና ይገለል የነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊም ወንድምና እህቶቻችንን ጉዳይ እንየው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ኃይማኖት የግል ነው፤ አገር ግን የጋራ ነው›› ያለው ነጋድራሰ ገብርህይወት ባየከዳኝ እንደነበረ ይነገራል፡፡ አፄ ኃ/ስላሴም ተቀብለው አስተጋቡት፣ ሆኖም በእሳቸው ፀናላቸው፡፡ እኔም እሰልሰዋለው ኢትዮጵያና ሌሎች ነብያት ያላቸውን ትስስር ያህል፣ ኢትዮጵያና ነብዩ መሀመድም አላቸው፡፡ እናም ኢትዮጵያዊ ለመባል በምድሪቷ መወለድ እንጂ የአንድ ሃይማኖት ተከታይነት በፍፁም ቦታ የለውም፡፡ ኢትዮጵያ የማንም አይደለችም-ከኢትዮጵያውያኖች በቀር፡፡ የማንም ወደብም፣ ደሴትም፣ ባህርም አይደለችም፡፡
ለዚህም ነው የአወሊያ ተማሪዎችን ጥያቄ ተከትሎ በርካታ ሙስሊሞች ኢማም፣ ሙአዚን፣ ሙፍቲ፣ ኡላማ፣ ዳኢ፣ ደረሳ፣ ኡስታዝ፣ ሀጂ፣ ሼኽን…. ከቁራን እንጂ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንቀበልም ሲሉ በየጁማው ህብረ-ድምፃቸውን እያሰሙ ያሉት፡፡
የእስልምና እምነት ተከታዮች ጥያቄ ሲጨመቅ እንዲህ የሚል ሆኖ ታገኘዋለህ፡- መጅሊሱ (የእስልምና ጠቅላይ ጉዳዮች ም/ቤት) የሚመሰረተው በሙስሊም ምዕምናን ምርጫ ብቻ ነው፡፡ ወይም ስልጣን ላይ ያለውን መጅሊስ አንፈልገውምና ይውረድ ሊባል የሚችለው በሙስሊሙ እንጂ በዶ/ር ሽፈራው ኃ/ማርያም አሊያም በኩማ ደመቅሳ ፍላጎት አይደለም፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹አህባሽ›› የሚባል የእስልምና አስተምህሮትን ‹‹ተቀበል››፣ ‹‹አልቀበልም›› በሚል በመጅሊሱና በምዕመናኑ መካከል የከረረ ውዝግብ ተፈጥሮ እያየን ነው፡፡ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትርም የአንድ ‹‹ኡላማ››ን ያህል ስለ አህባሽ እስላማዊነት እየሰበኩ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ ለምሳሌ በሐምሌ 2003 ዓ.ም. በሐረር ሐረማያ ካምፓስ በፌዴራል ጉዳዮችና በመጅሊስ ትብብር በተዘጋጀው ‹‹የአህባሽ›› ስልጠና ላይ ዶ/ር ሽፈራው እንዲህ አሉ፡-
‹‹ከመጅሊሱ እውቅና ውጪ የሚፈፀሙ ድርጊቶች ይቁሙ ብላችሁ ያቀረባችሁት አለ፡፡ ሼክ አህመዲን የሚያነሱት እንደተጠበቀ ሆኖ በኛ በኩል ከፍቃድ ውጪ የሚደረግ ትምህርት፣ ዳዕዋ፣ ስብከት፣ ከፈቃድ ውጪ የሚሰሩ መድረሳዎች፣ ከፈቃድ ውጪ የሚሰሩ መስጊዶች፣ ከፈቃድ ውጪ የሚሰሩ ኹጥባዎች ሁሉ መቆም አለባቸው ነው የምንለው››
የተከበሩ ሚኒስትር ለዳዕዋ እና ስብከት ፈቃድ ጠይቁኝ ማለታቸው በእጅጉ አስቂኝ ነው፡፡ መቼም በዚህ አያያዛቸው ሚኒስትሩ መስጊድ ለመሄድም ሆነ ለመስገድ ‹‹ቲን ነበር›› (Tin Number) አውጡ ከማለት የሚመለሱ አይመስሉኝም፡፡ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የብቸኛ ጠቅላይነት ጨዋታ ህግጋትም›› ይሉሃል ይህንን ነው፤ ሌላ አይደለም፡፡
እሺ እንቀጥል፡- የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ወይም የመጅሊሱን አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊነት (መንፈሳዊነቱ እንኳ ለጊዜው ይቆይ) እንመልከት፡፡ ደህና! እስቲ ደግሞ መጅሊሱ በ04/11/03 ‹‹ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር›› የፃፈውን ደብዳቤ እንየው፡፡ ‹‹ጉዳዩ ትብብር ስለመጠየቅ›› ይላል የደብዳቤው ርዕስ፡፡
‹‹የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና የኢ/እ/ጉ/ጠ/ም/ቤት በመተባበር ለጠቅላይ ም/ቤቱ ስራ አስፈፃሚዎችና ለሁሉም ክልሎች እ/ስ/ጉ አስፈፃሚዎች እንዲሁም የሁሉም ስራ አስፈፃሚዎች ከሐምሌ 16/11/03 ጀምሮ በሀረር ካምፓስ በሀረማያ ዩንቨርስቲ ሀገራዊ ስልጠና ይሰጣል፡፡ በዚሁ ስልጠና ሁሉም ስራ አስፈፃሚ ወደተባለው ቦታ ስለሚመጡ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ዞን ያሉትን የእስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት ባዶ ስለሆነ በእናንተ በኩል ለሁሉም ክልሎችና ዞኖዎች መስተዳደሮች የሙስሊሙ መሪዎች ለስልጠና የሄዱ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን የስራ ትብብር፣ ክትትል፣ እንዲሁም ለም/ቤቶቹ ጽ/ቤት አስፈላጊ ጥበቃ እንዲደረግልን መመሪያ እንዲያስተላልፍልን በአክብሮት እንጠይቃለን›› ይላል ደብዳቤው፡፡
ሌላ እንጨምር ዶ/ር ሰሚር የተባሉ ሊባኖስያዊ የአህባሽ ሰባኪ ወደ ኢትዮጵያ አህባሽን ለመስበክ መጥተው ነበር መቼም ዶ/ሩን የጋበዛቸው መጅሊሱ ወይም የአንዱ መስጊድ ኢማም እንዳይመስልህና እንዳትሳሳት፡፡ ምክንያቱም ሰባኪውን የጋበዘው አውራው ፓርቲ ነውና፡፡ ለዚህም ምስክር ይሆን ዘንድ ከዶ/ሩ ንግግር ልጭለፍልህ፡-
“When I was invited by D.r Shiferaw. I took some time to check the situation in Ethiopia before meeting with you… I believe the Ethiopian government Prime Minister Meles Zenawi, Shiferaw The Minister Of Federal Affairs and other Ministers understand the issues very well and they are taking the proper and wise steps. I thank all of them for their hospitality”
(በዶ/ር ሽፈራው ተጋብዤ ከመጣው በኋላ ከእናንተ ጋር ከመገናኘቴ በፊት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለማወቅ ሞክሬአለሁ… የኢትየጵያ መንግስት፣ ጠቅላይ ሚስትር መለስ፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚንስትሩ ዶ/ር ሽፍራው እና ሌሎችም ሚንስትሮች ጉዳዩን በደንብ ተረድተውታል ብዬ አስባለሁ፡፡ መደበኛና ትክክለኛውን መንገድም መርጠው ስለተደረገልኝ አቀባበልም አመሰግናቸዋለሁ)
ይህንን ነው እያልኩህ ያለሁት፡፡ ‹‹ወላጇ እያለች አዋላጇ አማጠች›› እንዲሉ ከኢማሙ፣ ከመአዚኑ፣ ከሙፍቲው… ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ክቡራን ሚኒስትሮቻቸው ‹‹አስፈላጊ ነው፤ አምነንበታል፣ ወደነዋል…›› የሚሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ እናም አልገባህም እንጂ የፖለቲካ መሪዎች መንፈሳዊ መሪዎችህም ነን እያሉህ ይገኛሉ፡፡
ሌላው ሐምሌ 12/2000 በታተመችው ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ ላይ የተዘገበው ዜና እንደሚያትተው ደግሞ አቶ ማህቡብ መሀመድ የመጅሊሱ ዋና ፀሐፊ የነበሩትን ሐጂ የሱፍን ተክተው ለሶስት ቀን ከሰሩ በኋላ በሶስተኛው ቀን ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ በም/ፕሬዘዳንቱ ፊርማ መገደዳቸውን ተከትሎ ምክንያቱን ሲጠይቁ ‹‹መንግስት የፀሐፊነቱ ቦታ ለምን ተለወጠ ብሎ ስለጠየቀ ነው የሚል መልስ ሰጥተውኛል፡፡ እኔም መንግስትን እጠይቃለሁ›› አሉ ይላል፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ የሃይማኖት ነፃነት፤ በህገ-መንግስቱ ‹‹አንቀፅ 15 ንዑስ አንቀጽ 1 መንግስትና ሀይማኖት የተለያዩ ናቸው፣ 2.መንግስታዊ ሀይማኖት አይኖርም 3.መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሀይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም›› የሚለው ድንጋጌ ትዝ ሲል ነው ህገ-መንግስቱ የኢህአዴግ መቀለጃ ወይም መሸወጂያ የሚሆንብን፡፡ መንግስታዊ ሀይማኖት የለም የሚባለውንም እርሳው! የመጅሊሱም ሆነ የሲኖዶሱ መሪዎች ቅርበታቸው ለሰማያዊው መንግስት አይደለም፤ ለምድራዊው የኢህአዴግ መንግስት እንጂ፡፡
መቼም በስልጣን ላይ ያለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጣልቃ ገብነት ከዚህ እስከዚህ ሊባል ስለማይችል አንድ ሁለት ማሳያዎችን ልጥቀስ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- በያዝነው አመት በመስከረም ወር በኮተቤ ኢትዮ-ቻይና ቴክኒክና ሙያ ካምፓስ የጀግናው ኢህአዴግ ካድሬዎች የእስላማዊ ሀይማኖታዊ ስልጠና እየሰጡ ነው፤ ቁርአንን ግን መሰረት አድርገው መስሎህ እንዳትስት፡፡ ምክንያቱም የስብከቱ መሰረት የፓርቲያቸው ፕሮግራምና የያዙት ስልጣን ነው፡፡ እናም ከአሰልጣኞቹ አንዱ የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ ጸጋዬ ኃ/ማርያም እንዲህ አሉ ‹‹…ቅንጅትና ኢህአዴግ አንድ ላይ ሊደራደሩ ይችላሉ?›› ጠየቁ፤ ተሳታፊዎቹም ‹‹አይችሉም›› ሲሉ በቡድን መለሱላቸው፡፡ ሀላፊውም ይበልጥ ቆፍጠን፣ ኮስተር ብለው ቀጠሉ ‹‹አዎ! እንደዚሁም ወሀቢያ እና ሱኒ አንድ ላይ ሊሆኑ አይችሉም!›› አሉናም የኢህአዴግን ‹‹በመቃብሬ ላይ ካልሆነ ድርድር የለም›› ፖለቲካን ደገሙት እልሃለሁ፡፡
መጋቢት 2003 ከታተመችው ቁጥር 10 ‹‹የሙስሊሞች ጉዳይ›› መጽሔት ደግሞ ማጣቀሻ እንውሰድ፡፡ ማጣቀሻውም ስለመንግስት ጣልቃ ገብነት የገለፀችበት ዘገባ እንዲህ ይላል፡-
‹‹በ1994 በኦሮሚያ ክልል በህዝቡ ምርጫ ወደ መጅሊስ አመራርነት የመጡ ባለስልጣናት ‹ደረሰብን› ባሉት በደል ምክንያት ለወቅቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ዳዊት ዮሐንስና ለኦህዴድ ዋና ፀሐፊ አቶ አባዱላ ገመዳ በጻፉት ደብዳቤ መንግስት ድንጋጌ በመጣስ የመንግስት ሹመኞች በህገ-ወጥ መንገድ ከስራ አግደውን በምትካችን ህዝብ የሚያውቃቸውን ወንጀለኞች ሾሙብን፡፡››
ይህ ነው እንግዲህ ከደርግ ‹‹ፈጣሪ የለም››ነት ወደኢህአዴግ ‹‹ልማታዊ ፈጣሪን›› ማምለክ የተደረገው ሽግግር፡፡ እናም የሸገር ልጆች እንዲህ ሲሉ ይነግሩሃል፡- ‹‹ኢህአዴግን እንደግል አዳኝ ከተቀበልክ ስራ ይሰጥሃል፣ የትምህርት እድል ይመቻችልሀል፣ ብድር ይፈቀድልሃል፣ የኮንደምንየም ተጠቃሚ ያደርግሃል የእምነትህን መሪም ከካድሬው መሀል ይቀርብልሀል፣ ልክ እንደ ፖሊሲ ፀሎትና የፀሎት ስርዓትንም ይቀርፁልሃል›› ይሉሃል፡፡
መንፈሳዊ ክንፍ ለምን?
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከዛሬ 20 አመት በፊት ጀምሮ ወሳኞች ‹‹ጥቂቶች ቆራጦች›› የህወሓት አመራሮች ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የህወሓት ሊቀመንበር ብቸኛው ወሳኝ ሰው ሆነዋል፡፡ በእርግጥ ይህ ማለት ሌሎች አስፈፃሚዎች ከጎናቸው የሉም እንደማለት አይደለም፡፡ እንዲህማ ሊባል አይችልም፤ ምክንያቱም የተለያዩ አጋዥ ክንፍ አላቸውና፡፡ ለምሳሌ ብአዴን አንዱ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክንፍ ነው፣ ኦህዴድ ሌላኛው ኦሮሞ ተናጋሪ ክንፍ ነው፣ የደቡብም፣ የሀረርም፣ የአፋርም…. ክንፍ አለ፡፡ ሆኖም ይሄ ብቻውን በቂ አይደለምና ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ››ም አስፈለገ፡፡ እናም ብልሆቹ የህወሓት አለቆች የኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ክንፍ፣ የእስልምና መንፈሳዊ ክንፍ፣ የፕሮቴስታንት መንፈሳዊ ክንፍ…እያሉ እሳት የላሱ ካድሬዎችን ፓትርያሪክ፣ ኢማም፣ ፓስተር… ሲሉም መደቧቸው፡፡
እናም እነዚህ መንፈሳዊ ክንፎች ለ‹‹ሰውየው›› የማያልቅ አብዮታዊ ምስጋና፣ የማያልቅ አብዮታዊ ፀሎት ማቅረብ እንዳለባቸው የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ሰርክ በተግባራቸው በመጠመዳቸው ከአማኞቻቸው ጋር አይናና ናጫ የሆኑት፡፡ ሆኖም እነሱ ፓርቲው የሚደሰትበትን ሲሹ አያንቀላፉም፡፡ ለምሳሌ ቢዮንሴን የተባለች አዝማሪ የሚሊንየሙ እንግዳ ሆነ በመጣች ጊዜ ፓትርያርኩ በተገኙበት መንፈሳዊ ምስጋና የሆነው ‹‹ወረብ›› ቀርቦላታል፡፡ እንደሚታወቀው ቢዮንሴ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ለቁልቢ ገብርኤል ንግስ አይደለም፤ ለዳንኪራ እንጂ፡፡ ብፁነታቸው ግን ምን እንዳደረጉ ያየነው ነው፡፡
ወደእስልምናም ፊትህን መልስ፣ ‹‹ሀይማኖታችንን ለእኛ ተዉልን፤ በእምነታችን፣ በስራአተ-አምልኮአችን፣ በቅዱስ ቁርአናችን ጣልቃ አትግቡ›› ያሉ ሙስሊሞች ‹‹አሸባሪ፣ አክራሪ፣ ተላላኪ፣ ፅንፈኛ…›› እየተባሉ ይፍረጃሉ፡፡ ለሌላ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊ ወንድማቸውም ስጋት እንደሆኑ ከአለም አቀፍ አሸባሪ ድርጅቶች ጋር እያቆራኙ ያስፈራሯቸዋል፡፡ ለዚህ አይነቱ ጥቃት ሙስሊሙን በዋናነት የሚያመቻቹት የኢህአዴግ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› መሪዎች ናቸው፡፡ መቼም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም፣ ለኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ስጋት ነው የሚሉት ጨዋታ የምትመች አይደለችም፡፡ አሸባሪነትም ከእስልምና ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ እስልምና ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደገባ ማስታወሱ በራሱ ለዚህ በቂ መልስ ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው የእስልምና እምነት ከሳውዲአረቢያ በተነሳ ጊዜ ወደ ሰሜን አፍሪካ ሲስፋፋ ‹‹እስልምና›› ብቻ አይደለም የተስፋፋው፣ የአረብ ባህልም ነው፡፡ Banu-hilal እና Banu Suliman የተባሉ የአረብ ጎሳዎች ወደ ሰሜን አፍሪካ ሲስፋፉ እስልምናን ብቻ ይዘው ሳይሆን አረባዊ ባህላቸውንም ጨምረው ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ግን ቅዱስ ቁርአኑ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን አይሁድ እንዳልሆነው ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊ ሙስሊምም አረብ አይደለም፡፡ እናም ኢትዮጰያውያን ሙስሊሞችን ‹‹አሸባሪ›› እያሉ ማሸማቀቁ ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ…›› ካልሆነ በቀር ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡
በእርግጥ ኢህአዴግ የራሱን ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› ማደራጀቱ ከፓርቲው የጠቅላይነት ባህሪ ስንነሳ የሚጠበቅ ነው፡፡ በአናቱም የማኬያቪሌ ምክር አለ፣ ከፋፍለ ግዛ (Divided and Rule) በዚህ ቀመር መሰረትም እስልምናን ለክርስትና፤ ክርስትናን ለእስልምና ስጋት አድርጎ ማቅረብ አንዱ አስተምህሮት ነው፡፡ እናም እኔ እልሃለሁ ‹‹ይሄ ቀመር ተባኖበታል››
እ.ኤ.አ. በ1962ዓ.ም የታተመው የGeorge Lipsky “Ethiopia its people its society its culture” በሚለው መጽሐፉ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1945 ዓ.ም. እንዲህ ማለታቸውን ጠቅሷል “The church is like sward, the government is like an arm-therefore the sward can not cut by it self with out the use of the arm” (ሃይማኖት ሠይፍ ነው፤ መንግስት እጅ ነው፡፡ ሠይፍ ደግሞ ያለእጅ አይቆርጥም)
ከዚህ ሁሉ ውጥንቅት መውጫ መንገዱ አንድ እና አንድ ነው፡፡ እጅግ ብዙ ጊዜ ደጋግሜ እንደምለው ቢያንስ ህገ-መንግስቱ ከተፃፈበት ቀለም በላይ ዋጋ ይኑረው፡፡ ኢህአዴግ ከመንፈሳዊ ተቋማቱ ላይ እጁን ይሰብስብ፣ ቢያንስ የተጠቀሰውን አንቀፅ ያክብር፡፡ አዎን! ኃ/ስላሴ ተሳስተዋል፡፡ ሃይማኖት ሰይፍ፣ መንግስትም ሃይማኖታዊ ሰይፍ ሰንዛሪ እጅ ሊኖረው አይገባም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲም ስሁት ነው እላለሁ፡፡ ምዕመናንን ለነፃ የእምነት ፍቃዶቻቸው አልተዋቸውምና፡፡
ኢህአዴግ መጅሊስን እና ሲኖዶሱን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጥመቂያ መድረክ ማድረጉን ይገታ ዘንድ ምዕመናኑም በርትተው ይተጉ ዘንድ እጣራለሁ፡፡ በኑሮ ውድነት እና በአፋኝ አገዛዝ የምትሰቃዩት አንሶ ከአላህ እና ከእግዚአብሔር ጋር ያላችሁን ሰማያዊ ግንኙነት የፓርቲው ካድሬዎች ሲወስኑባችሁ ካለፍርሃት እምቢ በሉ፡፡ ‹‹ነፍስን እንጂ ስጋን የሚገሉትን አትፍሩ›› እንዲል የአንደኛው ሃይማኖት መጽሐፍ፡፡ ኢህአዴጋውያንም ተጠንቀቁ፤ ‹‹የመጅሊስ ይጠረጋል›› ንቅናቄ እናንተ ወደምትፈሩት የአረቡ ዓለም መሰል አብዮት ስላለመቀየሩ ማን እርግጠኛ መሆን ይችላል? ሰዓቱ እየቆጠረ ነው! እናም ‹‹ሙስሊም የኢህአደግ አባላት፣ ክርስቲያን የኢህአዴግ አባላት፣ ኢ-አማኝ የኢህአዴግ አባለት ተሰብሰቡ፣ ተሰለፉ፣ ተበተኑ›› የሚለው ፖለቲካ ከ‹‹መአቱ›› አያድንም፤ አዎን! አያድንም፡፡

No comments:
Post a Comment