Thursday, December 6, 2012

  • የመሪዎቻችንን ጠበቆች መቃወሚያ፤ ሁሉም ሊያነበው የሚገባ፡፡

    ከሰሞኑ እንደተገለጸው የታሳሪ ወንድሞቻችን ጠበቆች ‹‹ደንበኞቻችን የታሰሩት በሕግ ወጥ መንገድ በመሆኑ ፍ/ቤቱ በነጻ ያሰናብታቸው›› ብለው መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ ጠበቆቹ ለዚህ መቃወሚያቸው መሰረታዊ መሟገቻ ነጥቦችን ከሕገ መንግስቱና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አቅርበዋል፡፡ በጣም በሚያስደንቅ መልኩ የመሪዎቻችን ጠበቆች በኢትዮጵያ ታሪክ እስከአሁን ያልተሞከረና ያልተደፈረ መንገድ በመምረጥም ጭምር ነው መከራከሪያቸውን ያቀረቡት፡፡ እንደሚታወቀው መሪዎቻችን በዋነኝነት ክስ የተመሰረተባቸውና በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት ከተያዙበት እለት ጀምሮ የተፈጸመባቸው በ2001 መጨረሻ በጸደቀው አዲሱ የጸረ ሽብር ሕግ በመመርኮዝ ነው፡፡ ይህን ሕግ መንግስት በርካታ ንጹሐንን በአሸባሪነት በማስፈረጅ ፖለቲካዊ ዓለማውን እያስፈጸመበት ይገኛል፡፡ ይህ ሕግ በትክክልም ሕገ መንግስታዊ ቢሆን ኖሮ ብዙም ባላስከፋ ሆኖም ከሕገ መንግስቱ መርህ ያፈነገጠ ነው፡፡
    ይህ ብቻ አይደለም የጸረ ሽብር ሕጉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተባበሩት መንግስታት ውስጥ የታቀፉ አገራት አምነውባቸው የፈረሟቸው የሰብአዊ መብቶችና መሰረታዊ ድንጋጌዎችና ስምምነቶችን የጣሰም ጭምር ነው፡፡ የመሪዎቻችን ጠበቆችም ይህ ሕግ እንኳን ደንበኞቻችን ሊከሰሱበት እራሱም ከሕገ መንግስቱ ያፈነገጡ ደንጋጌዎችን ያቀፈ በመሆኑ ሕጉ ሊመረመር ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በመቃወሚያቸው ላይም መሰረታዊ የሕጉን ስህተቶች ነቅሰው በማውጣት ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ የጠበቆቹ መከራከሪያዎች ግን እነዚህ ብቻ አልነበሩም፡፡ ሌሎችም በርካታ መሟገቻ ነጥቦችን በማቅረብ ኮሚቴዎቻችን በነጻ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

    የመሪዎቻችን ከሳሽ አቃቤያን ሕግ መቃወሚያው በቀረበበት እለት ከፍተኛ መደናገጥ ፊታቸው ላይ ይነበብ እንደነበር በስፋት ተገልጿል፡፡ ባለፈው ሳምንት ምላሹን ሲያቀርብም የተስተዋለው ይኸው ስሜት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ምላሾቹ በግዴለሽነት የተሞሉትና ሕጋዊ መሰረት በሌላቸው ሰበብ አስባቦች መቃወሚያውን ውድቅ ለማስደረግ ጥረት ሲያደርግ የነበረው፡፡ በዚህ ጉዳይ የበለጠ ማብብራሪያ የሚሰጥ ጽሑፍ በቅርቡ የሚወጣ መሆኑን እያስታወስን ዛሬ ይሄንን የመሪዎቻችንን ጠበቆች ሁለት መቃወሚያዎች በአንድ ላይ አጣምረን አቅርበንላቹሀል፡፡ በነገው ቀጠሮም ፍ/ቤቱ ይህንን መቃወሚያ ተቀብሎታል አልተቀበለውም በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን ጽሑፍ ማንበብ በፍርድ ሂደቱ ላይ መሰረታዊ ግንዛቤ እንዲኖረን የሚረዳ በመሆኑ ሁላችንም ጊዜ ሰጥተን ልናነበው የሚገባ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡

    አላሁ አክበር!

    አንደኛው መቃወሚያ
    ቀን 13/03/2005
    በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የመ.ቁ 124754
    ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት
    አዲስ አበባ
    ከሳሽ……….. የፌደራል ዐቃቤ ሕግ
    ተከሳሽ…….. እነ አቡበከር አህመድ (31 ሰዎች)

    በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 130 መሠረት በአ/ህ ክስ ከ1ኛ -27ኛ እና ከ29ኛ እስከ 31ኛ ተራቁጥር ላይ ላሉት የቀረበ የክስ መቃወሚያ
    አቃቤ ህግ በ15/02/05 ጽፈው ባቀረቡት ክስ 1ኛ) ክስ በሚል የወንጀል ህጉን አንቀፅ 32(1)(ሀ)(ለ)፣ 38(1) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)(2)(4)(6) እና 4 ስር የተቀመጠውን እንዲሁም 2ኛ) ክስ በ1996 የወንጀል ክስ አንቀጽ 27/1፡32/1/ሀ/ለ፣ 38/1 እና በአንቀጽ 238/1/ሀ እና ለ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ ሙከራ ወንጀል ክስ መስርቷል፡፡ በመጨረሻም በ3ኛ ክስና 4ኛ ክሶች በ1996 የወ/ህግ አንቀጽ 34/1 እና በጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5 /መ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ለሽብርተኝነት ድጋፍ መስጠት በሚል ወንጀል 30ኛና 31ኛ ተከሳሾች ላይ ክስ አቅርቧል፡፡ የተከሳሾች ጠበቆች በሁሉመ ክስ ላይ ከ28ኛ ተከሳሽ በስተቀር ላሉ ሁሉንም ተከሳሾች በሚመለከት በ1ኛ እና 2ኛ ክሶች ላይ ያለንን የክስ መቃወሚያ እናቀርባለን፡-

    1. ተከሳሾች በአንቀጽ 3 እና 4 በአንድ ላይ ሊከሰሱ አይገባም
    ዓ/ሕግ በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ክስ ስንመለከት ተከሳሾች በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 (1/2/4/6) እና በአንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ክስ ያቀረበ ሲሆን ክሱ በዚህ አቀራረብ በመመስረቱ ጉልህ የስነ-ስርዓት ግድፈት መፈፀሟል:: የወንጀል ህግ አጠቃላይ መርሆችንም ይጥሳል::

    ለምሳሌ አንድ ሰው ሌላውን በዱላ ደብድቦ ቢገድለው ገዳዩ በግድያው ወንጀል ከሚጠየቅ በስተቀር ከግድያ በፊት በሟች ላይ በፈፀማቸው የስድብ፣የዛቻ፣የአካል ጉዳት ማድረስ፣ የግድያ ሙከራ ድርጊቶች ሁሉ ነጣጥሎ በተለያዩ ህጎች እንደመክሰስ የሚቆጠር ነው::

    ስለዚህ ተከሳሾች ፈፅመውታል በተባሉት የሽብርተኝነት ድርጊቶችና እነዚህኑ ድርጊቶች እንደገና ለመፈፀም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሴር፣ በማነሳሳት እና በመሞከር በአንድ ነጠላ ክስ በሁለት የተለያዩ የወንጀል ድንጋጌዎች ስር መክስሱ የወጀል ዝርዝር ብሎ ያቀረባቸው ድርጊቶች እንደሚያሳዩት፤ አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ በህጉ አግባብ ተገቢውን እና ትክክለኛውን የወንጀል ክስ ለማቅረብ የሚያስችል ምንም አይነት የክስ ምክንያት እንደሌለው ነው::

    በአዋጁ አንቀê 3 ስር ክስ የሚቀርበው ፍጻሜ ላገኘ የሽብርተኛ ድርጊቶች ብቻ ሲሆን በአንቀጽ 4 ስር ግን ፍፃሜ ላላገኙና ከሽብርተኝነት ጋር ተያያዥ ለሆኑ እንደ ከሽብርተኝነት ጋር ተያያዥ ለሆኑ እንደ ሙከራና ማሴር ለመሳሰሉ ሌሎች ወንጀሎች ነው:: ከክሱ ዝርዝር መረዳት እንደሚቻለው ተከሳሾች ከአንቀጽ 3 /1/2/4/6/ የተገለጹትን የሽብር ድርጊቶች እንዲፈጸሙም ህዝብን በመቀስቀስና በማነሳሳት ረብሻ አስነስተዋል የሚል ነው፡፡ በክሱ አቀራረብ በሰውና በንብረት ላይ ደረሱ የተባሉት ጉዳቶች በሌላ አነጋገር ተፈጸሙ የተባሉት የኃይል ተግባራት ከተከሳሾች ውጭ በሆኑ ሌሎች ሰዎች እንደተፈጸመ ያሳያል፡፡ ስለዚህ የጸረ ሽብር ህጉ አንቀጽ 3 በቀጥታ እራሱ የተዘረዘሩትን ሽብር ተግባራት በፈጸመ ሰው ላይ የሚጠቀስ አንቀጽ ስለሆነ በጸረ ሽብር ህጉ አንቀጽ 3 መሰረት የሚከሰሱበት የህግ አግባብ የለም እንዲባልልን እንጠይቃለን፡፡

    በአቃቤ ህግ የቀረበው ክስ የፀረ ሽብር ህጉን አንቀጽ 3 እና 4 ያላግባብ በማጣመር የቀረበ ክስ ቢሆንም፤ አንቀጾቹ ግን በፍጹም አንዱ ባለበት ሌላው ሊኖር የማይችል (Mutually Exculsive) እና በአንዱ የተከሰሰ ሰው በምንም አይነት የህግ አግባብ በሌላው ሊከሰስ የማይገባ ናቸው :: የአቃቤ ህግ የክስ አቀራረብ በአንዱ መክሰስ ባይሳካ በሌላው ይሳካ ይሆና በሚል የተሳሳተ ግምት በግልጽ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ሥነስርአትን፣ የወንጀል ህግ መርህን እና ህገመንግስትን የሚጥስና ክሱም ከህግ ውጪ የቀረበ ስለሆነ፤ ክቡር ፍርድ ቤት ክሱ በህጉ መሠረት የቀረበ አይደለም በማለት ተሰግቶ ተከሳሾችን በነጻ እንዲያሳናብት እንጠይቃለን፡፡

    2. ክሱ በአንድ የወንጀል ተግባር አንድ ቅጣት ብቻ የሚለውን የህገመንግስት እና የወንጀል ህግ መርህን የሚጥስ ስለመሆኑ

    የወንጀል ህግን አጠቃላይ መርህ በሚያብራራው የወንጀል ህግ አንቀጽ 61 መሰረት ለአንድ የወንጀል ተግባር አንድ ክስ እና አንድ ቅጣት ብቻ መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ አቃቤ ህግ ግን የቀረበው የወንጀል ክስ ይዘቱና ዝርዝሩ ተመሳሳይ ሆኖ እያለ በተመሳሳይ ጉዳይ ወይም በአንዱ የወንጀል ድንጋጌ ሊጠቃለል የሚገባውን ድርጊት በሁለት የተለያዩ ህጎች ክስ አቅርቧል::

    1ኛው ክስ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)(2)(4)(6) በመተላለፍ እና 2ኛው ክስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27/1/32/1/ሀ/ለ እና 38/1/፣238/1/ሀ/ በመተላለፍ በሚሉ ናቸው፡፡ አቃቤ ህግ ለአንድ ተግባር ሁለት የወንጀል ክስ ማቅረቡ የተከሳሾች ድርጊት በአንዱ የወንጀል ህግ ላይ ባይወድቅ በሌላኛው ላይ ይወድቃል በሚል አማራጭ የሚመስል የክስ አቀራረብ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የክስ አቀራረብ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በህጉ አግባብም አይደለም፡፡ ስለዚህ የአቃቤ ህግ የክሱ አቀራረብ የህገመንግስቱን፣የወንጀል ህግን እና የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነስርዓቱን የክስ አቀራረብ የሚጥስ ስለሆነ ውድቅ ይደረግልን::

    በዚህ ተራ ቁጥር ከላይ ያቀረብናቸው መከራከሪያዎች በህጋዊ ምክንያ ከታለፉ በአንድ የወንጀል ድርጊት ሁለት ተመሳሳይ ክሶች ሊቀርቡ ስለማይገባ አንደኛው ክስ ይሰረዝልን::

    3. የክስ አቀራረቡ የወንጀል ህግ አንቀጽ 23/2/ን የማያሟላ ስለመሆኑ
    በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 መሰረት ወንጀል ተፈጽሟል የሚባለው ሕገወጥነቱ ወይም አስቀጭነቱ በሕግ የተደነገገ ድርጊት ሲፈጸም ነው፡፡ ዐ/ሕግ በክሱ የገለጻቸውና ከሳሾች ተናገሯቸው ተብለው የተቀመጡትም አብዛኞቹ ሀይማኖታዊ ትርጉም ያላቸው እና በህግ ወንጀል ተብለው ያልተገለጹ ናቸው:: በአቃቤ ህግ ክስ እንደ ወንጀል ድርጊት እንደወንጀል ከቀረቡት ለምሳሌ ‹‹ቢላል የሚተው ለእምነቱ ነው››፤ የሌላ አስተምህሮ ኢማም የሚያስተምራችሁን አስተምህሮ እንዳትቀበሉ”፤ “የመቱ ሙስሊሞች ፀጥ ብለው አክራሪ ያልሆኑ ስልጠና መከታተላቸው ትክክል አይደልም” የመሳሰሉት ንግግሮች በአቃቤ ህግ ክስ ውስጥ እንደወንጀል ድርጊት በመቁጠር በየቦታው የተበተኑ ቢሆንም፤ ተከሳሾቹ ንግግሮቹን አድርገዋል ቢባል እንኳን በህግም በማንኛውም መስፈርት እንደ ወንጀል ድጊት ተቆጥረው ክስ ሊቀርብባቸው አይገባም:: በክሱ የተጠቀሱት ግዙፋዊ ፍሬ ነገሮች በራሳቸው የሽብር ህጉን የወንጀል ድንጋጌ አያቋቁሙም፡፡

    በሌላ በኩል በሽብር ተጠርጥሮ እስር ቤት ላይ ላለ ግለሰብ ቤተሰቦች እርዳታ መስጠት በሚል የቀረበው የክስ አገላለጽ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 20/3/ ማንኛውም ሰው በህግ አግባብ ጥፋተኛ ካልተባለ ንጹህ ሆኖ መገመት መብትን የሚጥስ ነው፡፡ ስለዚህ ተከሳሾች ፈጸሙ የተባለው ድርጊት ታላቅ የሞራል ልእልናን የሚያመላክት፣ የሚያስመሰግን የሰብአዊነት ተግባር እንጂ በህግ ሊያጠይቅ የሚችል አይደለም፡፡

    በህግ አንድ ወንጀል ተፈጽሟል የሚባለው ወንጀሉን የሚያቋቁሙ ህጋዊ፣ ግዙፋዊና ሞራላዊ ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎች በሕጋዊ መልኩ ተሰብስቦ የእምነት ነጻነቱን እና መብቱን የሚጠይቀው ህዝብ በሰጣቸው ህጋዊ ውክልና በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን ማቅረብ ነው:: በሰላማዊ ህጋዊ መንገድ መብትን መጠየቅና በውክልና የህዝብን ጥያቄ ማቅረብ በወንጀል ህጉም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ህጎች ሕገወጥነቱና አስቀጭነቱ አልተደነገገም፡፡ ስለዚህም ወንጀል ተብሎ ሊቀርብ አይችልም፡፡

    አንድ የወንጀል ተግባር ተፈጽሟል ተብሎ በቀረበ ክስ ላይ የወንጀል ፍሬ ነገሮች አልተሟሉም በሚል ተከሳሽ መቃወሚያ ካቀረበ ፍ/ቤቱ በዚህ ረገድ የቀረበለት መቃወሚያ ላይ ምመራ አድርጎ ብይን መስጠት እንዳለበት በሁሉም ፍርድ ቤቶች አስገዳጅ ቅቡልነት ያለው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 57644 ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

    ስለዚህ የከበረው ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ ያቀረብነውን መቃወሚያ መርምሮ ክሱ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአትን እና የወንጀል ህግ መርህን የማያሟላ ነው በማለት እንዲሰርዘው እናመለክታለን፡፡

    4. ክሱ ተከሳሾች እራሳቸውን ለመከላከል በማያስችል መልኩ በጥቅል የቀረበ ስለመሆኑ

    4.1. አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ መግቢያ ላይ ተከሳሾች ከ1ኛ ተራ ቁጥር እስከ 29ኛ ተራ ቁጥር በሚል የወንጀል ድጊት ተሳትፎ ዝርዝር በደፈናው ካቀረበ በዃላ ከስር ወረድ ብሎ እንደገና የእያንዳንዱ ተከሳሽ የወንጀል ተሳትፎ በሚል በክሱ መግቢያ ላይ ካስቀመጠው ዝርዝር ጋር እርስ በርሱ በግዜና በድርጊት አፈጻጻም የሚጋጭ የክስ ዝርዝር አቅርቧል፡፡

    በክሱ መግቢያ ላይ በ2001 ወንጀሉን መፈጸም ጀመሩ በማለት ከገለጸ በዃላ የእያዳንዱን ተከሳሽ የወንጀል ተሳትፎ ዝርዝር በማለት ሲገልጽ ደግሞ የወንጀል ድርጊቱ 2004 ተጀመረ በሚል እርስበርሱ በሚጋጭ መልኩ አስቀምጧል፡፡ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገመንግስት አንቀጽ 20 መሰረት ክሱ ተከሳሾች እራሳቸውን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ በግልጽ እና በዝርዝር አለመቅረቡ፤ ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ማስጃዎች ይዘት(የሰው ምስክሮ የሚያስረዱት ጭብጥ አልተገለጸም) እንዲያውቁ አለመደረጉ የህገመንግስት መብትን እና የወንጀል ህግ ሥነስርዐትን የጣሰ ነው፡፡

    4.2. በክሱ ላይ ተከሳሾች ለአመጽ ጥሪ አድርገው በማነሳሳት ሐምሌ 6 ቀን 2004 አንዋር መስጊድና አወሊያ በተነሳ ረብሻ በኮ/ር ግርማይ ገ/ሚካኤል ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰ፣ በንብረት ላይም ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የተባለ ቢሆንም፣ ጉዳቱን በቀጥታ ያደረሱት ሰዎች ማንነትና የአካልና ንብረት ጉዳቱ በትክክል የት ቦታና በስንት ሰዓት እንደደረሰ በክሱ ላይ አልተገለጸም፡፡ በተከሳሾች አነሳሽነት ድርጊቱን በቀጥታ የፈጸሙት የተባሉ ሰዎች ተለይተው ባልተገለጹበት ሁኔታ ጉዳት አድራሾቹ በተከሳሾች ቅስቀሳና ማነሳሳት ተገፋፍተው ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ጉዳት ያደረሱ ስለመሆኑ መለየት የማያስችል እና ተከሳሾቹ እራሳቸውን በአግባቡ እንዳይከላከሉ የሚያስቸግር ህጉን መሰረት ያላደረገ የክስ አቀራረብ ነው፡፡

    ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ክሱ በህጉ አግባብ የቀረበ ክስ አይደለም ብሎ ክሱን በመዝጋት ተከሳሾችን በነጻ እንዲያሰናብት እንጠይቃለን፡፡

    5. ክሱ ከህገመንግስቱ እና ከወንጀል ህግ አጠቃላይ መርህ ጋር የሚጋጭ ስለመሆኑ
    ዐ/ሕግ በክሱ ዝርዝር ተከሳሾች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ አነሳሽ እና ቀስቃሽ በማለት በሽብር ወንጀል ክስ መስርቷል፡፡ ነገርግን በሌላ ችሎት እና መዝገብ በተመሳሳይ ቀን እና ቦታ ወንጀሉን ፈጸሙ ተብለው የተከሰሱ ሰዎች ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ በዚህ መዝገብ የተከሰሱት ሰዎች አነሳሽ ተብለው አልተጠቀሱም፡፡ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት አደረሱ የተባሉት ሰዎች በሽብር ህግ ወይም ህገመንግስትንና የህገመንግስት ስርዓት ማፍረስ በሚል ወንጀል አልተከሰሱም፡፡
    በሌላ በኩል ተፈጸመ የተባለውን ድርጊት በቀጥታ ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰቦች በመደበኛው ወንጀል ህግ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኮ.መ.ቁጥር 37997፤ 38045 እና 38042 መዝገቦች ከአንድ ወር በላይ በማያስቀጣ መደበኛ የወንጀል ህግ አንቀጽ ክስ ቀርቦባቸው ተቀጥተዋል፡፡ ሰዎቹ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት በዚህ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎች ቢሆኑ ከላይ በቀረቡት መዝገቦች ተጠርተው ጉዳያቸው ይታይ ነበር፡፡ ስለዚህ በአንድ ጉዳይ ተከሳሽ የሆኑ ሰዎች ክስ ተነጣጥሎ በድጋሚ ክስ ሊቀርብ አይገባም፡፡

    በህገ መንግስቱ አንቀጽ 25 ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደሆነ በየትኛውም መለኪያ ልዩነት እንደማይደረግ፣ በዘር፤ በሃይማኖት፤ በፖለቲካ አመለካከት እና በሌሎችም መለኪያዎች ልዩነት እንደማይደረግ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም በወንጀል ህግ አጠቃላይ መርህ በሚያብራራው አንቀጽ 4 መሰረት ሁሉም ወንጀል ፈጸሙ የተባሉ ሰዎች ባላቸው ማህበራዊ ኑሮ ደረጃ፣ በዘር፣ በቀለም፣ በፆታና በየትኛውም መለኪያ ልዩነት ልዩነት መደረግ እንደሌለበት ህጉ ላይ ተገልጾአል፡፡ ተከሳሾች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኩል ፍትህን የማግኘት መብት እንዳላቸው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 37 ላይ ተገልጾአል፡፡ ነገር ግን በዚህ መዝገብ ተከሳሾች አነሳሽነት በቀጥታ ወንጀል ፈጸሙ የተባሉ ሰዎች ከአንድ ወር በላይ በማያስቀጣ የወንጀል አንቀጽ ተከሰው ሲፈረድባቸው፤ የተከሰሱበትን የወንጀል ድርጊት በቀጥታ ከመፈጸም ይልቅ አነሳስተዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች ግን አቃቤ ህግ የማነሳሳት ድርጊት ያለውን እጅግ በጣም አጋኖ በጸረሽ ብር ህግ እና ህገመንግስትን በሀይል ለመናድ መሞከር በሚል ከባድ ወንጀል እንዲከሰሱ ማድረጉ የቀረበው ክስ ህገወጥነት ብቻ ሳይሆን ከክሱ ጀርባ ያለውን ነገር የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ክሱ ህገወጥ ስለሆነ የተከበረው ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ህገወጥ ነው ብሎ ውድቅ ያድርግልን፡፡

    6. ክሱ የምክንያትና ውጤት ግንኙነት የሌለው መሆኑ

    አቃቤ ህግ ባቀረበው የክስ ዝርዝር ተከሳሾቹ የማነሳሳት ተግባራት ናቸው የተባሉትን ንግግሮች አደረጉ ያለው ሐምሌ 7/2004 ዓ.ም እና ቀጥሎ ባሉት ሁለት ቀናት ሲሆን፤ በተከሳሾቹ ማነሳሳት ምክንያት በሌሎች ሰዎች የወንጀል ድርጊት ተፈጸመ የተባለው ቀን ግን ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ነው፡፡ የቀኑ እርስ በርሱ መጋጨት፤ ውጤቱ ከምክንያቱ መቅደሙ በክሱ ውስጥ ምክንያት እና ውጤት ግንኙነት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 24 መሰረት አንድ የወንጀል ድርጊት ተፈጽሟል ለማለት የምክንያት እና ውጤት ግንኙት መሰረታዊ ነጥብ መሆኑ ተደንጓል፡፡ አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ግን ይህ መስፈርት አልተሟላም፡፡ ተከሳሾች የምክንያት እና ውጤት ግንኙነት በሌለው ጉዳይ መከሰሳቸው በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 118 መሰረት ዋና ስህተት በመሆኑ የቀረበውን ክስ ዋጋ ያሳጣዋል፡፡

    በሽብር ህጉ ላይ ማነሳሳት ማለት ሰው በመጎትጎት፣ ተስፋ በመስጠት፣ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት አንድ የሸብር ወንጀል እንዲፈጸም ማድረግ እንደሆነ ተገልጾአል፡፡ የአቃቤ ህግ የክስ አቀራረብ ደግሞ የትኛውን ዘዴ ተጠቅመው እንዳነሳሱ በግልጽ ያላስቀመጠና ግልጽነት ጎደለው በመሆኑ በዚህ ምክንያትም የመንስኤ እና ውጤት ግንኙነት (cause and effect relationship) የሚጻረር፤ የቀረበው ክስ እርስበርሱ የሚጋጭ፤ ባጠቃላይ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 24 ላይ የተቀመጠውን የማያሟላ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ዘግቶ ተከሳሾችን በነጻ እዲያሰናብትልን እንጠይቃለን፡፡

    7. በህግ በግልጽ ትርጓሜ ያልተሰጣቸውን ቃላትና ሀረጎች በክስ ላይ መጠቀም አግባብ ስላለመሆኑ
    በወ/ሥ/ሕ/ቁ.112 እንዲሁም 114(1) መሰረት እያንዳንዱ ክስ ወንጀሉና ሁኔታውን በዝርዝር መያዝ ያለበት ሆኖ የተፈፀመው ተግባር ወንጀል ከሚያደርገው ህግ አነጋገር ጋር በጣም የተቀራረበ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር በክሱ ውስጥ በየቦታው ያለአግባብ የገቡ ቃላትና ሀረጎች በህጉ ወንጀል ከተባሉ ተግባራት ጋር የሚቃረኑ ብቻ ሳይሆኑ ከህጉ የቃላት አጠቃቀም የራቁ እና በአብዛኛው (prejudice) ማሸማቀቅና ማሳቀቅን አላማ ያደረጉ ናቸው፡፡ የአቃቤ ህግ ክስ ከስር በተዘረዘሩ በህግ የማይታወቁ ወንጀል ተብለውም ያልተደነገጉ የቃላት እና ሀረጎች ስብስብ የተገነባ መሆኑን ለማሳያ ያክል:-

    7.1 የሃይማኖት አስተማሪዎች /የኡስታዞች ቡድን/የአዳኢዎች ቡድን
    7.2 በእቡህ የተደራጀ የዳኢዮች ቡድን
    7.4 ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት አክራሪነት
    7.5 የሽብር ቡድን
    7.6 ጂሃድ
    7.7 ሌላው አስተምህሮ
    7.8 አክራሪነትን ማስፋፋት
    7.9 አክራሪነትን የሚሰብኩ መገናኛ ብዙሃን
    7.10 ከመጅሊስ እውቅና ውጪ አክራሪነትን ለማስፋፋት የሚረዱ ተቋማት ማቋቋም
    7.11 ከሽብር ቡድኑ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ የሚያራምዱ
    7.12 የሰደቃና የአንድነት ዝግጅቶች
    7.13 ከራሳቸው የአክራሪና አስተምህሮ ውጪ
    7.14 ከአክራሪ አስተምህሮት ውጭ የሚያስተምሩ ኢማሞችን መግደል ጅሃድ ነው
    7.15 ህገ ወጥ ኮሚቴ
    7.16. መስዋትነትን መክፈል አለብን
    7.17 ከኛ አስተሳሰብ ውጪ ያሉ አስተምህሮቶች
    7.18. ከኛ ከአክራሪዎች ውጪ ያላችሁ
    7.19. የሰደቃ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍና በመንቀሳቀስ
    7.20 ከአክራሪዎች ውጪ ያሉ አስተሳሰቦችን እንቃወማለን
    7.21 ‹‹ አዎ አሸባሪ ነኝ›› ‹‹ቢላል የሞተው ለእምነቱ ነው›› አመፅ ቀስቃሽ፣ ግጥሞችን ማቅረብ
    7.22 አክራሪ ኢስላማዊ የመገናኛ ብዙሃን ማቋቋም የሚሉትን ማየት ይቻላል፡፡
    እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ቃላት እና ሀረጎች በክሱ ላይ ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በየቦታው ያላግባብ ከሱን ለማወፈር የገቡ ስለሆነ በሚከተሉት ምክንያቶች ክሱን ውድቅ ያደርጋሉ፡-

    ሀ/ በኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግ ወይም በሌሎች ልዩ ህጎች የወንጀል ድርጊት ተብለው ያልተቀመጡ በመሆናቸው

    ለ/ በየትኛውም የኢትዮጵያ ህግ፤ ኢትዮጵያ በተፈራረመቻቸው ኮንቨየንሽኖች ወይም በአለም አቀፍ ህጎች ላይ የወንጀል ድርጊት ያልተባሉ፤ ትርጉማቸውም ተብራርቶ ያልተፃፈ በመሆኑ የነዚህ ድርጊቶች ውጤትም የማይታወቅ ነው፡፡

    ሐ/ በተለይ ‘ጅሃድ’ የሚለው ሀይማኖታዊ ቃል በእስልምና ሃይማኖት ሰፊ ትርጉም ያለውና በሌላ በማንኛውም ተነፃፃሪ ሰነድ፣ ፍልስፍና ወይም ሃይማኖት ሊተረጎም የማይችልና የማይገባው ሲሆን ትርጉሙም በቀጥታ በሃይማኖቱ አረዳድ ሊወሰድ የሚገባው ነው፡፡ ፍ/ቤት ጅሃድ የሚለውን ቃል ለመተርጎም ስልጣን የሌለው በመሆኑ፤ የትኛውም ተከሳሽ እምነቱን መሰረት አድርጎ በጥልቅ እሳቤ “Analitical Reasoning” የራሱን ትርጉም ሊሰጠው የሚችል ስለሆነ ማንኛውምሰው ወይም ተቋም በሚሰጠው ትርጉም ሊገደድ የማገባ ወይም እንደማስረጃ ሊያዝበት አይገባም፡፡ አቃቤ ህግ የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ ሀይማኖታዊ የሆኑ ቃላትን እንዳሻው ትርጉም እየሰጠ በህጉ ወንጀለው ከተባለው ውጪ ክስ ማቅረቡ ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 11 መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚለውን መርህ የሚጥስ ነው፡፡ በመሆኑም ፍጹም ሃይማኖታዊ የሆኑ ቃላቶች በህግ ትርጉም የሌላቸውን ቃላት በክስ ላይ አስገብቶ መጠቀም ህጉ አይፈቅድለትም፡፡

    መ/ በህገ መንግስቱ አ/27 የሃማኖትና የእምነት ነፃነት የተደነገገ ስለሆነ አንድን ሃይማኖት የሚከተሉ አማኞች ወይም እምነቱን ፅንፈኛ፣ አክራሪ፣ አክራሪ ያልሆነ፣ እያሉ የህግ አስፈጻሚው አካል (የዐ/ሕግ) ስልጣን አይደለም፤ በሃይማኖትም ጣልቃ መግባት ነው፡፡ ስለዚህ ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ መሰረት ያደረገው ከዚህ በላይ ለአብነት በተዘረዘሩት በህጉ በማይታወቁ ቃላት ፣ ሀረጎች እና አባባሎች በመሆኑ ክሱ ውድቅ ተደርጎ ደንበኞቻችን በነፃ እንዲሰናበቱ ይደረግ”::

    2ኛ ክስ ላይ የቀረበ መቃወሚያ

    8. ተከሳሾች ያላግባብ ከአንድ በላይ በሆነ ክስ መከሰሳቸው

    8.1.በአንድ የክስ ማመልከቻ ብዙ ክሶች ሊቀርቡ እንደሚችሉ ህጉ የሚፈቅድ ቢሆንም እያንዳንዱን የወንጀል ክስ የሚያቋቁሙ በቂ የወንጀል ማቋቋሚያ ህጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተሟልተው መገኘት አለባቸው:: ከዚህ በተጫማሪ አንዱ ክስ በሌላው ክስ ላይ ተደጋግፎ የሚቆም ሳይሆን እራሱን የቻለ ለእያንዳንዱ ክስ ማቋቋሚያ በቂ የግዙፋዊ ነገሮች በዝርዝር ያለው መሆን አለበት፡፡ አቃቤ ህግ ባቀረበው 2ኛ ክስ ላይግን የወንጀል ድርጊት ዝርዝር(ገጽ 21) ብሎ ያስቀመጠው በ1ኛ ክስ ላይ የዘረዘራቸውን ተግባራት ነው ይህም ፈጽሞ ተቀባይነት ያለው የክስ አመሰራረት አይደለም፡፡ አቃቤ ህግ ላቀረበው 2ኛ ክስ በተከሳሾች የተፈጸመ ድርጊት ካለ እንደጠቀሰው ህግ በዝርዝ የሚያስረዱለትን ሌላ ተግባራት ማቅረብ እንጂ በደፈናው በ1ኛው ክስ የተዘረዘሩት ለ2ኛ ክስም ተፈጻሚ ናቸው እንዲል የሚቅድለት ህግ የለም፡፡ ሰለዚህ 2ኛው ክስ ሊሰረዝ ይገባል፡፡

    8.2. የአቃቤ ህግ ክስ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 238 1/ሀ/ የተጠቀሰውን ወንጀል ሚያቋቁሙ ድርጊቶች ማለትም ሀይል፣ዛቻ ወይም አድማ በተከሳሾች መፈጸሙን የሚያመለከት አንዳችም ነገር የማያካትት በመሆኑ ተከሳሾቹ ከላይ በተገለጸው የወንጀል ህግ አንቀጽ ክስ ሊቀርብባቸው አይገባም ተብሎ ክሱ እንዲሰረዝ እንጠይቃለን፡፡

    8.3. የአቃቤ ህግ ከላይ በ1ኛ ክስ እንዳቀረው ተከሳሾቹ የማነሳሳት እን ቅስቃ ተግባር ፈጸሙ የሚል ነው፡፡ ከላይ ባቀረብነው መቃወሚያ ተራ ቁጥር 5 መሰረት ተከሳሾች አነሳስተዋቸው የወንጀል ድርጊት ፈጸሙ የተባሉት ሰዎች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ አንድ ወር ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት በሚያስቀጣ ወንጀል ተከሰው የተቀጡ መሆናቸው፤ በተለይም በዚህ መዝገብ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው በሚል በማስረጃነት የቀረቡት ኮማንደር ግርማይ በመዝገብ ቁጥር 38042 በተከሰሱት ሰዎች ላይ መማስረጃነት ቀርበው ተከሳሾቹ በቀላል እስራት እ በገንዘብ መቀጮ መቀጣታቸው፤ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 238 1/ለ በህዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ደርሶአል ሊያስብል የማያስችል ስለሆነ፤ ተከሳሾች በወንጀል ህጉ የተጠቀሰባቸው አንቀጽ ተገቢነት የሌለው እና ከድርጊታቸው ጋር የማይጣጣም ነው ተብሎ ክሱ እንዲሰረዝልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

    9. በተከሳሾች ተፈፅሞዋል የተባለው ድርጊቶች ህገ-ወጥ አና በወንጀል የሚያስቀጡ ስላለመሆናቸው እያንዳንዱን ተከሳሽ የሚመለከቱ በግል የቀረቡ መቃወሚያዎች
    በተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ አንድን የሽብር ድርጊት ለመፈፀም አቅደዋል ተዘጋጅተዋል የሽብር ድርጊት ፈፅመዋል፡፡ ድርጊቱ እንዲፈፀምም አነሳስተዋል የሚል ሲሆን ክሱ የሚመለከተው ደግሞ ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓም በአ/ከ/ክ/ከ በአወሊያ እና በአንዋር መስጊዶች በተነሳ ረብሻ በተፈፀመ ድርጊት የደረሰ የአካል እና የንብረት ጉዳት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በክሱ ላይ አንድም ተከሳሽ በክሱ ገፅ 20 የተመለከተውን ጉዳት አደረሰ የተባለውን ድርጊት በራሱ ፈፅሟል ወይም ይህንኑ ድርጊት ለመፈፀም አቅዷል፡፡ ተዘጋጅቷል፡፡ ያልተባለ በመሆኑ በዚህ ቀን (ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም) የተፈፀመውን ድርጊት ለመፈፀም ማቀድን መዘጋጀትንና ድርጊቱን መፈፀምን በተመለከተ በተከሳሾች ላይ ክስ እንደቀረበ አይቆጠርም፡፡

    በክሱ ላይ በግልፅ የተመለከተው (ገፅ 20) ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም በዃላ ባለው ጊዜ በፈፀሙት ለሽብር የማነሳሳት ድርጊቶች ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓም ከላይ በተመለከቱት ቦታዎች ረብሻ እንዲነሳ በማድረግ የተጠቀሱት የአካልና የንብረት ጉዳቶች በማድረሳቸው የተከሰሱ እንደሆነ የሚገልጽ ነው፡፡ በዚህ ቀን ተፈፀመ ከተባለው ድርጊት በስተቀር በክሱ ተከሳሾች ለመፈፀም አቅደዋል ተዘጋጅተዋል ወይም እንዲፈፀም አነሳስተዋል ተብሎ በተለይ የተገለፀው ሌላ በአንቀጽ 3 ስር የሚወድቅ ድርጊት ባለመኖሩ ተከሳሾች የተከሰሱት ይህንን ድርጊት እንዲፈፀም ድርጊቱን በማነሳሳት ሊከሰሱ የሚችሉበት አግባብ የለም፡፡ የክሱ ዝርዝር እንደሚያመለክተው በተለያዩ ጊዜያት በእያንዳንዱ ተከሳሽ በተደረገ ንግግር በተዘጋጀ ጽሑፍ የተላለፉ ናቸው ተብለው የቀረቡት እና ተፈፀሙ የተባሉት ሌሎች ድርጊቶች ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተባለውን ድርጊት ለማነሳሳት የተደረጉም ሆነ ሊያነሳሱ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ተከሳሾቹ በህግ በተጠበቀላቸው ገደብ ውስጥ በመብታቸው ሲጠቀሙ የፈፀሟቸው ድርጊቶች ስለመሆናቸው እያንዳንዱ ተከሳሽ ላይ ከቀረበው ከስ አንፃር እንደሚከተለው መቃወሚያችንን እናቀርባለን ፡-

    1ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    የካቲት 6 ቀን 2004ዓ.ም ቢላል የሞተው ለሃይማኖቱ መሆኑን ለሃይማኖት መስዋትነት ስለመክፈል ሌሎች አስተምህሮቶችን ስለመታገል ተናገረ የተባለውን አልተናገረም እንጂ ቢሆንም እንኳን ሃይማኖታዊ አስተምህረቶችን መግለፅ ማስተማር ነው ሊባል ከሚችል በስተቀር በማንኛውም ረገድ ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት ማነሳሳት ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በዚሁ ቀን መጅሊስ የሚያካሂደውን ስብሰባ እና ሌሎች ዝግጅቶች በረብሻ ማቋረጥ አለብን ብሏል የተባለውን በተመለከተ ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት የመጅሊሱን ስብሰባ ወይም ሌላ ዝግጅት ለማቋረጥ በተነሳ ረብሻ ባለመሆኑ ድርጊቱን ያነሳሳ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክሱ ተከሳሾች ድርጊቱን አነሳስተዋል የተባለው ከየካቲት 26 ቀን 2004ዓ.ም በኃላ ባለው ጊዜ ውስጥ በመሆኑ የካቲት 6 ተደረገ በተባለው ንግግር ክስ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ቀኑ ባልታወቀ በየካቲት ወር ስለ ጅሃድ ተነገረ የተባለው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ማድረግን በተለይ ደግሞ የተከሰሱበትን ድርጊቶችን እንዲፈፅሙ ማነሳሳትን የሚመለከቱ ሳይሆኑ ሃይማኖታዊ አመለካከቶችና አስተያየቶች ናቸው በተጨማሪም ቀኑ በውል ባልታወቀበት ከየካቲት 26 ቀን 2004ዓ.ም ጀምሮ የተደረጉ ድርጊቶችን ብቻ የሚመለከት ስለሆነ በዚህ ክስ ሊቀርብ አይችልም፡፡

    ሐምሌ 8 ቀን 2004ዓም ተናገረ የተባለውን በተመለከተ በዚህ ቀን በተደረገ ንግግር ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀመውን ድርጊት ለማነሳሳት የተደረገ ሊሆን ስለማይችል በዚህ ክስ ሊቀርብ አይችልም፡፡ 2ኛውን ክስ በተመለከተ በክሱ ላይ 1ኛተከሳሽ ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት የፈጸመ ስለመሆኑ በዝርዝ ያልተቀመጠ በመሆኑ በቀረበበት ክስ ሊጠየቅ አይገባም፡፡ በመሆኑም አንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው1ኛ ና 2ኛ ክስ ተሰርዞ በነጻሊሰናበት ይገባል፡፡

    2ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    2ኛው ተከሳሽ ሃይማኖትን ስለመጠበቅ፤ ለሃይማኖት መስዋትነት ስለመክፈል ስላለው ፋይዳ፤ ስለ እስልምና ሃይማኖት ሰላማዊነት በመጋቢት ወር 2004ዓ.ም ሃምዛ መስጊድ ለተሰበሰበው ህዝብ ተናግሯል የተባለውን በተመለከተ ይህ ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረግ ተፈፅሟል የተባለውን ድርጊት ለማነሳሳት የተነገረ ነው ሊባል የሚችል አይደም፡፡ ድርጊቱን ፈጽሟል ቢባል እንኳን በህገመንግስቱ ተፈቀደ ወንጀል ህግ ወንጀል ያልተባለ ሃይማኖታዊ አመለካከትን መግለፅን ወይም ማስተማርን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ ወሩ ባልታወቀ ጊዜ በ2004ዓ.ም ተናግረዋል የተባለው ከሐምሌ 6 ቀን 2004ዓም በፊት ይሁን በኃላ በማይታወቅበት በዚህ ክስ ሊቀርብበት አይችልም ሐምሌ 7 ቀን 2004ዓ.ም የተናገረው ነው የተባለውን በተመለከተ ይህ የተከሰሰበት ወንጀል ከተፈፀመበት ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም በኃላ ያለን ጊዜ የሚመለከት በመሆኑ በዚህ ድርጊቱን እንዲፈፅም አነሳስቷል ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በ2ኛው ክስም 2ኛ ተከሳሽ በወንጀል ህጉ የተገለጸውን የወንጀል ተግባር ስለመፈጸሙ የቀረበ ክስ/የወንጀል ዝርዝር ስለሌለ ተከሳሽ ላይ የቀረቡት ክሶች ተሰርዘው በነጻሊሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    3ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሰሽ መጋቢት ወር 2004ዓ.ም ተናገረ የተባለው የመንግስትን በሃይማኖት ጣልቃ መግባት መቃወምን፤ ሃይማኖትን ስለመጠበቅ በጅሃድ ስለመዘጋጀት ወዘተ በሚመለከት ሃይማኖታዊ አመለከታከትን እንጂ ለተከሰሰበት ሃምሌ 6 ቀን የተፈፀመ ድርጊት ለማነሳሳት የተደረገ ሆኖ ሊከሰስበት የሚቸል አይደለም፡፡

    በሰኔ ወር 2004ዓ.ም ‹‹የሌላ አስተምህሮት ኢማም የሚያስተምራችሁን እንዳትቀበሉ እሱ እምነቱን ክዷል…›› ብሎ ተናግሯል የተባለውን በተመለከተ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ቢሆን እንኳ ሃይማኖታዊ አመለካከቱን ወይም አቋሙን የገለፀበት እንጂ በህግ ሊያስከስ የሚችል ተግባር አይደለም፣ ስለሆነም የማነሳሳት ተግባር ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡

    ሐምሌ 7 ቀን 2004ዓ.ም እና ሐምሌ 8 ቀን 2004ዓ.ም የተነገሩ ናቸው የተባሉትን በተመለከተ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ሀምሌ 6 ቀን 2004ዓም የተፈፀመ ድርጊት ወደዃላ ሄዶ አነሳስቷል ሊባል የሚችልበት የህግ አግባብ የሌለ ስለሆነ በ2ኛ ክስም ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡ ተከሳሽ በነጻ እንዲሰናበት እናመለክታለን፡፡

    4ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ ለሃይማኖት መስዋትነት ስለመክፈልና ለጅሃድ ስለመዘጋጀት እንደተባለው ተናግሯል ቢባል እንኳን በሽብር ህጉ ማነሳሳት ለሚለው ትርጉም የተሰበት ላይ የሚካተት ስላልሆነ ሐምሌ 6 ተፈፀሙ ለተባሉ ድርጊቶችን ሆነ ሌላ ማንኛውም ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የሚያነሳሳ ሳይሆን በሃይማኖት መርሆች መመዘኛነት የሚታይ አመለካከት የተገለፀበት ብቻ ነው፡፡

    በተጨማሪ ሐምሌ 8 ቀን 2004ዓ.ም ተከሳሽ ተናገረ የተባለው ንግግር ወደዃላ ሄዶ ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ተፈፀመ ለተባለ ድርጊት የማነሳሳት ተግባርረ ነው ሊባል ስለማይችል እንዲሁም በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    5ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀመ ነው የተባለውን የወንጀል ድርጊት አነሳስቷል የተባለውን ሐምሌ 7 እና 8 ቀን 2004 ዓ.ም አድርጓል በተባለው ንግግሮች ነው እነዚህ ሐምሌ 7 እና 8 ቀን 2004ዓ.ም የተደረጉ ንግግሮች ተፈጸመ የተባለውን ድርጊት ወደዃላ ሄዶ ተከሳሾቹ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ተፈጠረ ለተባለው ነገርተጠያቂ የሚያደርግበት ህግ አግብ የለም፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    6ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ‹‹ከኛ ሌላ ሌሎች አስተምህሮቶች ማስተማር ካላቆሙ እስከ መጨረሻው ትግላችንን አናቋርጥም›› ብሎ ተናግሯል የተባለውን በተመለከተ ማንኛውም ሰው ትክክለኛ ነው የሚለውን እምነትና አመለካከት ለመጠበቅ ማንኛውም ሰላማዊ ትግል ማድረግ በህግ የተጠበቀ መብት በመሆኑ ይህን መናገሩ የተከሰሰበትን ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀመ ድርጊት ለማነሳሳት የተደረገ ነው ሊባል የሚችልበት አግባብ የለም፡፡

    ወሩ ባልታወቀ 2004ዓ.ም የተናገረው ነው የተባለውን በተመለከተ ጊዜው አነሳስቷል ከተባለው ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓም የተፈፀመ ድርጊት በፊት ወይም በኃላ መሆኑ ባልታወቀበት በግምት ብቻ ድርጊቱን አነሳስቷል ተብሎ ክስ ልቀርብበት አይገባም፡፡ ከሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም በፊት የተነገረ ቢሆን እንኳ በተከሳሽ እምነት መንግስት ሀይማኖቱን አስመልክቶ እየፈጸመነው ብሎ ያመነበተን መናገሩን የተናገረው መረጃው የተሳሳተ ነው ሊባል ከሚችል በስተቀር በህገመንግስቱ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብቱን በመጠቀሙ የተከሰሰበትን ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓም የተፈፀመ ድርጊት የሚያነሳሳ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    7ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ በመጋቢት፣ የካቲት እና ሐምሌ ወር 2004 ዓ.ምወር 2004ዓ.ም ‹‹ትግላችን እስከ ሞት ይቀጥላል መስዋትነትን እንከፍላለን›› ብሎ ያመነበተን መናገሩን የተናገረው መረጃው የተሳሳተ ነው ሊባል ከሚችል በስተቀር በህገመንግስቱ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብቱን በመጠቀሙ በ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ተፈፀመ የተባለን ድርጊት እንዲፈፀም የሚያነሳሳ ወይም ድርጊቱ እንዲፈፀም ለማነሳሳት የተደረገ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    8ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ ሰኔ 21 ቀን 2004ዓም ‹‹መጅሊስና መንግስት ሃይማኖታችንን እየከፋፈለብን ነው›› በመንግስት እየተፈፀመ ስላለው ያመነበተን መናገሩን የተናገረው መረጃው የተሳሳተ ነው ሊባል ከሚችል በስተቀር በህገመንግስቱ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብቱን በመጠቀሙ በሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ተፈጸመ ለተባለው ድርጊት የሚያነሳሳም ሆነ ለማነሳሳት ተብሎ የተደረገ ነው በሚል ክስ ሊቀርብበት የሚችል አይደለም፡፡

    የመንግስትን አሰራር በተመለከተ አስተያየትና ወቀሳ ማቅረቡ በህግ የተጠበቀ መብት እንጂ በወንጀል የሚያስቀጣ አይደለም የውስታዞችና/የዳኢዮች ቡድንና የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ተብሎ የሚጠራው ቡድን አባል መሆን ወንጀል ባልሆነበት ይህን መሰረት ያደረገ ክስ ሊቀርብበት አይችልም፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    9ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    የመጅሊስ ስብሰባን በረብሻ ማቋረጥ አለብን ብሏል የሚለውን በተመለከተ፤ ይህን ብሎ ቢሆን እንኳን በግልፅ የሚያመለክተው አላማው የመጅሊስን ስብሰባ ወይም ሌላ ዝግጅት በማቋረጥ አላማ ብቻ ያለውን ተግባር የሚመለክት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ክሱ ሀምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ተፈፀመ የተባለው ድርጊት ከመጅሊስ ስብሰባም ሆነ ሌላ ዝግጅት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው በመሆኑ በዚህ ንግግር ሀምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት አነሳስቷል ወይም ሊያነሳሳ ሞክሯል ሊባል የሚችለው አግባብ የለም፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    10ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ ከ2001ዓ.ም ጀምሮ ተደራጀው የተባለው ቡድን አባል መሆን አለመሆን በራሱ በወጅል የሚስጠይቅ ባልሆነበት ተከሳሽ ይህንን መሰረት ያደረገ ክስ ሊቀርብበት አይችልም፡፡
    ከሐምሌ 11 ቀን 2004ዓ.ም የፈፀማቸው ድርጊቶች ናቸው ተብሎ የቀረቡትን በተመለከተ ክሱ የቀረበበትን ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀመ ድርጊት የማነሳሳት ድርጊት ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ማነሳሰቱን ፈጽሟል ቢባል እንኳን በአዋጅ ቁጥር 652/2009አንቀፅ (3) ስር በተለይ ከተዘረዘሩት በተለይ የትኛውን የትኛውን ድርጊቶት እንዲፈፅሙ ለማነሳሳት የተደረገ እንደሆነ በግልፅ ባልተመለከተበት በአዋጁ አንቀፅ 4 መሰረት የማነሳሳት ክስ ሊቀርብ የሚችል ባለመሆኑ በተከሳሽ ላይ የቀረበው ክስ ውድቅ ሊሆን ይገባል፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    11ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ ሐምሌ 7 ቀን 2004 ዓ.ም ተናገረ የተባለው የማነሳሳት ድርጊት ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ተፈፀመ ለተባለ ድርጊት በማነሻሻነት ውሏል ሊባል የማይችል በመሆኑና ሌላ የሽብር ወንጀል የሚመለከት ነው ቢባል እንኳን በአዋጅ ቁጥር 652/2009 አንቀፅ 3 ስር ከተዘረዘሩት በተለይ የትኛውን ወይም የትኞቹን ድርጊቶች የተደረገ እንደሆነ በግልፅ ባልተመለከተበት በአዋጁ አንቀፅ መሰረት የማነሳሳት ወንጀል ክስ ሊቀርብ የሚችል አይደለም፡፡በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    12ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ ሐምሌ 1 ቀን 2004ዓ.ም ተደረገ በተባለው ንግግር ከአክራሪዎች ውጪ የሆኑ አስተሳሰቦችን እንቃወማለን ማለቱ በህግ በተጠበቀለት መብት ለማይደገፈው አስተሳሰብ ያለውን ተቃውሞ መግለፁን እንጂ ለወንጀል ድርጊት የማነሳሳት ድርጊት ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በመንግስት እየተፈፀመ ስላለው ያመነበተን መናገሩን የተናገረው መረጃው የተሳሳተ ነው ሊባል ከሚችል በስተቀር በህገመንግስቱ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብቱን በመጠቀሙ ወንጀል ለማነሳሳት የተደረገ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    13ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ የካቲት 2 ቀን 2004ዓ.ም አደረገ የተባው ንግግር የተከሰሰበትን ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ተፈፀመ የተባለውን ድርጊቶችንም ሆነ ማንኛውንም የወንጀል ድርጊት የሚያነሳሳ አገላለፅ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ንግግሩን አድርጓል ቢባል እንኳን ከሌላ ወገን የሚመጣን ተፅኖ መቋቋምን በተመለከተ የተደረገ ንግግር እንጂ በሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ተፈፀመ የተባለን የወንጀል ድርጊት አነሳስቷል ተብሎ ሊከሰስ አይችልም፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    14ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ በክሱ እንደተገለጸው ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በእቡህ የተደራጀ ነው በተባለ ቡድን አባል መሆን ስለሃይማኖታዊ መንግስት ምስረታ ውይይት ማድረግ በውይይቱ መሳተፍ ይህን የሚመለከት ስልጠና መውሰድ በቤቱ ስልጠና እንዲሰጥ ማመቻቸት ወዘተ በሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

    በክሱ አቀራረብ በድፈኑ በህቡእ የተደራጀ ቡድን የሚለው የህግ አገላጽ ያልሆነ ሲሆን ክሱ የተጻበት የቋንቋ አገላለጽ ድርጊቱን ወንጀል የሚያደርግው ህግ ከተጻበት ፈጽሞ የራቀ እና የማይገናኝ ነው፡፡ እንዲሁም ከታህሳስ ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ ቡድኑ የጀመረው ህዝበ ሙስሊሙን ለሽብር አላማ የማነሳሳት እንቅስቃሴ የሚለው አገላለፅ ምን ለማለት እንደተፈለገ ወይም ምን አይነት ድርጊቶችን እንደሚወክል በዝርዝ የማስቀምጥ ስለሆነ በወንጀል ስነስርዓ ህጉ ክስ የሚጻፍበትን ስርአት የሚተላለፍ ነው፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    15 ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ ከጥር ወር 2004ዓ.ም ጀምሮ ዘወትር አርብ ያቀርብ ነበር የተባሉት ግጥሞች ይዘትና መልዕክት በግልጽ ባልተመለከተበትና በተባሉት የተለያየ የሰደቃ ፕሮግራሞች ላይ ምን እንደተናገረ እንደኳን ሳይገለፅ አቃቤ ህግ ለክሱ ይጠቅመኛል የሚላቸውን ቃላት ብቸ በማሰባሰብ የወንጀል ድርጊቱ ሊፈጸም የቻለበትን ዝርዝር ሳያካትት ክስ ሊያቀርብ አይገባም፡፡ በተጨማሪ ቀስቃሽ ግጥም ምንማለት እንደሆነ በህግ ባልተገለጸመት ሁኔታ ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓዓም የተፈፀመውን ድርጊት በማነሳሳት ወንጀል ክስ ሊቀርብበት አይችልም፡፡ በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    16ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ሀምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት ፈፀሙ የተባሉ የተለያዩ ግለሰቦች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሽብርተኝነት ወንጀል ሳይሆን በሌላ ወንጀል ተከሰው ፍ/ቤቱ በቀላል የገንዘብ ቅጣት የተቀጡ ስለመሆኑ በመ/ቁ. 37979 ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡ ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን በማነሳሳትና ድንጋይ በመወርወር በረብሻው ተሳትፈዋል ከተባለ በዚያው መዝገብ እና ወይም በተመሳሳይ የህግ አግባብ ሊከሰስ ይገባዋል እንጂ በሽብርተኝነት ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ ክስ ሊቀርብበት ስለማይችል ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል፡፡በ2ኛ ክስ ተከሳሽ የፈጸመው የፈጸመው የወንጀል ተግባር ስለመኖሩ በአቃቤ ህግ የቀረበበት ክስም ሆነ ክሱን ሚያቋቋም ዝርዝር የቀረበበት ስላልሆነ ሊከሰስ አይገባም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበት እንጠይቃለን፡፡

    17ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    17ኛ ተከሳሽን በተመለከተ ‹‹የሙስሊሙ ህብረተሰብ መብትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ›› ተብሎ የሚጠራው ኮሚቴ በክሱ እንደተገለፀው የሽብር ኮሚቴ የሚል ስያሜ ሊያሰጠው የሚችል አንዳችም ምክንያት የሌለው በመሆኑ የዚህ ኮሚቴ አባል መሆን የሽብር አላማ የማስፈፀም ሃሳብ ስለመኖሩ ያረጋግጣል የሚል ግምትም መሰረት በማድረግ በ2004ዓ.ም ወሩ በማይታወቅበት ለኮሚቴው ሰብሳቢ ብር 200,000 ሰቷል በሚል ብቻ ክሱ የሚመለከተውን ሀምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት የማነሳሳት ክስ ሊቀርብበት አይችልም

    18ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    በተከሳሽ ላይ የቀረበው ክስ ‹‹አክራሪ ኢስላማዊ የመገናኛ ብዙሃንን›› በማቋቋም ባወጧቸው አመፅ ቀስቃሽ የሆኑና የተዛቡ ዘገባዎችና ፅሁፎች ህዝቡ ለሽብር አላማው ቀስቅሷል የሚል ነው ‹‹አክራሪ ኢስላማዊ የመገናኛ ብዙሃንን›› የሚለው አገላለፅ የሚኖረው ትርጉም ምንነት የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ በዚህ የመገናኛ ብዙሃን አመጽ ቀስቃሽና የተዛቡ ዘገባዎችና ጽሑፎች ይዘትና ለየትኛው የሽብር ተግባር እንዳነሳሱ አልተገለፀም ድርጊቱ በመገናኛ ብዙሃን የተፈፀመ ነው የሚል ቢሆንም በማስረጃነት የቀረቡት ግን በዚህ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የተሰራጩ ጽሑፎች ወይም ዘገባዎች ሳይሆኑ ከተከሳሽ ላፕቶብ የተገኙ ፅሑፎች መሆኑ በራሱ በተባለው የመገናኛ ብዙሃን ተሰራጩ ያላቸውን ጽሑፎችና ዘገባዎች ይዘት በክሱ በባልተገለፀበት ክሱ የሚመለከተውን ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ተፈፀመ የተባለውን ወንጀል ድርጊት አነሳስተዋል ወይም የሚያነሳሱ ነበሩ ለማለት የሚያስችል ሁኔታ በሌለበት ይህ ክስ መቅረቡ አግባብ ስላልሆነ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል፡፡

    19ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትኤ አፈላላጊ ተብሎ የሚጠራው ኮሚቴ ህገወጥና አሸባሪ የሚል ስያሜ ሊሰጠው የሚችልበት ምንም አይነት የህግ አግባብ በሌለበት ተከሳሽ የዚህ ኮሚቴ አባል መሆኑን እንደወንጀል የሚቆጠር ካለመሆኑም በተጨማሪ ለጀሃድ ተዘጋጁ መስጂድ ውስጥ ለተሰበሰቡ ወጣቶች በክሱ እንደተገለፀው ተናግሮ ቢሆንም እንኳን ይህ በክሱ የተመለከተውን ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀመው ወንጀል ድርጊት ለማነሳሳት የተደረገ ነው ሊባል ስለማይችል ክሱ ውድው ሊሆን ይገባል

    20ኛ ተከሳሽ ሙባረክ አደምን በተመለከተ

    አቃቤ ህግ ያቀረበው የወንጀል ድርጊት ዝርዝር እንደሚያመለክተው ሰርቶታል ተብሎ ቀረበው የወንጅል ድርጊት “ማይክ መቀማት”፣ “የመጅሊስ ሀላፊዎች መኪናቸው ላይ ጉዳት ማድረስ”፣ “መንግስት ከእኛ ውጪ ያሉ አስተሳሰቢችን እየደገፈ ነው የሚል የሀሰት ንግግሮችን ማድረግ” በቀረበበት 1ኛ ክስ የፀረሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)(2)(4)(6) እና 4 ስር ወይም በ2ኛ ክስ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 238(1) እና (2) ላይ ሊወድቅ ስለማይችል በወ/መ/ሥ/ሕ/ቁ 112 መሰረት አደረገ የተባለው የወንጀል ድርጊት እና የተከሰሰበት የፀረ ሽብር አንቀጾች እና የወንጀል ህግ አንቀጽ አብረው ሊሄዱ የማይችሉ ስለሆነ የቀረበበት ክስ ተገቢነት ስለሌለው በነፃሊሰናበት ይገባል፡፡

    21ኛውን ተከሳሽን በተመለከተ

    የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በማባል የሚታወቀውን ኮሚቴ ‹‹የአሸባሪ ቡድ›› ነው ተብሎ አልተሰየመም በዚህ እንዲሰየም ወይም እንዲፈረጁ የሚያበቃም ምንም አይነት የህግ አግባብ የለም፡፡

    - ስለሆነም የዚህ ኮሚቴ አባል መሆን በራሱ እንደ ወንጀል ድርጊት መፈፀም ሊወሰድ የሚችል አይደለም፡፡

    - መንግስት መጅሊሱን በራሱ አምሳል ለመቅረፅ ፍላጎት አለው ብሎ ተናግሮ ከሆነ ይህ ወይም ይህንን ስጋቱን በማንኛውም መንገድ ገንፆ ከሆነ ይህ የመንግስት አቋም ስለመሰለው ነገር (ጉዳይ) ያለውን አመለካከቱን የገለፀበት ነው ከሚለው በስተቀር የተከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት እንዲፈፀም ማነሳሳት ነው ሊባል ከሚባል መንግስትን የማይደግፍ አመለካከትን መግለፅ በህገ-መንግስቱ የተጠበቀ መብት እንጂ በወንጀል ሊስቀጣ የሚችል አይደለም፡፡

    - ‹‹ሌሎች አስተምሮቶች የተቆጣጠሯቸውን መስጊዶች ለማፍረስ ወኔ እንደሚያስፈልግና ህዝቡ ግን ወኔ እንደሌለው ገልጿል›› የተባለውም ይህን በእርግጥ ተናግሮ ቢሆንም እንኳ አመለካከቱን (ወይም አስተያየቱን) የገለፀበት ነው ሊባል ከሚችል በስተቀር በማንኛውም መመዘኛ ለአንድ ተለይቶ ለታወቀ በማንኛውም መመዘኛ ለአንድ ተለይቶ ለታወቀ ድርጊት በተለይ ደግሞ ክስ የቀረበበትን ድርጊት እንዲፈፀም ለማነሳሳት የተደረገ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡

    - በታህሳስ ወር 2004ዓ.ም በባሌና ምዕራብ አርሲ ዞን ሌሎች አስተምሮቶችን የማጥፋትና የማጥላላት ስራ እንዲሰራ ትዕዛዝ ሰጥቷል የተባለውን በተመለከተ ይህ ክስ የቀረበበትን ድርጊት የማነሳሳት ድርጊት ካለመሆኑ በተጨማሪ ክሱ ከሚመለከተው ጊዜ (ማትም በክሱ የተመለከተው ተከሳሾ ከየካቲት 26/2004ዓ.ም ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ሃምሌ 6/2004ዓ.ም የተፈፀመውን ድርጊት አነሳስተዋል በማለት ነው) ውጭ በመሆኑ በዚህ ሊከሰሱ አይችልም፡፡

    22ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    የቡድን የሽብር አላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም አልቦ የሽብር ቡድኑ በ08/11/2004ዓ.ም አቅዶት በነበረው የሰደቃ ፕሮግራም የቅድመ ዝግጅት ላይ ተሳ-------የተባለው በተመለከተ የሽብር ቡድን የሚባል ቡድን የቱና በምን ህግ አግባብ ይህ ስያሜ እንደተሰጠው ያለረተገለፀ በመሆኑ ሀምሌ 8 ቀን 2004ዓ.ም ለመዘጋጀት የታሰበ የሰደቃ ዝግጅት ላይ መሳተፍ በወንጀል ሊያስከስስ አይችልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ በማንኛውም ሁኔታ ለክሱ ምክከነያት የሆነውን ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓዓም የተፈፀመ ድርጊት ለማነሳሳት የተደረገ -------------------አይደለም

    - በተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ ከየካቲት 26 ቀን 2004ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በፈፀሙት ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀመ ድርጊት አነሳስተዋል የሚል ነው ይሁን እንጂ ይ አስመልክቶ በተጨማሪ የተከሰሱበት ድድርጊት ተፈፀሙ የተባበሩት ከጥር 7 እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2004ዓ.ም ድረስ ተደርገዋል የተባሉ የስልክ ንግግሮች ናቸው ይህ ደግሞ ሐምሌ 6 ቀን የተፈፀመውን ድርጊት ምንም አይነት ተያያዥነት የሌለውና ይህን ያነሳሱ ናቸው ተብለው የቀረቡ ወይም ሊቀርቡ የሚችሉ አለመሆናቸውን በግልፅ ያረጋግጣል፡፡

    23ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽ የተከሰሰበትን ድርጊት ፈፀመ የተባለው ከሃምሌ 14-16 ቀን 2004ዓ. በመሆኑ ከዚህ ጊዜ በፊት ሀምሌ 6 ቀን የተፈፀመውን ድርጊት የሚያነሳሳ ነው በማለት ክስ ሊቀርብ አይችልም፡፡

    24ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    - ቀስቃሽ ግጥሞች ወደ መድረክ ማቅረብ (ጊዜው አልተገለፀም ….)

    - መስጊዱ መቆጣጠርና ሰዎን መፈተሸ በህግ የተከለከለ ካለመሆኑም በተጨማሪ ለወንጀል ድርጊት ማነሳሳት አይደለም

    - ከ28/08/04 እስከ 20/10/04 የተፈፀመ የተባለው የሚመለከተው የቤቱ መስጊዶችን ብቻ ነው (ሐምሌ 6/2004 በአዲስ አበባ ተፈፀመ ከተባለው ድርጊት ጋር ምንም ተያያዥነት የለውም

    25ኛውን ተከሳሽን በተመለከተ

    ክሱ የቀረበው ከየካቲት 26 ቀን 2004ዓ.ም በኃላ በተፈፀሙ ድርጊቶች ሀምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀመውን በክሱ ገፅ 20 ላይ የመለከቱትን ድርጊቶች እንዲፈፀሙ አነሳስተዋል በማለት ነው፡፡ በመሆኑም ከየካቲት 26 ቀን 2004ዓ.ም በፊትም ሆነ ከሃምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም የተፈፀሙ ድርጊቶች ክሱ የማይመለከታቸው ናቸው፡፡ ተከሳሽ ወሩ ባልታወቀበት በ2004ዓም የፈፀማቸው ናቸው የተባሉትን ድርጊቶች በተመለከተ የቀረበበት ክስ ይህ የሆነው ከላይ በተጠቀሰው ከየካቲት 26 እስከ ሀምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተፈፀመ ስለመሆኑ ያልታወቀ ስለሆነ ይህን መሰረት ያደረገ ክስ ሊቀርብበት አይችልም፡፡

    26ኛ ተከሳሽን በተመለከተ

    ተከሳሽን በተመለከተ ተፈፅመዋል የተባሉት ድርጊቶች በ2004ዓ.ም ወሩ ባልታወቀ ጊዜ እንዲሁም በሐምሌ ወር 2004ዓ.ም ቀኑ ባልታወቀ ጊዜ እንዲሁም በነሐሴ ወር 2004ዓ.ም የተፈፀሙ ናቸው ተብሎ የቀረቡ ናቸው ክሱ የቀረበው ደግሞ ከየካቲት 26 እስከ ሐምሌ 26 ቀን 2004ዓ.ም ተፈፀመ ለተባሉ ድርጊቶች በመሆኑ

    27ኛ እና 29 ተከሳሾች ሼህ አብዱረህማን ሁስማን እና ዶ/ሀጂ ከለቱን በተመለከተ (ባህሩ)

    27ኛ ተከሳሽ በቀረበባቸው የወንጀል ድርጊት ውስጥ መስጂድ መገንባት እና የሃይማኖት ትምህርት የሚገል ይገኝበታል ይህ ድርጊት በወንጀል ህግ የወንጀል ድርጊት ተብሎ የተቀመጠ አይደለም በኢፌድሪ ህገ መንግስት ማንም ሰው የማሰብና የህሊና ነፃነት የፈለገውን እምነት የመከተል መብት አለው እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን የማስተማር እና የመተግበር መብት እንዲሁ የሃይማኖት ተከታይ እምነቱን ለማስፋፋት እምነት ተቋማትን ማስፋፋትና መገንባት መብት አለው፡፡ ሆኖም በዐ/ሕግ የቀረበው ክስ 27ኛ ተከሳሽ ይህንን ህገመንግስታዊ መብት ተግባራዊ በማድረጋቸው የቀረበ ነው ከዚህ በተጨማሪ ዐ/ሕግ በፍትህ ሚ/ስር የሚተዳደር የመንግሰት መ/ቤት እንደመሆኑ በሚያቀርባቸው ክሶች ላይ ያንድን ሃይማኖት ተከታዮች (የእስልምና) ባስተሳሰባቸው ምክንያት አንዱን አክራሪ ሌላውን አክራሪ ያልሆነ በማለት መከፋፈል በህገ መንግስቱ የተከለከለው የመንግስት በሃይማኖት ጣልቃ የመግባት ስለሆነ ድርጊቱም እንደወንጀል ተግባር ተቆጥሮ ክስ ሊቀርብበት የሚገባ ስላልሆነ የቀረበባቸው ክሶች ውድቅ እንዲደረጉ እናመለክታለን፡፡

    27ኛ እና 29ኛ ተከሳሾች ሼህ አብዱራህማን ኡስማን እና ዶ/ር ከማል ሀጂ ገለቱ ን በተመለከተ
    27ኛ ተከሳሽ በቀረበባቸው የወንጀል ድርጊት ዝርዝር ውስጥ መስጂድ መገንባትና የሀይማኖት ትምህርት ማስተማር የሚል ይገኝበታል፤ ይህ ድርጊት በወንጀል ህግ የወንጀል ድርጊት ተብሎ የተቀመጠ አይደልም፡፡ በኢፌድሪ ህገመንግስት ማንም ሰው የማሰብና የህሊና ነጻነጽ፣የፈለገውን እምነት የመከተል መብት አለው፤ እምነቱን ለብቻ ወይም ከሎሎች ጋር በመሆን የማስተማር እና የመተግበር መብት እንዲሁም የሀይማኖት ተከታይ እምነቱን ለማስፋፋት እምነት ተቋማትን ማስፋፋትና መገንባት መበት አለው፡፡ ሆኖም በአቃቤ ህግ የቀረበው ክስ 27ኛ ተከሳሽ ይህንን ህገመንግስታዊ መብት ተግባራዊ በማድረጋቸው የቀረበ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቃቤ ህግ በፍትህ ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር የመንግስት መስሪያቤት እንደመሆኑ በሚያቀርባቸው ክሶች ላይ የአንድን ሀይማኖት ተከታዮች(የእስልምና) በአስተሳሰባቸው ምክንያት አንዱን አክራሪ ሌላውን አክራሪ ያልሆነ በማለት መከፋፈል በህገመንግስቱ የተከለከለው የመንግስት በሀይማኖት ጣልቃ መግባት ሰለሆነ ድርጊቱም እንደ ወንጀል ተግባር ተቆጥሮ ክስ ሊቀርብበት የሚገባ ስላልሆነ ከክሱ ውስጥ እንዲወጣ በአክብሮት እናመለክታለን፡፡

    ፍርድቤቱን የምንጠይቀው
    ከላይ ባቀረብናቸው የህግ እና የፍሬ ነገር ትንተና እና ክርክር መሰረት የተከበረው ፍ/ቤት

    1ኛ. አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ አግባብነት ባላቸው የወንጀል ህጎች እና የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ተከትሎ ያልቀረበ በመሆኑ እና በዚሁ ክስም የተገለጹት ድርጊቶች በወንጀል የማያስጠይቁ በህግ የተፈቀዱ መብቶች እና ተግባራት በመሆናቸው ተከሳሾችን ለመክስ የሚያበቃ በቂ ምክንያት የለም በማለት መዝገቡን ዘግቶ በነፃ እንዲሰናበቱ በአክብሮት እነጠይቃለን፤

    2ኛ. ፍርድ ቤቱ በበቂ ህጋዊ ምክንያት ከላይ ያቀረብነውን የማይቀበል ከሆነ ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ትእዛዝ እንዲሰጥልን በአክብሮት እናመለክታለን፡፡

    ሁለተኛው መቃወሚያ

    የኮ.መ.ቁ.124754
    ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት
    4ኛ ወንጀል ችሎት
    አ.አ

    ከሳሽ ..ፌዴራል ዐ/ሕግ
    ተከሳሾች …..እነ አቡበከር አህመድ (31 ሰዎች)

    በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.130እና በአዋጅ ቁጥር 25/88 መሠረት የቀረበ መቃወሚያ(የህጋዊነት ጥያቄ)
    የተከበረው ፍ/ቤት በተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ የተጠቀሰባቸው ህግ ህገ-መንግስታዊ ባለመሆኑ ክሱም የማያስከስስ ግልፅ ያልሆነ እና ተከሳሾች በዚህ ሁኔታ ክሱን አውቀውት ሊከላከሉ የማይችሉ መሆኑን በተመለከተ የሚከተለውን መቃወሚያ እናቀርባለን፡፡

    ሀ/ በተከሳሾች ላይ የተጠቀሰው ህግ (አዋጅ ቁጥር 652/2001) እና ክስ የኢትዮጵያን ህገ-መንግስት የሚቃረን ስለመሆኑ፡-

    1. የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀፅ 9(1) ‹‹ህገ-መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው፡፡ ማንኛውም ህግ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ-መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም ›› ይላል፡፡

    2. በዚሁ ህገ መንግስት አንቀፅ 9(4) ላይ ከህገ-መንግስቱ ጋር አኩል ደረጃ ኖሯቸው የሱ አንድ አካል ተደርገው ስራ ላይ ይውላሉ የተባሉት ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውና የፈረመቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች ድንጋጌዎችና ሰነዶች ሲሆኑ ከነዚሁ ውስጥም፡-

    2.1 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ቁጥር 217ኤ(11) የፀደቀው የሰብዐዊ መብቶች አለም አቀፋዊ መግለጫ ወይም በተለምዶ አነጋገር አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ

    2.2 በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ቁጥር 2200ኤ(xxi) ዲሴምበር 16 ቀን 1966ዓም እ.ኤ.አ. ፀድቆ አባል አገሮች እንዲያፀድቁትና እንዲቀበሉት ቀርቦ እ.ኤ.አ ማርች 23 ቀን 1976ዓም ስራ ላይ የዋለው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች አለም አቀፍ ቃል ኪዳን

    2.3 የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ቁጥር 39/46 መሰረት ወጥቶ አባል ሀገሮች ከፈረሙበት እና ካፀደቁት በኃላ እ.ኤ.አ ሰኔ 26 ቀን 1987ዓ.ም ስራ ላይ የዋለው ማሰቃየትና ሌሎች ጭካኔ የተሞላባቸው ኢ-ሰብዓዊና አዋራጅ አያያዞችንና ቅጣቶችን ለማስቀረት የተደረገ ስምምነት ይገኙበታል፡፡

    3. አዋጅ ቁጥር 652/2001 ደግሞ በህገ-መንግስቱና በነዚህ ሰነዶች ላይ ህገ-መንግስታዊ ጥበቃ ያገኙ መብቶችን እንዳለ በመሻር ከህገ-መንግስቱ ጋር ይቃረናል፡፡ የምንልበትን ነጥብ አጠር አጠር አድርገን እናቀርባለን፡፡

    3.1 በህገ-መንግስቱ ያንድ ሰው የመኖሪያ ቤቱና የግል ህይወቱ ያለ ፈቃድ አይደፈርም ይላል፡፡ ይህም ያለ ህግ አግባብ ወይም ያለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ አንድ በርባሪ ፖሊስ ወደ አንድ ግለሰብ ቤት መሄድ ያለመቻሉን ብቻ ሳይሆን ባለቤቱ ወይም የሚመለከታቸው የቤተሰቡ አባላት ከሌሉ ህጋዊ የብርበራ ፍቃድ የተሰጠው አካል ትቶ ይመለሳል እንጂ ፍቃድ አለኝ በሚል ብቻ እነሱ በሌሉበት ገብቶ ቤቱን እንዲበረብር ህጉ እንደማይፈቅድለት ያሳያል፡፡ ይህም የፍ/ቤት ትዕዛዝ እንኳ ባለቤቱ ቤቱ መፈተሹን እንዲያውቅ ማድረግን መነሻ በማድረግ የሚጀምረው የቤቱ ባለቤት እና በቤቱ ላይ የማዘዝ ብቸኛው ባለመብት እሱ መሆኑን ዕውቅና በመስጠት መጀመር ህገ-መንግስታዊ ግዴታ ስለሆነ ነው፡፡

    ፈቃጁ አካል (ፍ/ቤት) ያለው ስልጣን ባለቤቱን በትዕዛዙ መሰረት ለመፍቀድ ትገደዳለህ ማለት እንጂ ወይም ያለባለቤቱ ፍቃድ ቤቱን የግል ህይወቱ የሚደፈርበት ምክንያት በፍ/ቤት ለዚህ እና ለዚያ አላማ ተፈቅዶልኝ ነው የምደፍረው በማለት ለባለቤቱ በርባሪው ፖሊስ ነግሮት እንዲፈትሽ ለማስቻል እንጂ ለሌላ ሶስተኛ ወገን በድብቅ እና ባለቤቱ በሌለበት እንደሌባ ተደብቆ ባለቤቱ ስለመደረጉ አሁንም ይሁን ወደፊት ሊያውቅ በማይችልበት ሁኔታ ስር ቤቱንና የግል ህይወቱን ለመድፈር መብት የሚሰጥ አይደለም፡፡ በድብቅ ፍተሻ (ብርበራን) መፍቀድ ለባለቤቱ ቤቱ ሊፈተሽ ስለመሆኑ ሳይነገር ሳያስታውቁ መፈተሽን ማስቻል ለዚህ መብት ዕውቅና መንፈግና ትርጉሙም በአንድ ሰው የግልና የቤተሰብ ህይወት ላይ ሌላ አካል ሊያዝበት ይችላል ማለት ነው፡፡ ያንን መፍቀድ ነው፡፡ ከሰው ክቡርነት (human dignity) የሚነሳውን ባለቤቱን (መፈተሹን) የማሳወቅ ሀሳብ በመቃረን በድብቅና መሳሪያ በማኖር መረጃ መሰብሰብን የሚፈቅድ አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 18 ህገ-መንግስቱንና የሰውን ክብር ይቃረናል፡፡

    3.2 ይህ አዋጅ ያለ ባለቤቱ እውቅና የማንንም ዜጋ (ሰው) ቤት መበርበርን፣ የግል ህይወትና መኖሪያ ቤቱን መድፈርን ብቻ ሳይሆን፣ ያለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ መያዝንና ማሰርን ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መልኩ የደምና የፀጉር(አካላዊ) ነገሩን በጉልበት ጭምር ናሙና መውሰድን (አንቀፅ 21) ክብሩን መድፈርን መልካም ስሙን መንካትን በአካሉ ላይ ጉዳት ማድረስን የመላላክ ግንኙነቱን መድፈርን፣ ከፍርድ በፊት ንፁህ ሆኖ የመገመት እና በህግ ፊት እኩል መታየትን፣ ተገቢ አካሄድን በተከተለ የክርክር ሂደት ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ያለን የህግ ሽፋን (due process of law) በእኩል ደረጃ አግኝቶ የመጠቀምን መብት በመደምሰስ ከህገ-መንግስቱ ይቃረናል፡፡ ማንም ሰው በምን እንደተከሰሰና ማንና ምን ማስረጃ እንደሚደረጉበት አውቆ ራሱን የመከላከል መብቱን በድብቅና ተደብቆ በሚቀርብበትና ከየትም በየትኛውም መንገድ በተገኘ ማስረጃ ትዳኛለህ በማለት መብቱን ገፍፏል አሁን በዚህ ጉዳይ እንኳ ማን ምስክር እንደሚሆንብን አናውቅም፡፡ ስላላቸው ተአማኒነት ጨምሮ የቀረበብንን አውቀን ለማዘጋጀት አልቻልንም፡፡ ህጉ በዚህም ለመንግስት(ዐ/ሕግ) የተሻለ ድጋፍ ሰጥቶ እኩልነታችንን አዛብቷል፡፡ በህገ-መንግስቱ ጥበቃ የተደረገለትን የተከሰሱ ሰዎች መብት ተመጣጣኝና ህገ-መንግስታዊ ላልሆነ የምስክሮች ደህንነት በሚል አባባል ጥሶታል፡፡ ገድቦታል፡፡ አሳንሶታል፡፡ ይህም አዋጁ ፍፁም ህገ-መንግስቱን የሚቃረን ብቻ ሳይሆን ህገ-መንግስታዊ ጥበቃ ያገኙ መብቶችን በሌላ ህግ መጣስን ለማለማመድ የወጣ ያስመስለዋል፡፡ ያደርገዋልም፡፡

    3.3 በዚህ አዋጅ ወንጀል የተደረገው (የሚያስቀጣው) ሀሳብ (intention) እንጂ መገለፅ (manifestation) አይደለም፡፡ ለምሳሌም ህጉ ስለማነሳሳት የሰጠውን ትርጉም ማየት ይበቃል፡፡ ይህም አንድን ሀሳብ የመያዝ ነፃነትን ቀርቶ መገለፁ እንኳ ገና ለገና የሚያመጣውን አደጋ መሰረት አድርጎ አይገደብም (ሊገደብ አይችልም) የሚለውን የህገ-መንግስቱን አንቀፅ የሚቃረን ነው፡፡ ሌላው የህገመንግስቱ አንቀፅ ን 29ን የሚጥሱት የአዋጁ አንቀፅ 5(1)(ለ)ና6 ናቸው፡፡ የትኛውንም ሀሳብ መፈለግን መያዝን እና ማስተላለፍን የሚፈቅደውን ይህንን የህገመንግስቱን አንቀፅ የዚህ አዋጅ እነዚህ አንቀፆች እንደ ተራ ነገር ደፍጥጠውት አልፈዋል፡፡

    እነዚህ ብቻ ህጉ-ህገ-መንግስቱን ለመቃረኑ በቂ ማሳያዊ ናቸው እንጂ የዚህን አዋጅ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ያፈረሰ (የጣሰ) መሆን ለተከበረው ፍ/ቤት እንደሚከተለው እናስረዳለን፡፡

    3.4 ህገ-መንግስት የመንግስት ስልጣን የሚገድብ የሚወስንና በዜጎች ነፃነት ወዘተ ላይ ያላቸውን ወሰን ዳርድንበር የሚከልል የሚያሰምር ቦታ ደልዳይ የበላይ ህግ ነው፡፡ መሰረቱ የመንግስትን የአቅም ወሰን በመገደብ (በማበጀት) ወደ ዜጎች መብቶች ሊጠጉ የሚችሉበትን የመጨረሻን ገደብ በመንግስትና ባለስልጣኖቻቸው ላይ በማስቀመጥ ለዜጎች ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡ ህገ-መንግስት በመሰረቱ የመንግስትን ስልጣን ገዳቢ ለዜጎች ዋስትና ሰጪ ህግ ነው፡፡ ስለሆነም ህገ-መንግስት የሚጠበቀው በህዝብ ሆኖ ከመንግስት (ጥሰት) እንጂ የተገላቢጦሽ አይደለም፡፡ ህገ-መንግስት የሚጥሰው መንግስት እንጂ ህዝብ ሊሆን አይችለም፡፡

    3.5 መንግስት ሲባል ህግ አውጪውን፣ ህግ አስፈፃሚውንና የዳኝነት አካሉን የሚጠቀልል ሲሆን የነዚህ ስልጣንና ተግባር ደግሞ በህገ-መንግስቱ ላይ ተወስኖ የተቀመጠ ነው፡፡

    3.6 ህገ-መንግስቱ የሚሻሻለውም ሆነ የሚቀነስበትም ሆነ የሚጨመርበት በራሱ በህገ-መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት ብቻ ነው፡፡ ማንም ወገን ከዚያ ውጭ በህገ-መንግስቱ ላይ የሌለውን ስልጣን ተጠቅሞ ቢሰራ ለምሳሌ ፓርላማው የመዳኘት ስልጣንን የራሱ የሚያደርግ ህግ ቢያወጣ ህገ-መንግስቱን ማሻሻል ስለሚሆንና አንድን የህግ ክፍል በመጨመርም ይሁን በመቀነስ መንካት ህጉን እንዳለ መናድ ስለሆነ በተለይ የህዝብ ፍላጎት ነው የተባለን እንደ ህገ-መንግስት ያለን ይቅርና ህግ in totality እንደ አንድ ነገር (entity) ስለሚታይ አንድ ክፍሉን መንካቱ ህጉን መናድ ስለሆነ ይህም ህገ-መንግስቱን መናድ ነው፡፡

    3.7 በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ለፍ/ቤት ብቻ ነው፡፡ ፍ/ቤቱም በአግባቡ with due process of law በህገ መንግስቱ በተፈቀዱ ማስረጃዎች መሰረት ይዳኛል ይፈረጃል ፡፡ ይህ የኢትየጵያ ህገ-መንግስት አንቀፅ ----- በግልፅ ያስቀመጠው ነው፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ስር ይህ የዳኝነት ስልጣን ለሌላ ለምሳሌ ለህግ-አውጪው የመንግስት አካል ይሰጣል (ሊሰጥ ይችላል) የሚል አንዳችም አንቀፅ በህገ መንግስቱ ውስጥ የለም፡፡ መዳኘት ሁለቱንም ወገኖች መስማትን ማከራከርን ተገቢውን የህግ አካሄድ (due process of law) መጠበቅን በሁለቱም ወገኖች የቀረበን ማስረጃ መመዘንን (በህግ ፊት እኩል ሆኖ የመቆጠርና በእኩልና ባግባቡ የመሰማትን የመዳኘትን ራስን የመከላከል ወዘተ መብት ህገ-መንግስታዊ መብት በመሆኑና እነዚህን ሁሉ የመፈፀም ችሎታ ደግሞ የፍ/ቤትና የመሰል የዳኝነት አካላት ተገቢ ስራ ወይም በነሱ ብቻ ሊሰራ የሚችልና የሚገባ በመሆኑ ነው፡፡

    ህገ-መንግስቱ ይህንን ስራ ለፍ/ቤት ብቻ የሰጠው ፓርላማው ይዳኝ ይፈርጅ ቢባል ህጉን ማን ያወጣለት ብቻ ሳይሆን ማን ባወጣው ህግ የሚለውም አለና ነው (ራሱ ባወጣው ህግ ራሱ ከዳኘ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነውና ምንቀረው) ስለሆነም ዳኝነት የፍ/ቤት ስልጣን ነው፡፡ መፈረጅም ዳኝነት ነው፡፡
    3.8 ይሁን እንጂ በተከሳሾች ላይ በቀረበው ለቀረበው ክስ መሰረት የሆነው አዋጅ ቁጥር 652/2001 በአንቀፅ 25 መሰረት የተወካዮች ም/ቤት አንድን ድርጅት በሽብርተኝነት የመሰየምና የሽብርተኝነቱን ስያሜውን የመሰየምንና የመሻር ስልጣን እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡ ይህንን ሁልጊዜም የፍ/ቤትና የፍ/ቤት ብቻ እንዲሆን የተፈለገውን የመዳኘት (የመፈረጅ) ስልጣን ህገ-መንግስቱ በአንቀፅ 55 ስር 20ኛው ስልጣኑ አድርጎ ለህግ -አውጪው አካል ያልሰጠው አብላጫ መቀመጫ ኖሮት ፓርላማውን የሞላ አንድ ፓርቲ በፈለገው ጊዜ የፈለገውን ፓርቲ ቡድን ግለሰብ እየፈረጀ ከሀገርና ከፓለቲካ መድረኩ ለማባረር እንዳይችል ለዜጎች ጥበቃ ስላደረገ ነው ወይም ይህንን ስለፈለገ ወይም ህገ መንግስታዊ ዋስትና (ጥበቃ)የሚባለውም ይሄው ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ያንን ቢፈልግ ኖሮ ያኔውኑ ሲወጣ የመፈረጅ ስልጣን የፓርላማውነው የሚል አንቀፅ በያዘ (በኖረው) ነበር፡፡ ነገር ግን በህገ-መንግስቱ ለፓርላማው (ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት) የተሰጠው ስልጣንና ተግባራት በአንቀፅ 55 ስር የተዘረዘሩት 19 ስልጣንና ተግባራት ብቻ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ፓርላማው ሌላ ስልጣን እንደአስፈላጊነቱ ለራሱ የሚጨምር ህግ ሊያወጣ ይችላል የሚል የለም፡፡

    - ፓርላማው በዚህ ህገ መንግስት መሰረት በአንቀፅ 55 ስር በተዘረዘረው መሰረት ይሰራል ህግ ያወጣል ነው የተባለው እንጂ የራሱን ስልጣን ህገ-መንግስቱ አስቀድሞ ያልሰጠውን ሊያክልለት የሚያስችለውን ህግ ያወጣል አላለም፡፡

    - ፓርላማው ይህን አዋጅ ሲያወጣ (በማውጣት) ያደረገው ነገር ህገ-መንግስቱን በአዋጅ አሻሽሎ ከናንተ ከፍ/ቤት አንድ ስልጣን ነጥቆ በዚህም ህገ- መንግስቱን በራሱ በህገ-መንግስቱ ላይ ህገ-መንግስቱ እንዴት መሻሻል እንዳለበት በአንቀፅ 104 እና 105 ላይ የተቀመጠውን በመተላለፍ በአዋጅ አሻሽሏል፡፡ ለራሱ ቀድሞ ያልነበረውን (አንቀፅ 55) ላይ አንድ ስልጣን ጨምሯል፡፡ ከፍ/ቤት ላይ አንድ ስልጣን ቀንሷል ይህ ህገ-መንግስቱን መጣስና ስርዓቱን መናድ ነው ህግ በአጠቃላይ(in its totality) ስለሚታይ ህግ አሁን በ1987 የወጣው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እንዳለ መኖር እንደነበረበት የለም፡፡

    3.9 በኢትዮጵያ የህገ መንግስት አንቀፅ 55 የፓርላማውን ስልጣን ደልድሏል ህግ የሚወጣው በህገ መንግስቱ ድልድል እና በሱ መሰረት ብቻ መሆን አለበት፡፡ በነዚህ 19 ስልጣኖቹ ላይ ከሌላ የመንግስት አካልም ቆርሶ ይሁን ከውጭ አምጥቶ (ስልጣኑን ተጠቅሞ በህገ-መንግስቱ ለምሳሌ ለፍ/ቤት ብቻ የተሰጠን የዳኝነት ስልጣን ለራሱ ለፓርላማው የሚሰጥ ህግ ቢወጣ አስቀድሞ በህገ-መንግስቱ ያልተሰጠውን ስልጣን የስልጣን ድልድል ለራሱ መውሰዱ (መጨመሩ) ስለሚሆን ይህም ህገ-መንግስቱን በህገ-መንግስቱ ላይ በተቀመጠው አንቀፅ 104 እና 105 መሰረት በማሻሻል ብቻ ሊጨመር የሚችልን ነገር ከዚያ ውጪ ለራሱ በመውሰድ ከህገ መንግስታዊ አካሄድ ውጭ ህገ መንግስቱን ያለስልጣኑ መለወጥ ነው፡፡ ይህም አሁን ደንበኞቻችን ሞከሩ የተባሉትን ህገ-መንግስትን በራሱ ላይ ካስቀመጠው ህገ-መንግስታዊ አካሄድ ውጭ የመለወጥ ድርጊትን መፈፀም ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መናድ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የሚባለው በህገ-መንግስቱ ላይ እንዴት እንደሚለወጥ ጨምሮ የተቀመጡትን አካሄዶች የጣሰ አካሄድን መከተል ወይም ከዚያ ውጪ መንግስት መመስረትን ጨምሮ መስራት ነው፡፡ አብላጫ መቀመጫ በፓርላማ ያለው ፓርቲ ህግ የማውጣት ስልጣን ያገኛል፡፡ መንግስትም ያቋቁማል፡፡ ሌላው ያንን ያላገኙ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንኑ ለማግኘት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ መንግስትን ይተቻል ይንቅፋል ካጠፉም ያለው ፓርቲ በፍ/ቤት በህጉ የተሰጡትን መብቶች በመጠቀም ተከራክሮ ይረታል ካጠፋ ይቀጣል ይፈጃል ይሰየማል፡፡ በህገ-መንግስቱ መንግስትን ያቋቋመም ሆነ ሌላው ፓርቲ እኩል ነው፡፡ ሁለቱም የሚንቀሳቀሱት የሚመሩትና የሚዳኙት በሱ ነው ሁሉም ያለውን ህገ መንግስት ራሱ ህገ-መንግስቱ ካለውና ካስቀመጠው መንገድ አይጨመርበትም አይቀንስበትም የሚለውን ተቀብለውና በሱ ተማምነው ነውና የሚሰሩት ለምሳሌ ከዚያ ውጭ ወጥቶ ስልጣን የያዘው ፓርቲ ፓርላማውን ሌሎችን ፓርቲዎች ዳኝቶ የመፈረጅ ስልጣን ቢሰጥ በፓርላማው ያሉትን አባላቶቹን ተጠቅሞ ወይም በራሱ የማይፈልገውን ወገን የመዳኘት ስልጣን አገኘ ማለት ነው፡፡ የፀረ -ሽብር አዋጁ ያደረገው ይህንነ ነው፡፡ ፓርላማው (አብላጫ መቀመጫ) በፓርላማ ያገኘ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ያልተመረጡትንና ማንኛቸውንም ያልተመቹትን ወገኖች ይህ ቡድን ሽብርተኛ ነው አይደለም ማለት ስለሚያስችለው ለፓርላማው በህገ-መንግስቱ ያልተሰጠውን የመፈረጅ የመሰየም (የዳኝነት) ስልጣን ይሰጠዋል፡፡ ይጨምርለታል ፓርቲም ሰው ነውና በህግ ፊት ሰው እኩል ነው የሚለውን ይጥሳል፡፡ ይህም የሚሆነው ሌሎቹን አስቀርቦ በማሰማትና ማስረጃቸውንና እነሱን በመመርመር መንገድ ባለመሆኑ(due process of law)ን ይጥሳል፡፡ ህገ - መንግስታዊ የህገ-መንግስት ማሻሻያ መንገድም ባለመሆኑ ስርዓቱን ይንዳል፡፡ ዛሬ ይህንን ካደረገ ነገ የሌለውን ስልጣን በመቀነስ ለራሱ በመጨመር ሌላ ህግ የማውጣት ስልጣኑን አይጠቀምበትም አይባልምና ዋስትና የለምና ያ እንዳይቻል ነው ህገ-መንግስቱ እንዴት እንደሚሻሻል በራሱ ውስጥ (ላይ) ያስቀመጠው፡፡ የህዝቡም ዘላቂ ዋስትና ያለው በዚህ ላይ ነው፡፡ ይሄምነው ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የሚባለው፡፡ ይህንን ማድረግ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መናድ ነው፡፡

    3.10 አንድ አዋጅ አንዱ ክፍሉ (አንቀፅ) ህገ-መንግስቱን አንቀፅ(ፆች) ጥሶት ቢገኝና ያ የአዋጁ አካል ክፍል (አንቀፅ) ህገ-መንግስቱን የሚቃረን ነው ተብሎ ትርጉም ቢጥስ ይህ መሆኑ አዋጁን እንዳለ ዋጋ ያሳጣዋል፡፡ ምክንያቱም አዋጅ የሚታየው እንዳለ እንደአንድ ነገር (entity) እንጂ በተናጠል አንቀፆች ስላልሆኑ ይህ አዋጅ እስካልተሻሻለ ድረስ ፍርስ (void) ነው፡፡ ይሆናል፡፡

    - የፓርላማን ስልጣን በህገ-መንግስቱ ሳይሆን በአዋጅ ጨምሮአል፡፡ የፓርላማውን ስልጣን መጨመር የሚቻለው ህገ-መንግስቱን በማሻሻል ብቻ ነው ያለበለዚያማ ይህ ከተቻለማ በየጊዜው በአዋጅ ለፓርላማው ስልጣን እየተጨመረ ስልጣኑ ያላግባብ ተለጥጦ ህገ-መንግስቱ ዋና አላማው የሆነውን የመንግስት አካላትን ስልጣን መገደብ እንዳይችልና እንዳይወጣ ያደርገዋል፡፡ ይህ አይነት አሰራር የጊዜ ጉዳይ እንጂ ህገ-መንግስቱን ሙሉ በሙሉ ዋጋ ያሳጣዋል፡፡ ይህ አሰራር የዜጎችን ህገ-መንግስታዊ (ጥበቃ) በማሳጣት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በገዘፈ ሁኔታ የመናድ ድርጊት ነው የተፈፀመው ህገ- መንግስታዊ ስርዓቱን የመናድ የተፈፀመው እና እየተፈፀመ ያለው በእንደነዚህ አይነቶቹ አዋጆች እንጂ በኛ ደንበኞች አይደለም፡፡

    3.11 የተከበረው ፍ/ቤት ዛሬ ጠበቆቻቸው ሆነን በዚህ ክቡር ችሎት ፊት መቃወሚያ እያቀረብንላቸው ያሉት እነዚህ ደንበኞቻችን (ተከሳሾች)ያለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ተይዘው ታስረው ከህግ አግባብ ውጭ ምርመራ ተፈፅሞባቸው በዚህም በጉልበትና ከህግ ውጭ በተገኘ ማስረጃ ተከሰው እዚህ ሊቀርቡ የቻሉት የህገ-መንግስታዊ ጥበቃቸውን የሻረው የነጠቃቸው ህገ-መንግስቱን ጥሶና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ንዶ የወጣው አዋጅ ቁጥር 652/2001 ሰለባ ሆነው እንጂ ምንም ያላጠፉ የተከበሩ አባቶች ምሁራን የሀገር ሽማግሌዎችና ለሁሉም ዜጋ በአርአያነት ሊወሰዱ የሚችሉ ዜጎች ናቸው፡፡ ህጉ ደግሞ ህገ-መንግስቱን በመቃረኑ ተፈፃሚ ስለማይሆን(በህገ መንግስቱ አንቀፅ 13 መሠረት ይህ ፍ/ቤት ይህን አዋጅ ተግባራዊ ያለማድረግ ግዴታ ስላለበት) በነፃ ሊሰናበቱ ይገባል፡፡ ያ የሚታለፍ ቢሆን በህገ መንግሰቱ አንቀፅ 92(2) መሰረት ለትርጉም ተልኮ እስኪመጣ ተከሳሾች ከእስር ውጭ እንዲሆኑ እንዲታዘዝልን በማክበር አመለክታለሁ፡፡

    ተፈጸመ

No comments:

Post a Comment