Sunday, December 16, 2012

ዛሬ በደሴ ከተማ ልዩ የዚያራ ፕሮግራም ተደረገ!!



ዛሬ በደሴ ከተማ ልዩ የዚያራ ፕሮግራም ተደረገ!!

መንግስት የሚያደርስበትን ጫና በመቋቋም ሰላማዊ ትግሉን ሲያካሂድ የቆየው የደሴ ህዝብ ዛሬም በማረሚያ ቤት ተገኝቶ ቆራጥነቱን እና ለዲኑ ያለውን ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል፡፡ በዛሬው የዚያራ መርሀ ግብር ላይ እጅግ በጣም ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ የተገኘ ሲሆን ከሀይቅና ከኮምቦልቻ ከተሞችም በዚያራው ፕሮግራም ላይ እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ያለምንም ክስ ከአራት ወር በላይ የታሰሩትን ውድ ኢማሞቹንና ወንድሞቹን ለመዘየር ህዝብ ቁጥር ገና ከጧቱ 2፡30 በማረሚያ ቤት የተገኘ ሲሆን በየጊዜው የህዝቡ ቁጥር ጨምሮ የማረሚያ ቤቱን ግቢ ሞልቶ ለሰልፍ እንኳን አስቸግሮ ነበር፡፡ ይህን የተገነዘቡት የማረሚያ ቤት አስተባባሪዎች ሙስሊሙን ለማንገላታት “ስንቅ ያልያዘ ይመለስ” በማለት ህዝቡን ሊበትኑ ቢሞክሩም በሙስሊሙ ቆራጥነት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዛሬው የዚያራ ፕሮግራም ላይ አንዳንድ ደህንነቶች በሰው መሃል ገብተው ችግር ለመፍጠር ቢሞክሩም ሙስሊሙ እስከዛሬ ድረስ ባሳየው የሰላም ወዳድነት ባህሪ ዛሬም በድጋሚ ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡

በዛሬው እለት የደሴ ሙስሊም ለኢማሞቹ ያለውን ፍቅር ከመግለፅ አልፎ ለአሚሮቹ ያለውን ታዛዥነትና አክብሮት በድጋሚ አሳይቶ አልፏል፡፡ መንግስት ምንም ያህል የሙስሊሙን ሰላም ለማደፍረስ ቢጥርም ሙስሊሙ ግን ዛሬም ፣ ነገም ምርጥ የሰላም አምባሳደር እንደሆነ እያሳየ ይገኛል፡፡ ይህን ምርጥ ትውልድ የሁሉም ጌታ የሆነው አላህ ይጠብቀው ዘንድ እንማፀንዋለን፡፡ በግፍ የታሰሩትን ኮሚቴዎቻችንን እንዲሁም ኢማሞቻችንን አላህ ነጃ ያውጣቸው፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment