Tuesday, July 31, 2012

ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ላለፉት ስምንት ወራት ሲያካሂድ የነበረው ሠላማዊ የተቃውሞ ሂደት

" ولا تهنوا ولا تحزنوا وأنتم الأعلون إن كنتم مؤمنين "
‹‹አትስነፉ፣ አትዘኑም፤ ምዕመናን እንደሆናችሁ እናንተ አሸናፊዎች ናችሁ›› ሱረቱል ኢምራን፤ 139

ስምንት አታካች ወራት፡፡ አታካች የተቃውሞና የጥያቄ ወራት፡፡ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ላለፉት ስምንት ወራት ሲያካሂድ የነበረው ሠላማዊ የተቃውሞ ሂደት ከሁሉ በፊት ሠላምን በሚወደውና ስሙም ‹‹ሰላም›› በሆነው ጌታ አላህ ፊት የሚያስመሰግነው ነበር፡፡ በመቀጠልም ሙስሊም ባልሆነው ወገናችንና በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ፊት የተወደሰ ሆኗል፡፡ ነገር ግን፤ ሕገ ወጥ በሆኑትና በሙስሊሙ ደምና ላብ ሆዳቸውን ሞልተው ለሚያድሩት ህገ-ወጦቹ የመጅሊስ አመራሮችና በ
ሙስሊሙ ላይ ድብቅ አጀንዳቸውን ማራመድ ለሚሹት ጥቂት ባለስልጣናት ይህ ሠላማዊና ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ‹‹አክራሪነት፣ ጽንፈኛነት፣ አዲስ እስልምና፣ ወዘተ›› ነው፡፡

ከሁሉ በፊት ‹‹የማንፈልገው እምነት (አህባሽ) አይጫንብን፣ ህገ-መንግስቱ ይከበር፣ መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ፣ መንፈሳዊ መሪዎቻችንን ከመንፈስ ተቋማችን (ከመስጂድ) እንምረጥ›› የሚል ህጋዊ ጥያቄያችንን ስናነሳ ሕገ-ወጦቹም ሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ድብቅ አጀንዳ ያላቸውን ግለሰቦች እንደማያስደስት ብሎም ሕዝበ-ሙስሊሙን ለማጥቃት የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ እናውቅ ነበር፡፡ ልክ እንዳሰብነውም ሆኖ በሠላማዊ መንገድ ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ ያነሳን ወገኖች ሕገ-ወጥ
የኃይል እርምጃ ተፈጽሞብናል፡፡ ብዙዎች ታስረዋል፣ ተደብድበዋል፣ ቆስለዋል፡፡ ኮሚቴዎቻችን በየመድረኩ ሲነግሩን እንደነበረው መብት በልፋት እንጂ በልመና የማይገኝ ነው፡፡

ዛሬም ጥያቄያችንን እንድናጥፍላቸው የሚፈልጉ ኃይሎች አይሳካላቸውም፡፡ የአህባሽ እጅ ጠምዝዞ አስተምህሮ ይቁምልን፡፡ የመጅሊስ አመራሮች ሕዝቡ ያመነባቸው ሆነው በመስጅድ ይመረጡ፡፡ አወሊያ ብቸኛው የሙስሊሙ ተቋም ነውና ሙስሊሙ ራሱ በሚመርጠው ቦርድ ይተዳደር፡፡ ጥያቄያችንን ሊያደናቅፉ የሚፈልጉ ህልመኞች ከዋናው ጥያቄ ወጥተን በወቅታዊ የቅጥፈት አጀንዳቸው ተውጠን እንድንዋዥቅ ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ሙስሊሞች ነን አላህን እንፈራለን እንደነሱ የምንወሸክትበት ጣቢያ የለንም፡፡ ቢኖረንም አንወሸክትም፡፡ የቅጥፈት ፖለቲከኛ ነው የሚወሸክተው፡፡ እኛ ለሃቅና ለዲን የቆምን ነን ከሃቅና ከዲነል ኢስላም መንገድ ለቅጽበት ፈቅ አንልም፡፡ “በዚህ አካባቢ ያሉ ሙስሊሞች ኮሚቴውን ተቃወሙ ሰልፍም ወጡ የዚህ አካባቢ ሙስሊሞች እንዲ አሉ” በሚል ተረት የምንረታ መስሏቸዋል፡፡ መንግሥት በርካታ ጀለቢያ ጥምጣምና ኮፍያ ገዝቶ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎተን ውሎ አበል እየከፈለ ሰልፍ እያስወጣ እንደሆነ ሰምተናል ይሄ አይደንቅም ከዚህም በላይ ድራማ አወሊያ ግቢ ውስጥ እየሰራ አይደል ሰዎችን መሣሪያ አሲዞ ‹‹ሽብርተኛ ነኝ›› ዓይነት የቅጥፈት ድራማ እየሠራ ነው፡፡

እንደሚታወሰው የመብት ጥያቄያችንን ስናነሳ መንግስት ተወካዮቻችን ሕጋዊ መሆናቸውን አምኖ በተደጋጋሚ ሲያነጋግራቸው ከርሟል፡፡ ሆኖም፣ ሙስሊሙን ለማታለልና ለማስተኛት የሰጡት ምላሽ ተቀባይነት ሲያጣ (ሲነቃባቸው) ጠዋት ‹‹ህጋዊ›› ያሉትን ኮሚቴና ጥያቄ ረፋድ ላይ ‹‹ህገ-ወጥ›› ብለው ማንቋሸሽ ተያያዙት፡፡ በዚህም አላቆሙም የኃይል እርምጃ በመስጂዶቻችን ውስጥ ፈጽመው ሲያበቁ ሕገ-ወጥና ነውረኛ ተግባራቸውን ለማድበስበስ ሲሉ በሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች ጆሮ የሚበሱ ውሸቶች መንፋት ተያያዙት፡፡ ሠማያትና ምድርን ለፈጠረው ጌታችን ምስጋና ይገባውና ዱላቸውም ሆነ ፕሮፓጋንዳቸው ያሰቡትን አላሳካለቸውም፡፡ ያሰቡት ጥያቄያችንን እንድናቆም ወይም በብስጭት ረብሻ እንድንፈጥር ነው፡፡
ሁለቱም እንደማይሆን ለሁለቱም (ለህገ-ወጦቹ መጅሊሶችና ለጥቂት ባለስልጣናቱ) ልንነግራቸው እንወዳለን፡፡ ተስፋ ቁረጡ ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄውንም አናቆምም ረብሻና ሁከትም አንፈጥርም!!!

‹‹በሕዝብ ተመርጫለሁ›› የሚል ፓርቲ ሕዝባዊ ጥያቄን በቆመጥና በመሣሪያ በመደብደብ ለማቆም ሲሞክር ማየት አስገራሚ ነው፡፡ ራሳቸውን መከላከል እንኳ የማይችሉ በኪሳቸው ከሚስባሃ ውጭ ምንም በሌላቸው ወገኖች ላይ ‹‹ድንበር ጥሰው የገቡ ጠላቶች›› ይመስል የተፈጸመው ድብደባ ኢ-ሰብዐዊ ድርጊት በመሆኑ ጊዜው ሲደርስ ፍትህ የሚገኝበት ይሆናል፡፡ ይህን ሕገ-ወጥ እርምጃ ያዘዙ አካላትም ከሁለት ሚሊየን ለሚበልጠው ሙስሊም የኢህአዴግ አባላት ያላቸውን ንቀትና በግልጽ አሳይተውናል፡፡ በቴሌቪዥን የሚታዩት ሠላማዊ ሠልፎችም አስቂኝ የግዳጅ ሰልፎች እንደሆኑ ለረጅም ዘመናት ደርሶብን ስላየነውና ልምድ ያለን በመሆኑ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የማይደበቁ ናቸው፡፡ ለነዚህ የግዳጅ ሰልፎች ሲባል የመንግስት መሥሪያ ቤቶችን መዘጋታቸውን፣ መሬትህን ትቀማለህ፣ ማዳበሪያ አይሰጥህም የሚሉ ማስፈራሪያዎች መኖራቸውን በደንብ እናውቃለን፡፡ አንዳንድ ቦታዎችም ገበሬውን ወገናችንን ‹‹አሕባሽን ተቃወም›› ብለው ሠለፍ ካስወጡት በኋላ በቲቪ ‹‹የሠደቃ ፕሮግራሞችን ተቃወመ›› ብለው ያሳዩናል፤ ሠልፈኛ ሲያንስ ሙስሊም ያልሆኑ የኢህአድግ አባላትን ይቀላቅላሉ፣ ሌላም ሌላም፡፡ እነዚህ ሠዎች ለእኩይ ተግባራቸው ከመቸኮላቸው የተነሳ ቴክኖሌጂ መራቀቁን ሌላው ቀርቶ ሁሉም ሠው እጅ ሞባይል መኖሩን እንኳ ዘንግተውታል፡፡

ዞሮ ዞሮ ጥያቄያችን የሚሊዮኖች ነው፡፡ መሠረቱም ሕገ-መንግስቱ ነው፡፡ ኮሚቴውን በማሰርና በሐሰት በመወንጀል ጥያቄውን ማቆም ከቶም አይቻልም፡፡ ነብያችን (ሶ.ዐ.ወ) ሲሞቱ ኢስላም አልቆመም ይልቅስ እሳቸው በሕይወት እያሉ ከነበረው ፍጥነት በላይ መጓዝ ቻለ እንጂ፡፡ ስለዚህ፤ ኮሚቴዎቻችንን በሐሰት በመወንጀል ትግሉን ለማዳፈን ማሰብ ቅዠት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ምርጫው የሚካሄደው በመስጅድ ነው መሆን ያለበት፡፡ ከሙስሊሙ ፍላጎትና ጥያቄ ውጭ በቀበሌ ለዚያውም በሕገ-ወጡ መጅሊስ ዑለማ ምክር ቤት የሚካሄድ ምርጫ ተቀባይነት የለውም፡፡ የታሰሩት መሪዎቻችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊፈቱ ይገባል፡፡ እነሱም ሆኑ እኛ ሰላማዊ ሰዎች ነን፡፡ ወንጀላችን ሙስሊም መሆናችን ብቻ እንደሆነ ገብቶናል፡፡
እስልምናችንን ደግሞ በዱላና በጥይት ብዛት ፈርተን አንለቅም፡፡ እኛ መብታችንን የምንጠይቅ ሰላማዊ ሰዎች ነን፡፡ አሸባሪነትን አክራሪነትን እንቃወማለን፡፡ ‹‹አሸባሪነትና አክራሪነት ለመታገል›› በሚል ስም የሚደረጉ ሠላማውያንን ማጥቃትም አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ሙስሊሙ የእምነት ነጻነቱ ታፍኖና የግዳጅ አስተምህሮ እንዲቀበል የሚደረገውን ሩጫ ሁሉ በሰላምና በህጋዊ መንገድ እንታገለዋለን፡፡ አላህም ይረዳናል፡፡

ምዕመናን ሆይ! ‹‹አትስነፉ፣ አትዘኑ ምዕመናን እንደሆናችሁ እናንተ አሸናፊዎች ናችሁ›› ብሎናል ጌታችን በቁርኣኑ፡፡ ስለዚህ፤ ጥያቄያችን መልስ ማግኘቱን አትጠራጠሩ፤ መልስ ያገኛል፡፡ በደለኞችንም አላህ የጃቸውን ይሠጣቸዋል፡፡ የመሸ ቢመስለንም ንጋቱ ቅርብ ነው፡፡

"إن موعدهم الصبح أليس الصبح بقريب"
‹‹(የበደለኞቹ የመጥፊያ) ቀጠሮ ንጋት ላይ ነው፡፡ ንጋቱ ቅርብ አይደለምን?›› ሱረቱል ሁድ፤ 81

" ولا تهنوا ولا تحزنوا وأنتم الأعلون إن كنتم مؤمنين "
‹‹አትስነፉ፣ አትዘኑም፤ ምዕመናን እንደሆናችሁ እናንተ አሸናፊዎች ናችሁ›› ሱረቱል ኢምራን፤ 139

No comments:

Post a Comment