Monday, September 17, 2012

ዜናው ከጉንጭ አልፋነት የዘለለ ትርጉም የለውም! ኢንሻ አላህ ፡፡


ዜናው ከጉንጭ አልፋነት የዘለለ ትርጉም የለውም! ኢንሻ አላህ ፡፡

ከዘጠኝ ወራት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ተቃውሞ መቋጫው ምን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ተቃውሞው መቋጫ እንዲኖረው ከሚያስችሉት አንዱና ዋነኛው መፍትሄ የሙስሊሙ ሕዝብ ሁለንተናዊ ይሁንታ የታከለበት ነፃ፣ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ የመሪ ተቋሙ ምርጫ መካሄድ ይሆናል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ ምላሽ ያገኙ ዘንድ ከበርካታ ወራት በፊት ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ሲያነሳ አቤት ያለው ለመንግስትና ለመንግስት ብቻ የነበረ መሆኑ የመጅሊስ ሙሰኛ እና ሕገ ወጥ አመራሮች ሕጋዊነት የሌላቸው መሆናቸውን ይፋ ያደረገበት አካሄድ ነበር፡፡ ሕገ ወጥ የመጅሊስ አመራሮች በጉልበት እና በማን አለብኝነት በወንበሩ ላይ ተቀምጠው ያሻቸውን ቢሰሩም ተግባራቸው ሁሉ ምንም አይነት ሕጋዊነት የለውም፡፡ የሙስሊሙን ሕዝብ ጥያቄ የመመለሥ፣ የማስተናገድም ሆነ የመመልከት ሕጋዊነት የላቸውም፡፡
አዲዮስ!
መንግስት ሕዝብን እንደሚያስተዳድር አካል ለሕዝብ በመወገንና የሠፊውን ሕዝብ ጥቅም የሚያስከብር አካሄድ በመከተል አግባብ ያለው ምላሽ መሥጠት ሲገባው “መንግስት በሐይማኖት ጣልቃ አይገባም!” በሚል ሽፋን የሕዝብ መብት እየተረገጠ ዳር ቆሞ ተመልክቷል፣ ግለሰቦች በማን አለብኝነት ያሻቸውን እየሰሩ በሰፊው ሕዝብ መብት ላይ እንዲረማመዱ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ሁኔታውን በውል የተረዳው ሠፊ ሕዝብ ከመንግስት በተሻለ የአስተሳሰብ ክህሎት በመጠቀም የነበረውን ብቸኛ አማራጭ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡የዚህ ሒደት ቀጣይ ምዕራፍ በደመቀ መልኩ መከፈቱን ያበሠረው የሚሊዮኖች የዒድ አደባባይ የተቃውሞ ውሎ ሕዝበ ሙስሊሙ ከተቃውሞ ሒደቱ የሚፈልገውን ምላሽ በድጋሜ ግልፅ አድርጓል፡፡ ከነኚህ ግልፅ ካደረጋቸው ድምፆች አንዱ ከምርጫ ሒደቱ ጋር በቀጥታ የተያያዘው ይገኝበታል፡፡በያዙት መፈክራቸው አማካይነት እንዲህ ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰሙ፡፡
1. ሕጋዊ ወኪሎቻችን ሳይፈቱ ምርጫ የለም/አንሳተፍም!
2. ምርጫችን በመስጂዳችን!
3. የዑለማ ምክር ቤቱ ምርጫውን የማስፈፀም ሕጋዊነት የለውም!
የምርጫው ሒደት ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው በመራጭነት እና በአስመራጭነት እንቅስቃሴ ውስጥ የሰፊው ሕዝብ ተሣታፊነት ሲረጋገጥ ብቻ ይሆናል፡፡የአፈፃፀሙም ሒደት ከ40 ሚሊዮን በላይ ሙስሊሞችን የሚመወክልና የሚመጥን ሊሆን ይገባዋል፡፡የምርጫው ሒደት በሠፊው ሕዝብ ዘንድ በጨዋነታቸው፣በሐይማኖት ዕውቀታቸውና ተግባራቸው በሚታወቁና ገለልተኛ በሆኑ አካላት ሊከናወን ይገባል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ የመጅሊስ ሙሰኛ አመራሮች አይወክሉንም በማለት በሕገ ወጥነት ሲፈርጃቸው የዑለማ ምክር ቤትን አያጠቃልልም፣ ስለዚህም ምክር ቤቱ እንደ ገለልተኛ አካል ተወስዶ ምርጫውን ያስፈፅማል ብሎ ማሰብ ከንቱነት ይሆናል፡፡ሕዝበ ሙስሊሙ የዑለማ ምክር ቤቱን ተክለ ቁመና በሚገባ ከመረዳቱ የተነሣ ከመጅሊሱ አመራሮች ነጥሎ አይመለከተውም፡፡
አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንዲሉ የሕዝብን የተቃውሞ ድምፅ “ምንም አያመጡም፣ የቁራ ጩኸት ነው፣ ጮኸው ጮኸው ሲደክማቸው ይተውታል” እና በመሳሰሉት ንቀት የተሞላበት ንግግራቸው የታጀበው ከንቱ ሩጫቸው ምርጫውን ለማስፈፀም ያገዛቸው መስሏቸው ላይ ታች ሲሉ ቢስተዋሉም ከያዘው አቋም ፍንክች ያላለው ሙስሊም ሁኔታውን በአንክሮ እየተከታተለው ይገኛል፡፡ ሕጋዊ ወኪሎቹ በእስር ቤት ታጉረው ባሉበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ ማለት ነገሩ ህልም ሆኖበታል፤እንዴት ተደርጎ? ከዚህ በፊት የተፈጠረው ችግር ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግና ሁነኛ ሰዎችን ለመምረጥ እንዲያስችለው መስጂድ የተሻለ መድረክ ሆኖ ሳለ ምርጫውን በቀበሌ ማካሄድ ማለት ነገሩ ህልም ሆኖበታል፤እንዴት ተደርጎ?
ከዚህ ቀደም ነሐሴ ወር ውስጥ እንደሚያካሂደው ሲገልፅ የቆየውን ምርጫ ሲያራዝም የ “ኡላማ ምክር ቤቱ” ያስቀመጠው ተጨባጭ ምክንያት ባይኖርም የሙስሊሙ ግብረ መልስ አብይ እንቅፋታቸው እንደነበረ አያጠያይቅም ፡፡ከዚህ ትምህርት በመውሰድ የምክር ቤቱ አባላት ሙሉ በሙሉ ኃላፊነታቸውን ለሕዝብ ማስረከብ ሲገባቸው እነሆ ተመሳሳይ ጥፋት ለመሥራት በቀጣይ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ማለቂያ ወደ ሌለው አተካራ ውስጥ ለመግባት በማሰብቅዳሜ ምሽት በኢቴቪ ዜና ምርጫ መሥከረም 27 ጀምሮ እንደሚያካሂድ ገልጧል፡፡ ምዝገባውም በየቀበሌው ከመስከረም 3 ጀምሮ እየተካሄደ እንደሆነ አስነግሯል፡፡
ይህ ወሬ,ያቸው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ጉንጭ አልፋ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ያውቁት ዘንድ ሕዝበ ሙስሊሙ የሆዱን በሆዱ ይዞ ታሪክ መስራቱን ይቀጥላል፡፡ኢንሻ አላህ

No comments:

Post a Comment