Wednesday, January 16, 2013

በአንድ አመቱ ሰላማዊ ጉዟችን የታለፉብን ህጎች

ድምፃችን ይሰማ
በአንድ አመቱ ሰላማዊ ጉዟችን የታለፉብን ህጎች
ክፍል አንድ
ከአንድ አመት በፊት የተጀመረው የህዝበ ሙስሊሙ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ በሁሉም እርምጃዎቹ ህጋዊ የሚባሉ አማራጮችን ብቻ ሲከተል ቆይቷል፡፡ ጥያቄዎቻችን ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄዎች፤ ያቀረብንበት መንገድና ወኪሎቻችን የመረጥንበት አካሄድም ፍፁም ህገ-መንግስታዊ ናቸው፡፡ ይህንን የህዝብ ጥያቄ በህግ አግባብ ሊመልስ የሚገደደው አካል ግን አክብሮ ሊያስከብራቸው የሚጠበቅበትን ህገ-መንግስታዊ መርሆዎችና ድንጋጌዎች ክፉኛ ለአደጋ አጋልጧቸዋል፡፡ እኛም በተከታታይ ክፍሎች የመብት ጥያቄዎቻችንን ተከትሎ የተጣሱ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን በጥቂቱ ለማየት እንሞክራለን፡፡
‹‹ሕገ-መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡›› ይህንን በህገ-መንግስቱ አንቀፅ ዘጠኝ ላይ ሰፍሮ ያገኙታል፡፡ የሃይማኖት አክራሪነትን በመከላከል ሽፋን በመንግስት እንደተረቀቀ የሚነገርለት ‹‹የሃይማኖት አክራሪነትና የህዳሴያችን ጉዞ›› ሰነድ የሙስሊሞችን የሃይማኖት እንቅስቃሴ በአክራሪነት ሽፋን ሙሉ ለሙሉ የሚገድብ ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ህገ-መንግስቱን የሚፃረሩ የሃይማኖት መብት እቀባ አቅጣጫዎችና ዕቅዶች ገና ከህዝብ እንደደረሱ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠሟቸዋል፡፡

ሰነዱ ከህገ-መንግስቱ ማፈንገጡን የሚያውቁት ሹማምንት ግን ዞር ብሎ ለመመልከት ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ በቀጣይም በስራዎቻቸው እንደተረዳነው ‹‹ሰነዳችን ከህገ-መንግስት መቃረኑን ካመንን ህገ-መንግስቱን እንቀይረዋለን እንጂ እቅዳችንን እንተገብራለን›› ነበር መልሳቸው፡፡ ኋላ ላይ ከየፀሎት ቤቱ እያፈሱ እስር ላጋዟቸው ፍትህ ጠያቂዎች ‹‹ህገ መንግስት እያልክ አትጩህ ከኛ ፍቃድ ውጭ የምትፈፀም አንዲትም ነገር አትኖርም›› ሲሉ ስንቶች የተዋደቁለትን ህገ-መንግስት ክፉኛ አኮሰሱት፡፡ እነሱ በማይመሩበት ህግ ሃገር እንዴት ሊመሩ እንደሚችሉም ለህዝብ ግልጽ አይደለም፡፡
‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም›› ይህ የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 11 ለማንም ግልፅ በሆነ መንገድ ነበር የተቀመጠው፡፡ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስም ህገ-መንግስቱ ካስገኛቸው አዎንታዊ ለውጦች ጋር ተደምሮ ሲቆጠር ቆይቷል፡፡ የመጅሊስ በእጅ-አዙር በመንግስት መሾፈርና አይን ያወጣው የነዶክተር ሽፈራው ከሊባኖስ የአህባሽ አንጃ ግብዣና ጠመቃ ጋር ሲያያዝ እነዚህ አንቀፆች ዛሬ ላይ የተወረወሩበትን ሸለቆ ጥልቀት ማንም ሊረዳው የሚችል ሃቅ ነው፡፡ እነዚህን ትእይንቶች ተንተርሶ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል ሳይሆን ከእነ ሙሉ አካሉ ሃይማኖት ውስጥ ጠልቆ ገብቷልም ሲባል ነበር፡፡ እናም ብዙ ግዜ በዚህ አናጠፋም፡፡ የዚህ ወሳኝ ህገ-መንግስታዊ መርህ መጣስ ያስከተላቸውን መዘዞች ግን አለፍ አለፍ እያልን እንመለከታለን፡፡
ፍትህ ስለማግኘት መብት የሚያትተው የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 37 ‹‹ማንኛውም ቡድን ወይም ተመሳሳይ ጥቅም ያላቸውን ሰዎች የሚወክል ግለሰብ ወይም የቡድን አባል በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለ›› ይላል፡፡ የህግ ጥሰቱ እዚህ ጋር ሀ ብሎ ይጀምራል፡፡ ያለማንም ቀስቃሽና ግፊት ከመላው ሃገሪቱ ያለን ሙስሊሞች ኮሚቴዎቻችንን ስንወክል ሁላችንንም የሚያመሳስሉንን ጥያቄዎቻችን በሃገሪቱ የሚገኙ ህጋዊ አካላት ጋር በማድረስ መፍትሄ እንዲያመጡልን ነበር፡፡ ይህ ውክልና ጥያቄያችንን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እስከማቅረብና በፍርድ ሂደትም እልባት ማስገኘትን የሚጨምር ነው፡፡
በመሰረቱ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 9/1 ድንጋጌ መሰረት ከህገ-መንግስቱ ጋር በሚቃረን ውሳኔ መሰረት የዜጎች ህገመንግስታዊ መብቶችና ነፃነቶች በመንግስት አካላትና ባለስልጣኖቻቸው ተገቢ ያልሆነ አሰራር ቢጣሱ በህገመንግስታችን አንቀፅ 62/1 እና 83/1 መሰረት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ ስልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ነው፡፡ የኛ ኮሚቴዎችም ሰላማዊውን የህዝብ ጥያቄ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ በኋላ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የማቅረብ ውሳኔ ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ከየካቲት 26 በኋላ በህግ አግባብ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ኮሚቴዎቻችንም ህግን አከበሩ እንጂ ሌላ የተላለፉት አንዲትም የህግ ድንበር አልነበረም፡፡ በኛ ላይ የተሰራው ግን ከየካቲት 26 ህዝብን የማጭበርበር ሙከራ በኋላ ኮሚቴዎቻችን ጉዳያችንን ለሌሎች የፍትህ አካላት እንዳያደርሱ መንገድ ተዘጋ፡፡ ፍትህ ሊያሰፍኑ የሚገባቸው አካላት የፍትህ ጋሬጣ ሆኑ፡፡ ፍትህ ጠያቂዎች ደግሞ ህግ ተጥሶባቸው ወህኒ ተወረወሩ፤ አስከፊ ግፍም ተፈፀመባቸው፡፡ ህገ-መንግስቱም አውቀው በጣሱት ባለስልጣኖች አማካኝነት የዜጎች ከለላ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ገባ፡፡
ክፍል ሁለት
በሰላማዊ ትግላችን ውስጥ የተፈፀሙትን የህገ-መንግስት ድንጋጌዎች ጥሰት መቃኘት ቀጥለናል፡፡ አንቀጽ 15 ደግሞ ‹‹ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም›› ይለናል፡፡ የመኖሪያ አድራሻው በውል የሚታወቅን አንድን ግለሰብ በወንጀል የጠረጠረ የህግ አካል እንዴት በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳለበት ካላወቀ ያሰማራውን አካል ለአቅም ማነሱ ይክሰስ፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች የጁመዓ ስግደትን አጠናቀው ሲወጡ ሆን ተብሎ ለማበጣበጥ ከመሃል ገብቶ ተጠርጣሪን በመያዝ ስም ሁከት መፍጠር ግን የመንግስት ሳይሆን የሽፍታ ስራ ነው፡፡ በአርሲዋ አሳሳ የተደረገውም ይሄው ነው፡፡ በዚህ አስቀድሞ በተጠና እና ዝግጅት በተደረገበት ሴራ አንድ ተጠርጣሪን በመያዝ ሰበብ አራት የንፁሃንን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ሙሳ ገቢ እድሜ 13፣ ከማል አሪኖ እድሜ 60፣ አልዩ ዋቆ እድሜ 40 እና ሻፊ ጃኖ እድሜ 35 የሆኑ የእምነት ወንድሞቻችን ከተማዋ ውስጥ አስቀድመው ገብተው በመሸጉ የፌዴራል ፖሊሶች ተገድለዋል፡፡
በገርባ የተፈፀመው ከዚህ በይበልጥ የተቀናበረ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የስድስት ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውና አንዱን በህግ ጥበቃ ስር ከዋል በኋላ በርሸና የተፈፀው ጭፍጨፋ ‹‹አክራሪዎችን ገደልኩ›› ብሎ ከመፎከር ባለፍ በየትኛው ወንጀልና በየትኛው ፍርድ ቤት ትእዛዝ እንደተፈፀመ ሊነግረን የሚደፍር የለም፡፡ የ 7 አመት ህፃንን ጨምሮ መንግስት ያላመናቸው ሌሎች ሁለት ሰዎች ነፍስ የጠፋበት የሃረሩ ግድያ አስቀድሞ የታቀደ ቢሆንም እንደታሰበው አለመሳካቱ በቂ ፕሮፖጋንዳ እንኳን ሳይሰሩበት እንዲያልፉ አስገድዷቸዋል፡፡
‹‹ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡›› ይህን አንቀፅ 16ን ስናነብ አንቀፁን የያዘው መፅሃፍ አፍ አውጥቶ እየቀለደ አንደሆነ እንገምታለን፡፡ በአንድ አመት ጉዟችን የፀጥታ ሃይሎች በአካል ላይ ጉዳት ማድረስን ከክልከላ ሳይሆን ካልፈፀሙት የሚያስቀጣ ተግባር አድርገው እንደሚወስዱት አውቀናል፡፡ የተጣራ መረጃውን በሌላ ግዜ የምናሳውቅ ሲሆን እስከአሁን እጃችን ላይ በደረሰን መረጃ መሰረት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ከመብት ጥያቄአችን ጋር በተያያዘ ደርሶብናል፡፡ ከዚህም ውስጥ ሴቶች፣ ህፃናትና አዛውንት ቀላል የማይባለውን ድርሻ ይዘዋል፡፡
በየሳምንቱ የሚካሄዱ የጁመአ ተቃውሞዎች ለድብደባ መነሻ ከሌላቸው ‹‹የፀጥታ ሃይሎች›› ዱላና ሰደፋቸው ቅር ከሚሰኝ ሰግዳ የምትመለስን ነፍሰጡር መደብደብ ወይንም አባቱ ጠፍቶበት በፍለጋ ላይ ያለን ህፃን በዱላ መቀባበል ምርጫቸው አድርገውታል፡፡ ከዚህ ተግባራቸው የሚያስቆማቸው የፍትህ አካልም አልተገኘም፡፡ ይህም ችግሩን የፀጥታ አስከባሪዎች ግለሰባዊ ስህተት ከመሆኑ ይልቅ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች አደጋ ላይ እንዳሉ የሚያሳይ ነው፡፡ የነዚህ አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣት ማለት ህገ-መንግስታዊ ስርአቱ በአግባቡ አለመተግበሩን ከዚህም አልፎ ሊያስከብሩት በቆሙ አካላት ለአደጋ መጋለጡን ነው የሚያሳየው፡፡
ሌላው ባሳለፍነው አንድ አመት እንዳልነበር ተደርጎ የተጣሰው የህገ-መንግሰቱ ድንጋጌ ‹‹የነጻነት መብት›› ተብሎ የተቀመጠው አንቀጽ 17/2/ ነው፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም›› ይለናል ይኸው አንቀፅ፡፡ የመብት ጥሰትን ስንቃወም በገፍ መታሰርን ከመላመዳችን የተነሳ ይህን መሰል አንቀፅ በህገመንግስቱ መኖሩንም ዘንግተነዋል፡፡ ተግብረው ሊያስተምሩን የሚገባቸው የፍትህ አካላትም ለህገ-መንግስታዊ ስርአቱ መጠናከር ያለባቸው ሃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ቸል ብለው መጣሱን ስራዬ ብለው ይዘውታል፡፡ በየቀኑ በገፍ ከሚያስሯቸው ሰዎች ብዛት ትክክለኛው የምርመራ ሂደትም ሆነ የእስረኛ አያያዝ የማይታሰብ ነው፡፡ መደበኛ ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች ያለምንም ቅድመሁኔታ እንዲፈቱ ህጉ ቢያዝም ከደርዘን በላይ የሚሆኑት ለምን እንደታሰሩ እንኳን ሳያውቁ ታጉረው ይገኛሉ፡፡
ለችግር እና አደጋ የተጋለጡ ታሳሪዎች ልዩ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ህጉ ቢያዝም ባል የተገደለባትን ንፁህ አራስ ሴት በእስር ቤት ከትቶ የህክምና እድልን መንጠቅ ነው በግልፅ የተፈፀመው፡፡ በአንቀጽ 79/3/ ላይ ‹‹ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነጻነት ያከናውናሉ፡፡ ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩ›› የሚል ውብ አንቀፅ ቢቀመጥም ደህንነት እንደፈለገ የሚያዝባቸው የፍርድ ሂደቶች በይፋ እየተፈፀሙ ነው፡፡ ለታሳሪዎች ደህንነት ስንል የቦታ ስም ባንጠቅስም ዳኞች በነፃ ያሰናበቷቸው እስረኞች ያለክስ ለወራት በእስር ማቆየት ከዚህም አልፎ ፍትሃዊ ሆኖ በተገኘ ዳኛ የተሰጠን ውሳኔ ወገንተኛ ዳኛ ወዳለበት አዙሮ ዳግም ማስፈረድ ማን ማንን እያዘዘ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ህገ-መንግስቱም ሊያስጠብቁት በቆሙለት አካላት እየተጣሰ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
የህገ-መንግስቱ የበላይነት የሚረጋገጠው ህገመንግስቱ መብታቸውን ያስጠበቀላቸው አካላት ሲከበርላቸውና የሚጥሱት ደግሞ በህገመንግስቱ መሰረት ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊረጋገጥ የሚችለው የመንግስት አካላት ለህገመንግስቱ በታማኝነትና በፅናት ሲቆሙ ነው፡፡ በአንድ አመት ጉዟችን የዚህ ወሳኝ መርህ የከፋ አደጋ ላይ እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ ዜጎችም ባፀደቁት ህገመንግስት አለመተግበር ምክንያት ደህንነት ፈፅሞ እየተሰማቸው አይደለም፡፡ ቀጣዩን እንመለስበታለን፡፡
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment