Thursday, December 6, 2012

ባለ 27 ቁጥር ጁመዓ


ባለ 27 ቁጥር ጁመዓ

አገራችን ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሰው ልጆች መብቶችን ለማስጠበቅ የሚያግዝ ሕገ መንግስት ማጽደቋ ይታወሳል፡፡ ይህ ሕገ መንግስት ከጸደቀ እነሆ በመጪው ቅዳሜ ኅዳር 29 18ኛ ዓመቱን ይደፍናል፡፡ ይህ ሕገ መንግስት በውስጡ የሰብዓዊ መብቶችን ጨምሮ በርካታ ውብ አናቅጽትን በውስጡ አቅፏል፡፡ እነዚህ ውብ አንቀጾችን ከወረቀት ላይ በዘለለ ግን በተግባር ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡ ከእነዚህ የሕገ መንግስት ውብ አንቀጾቸ አንዱ አነቀጽ 27 በዋነኝነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ አንቀጽ 27 እንዲሕ ይላል፡፡
አንቀጽ 27 የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት
1. ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡
2. በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 2 የተጠቀሰው አንደተጠበቀ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችሏቸው የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም ይችላሉ፡፡
3. ማንኛውንም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነጻነት በኃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይቻልም፡፡
4. ወላጆችና ሕጋዊ ሞግዚቶች በእምነታቸው መሰረት የሃይማኖታቸውንና የመልካም ሥነ ምግባር ትምህርት በመስጠት ልጆቻቸውን የማሳደግ መብት አላቸው፡፡
5. ሃይማኖትና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብን ደህንነት፣ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜችን መሰረታዊ መብቶች፣ ነጻነቶች እና መንግስት ከሃይማኖት ነጻ መሆኑን ለማረጋረገጥ በሚወጡ ሕጐች ይሆናል፡፡

አሁን በዚህ ዘመን እነዚህን አንቀጾች ያነበበ ሰው አነቀጾቹ በኢትዮጵያ ምድር ያሉት ወረቀት ላይ ብቻ እንጂ በተግባር ላይ አለመሆኑን ይገነዘባል፡፡ በተለይ ሙስሊም የሆነ ሰው ሁሉ ይህ ሕገ መንግስታዊ አንቀጽ ባለበት አገር የእምነት ነጻነት፣ በሃይማኖት የመደራጀት፣ በነጻነት የእምነት ሕግጋትን መፈጸም ወዘተ ያሉ ተግባራት በይፋ እየተጣሱ ነው፡፡ በአጠቃላይ አሁን ባለው የመንግስት ፖሊሲ እና አስፈጻሚ አካላት አማካኝነት ሙስሊም መሆን ወንጀል እየሆነ ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሙስሊም በመሆናችን ብቻ በመንግስት አካላት እንሰለላለን፣ እንሰደባለን፣ እንደበደባለን፣ ከቀያች ን እንፈናቀላለን ከዚህም ከፍቶ እየተገደልንም ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያት ሕገ መንግስቱን መንግስት ለማክበር ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው፡፡

እኛ ሕገ መንግስቱ 18ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ዋዜማ በይፋ ሕገ ምንግስቱ መጣሱን ከሚያሳዩ አንቀጾች አንኳር የሆነውን 27 ቁጥር ይዘን አደባባይ እንውላለን፡፡ ነገ ጁምዓ ኅዳር 28 ይህ አንቀጽ 27 በተግባር ይታይ፤ ያለቅድመ ሁኔታም ይከበር ስንል ጁመዓ በመቶ ሺዎች ሆነን በአንዋር መስጂድ ከባድ ተቃውሞ እናሰማለን፡፡ ተቃውሞው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ጠንካራና ሰፊ ህዝብ የሚሳተፍበት እንዲሆንም ተወስኗል፡፡ የተቃውሞአችን አርማ 27 ቁጥር ነው፡፡ ለዚህ እንዲረዳም በክልልም ሆነ በአዲስ አበባ የምንገኝ ሙስሊሞች 27 ቁጥርን በተለያየ አይነት ነገር ላይ በማስፈር፣ በምልክት በመግለጽ፣ በቅርጽ በማዘጋጀት፣ ወረቀት፣ ላስቲክ ፊኛ እና የመሳሰሉ ነገሮች ላይ በመጻፍ አንቀጽ 27ን መንግስት እንዲያከብር እንጠይቃለን፡፡ በዚህ እለትም ድምጻችንን ማሰማታችን ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ከግዝባቤ በማስገባት ተቃውሞአችንን ከፍ አድርገን እናሰማለን፡፡

-ተቃውሞ የሚጀምረው ልክ የጁምዓ ሰላት እንደተጠናቀቀ ሲሆን ዝርዝር ተቃውሞውም ይህን ይመስላል፡፡
1.እጅ ለእጅ በመያያዝ ለ5 ደቂቃ ተክቢራ!! እናሰማለን ከመሪዎቻችን ጋር የተጋባነውን ቃል ኪዳን በማስታወስ፡፡

ቀጥሎም ሁላችንም ባለንበት ሆነን በጽሑፍ ወይም በሌላ መልኩ የተዘጋጀ 27 ቁጥር እያውለበለብን ተከታዮቹን እንላለን

2.ለ5 ደቂቃ ‹‹ሕጉ ይከበር›› በማለት የአነቀጽ 27 ብሎም በጥቅሉ የህገ መንግስቱን መጣስ አስረግጠን አንገልጻለን፡፡

3.ለ5 ደቂቃ ‹‹ምርጫው ሕገ ወጥ›› በማለት በቅርቡ የተካሄደውን ሕገ ወጥ ምርጫ እንደማንቀበል በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡

4. ለ5 ደቂቃ ‹‹ኮሚቴው-ይፈታ›› በማለት ህጉ ተጥሶ መሪዎቻችን መታሰራቸውን በመቃወም መፈክራችንን እናሰማለን፡፡

ማሳሰቢያ
ምንም ዓይነት ትንኮሳ ቢኖር የተለመደውን ጥንቃቄ በማድረግ በሰላም ወደየመጣንበት መመለስ የተለመደ ኃላፊነታችን ነው፡፡

ይህ ተቃውሞ በመዲናችን ታላቁ አንዋር መስጂድ የሚከናወን እንደሚሆን ሁሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ላይ ባሉ ዋና ዋና መሳጂዶች ላይ እንዲደረግም ተወስኗል፡፡ በመሆኑም ጁመዓ በሀገር አቀፍ ደረጃ ድምጻችንን ከፍ አድርገን የምናሰማበት የተቃውሞ ቀን ነው፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ላይ ያሉ የመሳጂድ ጀመዓዎችና ሁላችንም ተቃውሞው በታቀደው መሰረት እንዲከናወን በበራሪ ወረቀቶች፣ በሜሴጅና በመሰል ዘዴዎች በመጠቀም ላልሰሙ ሁሉ የማሰማት ሀላፊነታችንን እንወጣ፡፡

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment