Thursday, January 10, 2013

ዚያራ

ዚያራ

ኢስላም እንደ እምነት የህይወት መርህ ሆኖ ለሰው ዘር የተበረከተ ፀጋ ነው፡፡ በውስጡም የዚህ ፀጋ አካል ሆነው የተሰደሩ በርካታ ተግባር ተኮር እሴቶች አሉት፡፡ አብዛኛዎቹ ተግባራት እውን ሲሆኑ መጨረሻቸው የሙስሊሙን ወንድማማችነትና አንድነት ጠንካራ በሆነ ገመድ ማስተሳሰር ይሆናል፡፡ ዘር፣ ቋንቋ፣ ቀለም፣ ብሔርና መሰል ልዩነቶች ደምቀው የማንነት መለያ እና መተዋወቂያ ይሆናሉ፡፡

የሰው ልጅ በተፈጥሮው አብሮነትን፣ ጓደኝነትን፣ ቅርርብን፣ መወዳጀትን ይወዳል፡፡ ኢስላም እንደ እምነት የአብሮነት፣ የፍቅር እና የሰላም መንገድ እንደመሆኑ መጠን ማሕበራዊ ግንኙነቶችንና በሰዎች መካከል ቤተሰባዊነትን የአስትምህሮቱ መሰረታዊ አካል በማድረግ ያስቀምጣል፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ብቻውን መሆን ከሚያበዛ ሰው ሰዎች ጋር የሚቀላቀልን ሰው ይወዳሉ፡፡ ኢብን ማጃህ በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ማለታቸው ተጠቅሷል ‹‹በሰዎች መሀል አብሮ የሚሆንና ችግራቸውን የሚካፈል አማኝ ብቻውን ከሚሆን፣ የሰዎችን ጉዳትም ከማይካፈል አማኝ የተሻለ ነው፡፡››
ዚያራ (ሰዎችን በተለያዩ መልኮች መጎብኘት) በእስልምና ተወዳጅ ዒባዳ ነው፡፡ ዚያራ ማህበረሰባዊነትን እውን የማድረጊያ አይነተኛ አጋዥ መሳሪያ ነው፡፡ ዚያራ ያማረ ጉድኝት ይፈጥራል፣ መዋድድን ያበረታል፣ ግንኙነትን ያጠነክራል፣ ዝንጉዎችን ያስታውሳል፣ የራቁትን ያቀርባል፣ ነፍስያንም ያድሳል… ሀዘንን፣ ጭንቀትን፣ ትካዜን ያርቃል፡፡
ኢስላማዊው የዚያራ ትንታኔ እና በተጨባጭ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ባሳለፉት አንድ ዓመት ትርጉሙም ሆነ ገፅታው የላቀ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ 365 ቀናትን ያስቆጠረው የዚህ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ትግል ካስገኛቸው ትሩፋቶች አንዱ ዚያራ እና በዚያራ አማካኝነት የተገኘው ስኬት ነው፡፡

መንግስት የሕዝበ ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ በተቃራኒው በወሰደው እና እየወሰደ ባለው ግፍና ሕ ወጥ እርምጃ የተነሳ ሕዝበ ሙስሊሙ በመንገላታት ላይ ይገኛል፡፡ ትርፍ አልባ የሆነውን ተቀፅላ ስም ከማውጣት ጀምሮ ሙስሊሙ ወኪል አድርጎ የመረጣቸውን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን አሸባሪ በማለት አስሯል፣ ዘግናኝ የሆነ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በወህኒ ቤት ፈፅሞባቸዋል፣ ንፁሀንን ጥይት በመተኮስ ገድሏል፤ አቁስሏል፤ አስሯል፤ ካገር እንዲወጡም አድርጓል…፡፡

ይሁንና እነኚህና መሰል ሰቆቃዎች በከፍተኛ ደረጃ ቢጨምሩም ትግሉ ሰፊ ሕዝባዊ መሰረትን ይዞ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ይህ አስገራሚ ገፅታ በሁለት መልኩ የሚታይ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያውና የላቀ ቦታ ይዞ የሚገኘው ጉዳይ ሕዝበ ሙስሊሙ አስተማማኝ ፅናትን መላበስ መቻሉ ነው፡፡ ሰቆቃ እና ግፍ፣ በደልና ጭቆና ጽናትን እና ጥንካሬን ወልደዋል፡፡ ‹‹በእሳት የተፈተነ ወርቅ…›› እንዲሉ ማለት ነው፡፡ ከአመት በፊት መሪዎቻችን በአካል ከኛ ጋር ሆነው ሂደቱን ስርኣት ባለው መልኩ ሲመሩ ሳሉ የነበረው ሚሊዮን ሕዝብ ዛሬ መሪዎቹ ከፍተኛ በሚባለው የአገሪቱ ወንጀል ተከስሰው እና ታስረው፣ አሰቃቂ ግፍ ተፈፅሞባቸው፣ ሙስሊሞች ደማቸው ፈሶ፣ ብዙሃን ታስረውና ተደብድበው እና ተንገላተው ባይኑ በብረቱ ቢመለከትም ቅሉ እነሆ ዛሬ ከአመት በኋላም ያው ሚሊዮን ሕዝብ አደባባይ መዋሉ በይፋ ተመስክሯል፡፡ የትኛው ሕዝብ ነው ቤቱ የገባው? የትኛው ነው የተታለለው? ጥቂቶቹ የት ዋሉ… አደባባይ ወይስ ጓዳ?

ሁለተኛውና እና አርኣያነቱ ለሌሎችም የተረፈው ጉዳይ በትግሉ ሰበብ ጉዳት የደረሰባቸውን ክፍሎች ሕዝበ ሙስሊሙ ትኩረት ሰጥቶ በቅርብ መከታተል የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ ኮሚቴዎቹን አሸባሪ ብሎ ቢያስር፣ የንፁሃንን ደም ቢያፈስ፣ ቢያስር ቢደበድብ… የዚህ አሰቃቂ ተግባር ዋና ዓላማ ህብረተሰቡ ትምህርት ወስዶ ሲያበቃ ‹‹ነግ በኔ›› በማለት ሁሉም አርፎ እንዲቀመጥ ማድረግ ነበረ፡፡ ይህ ሊሳካ ይቅርና እንዲያውም በተቃራኒው አስገራሚ ትዕይንቶች ተስተውለዋል፡፡ ህዝብ እርስ በርሱ በመጠራራት እና በመተጋገዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እስር ቤቶች ድረስ በአጀብ በመሄድ ወኪሎቹን ዘይሯቸዋል፣ አለኝታነቱን በገሀድ አስመስክሯል፡፡ የታሳሪ ቤተሰቦችን፣ የሸሂድ ቤተሰቦችን፣ በአጠቃላይ ጉዳተኞችን ባሉበት ሁሉ በመድረስ ዚያራ አድርጓል፣ እያደረገም ይገኛል፡፡

ይህ ታሪክ በደማቅ ብዕሩ በሰፊው ድርሳኑ ላይ ያሰፈረው እውነታ ተግባራዊ የሆነው በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ነው፡፡ ለዚህ ታሪካዊ ድርጊት ሰበቡ ደግሞ የተነሱለት የመብቴ ይከበርልኝ ፍፁም ሠላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከ 365 ቀናት በኋላም ጥያቄዎቹ አልተመለሱለትም፡፡ የንፁሃን ህይወት መቀጠፉ ዛሬም ቀጥሏል፣ እስራቱ፣ ድብደባው እና የመብት ጥሰቱ አላቆመም፡፡ ሂደቱ ትግል ነውና መስዋዕትነት ግድ ይላል…! ይህንን በፀጋ የምንቀበለው ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ግን የቆመው የወደቀውን እያነሳ፣ ጤነኛው የቆሰለውን እያከመ፣ ርዝቅ የሰፋለት የራበውን እያበላ፣ ያለው ለቸገረው እየሰጠ…እየተዘያየርን ትግላችንን አጠናክረን መቀጠላችን አሌ የሚባል አይሆንም፡፡

በዚህም መሰረት ‹‹365 ቀናት ለሃይማኖት ነፃነት!›› በዚህ ሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብሩር መሰረትም በአገር አቀፍ ደረጃ የዚያራ ሳምንት ይካሄዳል፡፡ በመሆኑም፡-

1. በመላ ሃገሪቱ ሁላችንም በምንኖርበት አካባቢ ለእስር የተዳረጉ ወገኖችቻችንን ቤተሰቦች (ወላጆች፣ ቤተሰቦች፣ ሚስቶችና ልጆች) ቤታቸው ድረስ በመሄድ ዚያራ እናደርጋለን፡፡ የኮሚቴዎቻችንን ጨምሮ የሌሎች ለእስር የተዳረጉትን ባለቤቶችን በተመለከተ የሚደረገው ዚያራ በሴቶች ብቻ ተሳታፊነት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ወንዶች ሊያደርሱት ያሰቡት መልዕክት ካለ በሴቶቹ (ለዚያራ በሚሄዱት እናቶቻቸው፣ ሚስቶቻቸው አልያም ሴት ልጆቻቸው) በኩል ማስተላለፍ ይቻላል፡፡

2. የሸሂድ ቤተሰቦችን ዚያራ ማድረግ፡- ይህ ተግባር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዳመችነቱ ሰብሰብ በማለት በልዩ ሁኔታ በሁሉም ከተሞች ተግባራዊ እናደርገዋለን፡፡

3. በሰላማዊ ትግላችን ውጣ ውረድ ውስጥ የጉዳት ሰለባ የሆኑትን በተለይም በፖሊስ ከፍተኛ አካላዊ ድብደባ የደረሰባቸውን ወገኖች በአጠቃላይ በዚህ ሳምንት ዚያራ እናደርጋለን፤ ኢንሻ አላህ፡፡

ዚያራችንን በደመቀ መልኩ ለማካሄድ ያስችለን ዘንድ ኢስላማዊ አደባችን ትልቁ መርሃችን በመሆኑ እርስ በርስ መተዋወሳችን የተወደደ ይሆናል፡፡ የዚህ ዚያራ ዋነኛ ዓላማ ወገንተኛነታችንን፣ አለኝታነታችንን፣ አጋርነታችንን እና አንድ አካል መሆናችንን ማስመስከር በመሆኑ ትልቅ ቁም ነገር የምንገበይበት ተግባር ይሆናል፡፡ አላህ ወፍቆን በዚህ ትግል ውስጥ ባሳለፍናቸው ወራት እንደሰራናቸው ታሪኮች ሁሉ ይህም ተግባራችን ፈር ቀዳጅነቱ በማያጠራጥር መልኩ ተሳክቶ በአላህ ዘንድም አጅር የምናገኝበት እንደሚሆን ቅንጣት ታክልም አንጠራጠርም… ኢንሻ አላህ!፡፡

የዚያራውን ፕሮግራምና አላማ ለመላው ቤተሰቦቻችን እንዲሁም በአካባቢያችን ለሚገኙ ሙስሊሞች ማስረዳት ተቀዳሚ ተግባራችን ነው፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ዚያራው በደመቀ ሁኔታ እንዲካሄድ መቀስቀስ የሁላችንም ግዴታ ነው፡፡ አንድ ሰው በአካባቢው (በሚኖርበት ከተማ) እንዳለው የታሳሪዎች፣ የተጎጂዎች እንዲሁም የሟቿች ብዛት በመነሳት እስከ ሶስት ለሚደርሱ ቤተሰቦች ዚያራ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከአካባቢ ቅርበት አሊያም በሌላ ተፅእኖ አማካይነት ዚያራችን አብዛኛው ሰው በሚበዛበት ቤተሰብ ላይ ብቻ አድርገን ሌሎቹን እኩል ዚያራ የሚያስፈልጋቸውን ቤተሰቦች ሳንዘይራቸው እንዳንቀር ልቦናችንን ሰብሰብ አድርገን በተቻለን መጠን በአካባቢያችን ያሉትን መዘየር ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ አጠቃላይ የጉዳት ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችንን በሙሉ መዘየራችንን እንድናረጋግጥም ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

በስተመጨረሻ ስንት ቤተሰብ በሳምንቱ ውስጥ ዘየርኩ የሚለውን ጥያቄ እራሳችንን ከአላህ ጋር ሂሳብ ማድረግም የስራችን አካል እንዲሆን እናስታውሳለን፡፡

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment