Saturday, December 8, 2012

አገር አቀፍ የመረጃ እና የግምገማ ሳምንት

አገር አቀፍ የመረጃ እና የግምገማ ሳምንት

የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ታሪክ ዳግም ያደሰ፣ የሰላምንና ሰላማዊነት ምንነትን ተተግብሮ እንዲታይ ያደረገ፣ ለሃገርና ለህዝብ ሰላም ሲል ለስቃይና ለመከራ ራሱን አሳልፎ የሰጠ ትውልድ የታየበት፣ እየተበደሉም መብትን ከመጠየቅ የማይቆጠብ ፅኑ ህዝብ ያየንበት የኛ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ከተነሳ ድፍን አንድ አመት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት ቀሩት፡፡ ክብር እና አድናቆት የሚገባቸው የአወሊያ ተማሪዎች መጅሊሱ የወሰዳቸውን ሕግ ወጥ ተግባሮች በመቃወም ተቃውሞ ማሰማት የጀመሩበት ታኅሳስ 24/2004 አንድ ዓመት ሊሞላው ከሦስት ሳምንት ያልበለጠ ጊዜ ብቻ ይቀረዋል፡፡
እኛ ሙስሊሞች ብሎም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት ጥቂት አስርት አመታት ከመብት ጥያቄ ትግልና መርህ የታቀብን ከመሆናችን በተቃራኒ ብዙ እንግዳ ነገሮችን ለታሪክ አስቀምጠናል፡፡ በእኛ አገር ተጨባጭ ህዝብ ለአገር ደህንነትና ለመብት ሁሌም ይታገላል፡፡ አገርም አገር ነችና ትኖራለች፡፡ ህዝብም ህዝብ ነውና ትናንት የከፈለውን መሰዋእትነት ቀጣይ ትውልዱ እንዲያጣጥመው የህያው ስራውን አሻራ አስቀምጦ ያልፋል፡፡ መንግስታት ግን በተለይ በእኛ ሃገር ጥቁር ታሪካቸው ጎልቶ እንዲወሳ የሚሆኑበት የራሳቸው እኩይ ውርስ ያኖራሉ፡፡ የአሁኑ ሥርዓት ደግሞ እንደቀድሞዎቹ ይፋ ከወጣው አግላይ ፖሊሲና አንባገነን ስርአት በተለየ በዴሞክራሲ ለምድ የተጀቦነ ክፉኛ የጠለሸ ታሪክ ለማኖር ጠልፎ የሚጥል ሩጫውን ያለረፍት ተያይዞታል፡፡ እሱም መንግስት ነውና ያልፋል፡፡ እኛም ህዝብ ነንና ውርሳችንን እናኖራለን፡፡ አገርም አገር ነችና እንደከዚህ ቀደሞቹ የሁለታችንንም ታሪክ ለነገው ታቆይልናለች፡፡ በየትኛውም ሚዛን ቢመዘን ከትግል ሂደት አንፃር ከታየ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ወደ ድል መቃረባችንን መረዳት አይከብድም፡፡

ከአላህ እገዛ ጋር በውስጣችን እምቅ ኋይልና ገና ያልተከፈቱ ብዙ ርቀት ሊያስጉዙን የሚችሉ የትግል ምእራፎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በሚደርስብን ወሰን ያለፈ በደል ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ፍርሃትና መረበሽን ከውስጣችን አስወግደን መጪ ግዜያችንን መንግስት ከፈጠረው ተራና ጠፊ ድቅድቅ መሳይ ጨለማ ጀርባ ወደምናየው የድል ጮራ ያደርሱናል፡፡ ባሳለፍነው አንድ ዓመት የኢስላምንና የህዝብን አላማ አንግቦ ለተነሳ መሪ ፅኑ አጋር የሚሆንና ታሪካዊ ታጋይ ህዝብ ታይቷል፡፡ እኛ የዘመናችን ሙስሊሞችም በግዜያችን የሚጠበቀብንን ትግል ‹‹ሀ›› ብለን እንደመጀመራችን ተዝቆ የማያልቅ ስንቅም እየቋጠርን ነው፡፡ ታዲያ በዚህ የአንድ አመት ጉዞ ያሳለፍናቸው ሂደቶች በአግባቡ ሊመዘገቡና ሊገመገሙ ግድ ነው፡፡ ከውድ ኮሚቴዎቻችን የወረስነውም ይህንን ነው፡፡ ኮሚቴዎቻችን ትግላችን አሁን ምን ላይ ነው? እስካሁን ምን ሂደቶችን አሳለፈን? ቀጣይ አቅጣጫችን ምን ይሁን? እና መሰል ጥያቄዎችን ሳያነሱና ሳይመዝኑ ስንዝር ተራምደው አያውቁም፡፡ የሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎችና ለህትመት ያበቁት ‹‹እውነቱ ይህ ነው›› መጽሃፍም የጥያቄያችንን እውነታ ለህዝብ ከማሳየት ባለፍ ራስን ለመገምገምና ሂደታችንንም ለታሪክ ማኖርን ያለመ ነበር፡፡ ምን ያማሩ አስተዋይ መሪዎች!፡፡

ከኮሚቴዎቻችን መታሰር በኋላ እኛ እንደህዝብ ይበልጥ ህዝባዊነትና ሃገር ወዳድነት እንዲዳብር ቤዛ ስንሆን መንግስትም በበኩሉ መንግስታዊ ባህሪ ከህዝብ ልብ እንዲፋቅና የመንግስት ውሳኔ በጥቂት የውስጥ ቡድንተኞች እጅ እንዲወድቅ ገበናውን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ዜጎች የሚጠለሉበት ሳይሆን የሚሸሹት፣ የሚያማክሩት ሳይሆን እሱ የሚመክርባቸው፣ ሰብአዊ መብትን የሚያከብር ሳይሆን የሰብአዊ መብት ፅንሰ ሃሳብ በመዝገበቃላት ትርጉሙ ሳይቀር እንዲቀየር የሚሻ አስገራሚ የሚና መዘበራረቅ ውስጥ ገብቷል - በዚሁ ባሳለፍነው አንድ አመት፡፡ ይህ ግዜ በተለይ በይበልጥ ሊዘገብ ይገባል፡፡ ለዚህም ሲባል አጠቃላይ ሂደታችን ከፍተኛ ሊባል በሚችል ጥልቀት እየተገመገመና እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ በቀጣይም ያሳለፍነውን አንድ አመት አስመልክቶ መጽሃፍት፤ ዶክመንተሪ ሲዲዎችና ሌሎች ዘጋቢ መረጃዎች ይዘጋጃሉ፡፡ ለዚህ ስራ ደግሞ ባለቤቱ እናንተ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ናችሁ፡፡ ይህ ስራ የሁላችሁንም አስተያየት ማግኘት ይሻል፡፡ በመሆኑም፡-

1.ስናደርገው የነበረውን ትግልና ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በእርሶዎ ምልከታ እንዴት ይገመግሙታል?
2.በመብት ማስከበር የትግል ሂደታችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተገኙ መልካም ነገሮች ምንድን ናቸው?
3.የመንግስትን የአፀፋ ምላሽ እንዴት ያዩታል? በትግል ሂደታችንስ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለው ያምናሉ?
4.ከመብት ጥያቄዎቻችን ጋር በተያያዘ በየአካባቢያችን የደረሱ የመብት ጥሰቶች፣ የተደረጉ ህዝባዊ ትግሎች፣ የታዩ ትንግርታዊ ጀግንነቶችና ከግለሰብ እስከ ቡድን የተከፈሉ መሰዋእትነቶች፣ የታዩ ለየት ያሉ አሳዛኝና አስገራሚ ክስተቶች (ገጠመኞች) ምንድን ነበሩ?
5.እንዲሁም ህዝባችን እየከፈለ ካለው መሰዋእትነት አንፃር የሚያሳየውን አስደናቂ ፅናት እንዴት ይገልፁታል? ሌላ ሳይጠቀስ መታለፉ የሌለባቸውን ምልከታዎች ብታካፍሉን፡፡

እነዚህን አምስት ጥያቄዎች በመላ ሃገሪቱ የምንገኝ ሙስሊሞች ሁለትና ከዚያ በላይ በመሆን በመወያየት በድምፃችን ይሰማ የውስጥ መልእክት (Message) እንድትልኩልን እንጠይቃለን፡፡ መልእክቱን ስትልኩም የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ እንድትሉ እንጠይቃለን

•በነጥቦቹ ላይ ከግል አስተያየት ይልቅ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ተወያይተው የተስማሙበት ቢሆን ይመረጣል፡፡
•ግምገማውን አመቺ በሆነላችሁ የትኛውም ቋንቋ ብታዘጋጁት ይቻላል፡፡ በየአካባቢው ቋንቋ መዘጋጀቱም ስራውን ይበልጥ ስለሚያቀለው ይበረታታል፡፡
•ለግዜና ለተፈለገው አላማ ሲባል ግምገማዎቹ በተጠቀሱት ነጥቦች ላይ ብቻ እንዲያጠነጥኑ እንጠይቃለን
•ምላሹን የምትልኩልን እስከሚቀጥለው ሳምንት ጁምአ ታህሳስ 5 ድረስ ቢሆን ይመረጣል፡፡
•መልሱን ስትልኩልን ለድምፃችን ይሰማ የውስጥ መልእክት (Message) በመላክ እንጂ በፔጁ ላይ ፖስት በማድረግና በሌሎች የፌስቡክ ቡድኖች ላይ በመለጠፍ እንዲሁም በማወያየት አይደለም፡፡

የግምገማችን ውጤት ታሪካችንን በአግባቡ ለትውልድ ለማስተላለፍና ለቀጣይ ሂደቶችም ትምህርት ለመውሰድ አጋዥ ስለሚሆን በጥልቅ በማጤን በተጠቀሰው ግዜ ውስጥ እንድታደርሱን በአላህ ስም እንጠይቃለን፡፡

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment