Friday, February 1, 2013

በስኬት የተጠናቀቀ ወር!

በስኬት የተጠናቀቀ ወር!
አመት የሞላውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ትግል ለማሰብ ለአንድ ወር ሙሉ ስናካሂድ የነበረው መርሀ ግብር በአላህ ፍቃድ በስኬት ተጠናቋል። ሚሊዮኖች በአላማ ተዋህደው፣ ጥረታቸውን አዋድደው በጋራ ለፍተውበታል። በእርግጥም ውጤታማ ወር ነበር። በሰላሳ ቀናት ውስጥ ብቻ በአገር ውስጥ ከ 35 በላይ ህዝባዊ የተቃውሞ ትእይንቶች ተደርገዋል፤ በአማካይ ቢሰላ በቀን ከአንድ በላይ ተቃውሞ ተደርጓል እንደማለት ያክል ነው፡፡ በውጭ አገራት ደግሞ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በካናዳና በአህጉረ አፍሪካ በርካታ የተቃውሞ ትእይንቶች እና ሴሚናሮች የተካሄዱ ሲሆን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ ሚዲያዎች ለአመት መታሰቢያ ዝግጅቱ ሰፊ የዘገባ ሽፋን ሰጥተውታል።
በዚህ የመታሰቢያ ተቃውሟችን ምን ጥቅም ለማግኘት እንደቻልን የተወሰነ ትንተና መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ ይታየናል። ምክንያቱም የስራችንን ውጤት ለመመዘን እና ድክመቶቻችንን ነቅሶ በማውጣት ለማሻሻል ይረዳናልና ነው። በመሆኑም ወር ከፈጀው ትግል የሰበሰብናቸውን ፋይዳዎች ጠቀስ ጠቀስ ለማድረግ እንሞክራለን።

1. የትግሉን ምሉእ ገጽታ እና ተፈጥሯዊ ይዘቱን ለመላው አለም ለማሳየት ረድቷል
የመታሰቢያ ተቃውሟችን የትግላችንን ምሉእ ገጽታ ዳግም በማሳየቱ በኩል የተሳካለት ነበር ማለት ይቻላል። ህዝባችን ያነሳው ጥያቄ ፖለቲካዊ ይዘት ያልተላበሰ፣ አልያም የአክራሪነትን አጀንዳ የያዘ አለመሆኑን በዙሪያችን ያሉ ሁሉ እንዲረዱት አድርጓል። መንግስት ትግላችንን ለማጥላላት የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ሀሰት መሆኑን በርካቶች ተረድተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ትግሉ ህዝባዊ መነሻ እንደነበረው ሁሉ እስካሁን ድረስ አላማውን ያልሳተ እና ከመንገድ ያልወጣ መሆኑ የተረጋገጠበትም ነበር ማለት እንችላለን።
2. ትግላችን አለማቀፍ መሆኑን ዳግም አሳይቷል
በትግሉ መታሰቢያ ወር እንቅስቃሴያችን አገር አቀፋዊም አለም አቀፋዊም እንደሆነ ለማሳየት አመቺ እድል ማግኘታችን ሌላው ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ ፋይዳ ሆኖ አልፏል። መንግስት በሃይማኖት ላይ እየተከተለው ያለው አጥፊ ፖሊሲ አገራችን ላይ እያሳረፈ ያለው ከፍተኛ ችግር ጠባሳው በአገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳለመሆኑ መጠን ራስን ለመከላከሉ ትግል አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የቆዩት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአገር ውስጥም በውጭ አገራትም የሚኖሩ ናቸው። በአገር ውስጥ ባሉ ወንድሞቻቸው ላይ የሚፈጸመውን በደልና ጥቃት በማውገዝ ረገድ ባሳለፍነው አንድ ወር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኮሚውኒቲ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል። ሴሚናሮችን በማዘጋጀት እና የትግሉን ትክክለኛ ገጽታዎች በማሳወቅ፣ የተቃውሞ ሰልፎችንም በአውሮፓና አሜሪካ በማዘጋጀት የመንግስትን አፍራሽ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ድባቅ መትቷል። ይህ ተግባር ደግሞ ትግሉ መንግስት እንደሚለው ‹‹የጥቂት አክራሪዎች ሴራ›› ሳይሆን አገር አቀፋዊና አለም አቀፋዊ የሃይማኖት መብት ንቅናቄ መሆኑን ለውጪው አለም ያስገነዘበ ነበር።
3. ሙስሊሞች በነፍስ ወከፍ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አስችሏል
ካለፈው የትግሉ አመት በተሻለ መልኩ ግልሰቦች በጋራም ሆነ በተናጠል በነፍስ ወከፍ የአቅማቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ መቻላቸው ከመታሰቢያው ወር ግዙፍ ጥቅሞች ውስጥ አንዱ ነው። መንግስት ‹‹ትግሉን አዳክሜዋለሁ›› እያለ ራሱን ማታለል በመረጠበት ሰአት ከእስከዛሬው ለየት ባለ መልኩ ግለሰቦች መርሀ ግብሩን ለማድመቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። የሞባይል አጫጭር መልእክቶችን (ኤስ.ኤም.ኤስ) እርስ በእርስ በመላላክ፣ በራሪ ወረቀቶችን በራስ ተነሳሽነት እያባዙ በማከፋፈል፣ በየመንደሩና ሰፈሩ የሚፈጠሩ ክስተቶችን መረጃ በማህበራዊ ድረ ገጾች ቶሎ ቶሎ በማቀበል፣ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በሶደቃ እና በትግሉ ሰለባዎች ሳምንታት ግላዊ ወጪዎችን በማውጣትና ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ እንዲሁም የታሰሩ ጀግኖቻችንን ቤተሰቦች በማገዝ ያደረጉት ጥረት ትግሉ ህዝባዊ እንጂ የጥቂቶች አለመሆኑን ያረጋገጠ ነው - ማስተዋል ለሚችሉ ሁሉ! በተለይ ባሳለፍነው ወር ጀግኖቹ ሴት እህቶቻችን በተቃውሞዎቹም ሆነ በቡድን የዚያራና ሰደቃ ፕሮግራሞቹ ላይ ያሳዩት እጅግ ጠንካራ ተሳትፎ ለዲኑ መስዋእትነት የማይከፍል አንድም ሙስሊም እንደማይኖር በቅጡ አሳይቶናል - አላህ ለእህቶቻችን ምንዳቸውን ያብዛላቸው!
4. የመታገል ብቃት ያለው ትውልድ መፍራቱን አስመስክሯል
ሌላው በወር መርሀ ግብሩ የተስተዋለው ፋይዳ የመታገል ብቃት ያለው ትውልድ መፍራቱን ዳግም ማረጋገጥ መቻላችን ነው። ወጣቱም ሆነ በመካከለኛ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ለትግሉ ሲያበረክቱ የነበረው አስተዋጽኦ ህዝበ ሙስሊሙ ወሳኝ የሰላማዊ ትግል ስልቶች ከተነደፉለት ለማስፈጸም ምሉእ ብቃት እንዳለው በግልጽ አሳይቷል። ግለሰቦች ግላዊ ብቃታቸውን ጊዜው በሚጠይቀው መልኩ አሳድገዋል። ጋዜጠኞች ‹‹አሸባሪ›› እየተባሉ በሚታሰሩባት አገራችን ኢ-መደበኛ ህዝባዊ ጋዜጠኝነት (ሲቲዝንስ ጆርናሊዝም) በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ሰዎች በዙሪያቸው የሚከሰተውን እየዘገቡ የማሳወቅ ልምዳቸውን አሻሽለዋል። ለመርሀ ግብራችንን በተደረገው ልፋት ወጣቶቻችን ከምንጊዜውም በበለጠ ጥሪዎችን በፎቶ ኤዲቲንግ በማስጌጥ እና ሼር በማድረግ ተክነዋል። ማህበራዊ ድረ ገጾችን ለመጠቀ አላማ የመጠቀም ልምዳቸውን አዳብረዋል፡፡
5. ትግሉ ለሴራ እንደማይንበረከክ ዳግም አረጋግጧል
ትግሉ ከተጀመረ አንስቶ ለማስቆም አንድ ሺ አንድ ድንጋዮችን የፈነቀለው መንግስት ሲፈጽማቸው የነበራቸው ሴራዎች መክሸፋቸውንና ወደፊትም ሊሳኩ እንደማይችሉ ዳግም አረጋግጧል - የአንድ ወሩ መርሀ ግብራችን። ተቃውሞዎችን ለማስቆም መስጊዶችን ደፍሮ በመግባት ሰላማዊ ሰጋጆችን ከመደብደብና ከማሰር አንስቶ ሙስሊሙን ለመከፋፈል የተደረገው መንግስታዊ ሴራ ቋጥኝ ጋር ተጋጭቶ እንደሚመለስ ማእበል አንድ በአንድ መና ሲቀር ተመልክተናል። በተለይ ደግሞ መውሊድን አስታክኮ በሙስሊሙ ማህበረሰብ መካከል ክፍፍል ለመፍጠር ቋምጦ የነበረው መጅሊሱ እና አይዞህ ባዩ መንግስት ፍቅር በሰበኩት ነቢይ ስም ጥላቻን ማራባት እንደማይቻል በአይናቸው በብረቱ ተመልክተዋል።
6. ሕዝባዊ አንድነትና ወንድማማችነት ተጠናክሮበታል
በህዝበ ሙስሊሙ ላይ ሲፈጸም የቆየው ግፍ እና ብሄራዊ ዘመቻ ካስገኛቸው መልካም ፍሬዎች አንዱና ዋነኛው ኢስላማዊ አንድነት መሆኑ ይታወሳል። ይህ ንጹህ ኢስላማዊ አንድነት ወር በፈጀው የትግሉ መታሰቢያ መርሀ ግብር ወቅት የበለጠ ጎልቶ እንዲወጣ እድል አግኝቷል። በተለይ ደግሞ በአንድነት እና በቃል ኪዳን ሳምንት የታዩት ክስተቶች እጅግ በጣም አስደማሚ ነበሩ። ከአንድ አመት በላይ በከፍተኛ ደረጃ ሴራ ሲጎነጎንበት እና ጥቃት ሲሰነዘርበት የነበረ ማህበረሰብ እስካሁን ባልታየ መጠን አንድነት ፈጥሮ ጠብቆ ማቆየት መቻሉ በራሱ ተአምር ነው። እንደመንግስት ሴራ ቢሆን እስካሁን ሙስሊሞች እርስ በእርስ ተቧድነን መባላት በጀመርን ነበር፤ ግና አልሆነም አልሐምዱሊላህ! ሰዎች ይለፋሉ - ሁሉ የሚፈጸመው ግን በአላህ ፈቃድ ነውና! አሁንም ህዝበ ሙስሊሙ ከጁምአ በኋላ እጆቹንና ቀልቦቹን አስተሳስሮ ‹‹አንድ ድምጽ እንጂ የለንም!›› የሚለውን ታላቅ መልእክቱን አስተላልፏል። ሴራ የማይተበትበውን፣ አፈሙዝ የማይሰብረውን ኢስላማዊ ወንድማማችነት እያሳየ ‹‹የእኛ መሳሪያ ይኸው ነው!›› ብሏል። ከስህተቱ የሚማር አጥፊ የለምን?
7. ሕዝቡ ለትግሉ ሰለባዎች የሁልጊዜም አጋር መሆኑን አስመስክሯል
በየትኛውም ትግል ሂደት ውስጥ ተጎጂዎችና ሰለባዎች ይኖራሉ። ጨቋኝ መንግስታት ከህዝባዊ ትግል ጋር ሲጋፈጡ መጀመሪያ የሚያደርጉት መሪዎቹ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሰንዘር መሆኑም ከታሪክ ያየነው እውነታ ነው። የእኛዎቹ ብርቅዬ መሪዎች ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መብት መከበር ሲሉ የሞቀ ቤታቸውን ትተው በቋሚ ውጥረት እና ጭንቀት አመት አሳልፈዋል። ለግላዊ መስዋእትነት ሳይሳሱ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። ይህንን ያደረጉት ደግሞ እነሱ ሻማ ሆነው ቀልጠው የእኛን ህይወት ሲያበሩ እኛ ፋናቸውን ተከትለን እንድንታገል፣ ለውጤትም እንድንበቃ ነው። ይህ ኪዳን ያስገቡን ቃላቸው የሚረሳን አይደለምና በዚህ ረገድም ቢሆን ባሳለፍነው የአመት መታሰቢያ መርሀ ግብር ቃልኪዳናችንን አድሰናል። በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመታገል ያሳለፉትን ቁርጥ ውሳኔ ዛሬም ዳግም እንደምናከብር አሳይተናል። ለዚህ ውለታቸው ክፍያው የአል ረህማን ጀነት ቢሆንም ህዝበ ሙስሊሙ ደግሞ በዱአም በትግልም አብሯቸው መሆኑን ‹‹በትግሉ ሰለባዎች ሳምንት›› ያለማወላወል አሳይቷል። ከአላህ በታች የጀግኖቹን ቤተሰቦች እንደሚንከባከብ እና ያለመኖራቸውን ናፍቆት እንደሚያቀል በተግባር አሳይቷል። ‹‹በትግሉ ሰለባዎች ሳምንት›› ዚያራ እና ድጋፍ የተደረገላቸው ቤተሰቦች በየክፍለ አገሩና እና ከተሞቹ የሚገኙ እና ከማእከላዊው አመራር በዘለለ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተቱ መሆናቸው ደግሞ መርሀ ግብሩን የበለጠ ፋይዳ አላብሶታል።
በጥቅሉ የመታሰቢያ መርሀ ግብሩ በበርካታ ጥቅሞችና ፋይዳዎች የተሞላ እና ለበለጠ ትግል የሚያዘጋጅ ታላቅ ጊዜ ሆኖ ነው ያለፈው። በሚሊዮኖች ልቦና የማይፋቅ ትዝታ ጥሏል። እርስ በእርስ ጥርጣሬና የጎሪጥ መተያየት እንዲፈጠር ጥረቶች ቢደረጉም ከክርስትና እና ከሌሎች ሀይማኖት ተከታይ ወንድሞቻችን ጋር የበለጠ የመደጋገፍ፣ የመቀራረብና የመተሳሰብ ግንኙነት እንዲፈጠር አድርጓል። መንግስት ሙስሊሙን አክራሪና የአገር ስጋት አድርጎ ለመሳል መከራውን እያየም እንኳን የሙስሊሙ ተቃውሞ በእለተ ጥምቀት የኦርቶዶክስ ክርስትና ሀይማኖት ተከታዮችን እንዳይረብሽ የተቻለው ጥረት ሁሉ ተደርጓል።
በአመት መታሰቢያው መርሀ ግብር በድጋሚ ከፍ ብሎ የተሰማው የትግላችን መልእክት ዛሬም ግልጽና ቀላል ነው፤ ጮክ ብሎም ይሰማል….. ‹‹የሃይል እርምጃ ትግልን ቢያፋፍም እንጂ አያዳክምም! ሕዝብ ምንጊዜም ያሸንፋል! መስዋእትነት የትግል ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት፣ ስብእናችንን የምናነጥርበት ፍሬ እንጂ ከጉዳት ከቶ አንቆጥረውም! ወርቅ በእሳት ይፈተናልና!!!››
ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለም!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment