በሰላማዊ ትግላችን አጋማሽ ወቅት ላይ የነበሩት የአንድነት እና የሰደቃ ፕሮግራሞች ትንግርታዊ ለእምነት ቀናኢነት የታየባቸው ወቅቶች ነበሩ፡፡ መላው ህዝባችን በአንድነት ፊቱን ወደ አላህ ያዞረበት፣ በደሉን ለሃያሎች ሃያል ለሆነው አላህ በሰደቃ ያቀረበበት፣ እውነተኛ የእምነት ፍቅር እና አስደናቂ የህዝብ ትስስር የታየበት ወቅትም ነበር፡፡ ያንን ወቅት በህሊናችሁ እስኪ ሳሉት፡፡ ወትሮም ዳር ዳሩን ሲያንዣብቡ የነበሩት የመንግስት ሃይሎች ድንገት መናደፍ የጀመሩትም ይህን የአንድነትና የሰደቃ ፕሮግራም ተከትሎ ነበር፡፡ ግን ለምን ይሆን? በርካታ መልሶች ቢኖሩም እነሱም እኛም የምናውቃቸውን ተጨባጭ ምክንያቶች በጥቂቱ እናያለን፡፡
አንድነት እና ሰደቃ ለበደልና በደለኞች ክፉ ጠላቶች ናቸው፡፡ አንድነት እና ሰደቃ ወደ አላህ ያቃርባል፡፡ ወደ አላህ የቀረበ ልብ ደግሞ ይበልጥ በፅናት ይተሳሰራል፡፡ ይህም ለመንግስት እረፍት የሚሰጥ አይደለም፡፡ በዳዮች የሚያደርሱብንን በደል ስለሚያውቁት በአንድነትና በሰደቃ መሽመድመዳቸውን ማየት አላስቻላቸውም፡፡ ይህ እውን እንዳይሆን የሰደቃ ፕሮግራሞችን ማጀት ገብተው ሊጥ በማስደፋት እና ከበረት የቁም ከብቶችን በመዝረፍ ማኮላሸት መንግስታዊ ስራ አደረጉት፡፡ ሁከት እና ዝርፊያ ህጋዊ የቢሮ አጀንዳቸው ሆነው ፋይል ተከፈተላቸው፡፡ የቀኑ ፀሃይ ሰላም ነስቷቸው ጨለማን ናፍቀው ሌት በፈጠሩት እረብሻ ሃገርና ህዝብ እረበሹ፡፡ ይህ እንግዲህ ከማይቀረው የአምላክ ተአምር ሽሽት መሆኑ ነው፡፡ የአላህ ፍርድ ይዘገይ ይሆናል እንጂ በበዳዮች ላይ መፈፀሙ ግን አይቀሬ ነው፡፡
እነዛ ድንቅ የአንድነት ፕሮግራሞች በሃገራችን ከተካሄዱ የህብረተሰብ ንቅናቄ ስራዎች ከግንባር ቀደሞቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ መንግስት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘቦችን እያፈሰሰ እና መላ መዋቅሩን ተጠቅሞ ሊያንቀሳቅሰው ያልቻለውን ህዝብ የሰደቃ ፕሮግራሞቹ ግን በቀላሉ ቻሉ፡፡ የሚደንቀው ደግሞ ህዝቡ በራሱ ጉልበት፣ ገንዘብና ንብረት ፕሮግራሞቹን ማካሄዱ ለመንግስት እረፍት የሚነሳ ነበር፡፡ በሰደቃና የአንድነት ፕሮግራሞቹ ምክንያት ውድ ኮሚቴዎቻችን እንደሃይማኖት መምህርነታቸውና ከመላው ሃገሪቱ ባሉ ሙስሊሞች በመወከላቸው ህዝብ የሰጣቸውን ሃላፊነት የት እንዳደረሱት ለማስረዳት ከአዲስ አበባ በመንቀሳቀሳቸው የሚፈጠረውን ህዝባዊ መነቃቃት ውጤቱን ያውቁት ነበር፡፡ የመብት ጥያቄያችንን የጥቂት ከተሜዎች ከዛም አልፎ የአወሊያ ስብስብ እያሉ ለማሳነስ ሲሮጡ የሰደቃ ፕሮግራሞች ግን ሊውጡት የሚመራቸውን እውነት ይፋ አወጣው፡፡ ጥያቄው ከከተሜው እኩል መላው ህዝባችንን ማነቃነቁን፡፡ የሰደቃውን ፕሮግራሞች ለማኮላሸት አንዱ ትልቅ ምክንያት ይህ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ፕሮግራሙን በማቋረጥ ግቡን መግታት ባይሳካላቸውም-ህዝቡ ዛሬም በእንድነትና በፅናት ተሳስሮ ዘልቋልና፡፡
በሃገር አቀፍ የሰደቃ ፕሮግራሞቹ ላይ ከሌላ እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ጋር የተፈጠረው የትብብር መንፈስ እነ ኢቲቪ የሚነዙትን ፕሮፖጋንዳ ሽባ አደረገው፡፡ በሚዲያ እንዲሰጋ የመከሩት ህዝበ ክርሰቲያን የንግስ ድንኳኑን አውጥቶ እንካችሁ በማለት በተቃራኒ ሆኖ ተገኘባቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ለነሱ በፍፁም የማይታለፍ ነበር፡፡ እናም የሰደቃና የአንድነት ፕሮግራሞችን ለማስቆም በሚደንቅ ሁኔታ የመንግስት ባለስልጣናት ስለሰደቃ ሰፊ ትንታኔ ሲሰጡ እና እነ ኢቲቪ የፈትዋ ቻናል የሆኑ ይመስል ስለሰደቃ ዳእዋ እና ፈትዋ ሲሰጥባቸው ከረሙ፡፡ በህግ አግባብ ተወክለው የህዝብን አደራ በሃቅ የተወጡ ወኪሎቻችን ያገኙት ህዝባዊ ቅቡልነት እና መንግስት በሚነዛቸው የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎች ህዝብ ዘንድ አመኔታ ማጣቱ በሰደቃ ፕሮግራሞች በመረጋገጡ ኮሚቴውን ለማስቆም ቀጣዩን ቀን እንኳን እንዲታገሱ አላስቻላቸውም፡፡ እናም ምክንያት ሲቆፍሩ አንድ ጉዳይ ቢያጡ በሰደቃና አንድነት ፕሮግራም ስም ህዝብን ለሽብር ቀሰቀሱ በሚል ሌላ እብለት ፈፀሙ፡፡ እነሱን ከብረት ጀርባ አውለው የመንግስትን መንግስታዊ ተክለሰውነት ከህዝብ ልብ ፋቁት፡፡
እኛ ግን ቀድሞም ሰደቃውን ያደረግንበት ምክንያት መንፈሳዊ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም መንፈሳዊነቱን ጠብቀን እንተገብረዋለን፡፡ አሁን ያለንበት ሳምንት የሰደቃና የአንድነት ሳምንት ተብሎ መሰየሙ የሚታወስ ሲሆን ለዚሁ የሚመጥኑ መርሃግብሮችም ተካተውበታል፡፡ ካለፉት ሳምንቶች በተለየ የያንዳንዳችን የነፍስወከፍ ተሳትፎን ለሚፈልጉት ተግባራት እራሳችንን እናዘጋጅ፡፡ ያኔ በሰደቃ ወደ ጌታችን ይበልጥ እንድንቃረብ ያደረገን በላዕ ዛሬም እንደተጋረጠብን ነው፡፡ በዳዮችን አላህ እጃቸውን እንዲይዝልን ስንማፀነው ዛሬም በዳዮች ድንበር አልፈዋል፡፡ አካላዊ ጉዳትን አልፈው ሃይማኖታዊ ማእዘናትና እሴቶቻችን ላይ እየዘመቱ ይገኛሉ፡፡ ‹በየመስኪዱ የምትጠሪው አላህ አሁን ይደርስልሽ ከሆነ እናያለን› ሲሉ እብሪተኝነታቸው ወሰን ተሻግሯል፡፡ አላህም በቃ እንዲለን በሰደቃ ወደሱ እንቃረባለን፡፡ ተአምሩን እንዲያሳየን በንፁህ ልብ እንቀርበዋለን፡፡ በሃላል ከስበን ካፈራነው ሰደቃ በማውጣት ከበደልና በደለኞች በቃ እንዲለን እንማፀነዋለን፡፡ ትናንት በዳዮችን ያንቀጠቀጠው መሳሪያ ዛሬም በጃችን ነው፡፡ አላህም የጠያቂዎችን እጅ በባዶ ለመመለስ የሚያፍር ጌታ ነው፡፡
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment